ለስላሳ መጠጥ አዘውትሮ መጠጣት ከሕይወት እልፈት ጋር ይያዛል ወይ?
 
ከዚህ ቀደም በጎሽ ድረ ገፅ፣ ቬፒንግ ሰለሚባለው ኤሌትሪክ ሲጋረ አደገኘነት ቀድም ብለን ለማሰጠንቀቅ ሞክረን ነበር፡፡ አሁን ግን ጉዳቱ በአደባባይ ስለወጣ፣ ብዙ የታመሙ ሰዎች መኖራቸውና እሰከ አሁን ድረስ በዚህ ምክንያት የስድስት ሰዎቸ ህይወት ማለፉ ግልፅ ስለሆነ፣ የአሜሪካ መንግሥት ርምጃ መውሰድ እንዳለበት ተነግሯል፡፡ የኒው ዮርክ መንግሥት ግን በዚህ የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ውስጥ የሚጨመሩ አጣፋጭ ነገሮች እንዲወገዱ በህግ ሊያፀና ነው፡፡
       በዚህ ርዕስ ደግሞ ሌላው ለጤንነትና ለሕይወት አስጊ የሆነውን ነገር በጥናት አስደግፈን ለአንባብያን አቅርበናል፡፡ መንግስት ርምጃ እስኪወስድ መጠበቅ አስፈላጊም አይሆንም፤ ጉዳቱን ተገንዝቦ የራስንና የቤተ ዘመድን ጤንነትና ሕይወት መጠበቅ ይጠቅማል፡፡
      ከላይ የተነሳው ጥያቄ አድገዋል በሚባሉ አገሮች በህዝብ ውስጥ በጉልህ ባይገለፅም የጉርምርምታ መንስኤ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
      ወደ ጥያቄው ስንመለስ፣ ለስለሳ መጠጥ አዘውትሮ መጠጣት ለአጠቃላይ ሕይወት ማለፍ ሰበብ ነው ወይ? ወይስ ደግሞ በራሱ የተወሰኑ ቸግሮች በማስከተል ለሕይወት ማለፍ ምክንያት ነው ወይ? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ፣ አጥኝዎቹ በአስር የአውሮፓ አገሮች፣ ከህዝብ በሚሰበሰብ መረጃ፣ የ451 743 ሰዎች ያሉበት ክትትል የሚደረግበት የጥናት ቡድን ነው የተመለከቱት፡፡ በዚህ የሰዎች ክትትል የታየውን ውጤት ነው ያካፈሉት፡፡ የውጤቱ ጭብጥ የሚለው፣ በስኳር የጣፈጡ ለስላሳ መጠጦችንና በአርቴፊሻል ማጣፈጫዎች የተሠሩ ለስላሳ መጠጦችን ማዘውተር፣ በማንኛውም ምክንያት ለህይወት ማለፍ አደጋ ከሚያሰከትሉ ሰበቦች ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው፡፡ ሁለቱ አይነቶች የለስላሳ መጠጦች በየግላቸው ሲታዩ፣ በአርቴፊሻል ማጣፈጫ የተሰሩ የለስላሳ መጠጦች በልብና በደም ሥር ምክንያት ከሚከሰተው የሕይወት ማለፍ ጋር የተያያዙ ሲሆን፤ በሰኳር ማጣፈጫነት የተሠሩት መጠጦች ደግሞ በጨጓራና በአንጀት ምክንያት ከሚከሰተው የሕይወት እልፈት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ጥናቱ ያስታውቃል፡፡
     እንደውነቱ ከሆነ የዚህ ጥናት ውጤት፣ ለአጠቃላይ ህዝብ ጤንነት ለሚጨነቁ ሰዎችና ባለሙያተኞች እንግዳ አይደለም፡፡ እንዲያውም የነዚህን የለስላሳ መጠጦች አጠቃቀም ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ድጋፍ የሚሰጥ ግኝት ነው፡፡  
      ስለጥናቱ ትንሽ ላካፍላችሁ፡፡ የዚህ ጥናት ውጤት የቀረበው JAMA በሚባለው ታዋቂ የህክምና መፅሄት ስለሆነ፣ ሰለ መረጃው ተቀባይነት ጥያቄ የሚነሳ አይመስለኝም፡፡ የዚህ መፅሄት አዘጋጆች፣ እንደዚህ ለህትመት የሚላክላቸውን ጥናት ለማተም ፈቃድ ከመሥጠታቸው በፊት እንዴት እንደሚመረምሩ፣ ብቃቱን ወይም ሳይንሳዊነቱን እንዴት እንደሚፈትሹ ራሴ ምስክር መሆን እችላለሁ፡፡ 
      የዚህ ጥናት ውጤት የመጣው፣ ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በህዝብ ደረጃ ክትትል ወይም በጥናት ከሚሳተፉ ቁጥራቸው 451 743 ሰዎች ነው፡፡ የዚህ የህዝብ ጥናት ቡድን በምህፃረ ቃል፣ EPIC (European Prospective Investigation into Caner and Nutrition) ይባላል፡፡ በነገራችን ላይ በአደጉ አገሮች፣ እንደዚህ ህዝብ ተሳታፊ የሆነባቸው ለተለያዩ የጤና ችግሮች ክትትል የሚደረግባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ ጥናቱ፣ በፈቃደኝነት የተመሠረተ ሲሆን፣ በአብዛኛው፣ መረጃ በመሰብሰብ የተወሰነ ነው፡፡ ምርምር አይደለም፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ቡድን በአስር አውሮፓ አገሮች የተዘረጋ ጥናት ሲሆን፣ እነሱም፤
 (ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ግሪክ፣ ኢጣልያ፣ ኔዘር ላንድሰ፣ ኖርዌይ፣ ሰፔይን፣ ስዊድንና ዩናይትድ ኪንግደም ናቸው)፡፡ ጥናቱ ሲጀመር፣ የካንሰር፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመም፣ ሰትሮክ አለብን ብለው ሪፖርት ያደረጉ ሰዎች ከጥነቱ እንዲገለሉ ተደረገ፡፡ በተጨማሪም የለሰላሳ መጠጥ አጠጣቸወን በደንብ መግለፅ ያልቻሉ ወይም ሪፖርት ማድረግ ያልቻሉ ሰዎች እንዲሁ ከጥናቱ ተገለሉ፡፡ ሰለዚህ ክትትል ላይ የቀሩት ሰዎች ቁጥር 521 330 ነው፡፡ 
     ትንሽም ወደ ጥናቱ ጠለቅ ብለን ስናይ፣ የጥናቱ ተሳታፊዎች ገፅታ ይህን ይመስላል፤
     አማካይ ዕድሜ 50.8 አመት፣ 71.1 ፐርሰንት ሴቶች፣ አማካይ የክትትል ጊዜ 16.4 አመታት ነው፡፡ የጥናቱ ዘመን፣ ከ ጥር 1፣ 1992 (የአውሮፓ አቆጣጠር) እሰከ ታህሳስ 31፣ 2018 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡
      በነዚህ ለጥናቱ ተሳታፊ ከሆኑ ሰዎች መሀከል 41 693 ሰዎች ሞተዋል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎችን አመጋገብና አጠጣጥ በዝርዝር በመመልከት ነው ከለስላሳ መጠጦች ጋር ግንኙነት እንዳለው የተመሠረተው፡፡ የጥናቱን ውጤት ስንመለከት፣ በቀን ከሁለት ብርጭቆ በላይ የለስላሳ መጠጥ የሚያዘውትሩ ሰዎች በወር ከአንድ ብርጭቆ በታች ከሚጠጡ ሰዎች በበለጠ በቁጥር ወይም በስታትሰቲክ ሲደግፍ ግንኙነት አለው ተብሎ መረጃ የሚጠቀስበት ደረጃ፣ ከሞቱት መሀል ለስላሳ መጠጡን ያዘወተሩ ሰዎች ቁጥር ከፍ ያለ ነው፡፡ 
    በርግጥ ዝርዝሩን ለአንባቢ ማቅረብ አሰልቺም ሰለሚሆን፣ የዚህን ጥናት ማጠቃለያውን ስንመለከት፤ በአርቲፊሻል ማጣፈጫም ይሁን በስኳር ማጣፈጫነት የተሠሩ ለስላሳ መጠጦችን ማዘውተር፣ ለህይወት እልፈት ምክንያት ከሚሆኑ ከሁሉም ነገሮች ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው፡፡ መጠጦችን የሚያዘውተሩ ሰዎች በምንም ምክንያት ህይወታቸው ቢያልፍም ለስላሳ መጠጦቹን ማዘውተራቸው አባባሽ ሆኖ መገኘቱን ነው፡፡ጆሮ ያለው ይስማ፡፡ አካፍሉ፡፡ 
ምንጭ

September 3, 2019 

doi:10.1001/jamainternmed.2019.2478

                           ከድጡ ወደ ማጡ
               Vaping (E – Cigarette) ና መዘዙ


ሲጋራና ሲጋራ ማጨስ ያሰከተለውና የሚያስከትለው ጉዳት ግልፅ በሆነበት ዘመን፣ ብልጣ ብልጥ አትራፊዎች ሌላ የሚጨስ ነገር ይዘው ብቅ ካሉ ሰንብተዋል፡፡ እሱም በእንግሊዘኛ  አጠራር ቬፒንግ (Vaping) የሚባለው ኤሌክትሮኒክ ሲጋሬት(E- cigarette)  ተብሎ የሚጠራው አጠቃቀም ነው፡፡ ይህ እንግዲህ በውስጡ ኒኮቲን የለውም ተብሎ፣ በአፋቸው ጭስ እንደ ማማ እንትና ምድጃ ቡልል እያለ ሲወጣ ነፍሳቸውን የሚያስደስታቸው ሰዎች ሰላሉ ነው የተፈበረከው፡፡ መኪና እየነዳችችሁ ስትሄዱ ሆነም ቀይ መብራት ላይ ስታቆሙ፣ ከጎረቤት መኪና መስኮት በኩል ጭስ መውጫ ወደ ውስጥ ገባ ወይ በሚያስብል ሁኔታ ጭስ ቡልቅ ሲል ይታያል፡፡ ካስተዋላችሁ ይህ ኤሌክትሮኒክ ሲጋሬት የሚባለውን ነገር ሲጠቀሙ ታገኛላችሁ፡፡ እንደ ጭስ የሚወጣው ነገር በተለያዩ ጣዕሞች ተቀምሞ ለአጫሾቹ ይሸጣል፡፡
     እንግዲህ እንደ ፋሽንም ሆኖ ወጣቶቹ በብዛት እየተረባረቡበት ነው፡፡ በአሜሪካ 10.8 ሚሊዮን ሰዎች ይህን ነገር ተጠቃሚ መሆናቸው በቅርቡ ተገልጧል፡፡ የኛም ወገኖች ከመልመዳቸው በፊት ሰሞኑን በጥናት የወጣውን አስደንጋጭ ነግር ላካፍላችሁ፡፡
     በቀረበው ጥናት መሠረት፣ ይህንን የኤሌክትሪክ ሲጋሬት ከሚጠቀሙ ሰዎች ምራቅ ይሰበሰብና ምርምር በሚደረግበት ጊዜ፣ በዚሁ ጭስ ምክንያት የሰውነት የዘር ሰንሰለት (DNA) የሚጎዱ ኬሚካሎች አንደሚፈጥር ይደረስበታል፡ እንግዲህ ከተጎዳ DNA ሰውነት ላይ ካንሰር የመብቀል ወይም የመፈጠሩ ሁኔታ ይጨምራል፡፡ ታዲያ ሲጋራ ማጨስስ በምን ተጠላ?
     ለጥናቱ ምራቃቸው የተሰበሰበው ሰዎች ለአስራ አምስት ደቂቃዎች ብቻ ካጨሱ በኋላ ነው ናሙናው የተወሰደው፡፡ እናም ይህ የሚጨሰው ነገር ከዚህ ቀደም ሰውነት ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ የሚታወቁ ኬሚካሎች ከመጠን በላይ በምራቃቸው እንደተገኘ ነው የሚያሰገነዝበው፡፡ ይህም ከማያጨሱ ሰዎች ምራቅ ጋራ ተወዳድሮ ነው፡፡
የሚከተሉት ኬሚካሎች መጠን ጨምሮ ነው የተገኘው፡፡ formaldehyde, acrolein, and methylglyoxal. በተለይም acrolein የተባለው ኬሚካል ከ30 እሰክ 60 ዕጥፍ በሆነ መንገድ መጠኑ ጨምሮ ነው የተገኘው፡፡ ይህ ኬሚካል ደግሞ የካንሰር ጠንቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው የሰውነት ሴሎች ላይ ጉዳት የሚያሰከትለው፡፡
     ይህ ጥናት በኦገስት 21 በቦሰትን ከተማ በተደረገው National Meeting & Exposition of the American Chemical Society ስብሰባ ላይ ነው የቀረበው፡፡
ባጠቃላይ እነዚህ ኢ - ሲጋሬት(E- cigarette) በሰውነት ላይ ሊያደርሱ የሚችሉት ጉዳትና የሚፈጠረው የጤንነት መቃወስ በአሁኑ ሰኣት ግልፅ ባይሆንም ጥብቅ ክትትል ወይም ጥናት እንደሚያስፈልግ ነው የጥናቱ አቅራቢዎች የገለጡት፡፡
ሆ ሆ፣ በኋላ ከማዘን…… ይላሉ ያገራችን ሰዎች፡፡ የሰውነት ሴሎችን የሚጎዳ የካንሠር ጠንቅ የሆኑ ኬሚካሎች መኖራቸው ከታወቀ የግድ ካንሰር እስኪመጣ መጠበቅ አለበት ወይ?
ላልሰማ አካፍሉ፡፡  የጫቱ ይበቃናል

ትርፍ ሲባል እንዴት መርዝ ይጨሳል? ሳያናይድ ተገኘበት! 10/06/2019

የኤሌክትሪክ ሲጋራና መዘዙን በህግ እሰኪለከል ድረስ እኔም ከመምከር አልቆጠብም፡፡ የምትከታተሉ ሰዎች ካላችሁ፣ ህዝቡም እየነቃ፣ መንግሥትም ጠበቅ ያለ ርምጃ እየወሰደ ነው፡፡ ለመሆኑ፣ የዚህ ቬፒንግ ወይም ኢ-ሲጋራ (e-Cigarettes) የሚባለው ጣዕም የሚሠጡ ተጨማሪ ነገሮች እንዴት ሊፈቀዱ ቻሉ?

እንደ ሎስ አንጀለስ ታይምስ ጋዜጣ ዘገባ፣ በ2015 FDA, የአሜሪካው የምግብና የመድሐኒት አስተዳደር (e-Cigarettes) የሚጨመሩ ማጣፈጫዎችን ለመከልከል ያደረገው የመጀመሪያው ጥረት በባለሀብቶቹ ታፍኖ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ በዚያው አመት፣ ከመቶ በላይ የሚሆኑ የትምባሆ ኩባንያ ወኪሎች እና አንዳንድ አነስተኛ ቢዝነስ የሚባሉ ቡድኖች፣ Office of Management and Budget ከሚባለው ድርጅት ባለሥልጣኖች ጋር ስብሰባ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ድርጅት፣ ከፍተኛ የሆኑ ህጎች ሲደነገጉ በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትሉትን ግፊት ወይም ውጤት የሚመረምር ነው፡፡ በዚህ ስብሰባ ከተሳተፉት፣ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ጠበቆች፣ ለኢ-ሲጋራ ማጣፈጫ የሚያመርቱ ኩባንያ ጠበቆች፣ እናም የምግብና የመድሐኒት አስተዳደሩ FDA በማጣፈዎች ላይ ያደረገውን ጥናት (research) ውድቅ ለማድረግ የሚጥሩ፣ ገንዘብ የሚከፈላቸው ምሁራኖችንም ይጨምራል፡፡ በግንቦት 2016 FDA፣ ትምባሆን በተመለከተ፣ ህግ ሲያወጣ፣ ማጣፈጫዎቹን የሚከለክለውን መመሪያ ትቶ ነበር፡፡ በጊዜው የነበሩት FDA ባለሥልጣኖች፣ ማጣፈጫዎች ቢከለከሉ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሰከትለውን ግፊት ለማጥናት ከፍተኛ ትግል እንዳደረጉ ገለፁ፡፡ ያም በፕሬዚደንት ኦባማ ጊዜ ነበር፡፡ እንደነሱ አባባል፣ የሳይንስ ምርምር ለሚያደርጉ ድርጅቶች ክብር ቢኖራቸውም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የተነሳው ጥያቄ፣ የጥናቱ ውጤት ግልፅ ስላልሆነ (በነሱ አባባል ነው፣ የኢ-ሲጋራ በተያያዘ ያሉ ንግድ ቤቶችን ጠቅላላ መዝጋት ተገቢ ነው ወይ? ብለው ነበር፡፡ ሰለዚህ ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በኢንዱስትሪ ጠበቆች ተፅዕመፐ አማካኝነት፣ ያሰቡትን ማድረግ ሰላልቻሉ፣ የወሰዱት አማራጭ ሁኔታው በዝግታ እንዲታይ ነው፡፡

መንግሥት ተቀየረና፣ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት ፕሪዚዳንት ሲተኩ፣ በ ኢ-ሲጋራዎች ማጣፈጫዎች ላይ ሊወሰድ የነበረው ጠበቅ ያለ ህግ አስከ 2021 ድረስ አይሰራም ወይም አይጀመርም ብለው አስታወቁ፡፡ ሰውየው፣ እንደዚህ አይነቶችን ህግጋት ሲሽሩ ወይም ሲያዘገዩ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ እንግዲህ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ማንበብ፣ ህጉ ተፈፃሚ ቢሆን፣ ማጠፈጨዎቹ ቢከለከሉ ኖሮ የሚያስብል ድምዳሜ ያደርሳል፡፡ አትራፊዎች፣ በመንግሥት ህግጋት ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ እንደሚፈጥሩ አንድ ምሳሌ ይሆናል፡፡

ሰሞኑን በመገናኛ ብዙሃን እንደሚጠቀሰው፣ ይህንን ኢ-ሰጃራ የሚጠቀሙ ሰዎች በከፍተኛ ቁጥር እየታመሙ፣ ህይወታቸውም እያለፈ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በጎሽ ድረ ገፅ፣ ስለዚህ ጉዳይ ቀደም ብለን ለማስጠንቀቅ ሞክረናል፡፡ ይህ ፅሁፍ አስከወጣበት እስካለፈው ሳምንት ድረስ፣ ይህን ቬፒንግ ከሚጠቀሙ ሰዎች፣ 805 ታመው ሆስፒታል የገቡ ሲሆን፣ 16 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ቁጥሩ እየጨመረ የሚሄድ ነው የሚመስለው፡፡

የህመምና የሞት ምክንያቱን ለማጣራት፣ ትልቁ የዜና አውታር ኤን ቢ ሲ፣ በራሱ ለቦራቶሮች ጥናት ያካሂዳል፡፡ አይ አገር! (የዜና አውታር ራሱ ጥናት የሚያደርግበት፤ ምክንያቱም ኢንዱስትሪው አትራፊ ስለሆነም አይታመንም)፡፡ የኛ አገር ጋዜጠኛ ተብየዎች፣ ጥናቱ ቀርቶ በመረጃ የተደገፈ፣ ግራ ቀኙን ያዳመጠ ዜና ቢያስተላልፉ፣ ምሬትና ጥላቻው በቀነሰ ነበር፡፡ አክቲቪስትና ጋዜጠኛ ሲደባለቅ ነው ነገር የተበላሸው፡፡ ማሞ ሌላ መታወቂያ ሌላ ይባል የለ፡፡ ይህ የኔ አስተያየት ነው፡፡ ልተንፍስ ብዬ ነው፡፡

ወደ ጥናቱ ልመልሳችሁ፡፡ በዚህ ጥናት፣ በጎዳና ላይ የሚሸጡ ማጣፈጨዎችን ናሙና ሰበሰቡ፡፡ እናም ከጎዳና ላይ ከሚሸጡት የተሰበሰቡት ናሙናዎች በሙሉ፣ ሲመረመሩ፣ ያም ለተባይ ማጥፊያ የሚውሉ ኬሚካሎች በውስጣቸው ይኖር ይሆን ተብሎ ነው፡፡ ታዲያ ሁሉም ከጎዳና የተሰበሰቡት ናሙናዎች፣ በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ለፈንገስ ማጥፊያ የሚውል ኬሚካል ስሙም ማይክሎቡታኒል የተባለ ኮምፓውንድ ይገኝባቸዋል፡፡ አሁን ልብ በሉ፣ ይህ ኮምፓውንድ በእሳት ሲለኮስ ወደ ሀይድሮጀን ሳያናይድ ወደ ተባለ ኬሚካል ይቀየራል፡፡ ሳያናይድ፣ የምታውቁ ከሆነ፣ በትንሹ እንኳን ሰዎች ከተጋለጡ ለሕይወት እልፈት የሚዳርግ፣ ምን አግደረደረኝ፣ ሰው የሚገድል ኮምፓውንድ ነው፡፡ የዛሬ ስንት አመታት፣ በኢትዮጵያ፣ ወጣቶች ላመኑበት ትግል ሲታገሉ፣ ከተያዙ ሚስጥር እንዳያወጡ ሳያናይድ እየዋጡ ራሳቸውን ያጠፉ ነበር፡፡ ይባላል፡፡ የደርግ መርማሪዎችም ይህንን ያውቁ ኖሮ፣ ያሠሩት ሰው እልም ስልም ሲልባቸው፣ ሎሚ ይግቱ ነበር፡፡ መርዝ ውጦ ይሆናል ብለው ነው፡፡ ይሄኛውን በደንብ አውቃለሁ፡፡

በሌላ ጥናት፣ ሌላ ድርጅት፣ መንገድ ዳር በህግ ወጥ (ብላክ ማርኬት) የሚሸጡና ከፋብሪካ የሚወጡ ሀሽሽ (ማሪዋና) ያለባቸውን ማጣፈጫዎች በመመርመር ያገኙት፣ በብላክ ማርኬት ከሚሸጡት፣ ከአስራ አምስት ናሙናዎቸ በአስራ ሶስቱ ቫይታሚን ኢ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በጭስ መልክ ሲገባ፣ ይህ ቫይታሚን ኢ ለህመም ይዳርጋሉ ከሚባሉት ኮምፓውንዶች አንዱ ነው፡፡ በሚዋጥ መልክ ለአንዳንድ በሽታዎች የሚታዘዝ ነው፡፡ እኔም የማዝበት ሁኔታ አለ፡፡ ግን በጭስ አይደለም፡፡ ከነዚህ ናሙናዎች በአስሩ ደግሞ፣ ያ ከላይ የተጠቀሰው ማይክሎቡታኒል ተገኝቶባቸዋል፡፡ ልብ ካላችሁ ይህ ኮምፓውንድ ሲቃጠል ወደ ሳያናይድ ይቀየራል፡፡ እኔም ካገር በፊት፣ ይህ ቬፒንግ የሚባል አደገኛ ነው፤ ልጆቻችሁ እንደፋሽን አድርገው እንዳይጀምሩት ብዬ ለማስጠንቀቅ ሞክሬ ነበር፡፡ አሁን ግን ይኸው መረጃው፡፡ ሰው እንዴት መርዝ ያጨሳል? እንደ ኤንቢሲ ዜና ባላሥልጣኖች አባባል፣ አጣፈጩ ቅመም ላዩ ላይ፣ ሳያናይድ አለበት የሚል ማስታወቂያ ቢለጥፍበት ኖሮ የሚገዛ አይኖርም ነበር ይላሉ፡፡ ውነት ነው፡፡ ይህም ሆኖ፣ ከላይ በተጠቀሱት ህሙማንና ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች፣ ጉዳት የደረሰባቸው በዚህ ኮምፓውንድ ነው ተብሎ ተነጥሎ የቀረበ ኬሚካል እሰካሁን አልተገኘም፡፡ ሰለዚህ ነገሩን የበለጠ አደገኛ ያደርገዋል፡፡ በሉ፣ ደንገጣችሁም፣ አሰባችሁም፣ መልሳችሁ አስተምሩ፡፡ አካፍሉ፣ ፌስ ቡክ ላይ ያለውን ገፅም ላይክ አድርጉ፡፡ ለፀሐፊ ሞራል ይሠጣል፡፡​

አዲሱ አጫጫስ ሰዎችን ወዲያውኑ ማጨስ ጀምሯል


ባለፈው፣ በጎሽ ድረ ገፅ፣ vaping (e-cigarette) ተብሎ ስሚጠራው አዲሰ ጭስ የማጨስ ተግባር ትምህርት ለመሥጠት ሞክረናል፡፡ ይህ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ የሆነ ህመም በአጫሾቹ ላይ ማሳየት ሰለጀመረ፣ የየሰቴት የጤና ቢሮዎች ለጤና ባላሙያተኞች ማሳሰቢያና መምሪያ እንዲልኩ አስግድዷቸዋል፡፡
     ሁኔታው እንዲህ ነው፡፡ ከነሀሴ 21 ጀምሮ አንድ መቶ በሚሆኑ ሰዎች በጣም ከባድ የሆነ የሳምባ በሽታ ተይዘው ወደ ሆስፒታሎች ለህክምና የዘለቁ ሲሆን፣ አንዳንዶቹም ከበሽታው ጥንካሬ ብዛት የአርቴፊሻል መተንፈሻ ማሽን ላይ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ማለት በራሳቸው መተንፈስ ሰላልቻሉ ነው፡፡ ሁሉም በሽተኞች ሲጠየቁ፣ በዚህ ቬፒንግ ውስጥ ኒኮቲን ወይም ማሪዋና (ሀሽሽ) ያለበት ጭስ መጠቀማቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህ እንደ ፋሽን ሆኖ  ኤሌክትሪክ ሲጋራ(e-cigarette) ተብሎ በሚጠራው አጫጫስ ሁኔታ ብዙ አሳሳቢ ሁኔታዎች መከሰታቸው የታወቀ ቢሆንም፣ አሁን በነዚህ መቶ ሰዎች ላይ የታየው ግን በጣም አደገኛ ነው፡፡ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ይህ የአጫጫስ ዘዴ ለወጣቶች በማስታወቂያ መልክ በመቅረቡ፣ መንግሥትና ተቆርቋሪዎች ተቃውሞና ክትትል እያደረጉ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ፣ እነዚህ የታመሙ ሰዎች የታመሙት በማጨሻው ቁሳቁስ ምክንያት ይሆን፣ ወይም የሚጨሰው ነገር ባልተጠበቀ ሁኔታ ለጤና አስጊ በሆኑ ኬሚካሎቹ የተናካካ ይሁን አልታወቀም፡፡ ለማንኛውም፣ ይህ አዲስ ነገር ለጤና አስጊ መሆኑ ስለሚታወቅ፣ ወላጅና ቤተዘመድ የሚያውቋቸው ልጆችና ዘመዶቻቸው ይህን ልምድ እንዳያነሱ አስቀድሞ መምከርና መከላከል አስፈላጊ ነው፡፡
     በዚህ አጫጫስ ለህክምና የቀረቡ ሰዎች የተሰማቸው ስሜትና የሚያሳዩዋቸው ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
     ራስ ምታት፣ የደረት ህመም፣ የምግብ ፍላጎት መዘጋት፣ ድካም፣ የትንፋሽ ማጠር፣ ትኩሳት፣ ሳል፣ ማቅለሽለሽ፣ የሰውነት ክብደት መቀነስን ይጨምራሉ፡፡
     እንግዲህ ከዚህ ውጭ በዘላቂነት የሚያሰከትላቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ያም ከጊዜ በኋላ የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ ይህ አሳሳቢ የጤና ጠንቅ ስለሆነ ላልሰማ አካፍሉ፡፡ ለውይይት መነሻ እንዲሆን በማለት አጠር ያለ አቀራረብ መርጠናል፡፡

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History