ስለ ኮቪድ-19 ቸር ወሬ  10/02/2021

 ስለ ኮቪድ-19 ቸር ወሬ ስንሰማ ከክትባቱ ወዲህ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡ መረጃው እንደተለቀቀ ታላላቅ የሚባሉት የዜና አውታሮች እየተቀባበሉ ሲገልጡት ያመሹበትን መልካም ዜና እኔም ለዘመዶቼ ላካፍል ብዬ ወደ ፅሁፌ ገባሁ፡፡

ነገሩ እንግዲህ በኮቪድ ለተያዙ ህሙማን አገልግሎት የሚውል በአፍ የሚዋጥ ወይም የሚወሰድ መድሐኒት መገኘት ነው፡፡ አስከዛሬ ድረስ፣ መድሐኒቶቹ አሉ ቢባሉም፣ በክንድ መርፌ በኩል የሚሠጡ፣ ከምንም ወይም ከባዶ ይሻላሉ በሚል አገልግሎት ላይ ያሉ መድሐኒቶች አሉ፡፡ ነገር ግን፣ እንደዚህኛው አሁን ተገኘ እንደተባለው ህሙማኑ የሆስፒታል ደጃፍ ሳይረግጡ በቤታቸው የሚወስዱት መድሐኒት ሲገኝ የመጀመሪያው ነው፡፡

የዚህ መድሐኒት ግኝት መደበኛ የጥናት ሳይንሳዊ ፕሮቶኮልን ተከትሎ የተጠና መሆኑ አንዱ ትልቁ የሚያረጋጋ ነገር ነው፡፡ ነገሩ ሲገለፅ፣ መጀመሪያ ለዚህ መድሐኒት ግኝት ባለቤት በኤምሪ ዩኒቨርስቲ ሥር የሚገኝ አትራፊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ድርጅት መድሐኒቱን እንዳገኝ፣ መርክ የተባለው ትልቅ የመድሐኒት ኩባንያ ከሌላ ሪጅባክ ባዮቴራፔቲክ ከሚባል ኩባንያ ጋር በመሆን፣ መድሐኒቱን ተረክበው ተከታይ ሥራውን እየሰሩ ነው፡፡ ለኤምሪ ዩኒበርስቲ የተከፈለ ገንዘብ መኖሩ ባይገለፅም፣ መርክ፣ ሪጅባክ ለተባለው ካምፓኒ አስቀድሞ ክፍያ ማድረጉን ራሱ ካምፓኒው ይገልጣል፡፡ መድሐኒቱ ፈቀድ ካገኘ ደግሞ የሚቀጥል ክፍያም አለው፡፡

ወደ ሳይንሳዊ ጥናቱ ልመልሳችሁና፣ የጥናቱ ስም፣ MOVe-OUT የሚባል ሲሆን፣ የተጠናው መድሐኒት ስም ደግሞ molnupiravir ይባላል፡፡ የዚህ ኮምፓውንድ በቫይረሱ ላይ ያለው ውጤት ቫይረሱ እንዳይረባ ማድረግ ነው፡፡ ጥናቱ ደረጃ ሶስት (Phase 3) ላይ ያለ ሲሆን፡፡ በጥናቱ ፕሮቶኮል፣ ለጥናት የቀረቡ ሰዎች በሁለት ተከፍለው አንደኛው ወገን መድሐኒቱ ሌላው ወገን ደግሞ ማስመሰያ(placebo) ተሠጥቷቸው ክትትል ለማድረግ ነው፡፡ ተሳታፊዎቹን ወደየምድባቸው ለማስቀመጥ ራንዶማይዜሽን የተባለ ዘዴ በመጠቀም አጥኝዎቹ እየመረጡ ሰዎችን ወደሚፈልጉት የጥናት ምድብ እንዳያደርጉ ይከላከላል፡፡ አለዚያ፣ ሰዎች እየተመረጡ ወደ አንድ ጎን ሊመደቡ ሰለሚችሉ የጥናቱ ውጤት ላይ አድልዎ ሊፈጠር ይችላል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ፣ ተሳታፊዎችም ሆነ አጥኝዎች ማን መድሐኒቱን ማን ማስመሰያውን እንደሚወስዱ በማያውቁበት ሁኔታ ነው የሚሠራው፡፡ ይህም በአንግሊዝኛው አጠራር double-blind ይባላል፡፡ ጥናቱ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ነው የተካሄደው፡፡ በዚህ መልክ የሚጠና ጥናት ነው በሳይንሱ አለም ተቀባይነት ያለው፡፡

የጥናቱ አላማ ደግሞ የሚመለመሉ ተሳታፊዎቹ በላቦራቶሪ የተረጋገጠ የኮቪድ በሽታ ያለባቸው፣ ያም ከመካከለኛ ህመም ጠንከር አስካለ ድረስ ሆኖ ነገር ግን ወደ ሆስፒታል የማያሰገባ ደረጃ ላይ ያሉ አዋቂ ሰዎች ላይ ነው፡፡ ነገር ግን፣ እንደሚታወቀው ተደራቢ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ኮቪድ ቢይዛቸው ሰለሚበረታባቸው፣ የጥናቱ ተሳታፊዎች ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ አንድ ተደራቢ ወይም ኮቪድ እንዲከፋባቸው የሚያደርግ ሰበብ ወይም ጠንቅ ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ በኮቪድ ከተያዙና የበሽታ ስሜት ከጀመራቸው በአምስት ቀናት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡

በክትትሉ የሚጠናው አይነተኛ ውጤት ወይም ቀዳሚ ጠቀሜታ፣ መድሐኒቱን የወሰዱ ሰዎች ካልወሰዱ ወይም ማስመሰያውን ከወሰዱ ሰዎች ጋር ሲነፃፀር፣ ምን ያህሉ በሽታ ጠንቶባቸው ወደ ሆስፒታል መግባታቸውና ከዛም በበሽታው ምክንያት ሕይወታቸው እንዳለፈ ለጥናት ከተሰታፉበት ቀን ጀምሮ ሀያ ዘጠኝ ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ክትትል በማድረግ ነው፡፡

ጥናቱ በ170 ቦታዎች በተለያዩ አገራት የተደረገ፣ በአፍሪቃ አህጉር ደቡብ አፍሪቃና ግብፅን ያካተተ ነው፡፡ ጥናቱ ያካተታቸው የከፋ የኮቪድ በሽታ ውጤት ከሚያመጡ ተደራቢ ሁኔታዎች መሀከል በብዛት የተካቱት፣ ውፍረት፣ ዕድሜ ከ60 አመታት በላይ፣ የስኳር በሽታና የልብ ህመም ናቸው፡፡ የነዚህ ሁኔታዎች በጥናቱ መካተት በጣም ወሳኝና ጠቃሚ ነው፡፡ በቫይረሱ በኩል ደግሞ፣ እንሚታወቀው የተለያዩ የቫይረሱ ዝርያዎች የሚሠራጩበት ጊዜ ሰለሆነ፣ በተለይም ወደኋላ የተከሰቱት፣ ዴልታ፣ ጋማና ኤምዩ በሚባሉ ቫይረሶች የተያዙ ሰዎች የተሳተፉበት ነው፡፡ ይህም በራሱ አንድ ጠቀሜታ አለው፡፡ በተለይም ለዚኛው ወይም ለዛኛው ቫይረስ አይሠራ ይሆን የሚለውን ጥያቄ መመለስ ሰለሚችል ነው፡፡ ጥናቱ ማለቴ ነው፡፡

ወደ ጥናቱ ውጤት ስንሄድ፣ የሚሠጠው የጥናት መድሐኒት በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ላለማድረሱ፣ መድሐኒቱን በወሰዱና ማስመሰያውን በወሰዱ ሰዎች መሀከል ንፅፅር አድርገዋል፡፡ በዚህ መሠረት የዳርቻ ጉዳትን በተመለከተ በሁለቱም ወገን ተመሳሳይ ውጤት ነው የታየው፡፡ ማለትም መድሐኒቱን በወሰዱ ሰዎች 12% ባልወሰዱ ሰዎች ደግሞ 11% በሚሆኑት ከመድሐኒቱ የመጣ ነው የሚባል የተለየ ዳርቻ ጉዳት ተዘግቧል፡፡ እዚህ ላይ ሳይገርማችሁ አይቀርም፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የጥናት ተሳታፊዎችም ሆነ፣ አጥኝዎቹ ማን መድሐኒት ማን ደግሞ ማስመሰያውን እንደሚውስድ ሰለማያውቁ፣ ታሳታፊዎች ተሰማን ያሉት የተለየ ስሜት ሁሉ ይመዘገባል፡፡ የዳርቻ ጉዳት መጠን መለኪያው አንዱ፣ ምን ያህል ሰዎች በሚሰማቸው ስሜት ምክንያት የሚወስዱትን ነገር በማቆም ጥናቱ አቋረጡ የሚለው ነው፡፡ በዚህ ጥናት፣ መደሐኒቱን ከወሰዱ ሰዎች 1.3% ማስመሰያው ላይ ከነበሩት ሰዎች ደግሞ 3.4% ጥናቱን አቋርጠዋል ይላል ሪፖርቱ፡፡ ባጠቃላይ ሲታይ በጣም ጥቂት ሰዎች ነው ከጥናቱ የወጡት፡፡

ጥናቱ ሳይጠቃለል በመሀል በተደረገው ግምገማ፣ መድሐኒቱን የወሰዱ ሰዎች ካልወሰዱ ሰዎች ጋር ሲነፃፀር፣ መድሐኒቱ ላይ የነበሩ ሰዎች ወደ ሆሰፒታል የመግባት ወይም በበሽታው ምክንያት ሕይወታቸው ማለፍ በሃምሳ ፐርሰንት ቀንሶ ታይቷል፡፡ መድሐኒቱን ከወሰዱ ሰዎች ከ385 መሀከል 28ቱ 7.3% አስከ ሀያ ዘጠኝ ቀናት ድረስ በተደረገው ክትትል ወይ ሆስፐታል ገብተዋል ወይም ህይወታቸው አልፏል፡፡ ማስመሰያውን ሲወስዱ ከነበሩ ሰዎች መሀከል ግን ከ377 ተሳታፊዎች 53ቱ 14.1% ሆስፒታል ገብተዋል ወይም ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ይህ ውጤት በስታቲስቲክ ሲሰላ p=0.0012 በመሆኑ የጥናቱ ውጤት አጋጣሚ እንዳልሆነ ማረጋገጫ ነው፡፡

እስከ ሀያ ዘጠኝ ቀናት በተደረገው ክትትል፣ መድሐኒቱን ከወሰዱ ተሰታፊዎች መሀከል ማንም ሰው ሕይወቱ ያላለፈ ሲሆን፣ ማስመሰያውን ከወሰዱ ሰዎች መሀከል ግን የስምንት ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ በጥናቱ አለም እንደዚህ አይነት ውጤት ሲከሰት፣ ማለትም መድሐኒቱን የሚወስዱ ሰዎች በጣም ተጠቃሚ ሆነው መገኛታቸው ሲታወቅ፣ ጥናቱ እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡ ይህም የሚሆነው፣ ከዚሀ በኋላ ተሳታፊዎች የማስመሰያውን ክኒን እንዳይወስዱና መድሐኒት ባለማግኘታቸው እንዳይጎዱ ለማድረግ ነው፡፡ እንዳያችሁት መድሐኒት የወሰዱት ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ እንዲህ አይነት የለየለት ልዩነት ሲታይም፣ ተሸፍነው የነበሩ ተሳታፊዎች የትኛው ምን እየወሰደ መሆኑ እንዲታወቅ ይደረጋል (unblinding)፡፡

ይህ ውጤት እንደተገኘ፣ መርክ የሚባለው ኩባንያ፣ ለመድሐኒቱ ፈቃድ ለማግኘት ወደ አሜሪካው የምግብና የመድሐኒት አስተዳደር (FDA) ማመልከቻ ለማስገባት ዕቅድ እንዳለው ገልጧል፡፡

ዋናው ጥያቄ ደግሞ፣ ፈቃድ ከተሠጠ ምርቱ በምን ፍጥነት ሊደርስ ይችላል የሚለው ነው፡፡ መርክ የሚለው በራሴ ኪሳራ መድሐኒቱን እያመረትኩ ነው ይላል፡፡ ማለትም፣ ድንገት የጥናቱ ውጤት ለፈቃድ የማያደርስ ቢሆን ምርቱ ዋጋ ሰለማይኖረው የተመረተው መድሐኒት ከጥቅም ውጭ ሊሆን ስለሚችል ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ካምፓኒዎች፣ ጥናቱ እሰከሚጠናቀቅ ድረስ ይጠብቃሉ፡፡ በዚህ መሠረት፣ መርክ እሰከ 2021 ማለቂያ ድረስ ለአስር ሚሊዮን ወሳጆች የሚሆን የመድሀኒቱን መጠን አመርታለሁ እያለ ነው፡፡ መድሐኒቱ ከተፈቀደ ደግሞ በውስጥ ባደረጉት ስምምነት ለአሜሪካ መንግሥት ለ1.7 ሚሊዮን ወሳጆች የሚሆኑ የመድሐኒት መጠን እንደሚሰጥ ነው፡፡ ያለው ማማሩ፡፡ የሚጠበቀው እንግዲህ ጊዘያዊ የኢመርጀንሲ ፈቃዱ ነው፡፡ እዚህ ላይ፣ መርክ ከሌሎች የአለም መንግሥታትም ጋር ስለ ግዥ አስቀድሞ እየተነጋገረ ነው፡፡

ለሀብታም አገሮች ብቻ ተዳርሶ እንዳይወሰን፣ መርክ፣ መድሐኒቱ ፈቃድ ካገኝ ለተለያዬ ሀገሮች እንደ ኢኮኖሚ አቅማቸው የተለያየ ቅናሽ ያለበት የዋጋ መጠን እንደሚተምን ይገልጣል፡፡ በተጨማሪም የምርቱን መጠን ለማፋጠንና በስፋት ለአለም እንዲዳረስ፣ የተለያዩ በየቦታው የሚገኙ መድሐኒት አምራቾች ጋር የፈቃድ ስምምነት በማደረግ መድሐኒቱን እንዲያመርቱ ፈቃድ እሰጣለሁ ይላል፡፡

እንግዲህ አምራች ኩባንያው ሰላለ ብቻ ሳይሆን፣ ጥናቱና ውጤቱ ላይ በምግብና በመድሐኒት አስተዳደሩ፣ ከዛም የባለሙያ አማካሪዎችና ሌሎቹም አቻ ሳይንቲስቶች በኩል ግምገማ ይደረጋል፡፡ በመሠረቱ በታየው ጥሩ ነው በተባለው ውጤት የጥናቱ ተሳታፊዎች ቁጥር ሙሉ በሙሉ ሳይደርስ ዘጠና ፐርሰንት ላይ እያለ ነው የተቋረጠው፡፡

ይህ ጥሩና ቸር ወሬ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ጥናቱ ያተኮረው መጠነኛና ትንሽ ከበድ ያለ ህመም ያላቸው ሰዎች ላይ ብቻ ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ታመው ሆስፒታል የገቡ ሰዎችን ሰላልጨመረ ፈቃድ ሲሠጥ እነዚህን ሰዎች አያካትትም፡፡

በክትባቱ እንዳየነው ሁሉ፣ ታዳጊ አገሮች፣ ወረፋ ቢጠብቁ እንጂ ለዜጎቻቸው የሚበቃ የመድሐኒት መጠን ላያገኙ ይችላሉ፡፡ ያም ሆኖ፣ የህ ትልቅ የምሥራች ነው፡፡

የቀረ ነገር ቢኖር፣ ለቫይረሱ የተጋለጡ ሰዎቸ፣ በቫይረሱ እንዳይጠቁ አስቀድሞ መውሰድ የሚችሉት መድሐኒት መሆኑ ገና አልታወቀም፡፡ ማለትም ለታመሙ ሰዎች አንጂ ለመከላከያነት መጠቀም መቻላችን ገና አልታወቀም፡፡ ሰለዚህ በቫይረሱ ላለመያዝ የሚደረጉ መከላከያዎች በተለይ አሁን ጠንከርና ኮሰትር ባለ ሁኔታ መተግበር አለባቸው፡፡ ይህም ክትባቱን ይጨምራል፡፡ ይህ መድሐኒት ያሳየው ውጤት በጣም ጥሩ ቢሆንም፣ በሃምሳ ፐርሰንት የታመሙ ሰዎች ወደ ሆስፒታል እንዳይገቡ ይረዳል ነው፡፡ ቀሪውን ሃምሳ ፐርሰንትም ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ሰለዚህ፣ ስብስብ መቀነስ፣ ማስክ ማድረግና ክትባት፣ የከፋውን ጊዜ እንድንሻገር ይረዳሉ፡፡

“የሚያልፍ ዝናብ አይምታህ” እንዳይሆን መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡


​​​የምሥራች  የሚያስብል ለኮቪድ በሽታ ህክምና ተጨማሪ አዲስ በአፍ የሚዋጥ መድሐኒት መገኘት

አርማት 11/14/2021 

ይህ ዜና አስካሁን ድረስ ሰለ ኮቪድ ጥሩ ግኝቶች ከሚባሉት ሁሉ የላቀ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ብሎ፣ ብክኒን (በአፍ የሚወሰድ) ነገር ግን በኮቪድ ምክንያት ከበሽታ ወይም ሞት በሃምሳ ፐርሰንት የሚያስጥል መድሐኒት መገኘቱን አካፍለን ነበር፡፡ አሁን ግን ከዚህ የበለጠ በኮቪድ ከተያዙ ሰዎች 89 በመቶ ከሞትና ከበሽታ የሚያስጥል፣ በአፍ የሚወሰድ እናም በቤትዎ እያሉ ማለትም ከሆስፒታል ውጭ መሠጠት የሚቻል መድሐኒት መገኘቱን የፋዘር ኩባንያ አስታውቋል፡፡

ያው እንደተለመደው የሳይንሳዊ ጥናትን መረጃ በማድረግ ሰለ መድሐኒቱ ልግለፅ፡፡

ፋይዘር የመድሐኒቱን ስም፣ (PAXLOVID)ብሎ ነው የሚጠራው፡፡ ሳይንሳዊ ስም ወይም የኮምፓውንዱ ሰም ደግሞ (PF-07321332; ritonavir ይባላል፡፡ በምድብ ደረጃ Protease Inhibitors የሚባሉ ኮምፓዎንዶች ውስጥ ነው፡፡ ይህ ኮምፓውንድ የሚሠራው ቫይረሱ ላይ ነው፡፡ ቫይረሱ ላይ ፕሮቲኤዝ Protease የሚባለው ኤንዛይም የኮሮና ቫይረስን እንዲራባ የሚያደረገው ነው፡፡ እናም ይህ ኮምፓውንደ ይህንን ኤንዛይም ሥራውን እንዳይሠራ በማድረግ ቫይረሱ እንዳይራባ ያደርጋል፡፡ ሪቶናቪር ritonavir የሚባለው ኮምፓውንድ ደግሞ በመጠነኛ መጠን ከኮምፓውንዱ አብሮ በመሥጠት መደሐኒቱ በሰውነት ውስጥ ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ ያደርገዋል፡፡ (የሚገርመው ይህ ሪቶናቪር የተባለውን መድሐኒት ከዚህ ቀደም በስፋት አሁን ደግሞ በመጠኑ ለኤች አይ ቪ ህክምና እንጠቀምበታለን፡ው፡፡ ለኤች አይ ቪ ህክምና ስንጠቀም፣ ሰዎች ይህንን መድሐኒትና ወይም በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገኙ መድሐኒቶችን ከሌሎች መድሐኒቶች ጋር በማቀላቀል ለረዥም ጊዜ ነው የሚወስዱት፡፡ ለአመታት፣ ያላማቋረጥ፡፡ ሰለዚህ የመድሐኒቶቸን ዳርቻ ጉዳት (side effect) በደንብ ስለምናውቅ፣ ለኮቪድ ህክምና አገልግሎት ሲውል ሊኖረው የሚችለውን የዳርቻ ጉዳት አስቀድሞ መገመት ሰለሚቻል፣ ሰለ መድሐኒቱ አደጋ ያመጣ ይሆን የሚለውን ጥያቄ በትልቁ ይመልሰዋል፡፡ ነገር ግን ዋናው መድሐኒት ወይም ኮምፓውንድ PF-07321332 የኮሮና ቫይረስ ላይ የሚሠራ አዲስ ኮምፓውንድ ሰለሆነ ሰለ ዳርቻ ጉዳቱ ከጥናቱ ውጤት መረዳት ይኖርብናል፡፡

ፋይዘር የዚህን መድሐኒት ለኮቪድ አገልግሎት ሊውል እንደሚችል ያስታወቀው እያካሄደ ካለው ቀጥሎ ከተጠቀሱት ጥናቶቸ ፕሮቶኮል በተከተለ አስቀድሞ በሚደረግ የጥናቱ ግምገማ ላይ የተገኘውን ውጤት በማየት ነው፡፡ ጥናቱ በዚህ ጊዜ  የጥናት ደረጃ ሁለተኛና ሶስተኛ ላይ የሚገኝ በአንግሊዝኛ ስያሜ EPIC-SR (Evaluation of Protease Inhibition for COVID-19 in Standard-Risk Patients) and EPIC-PEP (Evaluation of Protease Inhibition for COVID-19 in Post-Exposure Prophylaxis) የሚባል ነው፡፡

ጥናቱ የተጀመረው በነሐሴና በመስከረም 2021 ዓ.ም ነው፡፡ ጥናቱ ሳይገባደድ በመሀል፣ በፕሮቶኮል መሠረት በሚደረግ የጥናቱ ውጤት ግምገማ የታየው ውጤት በጣም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡ በዚህ መሠረት፣ በመላው አለም በተለያዩ ቦታዎች ሶስት ሺ የሚሆኑ የጥናቱ ተሳታፊዎችን ለመመልመል ዕቅድ ተደርጎ፣ ነገር ግን በጥናቱ ላይ ያሉ የ1219 ሰዎች ውጤት ሲታይ፣ በተገኘው መረጃ መሠረት ምልመላው እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ለምን ሲባል፣ የታየው ውጤት ከተጠበቀው በላይ ጠቃሚ በመሆኑ፣ መድሐኒቱ የሚያስገኘው ጥቅምም ስለታወቀ፣ ሰዎችን በመመልመል ለማወዳደር እንዲመች በማስመሰያ መድሐኒት ላይ ማድረግ አግባብ ወይም ግብረገባዊ ስለማይሆን ነው፡፡ ሌላ ጥናት የሚቋረጥበት ሁኔታ ቢኖር፣ ከዚህ በተቃራኒ በጥናቱ የሚሠጠው ኮምፓውንድ በሰዎቹ ላይ ያልተጠበቀ ከፍተኛ አደጋ ሲያሳይ ነው፡፡

ታዲያ ምን አይነት ውጤት ቢታይ ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ከመስጠት በፊት፣ መጀመሪያ፣ መድሐኒቱን በወሰዱና ማስመሰያውን (placebo) በወሰዱ ሰዎች የታየውን ዳርቻ ጉዳት ስንመለከት፣ ትክክለኛውን መድሐኒት በወሰዱ ሰዎች በ19 % ማስመሰያውን በወሰዱ ሰዎች ደግሞ 21% በሆኑ ሰዎች ላይ የተመዘገቡ ሁኔታዎች አሉ፡፡ እነሱም በአብዛኛው መጠነኛ የሆኑ ስሜቶች ናቸው፡፡ ልብ በሉ፣ ማስመሰያውን እንጂ መድሐኒቱን ያልወሰዱ ሰዎችም ይህ ተሰምቶኛል ካሉም ይመዘገባል፡፡ የዳርቻ ጉዳት ስሜት ሌላው መለኪያ፣ ሰዎች በተሰማቸው ስሜት ምክንያት ምን ያህሉ መድሐኒቱን አቆመዋል የሚለው ነው፡፡ በዚህ በኩል፣ መድሐኒቱን ከወሰዱ መሀል 2.1%፣ ማስመሰያውን ከወሰዱት መሀል 4.1% የሚሆኑት የሚወስዱትን ነገር አቆመዋል፡፡

ጠንከር አለ የሚባል የዳርቻ ጉዳትን በሚመለከት፣ መድሐኒቱን ከወሰዱት በ1.7% ማስመሰያውን ከወሰዱትደግሞ በ4.1% ላይ የታየ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ፣ ትክክለኛውን መድሐኒት የወሰዱት ሰዎች ላይ የተለየ ወይም የተነጠለ አደጋ አለመኖሩ ነው፡፡፡ በነገራችን ላይ፡፡ መድሐኒቱን እስኪያቆሙ ድረስ፣ የጥናቱ ተሳታፊዎች፣ መድሐኒት ወይም ማስመሰያውን መውሰዳቸውን አያውቁም፡፡

በዚህ 45% ተሳታፊዎች ከአሜሪካ በተሳተፉበት ጥናት፣ የመመልመያው መመዘኛ የነበረው፣ በኮቪድ መያዛቸው በላቦራቶሪ ከተረጋገጠ በአምስት ቀናት ውስጥ፣ በተጨማሪም ከመጠነኛ አስከ ትንሽ ጠንከር ያለ የበሽታ ስሜት ያላቸው ሆኖ እንደገናም በኮቪድ ምክንያት የከፋ ደረጃ ሊያደርሳቸው ከሚችሉ ሁኔታዎች ቢያንስ ቢያንስ አንዱ ያለባቸው ሰዎች ማሳተፍ ነው፡፡ የተመለመሉትን ሰዎች፣ በእኩል ቁጥር ከሁለት ምድብ በመመደብ አንደኛው ወገን መድሐኒቱን፣ ሌላኛው ወገን ደገሞ ማስመሰያውን እንዲወስዱ ተደረገ፡፡ ከዚያም እያንዳንዱ ሰው፣ የሚሰጠውን መድሐኒት ወይም ማስመሰያ በቀን ሁለት ጊዜ ማለትም በየ12 ሰኣታት ልዩነት በአጠቃላይ ለአምስት ቀናት ብቻ እንዲወስዱ ተደረገ፡፡ መድሐኒቱን ወይም ማስመሰያውን የወሰዱ ሁሉም ወገኖች የሚሰማቸውን ስሜት ለአጥኝዎቹ ሪፖረት ያደርጋሉ፡፡ እዚህ ላይ አጥኝዎችም ቢሆን የትኛው ተሳታፊ ምን እየወሰደ አንደሆነም አያውቁም፡፡ የጥናቱ ፕሮቶኮል (Double Blind) የሚባለው ለዚህ ነው፡፡

ጥናቱ ግብ ያደረገው፣ መድሐኒቱን ከወሰዱ ሰዎች ምን ያህሉ ሆስፒታል እንዳይገቡ ወይም በኮቪድ ምክንያት እንዳይሞቱ አደርጓቸዋል ወይም አስጥሏቸዋል ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ በዚህ ጥናቱ ሳይገባደድ በተደረገው ግምገማ፣ መድሐኒቱን ከወሰዱ ሰዎች 89 በመቶ የሚሆኑት በኮቪድ ምክንያት በጠና ታመው ወደ ሆስፒታል ከመግባት አልፎም በኮቪድ ምክንያት ከመሞት አስጥሏል ነው፡፡ ይህም ማስመሰያውን ከወሰዱ ሰዎች ጋር ሲነፃፀር ነው፡፡

በዝርዝር ሲታይ፣ ተሳታፊዎች የበሽታ ስሜት ከተሰማቸው በሶሰት ቀናት ውሥጥ መድሐኒቱን ወይም ማስመሰያውን ከወሰዱ በኋላ፣  መድሐኒቱን ከወሰዱ ከ389 ሰዎች መሀል ሶሰት ሰዎች ወደ ሆስፒታል የገቡ ሲሆን (አንደኛቸውም አልሞቱም)፣ ማስመሰያውን ሲወስዱ ከነበሩት መሀከል ከ385 ሰዎች መሀል 27 ሆስፒታል የገቡ ከነዚያም መሀል 7 የሞቱ መሆኑን ማወቅ ተችሏል፡፡ በፐርሰንት ሲታይ፣ 0.8% በመድሐኒት ወገን ባሉት 7.0% ማስመሰያ በወሰዱት ወገን ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ውጤት በስታቲሰቲክ ሲሰላ ልዩነቱ የአጋጣሚ ሳይሆን በእውን የመድሐኒት ውጤት መሆኑን ተረጋግጧል፡፡

ነገር ግን ትንሽ ዘግየት ብለው ማለትም የበሽታ ስሜት ከተሰማቸው በአምሰተኛው ቀን ቢወስዱስ ለሚለው ጥያቄ ደግሞ ጥናቱ ያሳየው መልስ ተመሳሳይ ነበር፡፡ መድሐኒቱን ከወሰዱት ከ607 ሰዎች ስድስቱ ወደ ሆስፒታል የገቡ ሲሆን ከመሀከላቸው አንደኛቸውም አልሞቱም፡፡ በሌላ በኩል ግን ማስመሰያውን ከወሰዱ ከ612 ሰዎች 41 ወደ ሆስፒታል የገቡና ከነሱም መሀል 10 የሞቱበት ሁኔታ ነው የታየው፡፡ በፐርሰንት ሲነፃፀር፣ ከመድሐኒቱ ወገን 1%፣ ከማስመሰያው ወገን ደግሞ 6.7%፣ ማለት ነው፡፡ በስታቲስቲክ ሲሰላም (p<0.0001) ነው የታየው፡፡ ልዩነት ዕውን ነው ማለት ነው፡፡

ሶሰተኛው ግምገማ ደግሞ በ28 ቀናት ውስጥ በተደረገው ክትትል፣ መድሐኒቱን ከወሰዱ ሰዎች መሀከል ማንም ሰው ያልሞተ ሲሆን፣ ማስመሰያውን ከወሰዱ ሰዎች መሀከል 10 ሰዎች (1.6%) ህይወታቸው አልፏል፡

እንግዲህ እንደዚህ አይነት በሰታቲሰቲክ የተደገፈ ግልፅ ያለ የመድሐኒቱ ጠቀሜታ ሲታይ፣ ጥናቱን መቀጠልና፣ ሰዎችን በማስመሰያው መድሐኒት መመደብ አግባብ አይኖረውም፤ ግብረገባዊም አይደለም፡፡ ምክንያቱም በግልፅ እንደታየው ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ ሰለዚህ ጥናቱ ወይም ምልመላው መቆም አለበት፡፡

አሁን የሚቀረው የተገኘውን ውጤት ይዞ ለሚመለከተው ባለሥልጣን በማቅረብ የአሰቸኳይ ጊዜ ፈቃድ ማግኘት ነው፡፡

መድሐኒቱ ከተፈቀደ፣ አቅም ለሌላቸው አገሮች አንዲዳረስ፣ ፋይዘር በመግለጫው ያወጣው ነገር ቢኖር፣ አንደየሀገሩ የገቢ መጠን የመድሐኒቱን ዋጋ ዝቅ እንደሚያደርግ ነው፡፡ በተጨማሪም፣ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር በማውጣት፣ በተለያዩ አገሮች መድሐኒቱ የሚሠራበትና የሚመረበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች ነው፡፡

የኔ የግሌ አስተያየት፣ ይህ ውጤት በጣም ጥሩ፣ ፈቃድ ከተሠጠው በኋላ፣ ለኮቪድ የተጋለጡ ሰዎችና ብሎም ከፍተኛ ህመም ወይም ሞት ደረጃ ሊያደርሳቸው የሚችሉ ተደራቢ ሁኔታዎች ያለባቸው ሰዎች በቤታቸው ሆነው ሊወስዱት የሚችሉት መድሐኒት በመሆኑ እንደትልቅ የምሥራች ነው የሚቆጠረው፡፡

አሁንም ቢሆን በሽታው እንዳይሠራጭ የሚቻለንን ያህል ጥረት አንድናደርግ በማሳሰብ፣ የተለያዩ መንግሥታት ከፋይዘር ጋር በተለየ ስምምነት መድሐኒቱን አስቀድመው ለመግዛት እንደሚችሉ ሰለተገለፀ፣ ለወደፊት ህብረተሰቡ በጋራ በመረባረብ ይህን መድሐኒት በቀጥታ ከአምራቹ ለማግኘት ጥረት የሚደረግበትና የሚቻለንን ለማድረግ የምንረባረብበትን ሁኔታ ማሰብና መዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡

ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ (የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያተኛ፣ ስፔሺያሊስት)


ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic