Community health 

education in Amharic 

​​​​​​​​​​እየጨመሩ የመጡት በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ሊኖሯቸው የሚችሉ የበሽታ ስሜትና ምልክቶች 

በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች የሚኖሯቸው የበሽታ ሰሜትና ምልክቶች እየጨመሩ ነው፡፡ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሁሉም አንድ አይነት ሁኔታ አይታይባቸውም፡፡ ማለትም በቀላሉ ከሚለቃቸው ጀምሮ በጠና የሚታመሙና ህይወታቸው የሚያልፍም ድረስ ነው፡፡
ሰሜቶች በቫይረሱ ከተጋለጡ ከ2-14 ቀናት ባሉት ጊዜ ውስጥ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ሁሉም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሰሜቶች አንድ ላይ ላይገኙ ይችላል፡፡

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ስሜቶች ያሉባቸው ሰዎች በኮቪድ-19 ተይዘውም ሊሆን ይችላል፡፡

 1. ብርድ ብርድ ስሜትና ትኩሳት
 2. ሳል
 3. የትንፈሽ ሰሜት ማጠርና ለመተንፈስ መቸገር
 4. የድካም ስሜት
 5. የጡንቻና የሰውነት ህመም
 6. ራስ ምታት
 7. ድንገተኛ የማሽተትና የመቅመስ ችሎታ ማጣት
 8. የጉሮሮ መቁሰል
 9. አፍንጫ መታፈንና ንፍጥ መውረድ
 10. ማቅለሽለሽና ማስታወክ
 11. ተቅማጥ

 
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ይሁኑ እንጂ ሰዎች ሌሎች ተጨማሪ ስሜቶችና ምልክቶች ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ቫይረሱ የማየድርስበት የሰውነት ክፍል ሰለሌለ፣ በቆዳ፣ በአይንም በኩል የበሽታ ምልክት እያሳየ ነው፡፡ ስትሮክና የልብ ህመም ታይቷል፡፡ ልጆች ላይ የተከሰተው በኢንፍላሜሽን አማካኝነት የሚመጣው በሽታም ሌላ መገለጫ ነው፡፡


​​ኮቪድ-19 ጉልበቱን በሚያሳይበት ቦታ ከተያዙት 43% ይገድላል    6/03/20

በአሜሪካ በተቀዳሚነት በኮቪድ-19 ከተጠቁት ሶስት ክፍሎች አንዱ ነርሲንግ ሆም (የአዛውንቶች መጦሪያ) ቦታ ነው፡፡ ከዛ ቀጥሎ ቤተሰብ፣ ከዛ ደግሞ የጤና በለሙያተኞች ናቸው፡፡

የነርሲንግ ሆም ጥቃት ከሌሎች የሚለየው፣ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ምን ያህሉ እንደሚሞቱ ነው፡፡ የአሜሪካው CMS (Center for Medicaid and Medicare Services) ሪፖርት ከሠጡት አብዛኞች የነርሲንግ ሆም ተቋሞች ያጠናከረውን አስደንጋጭ መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ በቻርቱ እንደምታዩት፣ በበሽታው ከተያዙት ከ60 439 ሰዎች መሀከል፣ 25 923 ሞተዋል፡፡ በፐርስንት ሲሰላ 43 ነው፡፡ ግማሹን በሉት፡፡ በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ ምክንያት አለ፡፡ የነርሲንግ ሆም ሰዎች፣ በዕድሜ የገፉና በብዛት ሌሎች ተደራቢ በሽታዎች አንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ ተደጋግሞ እንደታየው፣ በኮቪድ ከተያዙ በኋላ አሰከፊ ውጤት የሚደርስባቸው ሰዎች ናቸው፡፡

ወደ ሀገር ቤት ብንመለስ፣ እንደ አሜሪካ አዛውንቶችን አንድ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚረዱ ተቋማት ብዛት እንደሌለ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን፣ እንደ ባህላችን፣ ወላጆችን በቤታቸው ወይም በየልጆቻቸው ቤት መጦር የተለመደ ነው፡፡ ፍራቻው ደግሞ፣ እነዚህ በየቤቱ የተቀመጡ የዕድሜ ባለፀጎችን፣ ሌሎች አብረዋቸው የሚኖረ ወጣ ገባ የሚሉ ሰዎች ቫይረሱን ሊያቀብሏቸው እንደሚችሉ ነው፡፡ ለዚህ እንግዲህ፣ እንደዚህ አይነት ሰዎች በየቤቱ ያሉባቸው ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ነው፡፡ በጥናት የረዳ ነገር የታየው፣ ወጣ ገባ የሚሉትም፣ አዛውንቱም ማስክ ቢያደርጉ ሠርጭቱን ይቀንሱታል፡፡

በተጨማሪማ፣ ወረርሽኙ አስከሚያልፍ ድረስ፣ እነዚህ በዕደሜ የገፉ ሰዎች ከቤት ውጭ መውጣትና ርቀው መሄድ እንዳይሄዱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ፣ ቤተክርስቲያንና ፀሎት ቤቶችንም ይጨምራል፡፡(ይከብዳል) ነገር ግን አማራጭ ሰሌለም ነው፡፡

መረጃው የሚያሳየው፣ የነርሲንግ ሆም ሠራተኞች በቫይረሱ ከመያዝ አላመለጡም፡፡ ደግነቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በንፅፅር ሲታይ አነስተኛ ነው፡፡ ማለትም ከ34442 ሠራተኞች መሀከል፣ 449 ሞተዋል፡፡

ሌላው አስፈሪ ቁጥር የወጣው ደግሞ፣ የአሜሪካው CDC ይፋ ያደረገው በቫይረሱ የተያዙ የጤና ባለሙያተኞች ቁጥርና በዚሁ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ነርስና ሀኪሞች ሌሎችንም ጨምሮ ነው፡፡ በቫይረሱ የተያዙት የጤና ባለሙያተኞች ቁጥር 66 770 ሲሆን ከነሱ መሀከል 323 ሞተዋል፡፡

እንደገና ወደ ሀገር ቤት ዞር ብለን ብንመለከት፣ የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረ መሄዱን አናያለን፡፡ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎችን ማጨናነቃቸው የሚቀር ነገር አይደለም፡፡ መለስ ብለን የአሜሪካውን ችግር ብናይ፣ በቂ የሆነ ሙሉ የጤና ባለሙያተኞች የሚለብሱት መከላከያ በበቂ ደረጃ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያም ቢሆን ይህ ችግር የከፋ እንደሚሆን ነው፡፡ ሰለዚህ ርዳታችን አንደሚያስፈልጋቸው አስቀድሞ መገንዘብም ያስፈልጋል፡፡


በኮቪድ ሥርጭት ቤተሰብዎን ለማዳን የሚረዳ ታላቅ ግኝት “የጨነቀ ዕለት” አለ ድምፃዊው 5/31/20

የሳርስ ኮሮና ቫይረስ ቁ2 (ሳኮ2) ከሰው ወደ ሰው በመሸጋገር አደገኛነቱን ወይም የተዋጣለት መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ታዲያ በጣም የሚሸጋገርባቸው ቦታዎችን ካየን፣ አንዱና ትልቁ በቤተሰብ መሀል በቤት ውስጥ ነው፡፡
ለምን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው


In 2020 

የድረ ገፁ ጉብኝት ቁጥር

387,142

ቨርጂኒያ ሰቴት በአለክሳንደሪያ በሚገኝ የኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን የኮቪድ-19 ሥርጭት 08/21/2020

 
 በዚህ ሥርጭት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በትክክል ባይታወቅም፣ ቁጥራቸው ከሀምሳ በላይ የሆኑ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ነው ተብሎ ይነገራል፡፡ ለኮቨደ-19 ተጋልጠው ሊሆን ይችላል የተባሉት ቀናት አገስት 14-17 ባለው ጊዜ ነው፡፡

በዚህ ሥርጭት በቫይረሱ ከተያዙ መሀከል ሰባት ሰዎች ሆሰፒታል ገብተው ርዳታ እየተደረገላቸው ነው፡፡ ከነዚህ መሀከል ደግሞ ሶስቱ በICU እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ የታመሙት ሰዎች ባካባቢው ባሉ ሁለት ሆስፒታሎች ውስጥ ነው ርዳታ እየተደረገላቸው ያለው፡፡ በተላላፊ በሽታዎች መጋለጥ ሲኖር የሚደረገው የተጋለጡ ሰዎች ክትትልና ምርመራ ይካሄዳል፡፡ ለዚሀም ከላይ የሚታየው በራሪ ወረቀተ በአካባቢው የጤና ቢሮ በኩል ጥሪ እንዳደረገ ያሳያል፡፡

መረዳት ያለብን፣ ምርመራ ማድረግ የሚገባቸው ሰዎች፣

 1. በዋናነት በቤተ ክርስቲያኑ በተጠቀሱት ቀናት አገልግሎት ለማግኘት የሄዱ ሰዎች
 2. ቤተክርሰቲያን ሄደው ምርመራ ተደርጎላቸው መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቤተሰቦች
 3. በቤተክርስቲየኑ የነበሩ ምርመራ ባያደርጉም፣ የኮቪድ-19 ህምም ስሜት ያለቸው ሰዎች ቤተሰቦች
 4. ከላይ የተጠቀሱት ሰዎቸ ጋር በቫይረሱ ሊጋለጡ በሚችሉበት ደረጃ ግንኙነት የነበራቸው ሰዎቸ

እንደሚታወቀው በቫይረሱ ተይዘው ምንም አይነት የበሽታስሜት ላይኖራቸው የሚችሉ ሰዎች አሉ፡፡ የበሽታ ስሜትና ምልክት ባይኖራቸውም ቫይረሱን ወደሌሎች ማስተላለፍ እንደሚችሉም ይታወቃል፡፡ አሳዛኝ ሆኖ የነዚህ ሰዎች ቁጥር እስከ 40% ወይም ከዛ በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰለዚህ በቤተክርሰቲያኑ ውስጥ አገልግሎት ለማግኘት የሄዱ ሰዎች በሙሉ ምርመራ አድረገው በቫይረሱ አለመያዛቸው አስኪረጋገጥ ድረስ፣ ራሳቸውን ከቤተሰብና ከቤተዘመድ ወይም ከሥራ ቦታ አግልለው መቆየት የግድ ነው፡፡ ሰብኣዊነትም ነው፡፡

በአጠቃላይ፣ ቫይረሱ ከሚዛመተባቸው ቦታዎች አንዱ ሰዎች በብዛት የሚሰበሰቡት ቦታ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በተለይም በቤት ውስጥ በቂ ጥንቃቄ፣ ማለትም መራራቅና ማሰክ ማድረግ ቢኖርም፣ በሌሎች የአሜሪካ ከተሞች ቤተክርስቲያናት እንደተዘገበው ሥርጭት ሊኖር ይችላል፡፡ ዋናው ችግር ደግሞ፣ ወደ ቤተክርስቲያን ከሚሄዱት ምዕመናን መሀከል በዕድሜ የገፉ በቫይረሱ ቢያዙ ከፍተኛ ችግር ላይ ሊወድቁ የሚችሉ ሰዎች አሉበት፡፡

ሰለዚህ በኣካባቢው የኮቪድ ሥርጭት በሚገባ መጠን ባልወረደበት፣ በተለይም በማሀብረሰቡ ውስጥ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍ ባለበት ሁኔታ፣ አማራጩ፣ የሥርጭቱ ቁጥር በሚገባ እስኪወርድ ድረስ፣ የሰዎች ስብስን ማቆም ነው፡፡ በተለይም በዕድሜ የገፉ ሰዎችና ተደራቢ በሽታ ያለባቸው ሰዎች፡፡ ይህ ማለት፣ እያንዳንዱ ሰው የአካባቢውን የኮቪድ ሥርጭጥ መከታተል፣ በተለይም በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የኮቪድ መጠን ማወቅ ይገባዋል፡፡ በበቂ መረጃ ቁጥር መሥጠት ባይቻልም፣ የኢትዮጵውያኑ ማህበረሰብ ከሚገባው ድርሻ በላይ በኮቪድ የተያዙ ሰዎች እንዳሉበት የሚጠቁሙ ነገሮች አሉ፡፡ ችግሩ ሌሎች በተለይም ዕድሜያቸው ያልገፋ ሰዎች ወጣ ወጣ ቢሉና ቢያዙ ተመልሰው ወደየቤቱ መውሰዳቸው አይቀርምና፣ ለሌሎች ሰዎች፣ ለማህበረሰቡም ሲሉ በቂ ጥንቃቂ ቢያደርጉ ሰብአዊነት ነው፡፡ በቅርቡ በወጣ ዘገባ፣ የበሽታውን ሥርጭት የሚያጋግሉት ዕድሜያቸው በ30ዎችና በ49ዎች አመታት ውስጥ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡

እንደ ማህበረሰብ ማሰብ ሰለሚኖርብን፣ በቂ ጥንቃቄ አለማድረግና ቫይረሱ እንዲሠራጭ ምክንያት መሆኑ የሚያሰክትሏቸውን መመልከት ያስፈልጋል፡፡

 1. በቫይረሱ ተይዘው የሚታመሙ ከዛም ህይወታቸው ሊያልፍ የሚችሉ ሰዎች መኖራቸው
 2. በማህበረሰቡ ውስጥ ሥርጭቱ ከፍ ባለ ቁጥር ማህበረሰቡ በሌሎች በኩል በተለየ አይን መታየት ሊጀምር ይችላል
 3. በንግዱ ወይም በቢዝነስ ላይ ያለው ወገን፣ ሥርጭቱ ቶሎ ወርዶ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲመለስ በሚመኝበት ወቅት፣ አዲስ የቫይረስ ሥርጭት ሲካሄደ ቢያዩ በፀጋ የሚቀበሉትም ነገር አይደለም፡፡
 4. ከላይ ቤተክርስቲያኑ በኩል ሥርጭት ሲከሰት፣ የመንግሥት አካላት በተለይም CDC ሰለ ሥርጭቱ ጥናት ማድረጉ የሚቀር ነገር አይደለም፡፡ ጥናት ካደረጉ ደግሞ ሁሉም ነገር በደንብ አጥንተው በፅሁፍ ማውጣታች አይቀርም፡፡ ሰለዚህ የኢትዮጵውያን ማሀበረሰብ ተብሎ መጠቀሱም አይቀርም፡፡ በእንደዚህ አይነት ጥናታዊ መግለጫ ስማችን መጠራቱም ሌላ ስሜት የሚፈጥር ነገር ነው፡፡

ሰለዚህ ቫይረሱን የምትደፍሩ ሰዎች፣ ለቤተሰብ፣ ለጓደኛ፣ ለማህበረሰቡም ስትሉ ሥርጭቱ ለመቀነስ ከሚታገሉ ሰዎች ጋር በመተባበር የሚገባውን ጥንቃቄ አድርጉ፡፡ እዚህ ላይ፣ በቫይረሱ ተጋልጠው፣ ነገር ግን ምርመራ አናደርግም በማለት ምንም እንደሌለ አድርገው ከቤተሰብና ከሌሎች ጋር የሚደባለቁ ሰዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም፣ በእንደዚህ አይነት ፅሁፍ ላይ እከሌ ወይም እነከሌ ማለት አግባብ ሰለማይሆን እንጂ፣ መታመማቸውን እያወቁ ወደ ሥራ ቦታ በመሄድ ሌሎቹን ሰዎች ያጋለጡ ሰዎች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ በአሸማጋዮች ሁል ጊዜ የሚጠቅስ ነገር ቢኖር፣ አባክህን “ለሰው ብለህ” የሚለው አባባል ነው፡፡ 

ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጋር ያገናኘን ነገር

ነብሳቸውን በገነት ያኑረውና በቅርቡ ያረፉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ የተደበቀው ማስታወሻ የተባለውን በእኔና በአቶ ደሳለኝ አለሙ ለህዝብ የቀረበውን መፅሐፍ እንዳነበቡና፣ መፅሐፉን ብዙ ቦታዎች ላይ ምልክት እንዳደረጉበት አንድ ሰው ሹክ ብሎኝ ነበር፡፡ ቆየት ብለው ግን፣ በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ፣ የሚከተለውን አስተያየት ፅፈው አነበብኩ፡፡ መፅሐፉን ያነበበ ሰው፣ ፕሮፌሰሩ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ብዙ ቦታ ምልክት ማድረጋቸው የሚያስገርመው አይመስለኝም፡፡ ያላነበባችሁ ብታነቡት ይመከራል፡፡ በማንበባችሁ እንደምተደሰቱ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እንደዚያ ባይሆን አይደክምበትም ነበር፡፡ ትርፍ ቀርቶ ዋናውን በመለሰ፡፡

A post from Professor Mesfin's page
Mesfin Wolde-Mariam
December 9, 2015 ·


የወኔ ተስፋ

በኢጣልያ ወረራ ጊዜ በደጃዝማች አያሌው ብሩ የጦር ሰፈር አንድ አማርኛን አቀላጥፎ የሚናገር ስዊድን ሀኪም አብሮ ነበረ፤ ትዝብቱን ጽፎ የተተረጎመውን ሳነብ አንድ ልብን በኩራት የሚያሳብጥ ታሪክ አነበብሁ፤ ስለደጃዝማቹ ጦር ሲናገር በከፊል እንደሚከተለው ነው፤--

‹‹በግምት ከየመቶው ሰው ሰባቱ ጎራዴ ብቻ ወይም በትር የያዙ ናቸው፤ በተለይ የማስታውሰው የአሥራ ስምንት ዓመት ወጣት ልጅ በኩራት መንፈስ ዱላውን በቀኝ ትከሻው ላይ አድርጎ ይንጎራደድ ነበር፤ ዱላው የእንጨት ሲሆን ቀይ ቀለም ያለው ሆኖ እላዩ ላይ ጌጥ ተቀርጾበታል፤ የዚህ ወጣት ልጅ የተለየ ኩራትና አካሄድ የሰዎችን ዓይን የመሳብ ችሎታ ፈጥሯል፤

ደጃዝማች አስጠሩትና
ዕድሜህ ስንት ነው?
አባቴ የሚነግረኝ በንጉሥ ሚካኤልና በሸዋ ገዢዎች መሀከል በተደረገው የሰገሌ ጦርነት ወር ነው የተወለድኩት፤
መልካም በዚህ በሚያምር ዱላህ ምን ልታደርግበት ነው?
በዚህ ዱላ ነጭ ልገልበት ነው፤
እንደሱ እንኳን ማድረግ አትችልም፤ በምትኩ ጠመንጃ ልስጥህ፤
የለም አመሰግናለሁ፤ ለአባቴ የማልኩት ቃለ መሐላ ጣልያን ገድዬ ጠመንጃውን ወስጄ አሳያለሁ፤ አለዚያ በዚህ በጦር ሜዳ እቀራለሁ፤››


የተደበቀው ማስታወሻ ከሚል መጽሐፍ፡፡

እኔ መስሎኝ የነበረውና የማምነው ኢትዮጵያውያን ምርጫ ካላቸው ቀላሉን እንጂ ከባዱን አይመርጡም የሚል ነበር፤ ይህ ወጣት የቆየ እምነቴን አነከተው! አንዳንድ ኢጥዮጵያውያን ከባዱን የመምረጥ ወኔ አላቸው ማለት ነው፤ አምላክ ዘሩን ያበርክተው! ልቤን በኩራት አሳበጠው፤ የኢትዮጵያዊነት ክብሬንም አደሰው! የዚህ ወጣት ወኔ በብዙ መልኩ የሚታይ ነው፤ የዛሬ ወጣቶች አባባሉን እንዲመረምሩት እተውላቸዋለሁ፡፡

መስፍን ወልደማርያም 

የኮቪድ - 19 ክትባት ጥናት በአካባቢዎ

 ይህ ክትባት አሁን በጥናት ላይ ነው፡፡ ደረጃዎችን ተሻግሮ፣ ለህዝብ አግልግሎት በስፋት መድረስ እንዲችለ በሳይንሳዊ ጥናት በኩል ማለፍ አለበት፡፡ ብዙ ጊዜ ጥናቶች በተወሰኑ የህብረተሰብ ወገኖች ላይ ብቻ ሰለሚጠኑ፣ ጥነቱ ተጠናቆ ውጤት ሲመጣ፣ በጥናቱ ላይ ያልተሳተፉተን የህብረተሰብ ክፍሎች ይረዳ ይሆን ተብሎ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ እንደሚታወቀው አብዛኞቹ ጥናቶች የነጭ ዝርያ ባላቸው ሰዎች ላይ ሰለሚደረግ፣ የጥናቱ ውጤት ለሌሎች የነጭ ዝርያ ለሌላቸው ሰዎች ይሆናል ወይ የሚል ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ልዩነት የሚፈጠረው፣ ከዚህ ቀድም የነጭ ዝርያ ያልሆኑ ሰዎችን በጥናቱ በስፋት በላማሳተፍ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን፣ የነጭ ዝርያ የሌላቸው (ማይኖሪቲስ) በበቂ መጠን በጥናቱ ውስጥ አለመሳተፍ ነው፡፡

እንደሚታወቀው የኮቪድ-19 ሥርጭት ድንበርና ዘር ሳይለይ ሁሉንም እያጠቃ ባለበት ጊዜ፣ በተለይ በአሜሪካ በጣም ተጎጂ ሆነ የተገኘው ህብረተሰብ (ማይኖሪቲ) የሚባለው ነው፡፡ ይህንን ፓንደሚክ ለማስቆም ዋናው መንገድ ክትባት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ክትባቱም በቶሎ መድረስ አለበት፤ ነገር ግን በሚገባ በሳይንሳዊ ጥናት በኩል አልፎ መሆን አለበት፡፡

በዲሲ ሜሪላንደና ቨርጂኒያ አካባቢ ይህንን የክትባት ጥናት የሚያካሂዱ ድርጅቶች አሉ፡፡ ለዚህ ጥናት ደገሞ በቂ የሆነ መጠን የነጭ ዝርያ ለሌላቸው ሰዎች የተከፈተ በመሆኑ፣ በጥናቱ የመሳተፍን ዕድል ፈጥሯል፡፡

በዘር የምንለያየውን ያህል፣ በተፈጥሯችን ለበሽታዎች የምንሰጠው ምላሽ፣ ለመድሐኒትና ለክትባቶች የምንሰጠው ምላሽ የተለያዬ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ልዩነት መኖሩን ለማወቅ በጥናቶች መሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ጥናት መሳተፍ ደግሞ፣ ለህብረተሰቡ ከፍተኛ ርዳታ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ላለው ህብረተሰብ ብቻ ሳይሆን በሀገር ቤት ለሚኖሩ ወገኖችም ታላቅ ርዳታ ነው፡፡ ምክንያቱም ጥናቱ ተጠናቆ ለሥራ ቢውል፣ በጥናቱ ላይ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ሰዎች ሰለተሳተፉብት በነዚያ ሰዎች ላይ የሚታየው ምላሽ በግልፅ ሰለሚታወቅ ወዲያውኑ ለአገልግሎ ይውላል፡፡ መታወቅ ያለበት፣ ጥናቶቹ በዚህ ደረጃ ሲመጡ የጥናት ተሳታፊዎች ላይ ክፈተኛ ጉዳት የማያደርሱ መሆናቸው ከታየ በኋላ ነው፡፡ አለበለዚያ ከመጀመሪያው አንዲቆሙ ነው የሚደረገው፡፡

በዲሲ ሜሪላንድና ቪርጂኒያ አካባቢ ለምትኖሩ ሰዎች፣ ከሥር በበራሪው ወረቀት እንደሚታየው፣ የክትባት ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡ ሞደርና የሚባል ካምፓኒ ከአካባቢው የህክምና ባለሙያተኞች ጋር በመሆን፣ የክትባት ጥናት እያካሄደ ነው፡፡ ጥናቱ የሚካሄደው በሮክቪል (Rockville) ከተማ ነው፡፡ በጥናቱ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ከሆኑ፣ በስልክ 912- 623 2240 ይደውሉ፡፡ አለዚያም ወደሚከተለው ድረ ገፅ በመሄድ (MCRMED.COM/COVID) መመዝገብ ይችላሉ፡፡


በጥናቱ ውስጥ መሳተፍ የሚችሉ መሆኑ ከታወቀ፣ ከጥናቱ ጋር በተያያዘ የሚወጣውን ወጭና የላቦራቶር ምርመራዎችን ጥናቱ ራሱ ይሸፍናል፤ ሰለዚህ ኢንሹራንስ አያስፈለግዎትም፡፡ በተጨማሪም፣ በጥናቱ ለመሳተፍ የሚወስዱትን ጊዜና ትራንሰፖርት ታሰቢ በማድረግ ክፍያ ይኖረዋል፡፡ የበለጠ ለመረዳት ከላይ የተጠቀሰውን ቁጥር ይደውሉ፡፡ 

የቫይታሚን ዲ (Vitamin D) ዕጥረትና እና ኮቪድ-19

ኮቪድ-19 ከተከሰተ ወዲህ፣ አሁን ረገብ አለ እንጂ፣ ይህን ብሉ፣ ይህን ጠጡ፣ ይህን አጭሱ፣ ይህን ቆርጥሙ እየተባለ እየተመከረ ብዙ ጉዳትም ሲደርስ አይተናል፡፡ ክሎሮኪዊን ያለበትን የአሳ ገንዳ ማጠቢያ ኬሚካል ጠጥተው የሞቱና የታመሙም አሉ፡፡ ለእጅ መታጠቢያ የሚሆነውን አልኮል ጠጥቶ ድንገተኛ ክፍል ድረስ የደረሰ ሰው አለ፡፡ ወደ አሪዞና ደግሞ፣ ለእጅ ንፅህና የሚዘጋጅ ሳኒታይዘር ተጠቅመው የታመሙ፣ የአይን ብርሃን ያጡ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ እንኳን አደጋው የደረሰባቸው፣ ለእጅ መፅጃ የሚዘጋጀው አልኮል፣ ኤቲል አልኮል (Ethyl alcohol)  መሆን ሲገባው፣ ሰዎቹ የተጠቀሙት ግን ሜቲል አልኮል (Methyl alcohol)  የሚባል፣ ያልተፈቀደ የአልኮል ዝርያ የሆነ ኮምፓውንድ በሳኒታይዘሩ ውስጥ መገኘቱ ነው፡፡ አንባቢዎች፣ ለእጅ ማፅጃ የምትጠቀሙበት አልኮል (Ethyl alcohol) ኤትል አልኮል መሆኑን አረጋግጡ፡፡ ድንገት በግርግር ትርፍ ለማግኘት ያሰበ ሜቲል (Methyl alcohol) አልኮል ያለበት ሳኒታይዘር ሊያቀርብ ስለሚችል፣ ሜቲል አልኮል ያለበት ማፅጃ እንዳትጠቀሙ አደራ እላለሁ፡፡

ወደ ርዕሱ ስንመለስ፣ የቫይታሚን ዲ ዕጥረት ለብዙ በሽታዎች ምክንያት ይሆናል ተብሎ ያልተበረበረ ጥናት የለም፡፡ አንድ ሰሞንማ በህክምናው አለም፣ ቫይታሚን ዲ ወሳኝ ነብስ አድን አይነት መድሀኒት ሊሆን ምንም አልቀረውም፡፡ በመረጃ ወይም በጥናት የተደገፈ ምንጭ ሲኖር፣ በባዶ የሚወራውም ነገር እየከሰመ ይሄዳል፡፡ ቫይታሚን ዲ ከኮቪ-19 ጋር በተያያዘም ቀደም ብሎ የወጡ አመለካከቶች ነበሩ፡፡ አሁን ግን፣ የአሜሪካ የአጥንትና የሚኔራል ምርምር ቡድን በቅርቡ ባደረገው ስብሰባ፣ በአካል አይደለም፣ ያው ቨርቹዋል (virtual) ያቀረቡት ነገር፣ የቫይታሚን ዲ ዕጥረት ያለባቸው በኮቪድ-19 የተያዙ ህሙማን፣ ህመሙ ጠንቶባቸው ወደ ICU እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል የሚል ነው፡፡ ወደ ICU ለመግባት ዋናው ምክንያት ሳምባ ላይ የሚደርሰው አጣዳፊ የሆነ የሳምባ ሥራ መታወክ ብቻ ሳይሆን ሥራውን ማከናወን የማይችልበት ደረጃ ሲደርስ ነው፡፡ በአንግሊዘኛ Acute Respiratory Distress Syndrome (ARDS) ይባላል፡፡ ለብዙ በኮቪድ-19 ለተያዙ ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያትም ይህ የተገለፀው የህመም አይነትና ደረጃ ነው፡፡ በዚህ ህመም፣ ሰዎች በራሳቸው በመተንፈስ በቂ አኮስጅን ወደ ሰውነት ማድረስ ሰለማይችሉ ወደ ICU እንዲገቡ ተደርጎ ቬንቲሌተር (አርቲፊሻል መተንፈሻ) ላይ  ይሆናሉ፡፡

ጥናቱ የቀረበው በኢጣልያ ሀኪሞች በኩል ነው፡፡ እንደነሱ አገላለፅ፣ የቫይታሚን ዲ ዕጥረት ያለባቸው ሰዎች ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ARDS ውሰጥ የሚገቡ ሲሆን፣ እንደ ሀኪሞቹ ገለፃ ደግሞ፣ በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኘው የቫይታሚን ዲ መጠን ከ20ng/ml በታቸ ከሆነ ደግሞ ህሙማኑ ወደ ሕይወት ማለፍ ደረጃ መድረስ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ፡፡ ሳትጠይቁ፣ ጤናማ የቫይታሚን ዲ መጠን ስንት እንደሆነ ላካፍላችሁ፡፡ ጤናማ መጠን የሚባለው ከ30 ng/ml በላይ ሲሆን ነው፡፡ ገደቡ ትንሽ ይለያያል፣ ከ20 እሰከ 40 ጤናማ ነው የሚሉም አሉ፣ ከ30 እሰከ 50 ጤናማ ገደብ ነው የሚሉ አሉ፡፡ በዕለት ከዕለት ሥራችን ከ30 በታች ከሆነ፣ ያነሰ ነው እንላለን፡፡

ሰለ ቫይታሚን ዲ፣ ከሚታወቀው ከአጥንት ጥንካሬ ጋር ካለው ግንኙነት በተጨማሪ፣ ሰውነታችን በህዋሳት በሚወረርበት ጊዜ (ኢንፌክሽን)፣ ሰውነት ራሱን ለመከላከል በሚለቃቸው ኬሚካሎች አማካኝት የሚከሰተውን ኢንፈላሜሽን የተባለ ሂደት ይቆጣጠራል፡፡ ካስታወሳችሁ፣ ኮቪድ-19፣ አንዱ ትልቁ ችግሩ ይህ ኢንፈላሜሽን የሚባለው ሂደት ከመጠን በላይ በመሆን መልሶ ሰውነትን ይጎዳል፡፡ በተለይም ከዚህ ጋር በተያያዘ በልጆች ላይ የሚከሰት በሽታም አለ፡፡ (Mutlisystem Inflammatory Syndrome in Children, MIS-C) ይባላል፡፡ እንደ ሳይንቲሰቱ አገላለፅ፣ ቫይታሚን ዲ፣ ሰውነት ቫይረሱን ለማጠቃትነገር ግን ከመጠን በላይ የሚለቃቸው ኬሚካሎችን በመቀነስ፣ የደም ሥሮች ግድግዳ ላይ ያሉ ሴሎችን ጤናማ እንደሆኑ እንዲቆዩ ማድርግና፣ ከዛም በብዛት በኮቪደ-19 ላይ እየታየ ያለውን በደም ሥሮች ውስጥ የደም መርጋትን ሁኔታ እንዲቀነስ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሌላ አገልግሎት ያለው መሆኑ ተገልጧል፡፡ እንግዲህ እንዲህ አይነት ሥራን ለማከናውን፣ በሰውነት ውስጥ የቫይታሚን ዲ መጠን ጤናማ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ሁላችንም እንስማማለን፡፡

ከዚህ በፊት የተጠኑ ጥናቶች የሚጠቁሙት፣ የቫይታሚን ዲ ዕጥረት መኖር፣ ባጠቃላይ በመተንፈሻ አካላት ላይ ኢንፊክሽን እንዲኖር አደጋውን እንደሚጨምር ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ ቫይታሚን ዲ መውሰድ በመተንፈሻ አካላት ላይ የሚደርሰውን ኢንፌክሽን ይቀንሳል የሚሉ ናቸው፡፡

አስታውሳችሁ ከሆነ፣ የፀሀይ ብርሃን በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የቫይታሚን ዲ መጠን አንዲጨምር የሚረዳ ሲሆን፣ የቫይታሚን ዲ መጠን ባጠቃላይ በክረምት ወራት አነስ ብሎ ሲታይ፣ በበጋው ወራት ደግሞ መጠኑ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ ይህ እንግዲህ በሰዎች ደም ውስጥ ሲለካ ነው፡፡ እንደምንኖርበት አካባቢም የቫይታሚን ዲ መጠን የተለያየ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ውዝግብም ነበር፡፡ ጤናማ መጠን የትኛው ነው የሚል፡፡ ምክንያቱ ግልፅ ባይሆንም፣ በአውሮፓ ካሉ አገራት የኢጣልያ ሰዎች፣ በከፍተኛ ደረጃ የቫይታሚን ዲ ዕጥረት አለባቸው ተብሎ ይታወቃል፡፡ ኢጣልያዊው ዶክተር የሚሉት በኢጣልያ በተለይ በክረምቱ ወራት፣ በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍ ያለ ነበር፣ በጋው ሲመጣ ግን የሞቱ ቁጥር ቀነሰ፡፡ በበጋው ወራት በፀሀይ ብርሃን ምክንያት የቫይታሚን ዲ ዕጥረት እንደ ክረምቱ ወራት አይከፋም፡፡

ይህንን እየፃፍኩ፣ አፍሪካ ትዝ አለኝ፡፡ እንደምታውቁት በኮቪድ-19 ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከሌሎች አህጉራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅ ያለ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ እስካሁን ድረስ፡፡ ህም፣ ቫይታሚን ዲ መላ ምት፣ በመላ ምት ደረጃ ይቻል ይሆን?

ወደ ጥናቱ ስንመለስ፣ የቫይታሚን ዲ ዕጥረት ያስከትላል የተባለውን ችግር ለመመርመር፣ በኢጣልያ በኮቪድ -19 በከፍተኛ ደረጃ የታመሙ በሚላን፣ ሳንታ ሉካ ሆስፒታል የገቡ 103 ሰዎችን ለጥናቱ መለመሉ፡፡ ከማርች 9 አስከ አፕሪል 30 ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ እነዚህን ሰዎች ደግሞ 52 በኮቪድ የተያዙ የበሽታ ስሜት ወይም ምልክት የሌላባቸው ወይም ቀለል ያለ ህመም ከታየባቸው ሰዎች ጋር ለማነፀፀር ጥናቱ ውስጥ እንዲገቡ ተደረገ፡፡ ከነዚህ በተጨማሪ፣ 206 ሰዎች፣ በእድሜና በፆታ ከህሙማኑ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ነገር ግን በኮቪድ-19 ያልተያዙ፣ በመደበኛ ጤና ምርመራ ጊዜ የቫይታሚን ዲ መጠን የተለካላቸውን ሰዎቸ ከህሙማኑ ጋር ማነፃፀሪያ አደረጉ፡፡ በጥናቱ የተሳተፉ ሰዎች አማካይ ዕድሜ 66 ነበር፡፡ ከሌሎቹ ጋር ሲወዳደር፣ በዕድሜያቸው የገፉ፣ ወንዶች እና በኮቪድ-19 ህመም የጠናባቸው ሰዎች የነበራቸው የቫይታሚን ዲ መጠን በጣም ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡  በተደረገው ምርመራ፣ የቫይታሚን ዲ መጠን ዝቅ ባለ ቁጥር፣ ኢንፈላሜሽን ለመኖሩ ምልክት የሚሠጡ ሁለት ኮምፓውንዶች መጠን ከፍ ብሎ ታይቷል፡፡

ወደ ሆስፒታል ሲገቡ፣ በጠና የታመሙ ሰዎች የቫይታሚን ዲ መጠን ዝቅ ያለ ሆኖ ተገኝቷል፣ 18.2ng/ml፡፡ በኮቪድ -19 ቀለል ያለ ህመም የታየባቸው ሰዎች ደግሞ የቫይታሚን ዲ መጠን 30.3ng/ml ሲሆን፣ በሌሎቹ ለማነፃፀሪያ ጥናቱ ውስጥ የተካተቱ ግን በኮቪድ-19 ያልተያዙ ሰዎች የቫይታሚን ዲ መጠን 25.4ng/ml ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በስታቲሰቲክሰ ሲታይ፣ ይህ ልዩነት ትክክለኛ ልዩነት ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ማለትም የቁጥር ልዩነት ብቻ አልነበረም፡፡

ARDS ደረጃ ደርሰው ወደ ICU የገቡት 54 ሰዎች፣ በጠና ታመው ማለት ነው፣ የቫይታሚን ዲ መጠን ሲለካ 14.4ng/ml ሆኖ ተገኝቷል፡፡ እነዚህ ሰዎች፣ ተደራቢ በሽታ ያለባቸው ሲሆን፣ የቫይታሚን ዲ መጠን ዝቅ ብሎ መገኘት ብቻ ሳይሆን፣ የኮቪድ በሽታ መበርታት ምልክት ነው የሚባለው IL-6 የኢንፍላሜሽን ጠቋሚ ኮምፓውንድ ከፍ ብሎ ተገኝቷል፡፡ 19 ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ የሞቱትም በ ARDS ነበር፡፡ በህይወት ከተረፉት ጋር ሲወዳደር፣ የቫይታሚን ዲ መጠን 13.2 ng/ml ነበር፣ የተረፉት ደግሞ የቫይታሚን ዲ መጠን 19.3 ng/ml ሆኖ ተገኝቷል፡፡

እንደ ሀኪሙ ማጠቃለያ፣ የቫይታሚን ዲ መጠን ዝቅ ማለት በራሱ ብቻውን ከከፍተኛ ህመም ደረጃ በመድረስ ወደ ICU ለመግባትና የህይወት ማለፍ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ፡፡

እንግዲህ በሳይንሳዊ ጥናት የተሳታፊ ቁጥር ማነስ ለጥናቱ ጥንካሬ ባይሰጠውም፣ ሀኪሞቹ የሚሉት፣ ተጨማሪ ቫይታሚን ዲ መስጠት በኮቪደ-19 ምክንያት የሚደርሰውን የመተንፈስ ችሎታ መድከም ይቀንስ እንደሆን ተጨማሪ ሥራ ይሠራ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም፣ የቫይታሚን ዲ መጠን ጤናማ መጠን እንዲሆን ማድረግ ወደፊት በኮቪድ-19 ምክንያት የሚከሰተውን የበሽታ መበርታት ለመቀነስ አስተዋፅኦ ያደርጋል ይላሉ፡፡

ዋናው መልክት የቫይታሚን ዲ ዕጥረትን ማስተካከል ነው እንጂ ከሚገባው በላይ ቫይታሚን ዲ መውሰድ ተገቢ እንደማይሆን ነው፡፡ ይህ ጥናት ከመውጣቱም በፊት፣ ዕጥረት አስተካክሉ ነበር መልክቱ፡፡ በአብዛኛው በሥራ ቦታ የቫይታሚን ዲ መጠን ስንለካ፣ በጣም ጥቂት ሰው ነው ጤናማ መጠን ያለው፡፡ በአሜሪካ፣ ለፀሀይ ብርሃን የምንጋለጥባቸው ወራቶች በጣም ጥቂት ሆነው፣ ለሱም ቢሆን ከቤት ወጥቶ ወደ መኪና፣ ከመኪና በአብዛኛው የፀሀይ ብርሃን ማግኘት ቀርቶ ማየት ወደማይቻልባቸው የሥራ ቦታዎች ነው የምንገባው፡፡ በምግብ በኩል፣ ቫይታሚን ዲ በበቂ መጠን አለባቸው የሚባሉ እንደ አሳ (በተለይ ሳልመን) ቱናን ጨምሮ፣ በመጠኑም ቢሆን በአይብ፣ በእንቁላልም፣ በወተትም ይኖራል፡፡ ይህንን ስዘረዘር ከይቅርታ ጋር ነው፡፡ ለምን እንዳልኩ ይገባችኋል፡፡

ሰለዚህ ቢቻል የቫይታሚን ዲ መጠን መለካትም ጥሩ ነው፡፡ ኮቪድ ባይኖም ለአጥንት ጥንካሬ ይፈለጋል፡፡ ዕጥረት ካለ፣ ዕጥረቱን ለማስተካከል የሚሰጥ ቫይታሚን ዲ መጠን ይለያያል፡፡ ከዛ ውጭ ግን በቀን አስፈላጊ መጠን የሚባለው የቫይታሚን ዲ መጠን መውሰድ ጠቃሚ ነው፡፡ አቅም ላለው አጥኝ፣ አፍሪካ ወይም በኢትዮጵያ ይህንን ጉዳይ በጥናት ቢመለከቱት ጥሩ ነበር፡፡ ድህነት የሚጎዳው በብዙ መልኩ ነው፡፡ ከመጨረሴ በፊት ግን፣ ቫይታሚን ዲ ከመጠን በላይ ከተወሰድ ጉዳት ያስከትላል፣ የሆድ ህመም፣ ማስታወክና ሌሎችን ጨምሮ በተገላቢጦሽ አጥንት እንዲሳሳ ያደርጋል፡፡ 13 ወራት የፀሀይ ብርሃን ጥቅሙ ይኸው፡፡ ለአጥንት ጥንካሬ ቫይታሚን ዲ የሚወስዱ ከሆን ከካልሲየም ጋር መውሰድ ይረዳል፡፡ ከአፍሪካ ውጭ ለሚኖሩ ሰዎች በቀን መወሰድ የሚገባው የቫይታሚን ዲ መጠን እንደ ዕደሜያችን ስለሆነ የሚከተለውን ሠንጠረዥ ይመልከቱ፡፡ ምንጭ (National Institute of Health office of Dietary Supplements) ይህንን እንኳን በደንብ አካፍሉ፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

የኮቪድ-19 ሥርጭትን በተሳካ ሁኔታ ያሰቆመ አገር አለ ወይ? 08/09/2020

 እንዴታ፣ በደንብ፡፡ ግን ያልተጠበቀ፣ ትንሽ አገሮች ከሚባሉት አንዱ ኒውዚላንደ፣ የኮቪድ-19 ሥርጭትን አስቆመናል ሲሉ በቅርቡ በታወቂው የኒው ኢንግደላንድ መፅሔት ገልፀዋል፡፡
ኒውዚላንድ የማስታወሰው፣ የአጼ ቴዎድሮስ ባለሟል የነበረው ባሻ ፈለቀ (ካፒቴን ሰፒዲ)፣ ከቴዎድሮስ ተለይቶ ከሄደ በኋላ፣ ቅጥር ወታደር በመሆን፣ በኒወዚላንድ የማኦሪወች ጦርነት መካፈሉን ነው፡፡ ማአሪዎች በርግጥም፣ የኒውዚላንድ ቀደምት ኗሪዎች ናቸው፡፡

ማስክ በማድረግ አፍና አፍንጫን መሸፈን ምን ያህል የኮቪደ-19 ሥርጭት ይቀንሳል?
የሚባልላቸውን ያህል ያስጥላሉ ወይ? 6/15/20 


በግልፅም ሆነ በሥውር፣ ዋናው የኮቨድ-19 ሥርጭት መከላከያው፣ ከሰው ራቁ የሚለው መልክት ነው፡፡ ከዛ በተጨማሪ፣ አፍና አፍንጫችሁን ሸፍኑ ነው፡፡ አፍና አፍንጫን ለመሸፈን የተለያዩ አይነት ማስኮች (መከለያ ወይም ጭምብሎች) አሉ፡፡ ለህብረተሰብ አገልግሎት የሚውሉት፣ በአንግሊዝኛው አጠራር (Surgical masks) የሚባሉት ሲሆን፣ ከጨርቅ የተሠሩ ማስኮችም ለአገልግሎት ይውላሉ፡፡ ለአገራችን ገበሬ ወይም የገጠሬው ሰው ደግሞ በጋቢው አፍና አፍንጫውን ከሸፈነም ይረዳል፡፡

በኮቪድ ተይዘው የነበሩ ሰዎች፣ መልሰው በኮቪድ ይያዛሉ ወይ?

መውደድ እንደገና 08/29/2020

 የፍቅር አይደለም፣ የፈረደበት ኮቪደ-19 ነው፡፡

ከዚህ ቀደም እኔም ራሴ ብሆን በማውቀው ሰው በህክምና፣ በኮቪድ-19 ተይዞ ካገገመ በኋላ እንደገና በተመሳሳይ ሁኔታ ሲታመም ታዝቤያለሁ፡፡ ሰውየው አንደገና የታመመው፣ የቤተሰብ አባል የሆነ ሰው ከታመመ በኋላ ነበር፡፡ ያን ጊዜ፣ ጥያቄው፣ አንደገና ወዲያውኑ ከተያዘ፣ መጀመሪያ ከያዘውና ከዛም ካገገመ በኋላ ምንም አይነት የመከላከያ ዘዴ አልነበረውም የሚል ነበር፡፡ እንደዛ ከሆነ ደግሞ፣ ሰዎች መልሰው ተመላልሰው ሊያዙ ይችላሉ ማለት ነው(Reinfection)፡፡ የዚህን ሚስጥር ማወቅ  ብዙ መልስ የሚሠጥ ነገር አለው፡፡

እንግዲህ በጥርጣሬ ላይ እያለን፣ ወደ መጠንቀቁ እየመከርን ባለንበት ወቅት፣ ከሆንግ ኮንግ በኩል በመረጃ የተደገፈ ዘገባ ይቀርባል፡፡፡ የ33 አመት የሆነው ሰው በማርች 26 ታሞ ከዳነ በኋላ፣ እንደገና በኦገስት 15 ይያዛል፡፡ በሁለቱም ጊዜ ሰውየውን የያዘው ቫይረስ በመወሰድ(ፈይሎጀነቲክ) የሚባል ምርመራ ያደርጋሉ፡፡ ባጭሩ የቫይረሱን ዝርያ ማጥናት ነው፡፡

ይህ ቫይረስ ወደ 30ሺ የሚሆኑ የዝርያው አይነት ወይም የዘርገ ሀረጉን የሚወስኑ ኮዶች አሉት፡፡ የዝርያ ለውጥ የሚመጣው ከነዚህ ከ30ሺ ኮዶች ሁለቱ ወይም ሶስቱ ከተቀየሩ፣ ዋናው ሀረጉ ኮሮና ቢሆንም፣ ለየት ያለ አዲስ የኮሮና ቫይረሰ ትውልድ ይሆናል፡፡

ታዲያ በሁለቱም የህመም ጊዜ  ሰውየውን የያዙት ቫይረሶች ጥናት ሲደረግ፣ ሁለቱም ቫይረሶች በመጠኑ የተለየ ዝርያ ያላቸው ሆነው ይገኛሉ፡፡ ማለትም ሰውየው በኦገስት ሲታመም መጀመሪያ በያዘው ቫይረስ ምክንያት ያገረሸ በሽታ ሳይሆን፣ በሌላ ቫይረስ በመያዙ ነው፡፡ እረፉት፣ አንዱ ትልቁ ሥጋት ይህ ነው፡፡ ሁለት ሥጋት በሉት፡፡

አንደኛ፣ በቫይረሱ የተያዘ ሰው በቂ መከላከያ በሰውነቱ ውስጥ አለመኖሩ በመጠኑ ለየት ባለ ሌላ የኮሮና ቫይረስ መያዙ ነው፡፡

ሁለተኛ፤ የኮሮና ቫይረስ ቁ2 (ኮቪድ-19ን የሚያመጣው) በተራባ ቁጥር አዳዲስ ልጆች እየፈጠረ መሄዱ ነው፡፡ አዲስ የተፈጠረው ቫይረስ ደግሞ፣ ከዚህ ቀደም ያልተያዙ ሰዎችን፣ ተይዘው የነበሩ ሰዎችንም መያዝ ከቻለ ሥርጭቱ ማባሪያ የለውም፡፡ ለዚህ መፍትሄው ላለመያዝ፣ ከዛም ቫይረሱን ላለማዛመት የሚገባውን ጥንቃቄ ሳይሰላቹ ማድረግ ነው፡፡

ሌለው፣ ሶስተኛ ሥጋት ደግሞ፣ ይህ እየተቀየረ የመጣው አዲስ የቫይረሱ ዝርያ፣ ባህሪውን ይቀይር ይሆን ነው፡፡ ባህሪውን መቀየር ማለት ደግሞ፣ አስከፊ በሽታ ማምጣት፣ ሰዎችን የመግደል ችሎታ መጨመር ነው፡፡

በሆንግ ኮንግ ሰውየ ስንገረም፣ ከአውሮፓ በኩል ሌላ ዘገባ ወጣ፡፡ ይህም፣ ሁለት ሰዎች እንደገና በኮሮና ቫይረስ ቁ 2 መያዛቸውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

መልክቱ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ያገገሙ ሰዎች፣ እንደገና እንያዝም ብለው እንዳይዘናጉ ነው፡፡ እንዲያውም ከመጀመሪያው በኮሮና ቫይረስ እንዲያዙ ያደረጋቸውን ሁኔታ መልሰው በመገምገም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዝ፣ ይህ ቫይረሰ ብዛት ያላቸው አዳዲስ ዝርያዎችን እየፈጠረ መሄዱ ግልፅ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚፈጠረው፣ ቫይረሱ ራሱን ለማባዘት ወይም ከመጠን በላይ በሚራባበት ጊዜ በሚፈጠር ስህተት አንድ ወይ ሁለት ወይም ከዛ በላይ የዘር ሀረጉን የሚፈጥሩት ኮዶች መሳሳት ነው፡፡ አንግዲህ አዲስ የተፈጠረው በመጠኑም ቢሆን ሳት ያለ ኮድ ያለው ቫይረስ መራባት ከቻለ የራሱን ዘር እያስፋፋ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡

ከወደ ቦሰትን በዘለቀ መረጃ፣ ወደ ቦስተን ወደ ስምንት ጊዜ የኮረና ቫይረስ የገባ ሲሆን፣ በቦሰተን ተስፋፍቶ ከዛም አልፎ አስከ አላስካና ሲንጋፖር ድረስ የተዛመተው ግን የአንድ የተለየ ቫይረስ ዝርያ ብቻ ነው፡፡ ይህ ቫይረስ የተነሳው የአንድ ካምፓኒ አመታዊ ስብሰባ ላይ በተገኝ አንድ ግለሰብ አማካኝነት ነው፡፡ በየካቲትም ሰለነበር፣ ምንም ያልጠረጠሩት የካምፓኒው ሰዎች ሲተቃቀፉ፣ ሲዝናኑ ከርመው፣ ተስብሳቢዎች ወደ የቤታቸውና አገራቸው ሲመለሱ ቫይረሱን ይዘውት ሄዱ፡፡ ቦሰተንም ቆየት ብሎ ይህ ቫይረስ በመጠለያ ቦታዎች ድረስ ዘልቆ በመሄድ ብዙ ሰዎች መያዙን ባወጡት ጥናታዊ ፅሁፍ ገልጠዋል፡፡

አንድ ሰው፣ አንደ የቫይረስ ዝርያ ከአንድ ቦታ ብቻ ተነስቶ ተሰብሳበዊንም ከዛም አልፎ ሌሎችንም ሲይዝ በምስክርነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በእንግሊዝኛው  Super spreading event የሚባለውም ይህ ነው፡፡

ከዚህ መማር የምንችለው፣ በቂ ጥንቃቄ ካልተደረገ በስተቀር ለማሠራጨት አንድ ሰው ይበቃል፡፡ ይህንን ቫይረስ የሚያመላልሰው ሰው ነው፡፡ ሰውና ሰው ከተገናኘ ደግሞ ችግር ይፈጠራል፡፡ ችግሩ፣ አስተላላፊው ሰው የህመም ስሜት ላይኖረው ይችላል፡፡ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በዚህ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍ ያለ ከሆነ ከፍ እያለም ከሄደ፣ ለጊዜውም ቢሆን ከሰዎች ጋር የሚደረገውን ግንኙነት መቆጠብ ያስፈልጋል፣ በተለይም በቤቶች ወይም በአዳራሾች ውስጥ መሰባሰብ ካለ፡፡

መረዳት የሚገባን፣ የምናደርገው ሰርጂካል ማስከ፣ በቫይረሱ ከተያዘው የሚወጣውን ቫይረሰ ይገድበው እንደሆነ እንጂ፣ ላልተያዘ ሰው ሙሉ በሙሉ የመከላከል ችሎታው ርግጠኛ አይደለም፡፡ ለመጋለጥ ዋና ምክንያቶች ቫይረሱን ከሚተነፍሱ ሰዎች አጠገብ መገኘት፣ ከተገኙም ቆይታው ረዥም ጊዜ በሆነ ቁጥር አደጋው እየጨመረ እንደሚሄድ ነው፡፡

ማስክ አድርጉ ሲባል ብትክክል መሆን አለበት፡፡ አፍና አፍንጫ በደንብ ተሸፍኖ፣ ትንፋሽ በጎን የማየወጣበት ሁኔታ መሆን አለበት፡፡ አንዳንድ ሰው ማስክ ሲያደርግ፣ በጎን በኩል ጣት ማሾልክ የሚያስችል ክፍተት ይታያል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ፣ አፋቸውን ብቻ ዘግተው፣ አፍንጫቸውን አይሸፍኑም፡፡ ዋናው የቫይረሱ መዘጋጃ ቦታ አፍንጫ ነው፡፡

በጤና መስኩ፣ እንደምታውቁት፣ ሰርጂካል ማስክ ሳይሆን፣ N95 የተባለ ማስክ ነው የሚደረገው፡፡ እሱም ቢሆን በትክክል መሸፈን መቻሉን ለማረጋገጥ እያንዳንዱ ጤና ሙያተኛ Fit testing አድርጎ ነው፡፡ ማስኩ በተለያየ መጠን ሰለሚመጣ ባለሙያተኛው የሚስማማውን መጠን ካደረገ በኋላ፣ ማሰኩ ላይ የሚረጭ ነገር አለ፡፡ የተረጨበት ሰው ምንም ስሜት ካልተሰማው፣ ማስኩም አደራረጉም ትክክል ነው፡፡ አለበለዚያ የተረጨውን ነገር መቅመስ ከቻለ፣ ማስኩ ወይ በትክክል አልተደረገም ወይም ትክክለኛው መጠን አይደለም ማለት ነው፡፡ ከዚህ ላይ እንግዲህ ፌስ ሺልድ የሚባል መስታውት ነገር አይንን እንዲሸፍን ተደርጎ ነው የጤና ባለሙያተኞች የሚሠሩት፡፡ እንደዛም ሆኖ፣ በአሜሪካ ከ130ሺ በላይ የጤና ባለሙያተኞች በዚህ ቫይረስ መያዛቸው ይታወቃል፣ ከነዚህ መሀል ወደ 662 ነርሶች፣ ሀኪሞችና ሌሎች ህይወታቸው አልፏል፡፡ (የሲዲሲ መረጃን ይመልከቱ)

ይህን ቫይረስ መናቅም፣ መዳፈረም ጉዳት አለው፡፡ እያወቁ ቫይረሱን የሚያሻግሩ ሰዎች በሰማይ ሳይሆን በምድር የሚጠየቁበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም፡፡ በቫይረሱ ሥርጭት ምክንያት ኢኮኖሚው የተዘጋበት ህብረተሰብ ክፍል እነዚህን ሰዎች በክፉ ቢያያቸው የሚገርም አይሆንም፡፡ መንግስት፣ የንግዱና የሌላው ኢኮኖሚ፣ በትግስት የሚጠብቀው ነገር ቢኖር፣ የአካባቢው ሥርጭት ከ1 ቁጥር በታች እንዲሆን ነው፡፡ ማለትም አንድ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ከአንድ ሰው በላይ አለማስተላለፍ ማለት ነው፡፡ የዋሸንግተን፣ ዲሲ ከተማ፣ ይህ ቁጥር ከ1 በታች ሰላልሆነ፣ ከphase 2  ወደ phase 3 መውረድ አልቻለም፡፡ ሥርጭቱ በቀጠለ ቁጥር፣ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሌሎችም፣ ሰዎች እንዲሰባበሰቡ የሚያደርጉ ጥሪ የሚያቀርቡ ሰዎች ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡ የጠራናቸው ሰዎች ባህሪ ነው ብሎ ዝም ማለትም አይቻልም፡፡ እያመመው የሚመጣ ሰው መኖሩ ከታወቀ፣ ወይ አለመጥራት ወይ ደግሞ ይህ ሰው እንዳይመጣ አስፈለጊውን ጥንቃቄና ዝግጅት ማድረግ ነው፡፡ በማህበረሰባችን ውስጥ ቫይረሱ ከሚገባው ቁጥር በላይ መኖሩን መገመት አያዳግትም፡፡ በደንብ ከማውቀው፣ በዲሲ፣ የቫይረሱ ሥርጭት መጠን ከሌሎች የዲሲ ክፍሎች በላይ በአፍሪካን አሜሪካውን ላይ ከፍ ያለ ነው፡፡ ከዲሲ አማካይ በላይም ነው፡፡ በዚህ ቫይረስ ሥርጭት መቀጠል ማን እየተጎዳ መሆኑን መግለፅም አያስፈልግም፡፡


መልካም ንባብ፣ አካፍሉ

የ1918 ስፓኒሽ ፍሉ በኢትዮጵያ ደግሞ የህዳር በሽታ ተብሎ

የሚጠራው ወረርሽኝን አስገራሚ ታሪክ ያዳምጡ

የሳረስ ኮሮና ቫይረስ ቁጥር 2 (ሳኮ2) ወይም ኮቪድ-19 ሥርጭት ከሚታወቀው በላይ በአስር ዕጥፍ ይበልጣል፡ 07/23/2020
 
በየጊዜው አዳዲስ ግኝቶችን በማሳየት እንደዚህ አይነት በሽታ ታይቶም አይታወቅም፡፡ ከጥያቂዎች አንዱና ዋናው፣ በህብረተሰቡ ውስጥ በሽታው ምን ያህል ተሠራጭቷል የሚለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ የበሽታ ምልክት የሌለባቸው ሰዎች ቫይረሱን በስፋት እያሠራጩት እንደሆነ ከታወቀ ስነብቷል፡፡ 

Copyright 2013. Gosh Health. 

All Rights Reserved.