ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

የኮቪድ ክትባቶችን አቀላቅሎ መውሰድ ይቻላል ወይ?
10/16/2021


አድልዎ የተመላበት አለም መሆኑን መግለፅም አስፈላጊ አይደለም፡፡ በአንደኛው የአለም በኩል የክትባት ያለህ እየተባለ በቂ ክትባት ማግኘትና መስጠት የሚቻልበት ሁኔታ በሌለበት በሌላው ወገን ደግሞ በቂ የሆነ ምክንያት ቢኖረውም ተጨማሪ ማጠናከሪያ ክትባት ይሰጥ አይሠጥ የሚለውን ጉዳይ የባለሙያተኞች አማካሪ ቡድን ሲወያይበት ሰንብቶ ምክረ ሀሳቡን አቅርቧል፡፡

ወደ ማጠናከሪያው ክትባት ከመሄዳችን በፊት ግን፣ በወቅቱ የተፈቀዱ የተለያዩ ክትባቶች መኖራቸውን እያስታወስን፣ የተነሳው ጥያቄ ፣ አንደኛውን አይነት ክትባት የወሰዱ ሰዎች ሌላ አይነት መውሰድ ይችላሉ ወይ የሚል ነው፡፡፡ ምንም አንኳን ይህ ነው ተብሎ የተፈቀደ ነገር ባይኖርም፣ ሰዎች ክትባቶችን እያቀላቀሉ መውሰዳቸው ይታወቃል፡፡ ይህም በአብዛኛው ሰለ ክትባቶቹ አሠራር በቂ ግንዛቤ ያላቸው ባለሙያተኞችም ቢሆኑ ማቀላቀሉን መቃወም ቀርቶ መደገፋቸውን የሚታወቀው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ማቀላቀል ይቻል ይሆን ለሚለው ጥያቄ በአሜሪካው ብሔራዊ የጤና ኢንስቲቲዩት National Institute of Health- NIH በኩል ይህን በሚመለከት ያደረጉት ጥናት ውጤት ለአደባባይ ቀርቧል፡፡ በጥናት ወይም በመረጃ የተደገፈ አሠራር ለምንከተል ባለሙያተኞች ይህ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡

ወደ ጥናቱ ልውሰዳችሁ፤
ጥናቱ የተካሄደው በአሰር በአሜሪካ በሚገኙ ከተሞች ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የተፈቀዱ ሶሰቱን ክትባቶች የወሰዱ ሰዎች በተጨማሪም በኮቪድ ያልተያዙ መሆናቸው የሚታወቁ በዕድሜ ዐዋቂ ሰዎች፣ ማጠናከሪያ ክትባት (Booster) እንዲወሰዱ ይደረጋል፡፡ ማጠናከሪያውን የወሰዱት የመጀመሪያ ዙር ክትባታቸውን ከወሰዱ ከ12 ሳምነታት በኋላ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ዙር ክትባቱ ከተፈቀዱት ሶስት ክትባቶች ማለትም ከሞደርና፣ ፋይዘርና ከጆንሰን ጆንሰን አንዱን ነው፡፡ በክተትሉ ጥናቱ መጀመሪያ ወይም ቀዳሚ የጥናት ውጤት ያደረገው፣ ክትባቱን አቀላቅለው በወሰዱ ሰዎች ላይ አደጋ ወይም ችግር የተከሰተ መሆኑን፣ በክትባቱ ምክንያት ሰውነት ያሳየውን ምላሽ፣ እና ደግሞ ምን ያህል የመከላከያ አንቲቦዲ መፍጠር መቻሉን ነው፡፡ እንደማንኛው ሰዎች ላይ የሚደረግ ጥናት ቅድሚያ የሚሠጠው በክትባቱ ምክንያት አስጊ ቸግር ወይም አደጋ መፈጠሩ ነው፡፡

በዚህ ጥናት 458 ሰዎች ተሳታፊ ሲሆኑ፣ ማጠናከሪያ ክትባት ሲታይ 154 ሞደርና፣ 150 ዎቹ ጆንሰን ጆንሰን ቀሪ 154 ደግሞ ፋይዘር ክትባት ነው የወሰዱት፡፡ በዚህ መንገድ ሲታይ ዘጠኛ ቡድኖች ሊኖሩ ነው፡፡ የመጀመሪያውን የጨረሱ ማለትም ሞደርና ሁለት ክትባት፣ ፋይዘር ሁለት ክትባት እና ጆንሰን ጆንሰን አንድ ክትባት የወሰዱ ሰዎቸ፣ ማጠናከሪያው ላይ፣ ከላይ እንደተገለፀው ከሶስቱ አንዱን አቀላቅለው ነው የወሰዱት፡፡ ለምሳሌ በመጀመሪያው ዙር ጆንሰን ጆንሰን የወሰዱ ሰዎች ማጠናከሪያቸው ራሱ ጆንሰን ጆንሰን ወይም ሞደርና ወይም ፋይዘር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ለሌሎቹም እንደዚሁ፡፡

ክትትል የተደረገበትን ቀዳሚ ውጤት ስንመለከት፡ ማጠናከሪያ ክትባት በወሰዱ ሰዎች በሁሉም ላይ የሰውነት ምላሽ በተመለከተ ማጠናከሪያን ሲወስዱ ቀድመው በወሰዱት ክትባት ከታየው ውጭ ተጨማሪ ወይም የተለየ ነገር አልተከሰተም፡፡ የዳርቻ ጉዳትን በሚመለከትም መርፌ የተወጉበት ቦታ ህመም፣ የድካም ስሜት፣ ራስ ህመምና የጡንቻ ህመም ከግማሽ በላይ በሚሆኑ ሰዎች ታይቷል፡፡ ያም ከመጀመሪያው ዙር የተለየ አየደለም፡፡ እንግዲህ አሳሳቢ ወይም አስጊ ችግር አለመታየቱ ደግ ነገር ነው፡፡ የሚቀጥለው ጥያቄ ደግሞ ሰውነት ምን ያህል የመከላከያ ምላሽ ሠጠ የሚለው ነው፡፡ ይህ ምላሽ በላቦራቶሪ መለካት የሚችል ሲሆን፣ ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች ሰውነታቸው ሁለት አይነት አንቲቦዲ እንዲሠራ ይጠበቃል፡፡ ይሀ ነገር በሌሎችም ክትባቶች የሚታይ ሰለሆነ፣ ሰፋ ላድርገውና በትግስተ ተከታተሉ፡፡ አንደኛው አንቲቦዲ ቫይረሱን እንዳለ የሚያመክን በእንግሊዝኛ አጠራር፣ neutralizing antibody የሚባል ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ በቀጥታ የቫይረሱን አካል መርጦ የሚያጠቃ ነው፡፡ መርጦ የሚያጠቃው የቫይረሱ አካል ደግሞ፣ ቫይረሱ ከሰውነት ሴሎች ጋር የሚገናኝበት መገናኛ ወይም Binding Protein የሚባል ነው፡፡ እናም ለዚህ ክፍል አጥቂ አንዲሆን የክትባቱ ምላሽ ሆኖ የሚፈጠረው አንቲቦዲ binding antibody ይባላል፡፡ ሁለቱም በደም ምርመራ መለካትና መጠናቸው መታወቅ ይቻላል፡፡ ይህ ምላሽ ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ላይ በቂ ምላሽ ከሌለ አስቸጋሪ ነው፡፡

ወደ ጥናቱ ውጤት ስንመለስ የትኛውንም አይነት ማጠናከሪያ ክትባት በወሰዱ ሰዎች የ neutralizing antibody መጠኑ ከ4.2 እሰከ 76 ዕጥፍ የጨመረ ሲሆን፣ የ binding antibody መጠን ደግሞ ከ4.6 እሰከ 56 ዕጥፍ ጨምሯል፡፡

ክትባት ባላደባለቁ በጀመሩበት ክትባት ተመሳሳይ ክትባት እንደማጠናከሪያ በወሰዱ ሰዎች ላይ፣ neutralizing antibody መጠን 4.6 እሰከ 56 ዕጥፍ፣ ጨምሮ ታይቷል፡፡ ወደ የሚያጓጓው በጀመሩት ክትባት ሳይሆን በሌላ ክትባት ማጠናከሪያውን የወሰዱ ሰዎች ላይ ሲታይ፣ neutralizing antibody ከ6.2 አስከ 76 ዕጥፍ ጨምሯል፡፡ ማጠቃለያ ሀሳቡ፣ በተመሳሳይ ክትባት ማጠናከሪያ በወሰዱና መጀመረያ ከወሰዱት ይልቅ በሌላ ክትባት ማጠናከሪያ የወሰዱት ሰዎች ላይ ክትባቱ አስጊ ውጤት አለማሳየቱና በቂ ምላሸ መገኘቱን ነው የሚገልፀው፡፡ ባጭሩ ማቀላቀሉ ያሰከተለው ችግር ወይም ያጎደለው ነገር የለም ነው፡፡

ይሀ ውጤት በተለይም ከአገር ቤት ሌሎች ክትባቶችን ወሰድው ባጋጣሚ አውሮፓና አሜሪካ ለሚዘልቁ ወገኖቻችን፣ ሁለተኛ ወይም ሶሰተኛ ክትባቶች ፋይዘር ወይም ሞደርና ሊወስዱ እንደሚችሉ ነው፡፡ ክትባትን በማቀላቀል አንድ ታዋቂ ሰው ብጠቅሰላችሁ፣ የጀርመን ቻንሰለር የነበረችው አንጀላ መርክል ነች፡፡ እሷም በመጀመሪያ የአስትራ ዜኒካን ክትባት ወስዳ በሚቀጥለው ግን ሞደርናን እንደወሰደች ይታወቃል፡፡ ክፋት ቢኖረው፣ ጀርመኖች መሪያቸውን ይህንን ክትባት እንድትወሰድ ባላደረጉ ነበር፡፡

አሁን የክትባት አይነቶች በርከት ያሉ በመሆናቸው በመሀከላቸውም ልዩነታቸው እየጎላ በመምጣቱ ተከታቢዎች የትኛውን እንውሰድ ብለው ሲጨነቁ ይታያል፡፡ በተለይ ግን፣ በዚህ በአሜሪካ፣ ወደ አስራ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ጆንሰን ጆንሰን እንዱን ክትባት ብቻ የወሰዱ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ቆየት ብለው የተገነዘቡት ነገር ቢኖር፡፡ የጆንሰን ጆንሰን ክትባት ከሞደርናና ከፋይዘር ጋር ሲወዳደር የመከላከል አቅሙ በፐርስንት ሲታይ ዝቅ ብሎ በመገኘቱ፣ (ለነገሩ ከጠዋቱም ይታወቃል) ጆንሰን ጆንሰን የወሰዱ ሰዎች ምን በወጣን በማለት ሞደርና ወይም ፋይዘር ይሠጠን እያሉ፣ ከዛም እነዚህን ክትባቶች በግላቸው መውሰዳቸውም ይታወቃል፡፡

ምንም አንኳን በመንግሥት ደረጃ እንደዚህ ለማቀላቀል ፈቃድ ባይሠጥም፣ ከላይ የተጠቀሰው ጥናት ጆንሰን ጆንሰን ለወሰዱና የሚቀጥለውን ክትባት ሞደርና ወይ ፋይዘር ለሚወስዱ ሰዎች የአእምሮ እረፍት ይሠጣል፡፡ ታዲያ ከዚህ ጋር አያይዤ የምመክረው፣ ከኢትዮጵያ የዘለቁ ሰዎች፣ ኢትዮጵያ ሊያገኙት የሚችሉት፣ አስትራዜኒካ፣ ጆንሰን ጆንስን ወይም የቻይናው ሳያኖፋርም ነው፣ እናም እዚህ መጥተው ሌላ ክትባት መውሰድ ከፈለጉ፣ የሚበጀው በመከላከል ውጤት ላቅ ያለ ደረጃ ያላቸውን ሞደርና ወይም ፋይዘር ቢሆን ይመረጣል፡፡ የእነዚህ ሁለት ክትባቶች አሠራር አንድ አይነት ዘዴ በመሆኑ፣ ምንም አይነት የቫይረስ አካል ሰለማይጠቀሙ፣ በተጨማሪም ከበሽታ የማስጣል ችሎታቸው 94ና 95 ፐረስንት በመሆኑ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ነው የሄደው፡፡ ይህንን ሲባልም፣ አማራጭ ነው እንጂ፣ በወቅቱ የሚሰጡ ሌሎች ክትባቶችም በቂ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ከበሽታ ማስጣል ሰለሚችሉ፣ የተገኘውን ክትባት መውሰድ ጠቃሚ ነው፡፡

ሌላ ዋናው ነገር፣ ክትባት ከመከሰቱ በፊት የዚህን ቫይረስ ሥርጭት ለመግታት አይነተኛ መከላከያ መንገዶች ያልተለወጡ በመሆናቸው፣ በተጨማሪም ቁጠራቸው በርከት ባሉ በሩቅ ምሥራት አገሮችም የዜጎቻቸውን ህይወት ማዳን ያስቻሏቸው መንገዶች ዋናኘው ማስክ ማድረግ ሲሆን፣ ረቀት መጠበቅ፣ ስብስቅ ማቆም የመሰሉ ነገሮችን፣ አንኳን ክትባት ባልወሰዱ በወሰዱ አካባቢዎች የሚተገበሩ በመሆናቸው፣ ለነዚህ መከላከያ መንገዶች ትኩረት መሥጠትና መተግበር አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ በክትባት ብቻ ወረርሽኙን መወጣት የሚቻል አይሆንም፡፡ ቢቻል ኮቪድ ቢይዛቸው ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚወድቁ የቤተሰብ አባላትን መጠበቅና መከላከል ተገቢና ቅድሚያ የሚሠጠው ነገር መሆን አለበት፡፡