​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

ሲስተር መዓዛ እንዴት በኤች አይ ቪ ልትያዝ ቻለች? 
 04/15/2019


    መቼም ቢሆን ድራማ ሲሰራ ከጀርባው ትምህርት ይሠጣል ብሎ ማሰቡ የቀረ ይመስላል፡፡ የሚያጓጓ፣ የሚያሳዝን ወይም የሚያስደነግጥ ትዕይንት መፍጠር የተመልካች ቁጥር ይጨምራል በሚል ምክንያት ይሆናል፣ ትዕይንቱ ትክክለኛ መልክቱን እንደማይሠጥ ሆኖ የሚሠራው፡፡ የኔ ግምት ነው፡፡
    የሞጋቾቹ ሲ/ር መዓዛ ከበሽተኛ ደም ስትቀዳ፣ መርፌው እሷኑ ስለወጋት ለኤች አይ ቪ ተጋለጠች፡፡ እናም እንደ አሠራሩ መድሐኒት መውሰድ ነበረባት፡፡ ለምን ቢባል፣ ለኤች አይ ቪ ከተጋለጠች በኋላ በሁለት ሰአታት ውሥጥ መድሐኒት ከጀመረች በቫይረሱ እንዳትያዝ ይረደታል፡፡ ወደ ሲ/ር መዓዛ ከመመለሳችን በፊት ሰለዚህ ሁኔታ ትንሽ እንማር፡፡
    የጤና ባለሙያተኞች በሥራቸው ላይ እንደዚህ ስለት ባለው የሌላ ሰው (በሽተኛ) ደም ወይም ፈሳሽ በነካ ነገር ሲወጉ፣ ለኤች አይ ቪ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ይጋለጣሉ፡፡ ለዚህ ርዕስ ኤች አይ ቪ ላይ እናተኩር፡፡ በዚህ ጊዜ በፍጥነት በተለይም በሁለት ሰአታታ ውስጥ መድሀኒት እንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡ ነገሩ፣ ባለሙያተኞቹ በቫይረሱ እንዳይያዙ ለማድረግ ነው፡፡ ይህ ነገር በእንግሊዝኛ Post Exposure Prophylaxis (PEP) ተብሎ ይጠራል፡፡ የቀዶ ህክምና ሐኪሞችን ጨምሮ ብዛት ያላቸው ሙያተኞች ለዚህ ነገር ይጋለጣሉ፡፡ አብዛኘው አደጋ የሚደርሰው፣ በሽተኛ ላይ የተጠቀሙበትን መርፌ ለመዝጋት ሲዘጋጁ ነው፡፡ በአሜሪካና በሌሎቹም፣ መርፌዎች ሠራተኞች ላይ አደጋ እንዳያደርሱ ወዲያውኑ ወደ ፕላሰቲክ ማሸጊያ አውቶማቲካሊ እንዲገቡ ሆነው እየተሠሩ አገልግሎት ላይ እየዋሉ ነው፡፡
ይህ አይነት አደጋ ሲደርስ የሚከተሉት ነገሮች መታወቅ አለባቸው
    በሽተኛው በኤች አይ ቪ መያዙ መታወቅ አለበት፣ መድሐኒት ላይ መሆንና አለመሆኑም ይረዳል
የተጋለጠው ባለሙያ ራሱ ወይም ራሷ በኤች አይ ቪ መያዝና አለመያዙ መታወቅ አለበት፣ ሰለዚህ ምርመራ ያደርጋሉ ማለት ነው፡፡
    ከዚያ በፊት ግን በምን አይነት ስለት እንደተወጉ፣ ከዚያ ውጭ ደግሞ በምን አይነት የበሽተኛ ፈሳሽ እንደተጋለጡ፤ ከተጋለጡም የትኛው የሰውነት ክፍላቸው እንደሆነ በደንብ ይጣራል፡፡
   አደጋው ለቫይረሱ የሚያጋልጣቸው ከሆነ፣ በሁለት ሰአታት ውስጥ የኤች አይ ቪ መድሀኒት ይጀምራሉ፡፡ ነገር ግን አስከ ሶስት ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥም መድሐኒት መጀመር ይችላሉ፡፡ ሶስት አይነት ፀረ ኤች አይ ቪ መድሐኒቶች ያለበት መሆን አለበት፡፡ የሚወስዱትም ላንድ ወር ብቻ ነው፡፡ የመድሐኒት አይነት አመራረጥ የራሱ አቀራረብ አለው፡፡ ዝርዝሩ አስፈላጊ አይሆንም
    መድሐኒት ቢጀምሩም፣ ራሳቸው ከኤች አይ ቪ ነፃ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ምርመራ ያደርጋሉ፡፡ ውጤቱ ከቫይረሱ ነፃ ናቸው የሚል ከሆነ፣ መድሐኒቱን ለአንድ ወር ይወሰዳሉ፡፡ ምርመራው ኤች አይ ቪ አለ የሚል ከሆነ ግን፣ በቫይረሱ የተያዙት ቀደም ብሎ እንደሆነ ሰለሚገልፅ ወደ ህክምና ወይም ክትትል ይላካሉ፡፡ ያ እንግዲህ በተወጉት መርፌ ምክንያት አይደለም ማለት ነው፡፡
   መድሐኒቱን ለአንድ ወር ወስደው እንደገና የደም ምርመራ ይደረጋል፡፡ ከዚያም በየሶሰት ወራቱ ክትትል ይደረግና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነፃ መሆናቸው ይረጋገጣል፡፡ ለቫይረሱ ደም ምርመራ የሚያደርጉት፣ በስድስት ሳምነት፣ በ12 ሳምነትና በስድስት ወር ነው፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን በምንም መንገድ ሌሎቹን ለቫይረስ ከሚያጋልጡ ነገሮች ይቆጠባሉ ያም በመጀመሪያዎቹ ከስድስት እሰከ 12 ሳምነታት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ሰለዚህ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ክልክል ነው፡፡ ጡት ማጥባት ወይም ማርገዝ፣ ደም ለሌላ ሰው መስጠትም ክልክል ነው፡፡
    በዚህ ሁኔታ ተጋልጠው መድሐኒት በሰአቱ የወሰዱ ሰዎች መሀል ምን ያህሉ በቫይረሱ ይያዛሉ የሚለውን ለመረዳት መረጃዎች እንመልከት፡፡
    በመርፌ ወይም በስለት ከተወጉ መድሐኒት ባይወስዱ እንኳን በቫይረሱ የመያዝ ዕድሉ 0.3% ነው
በስለት ሳይወጉ የሰውነት ክፍል ላይ ቢጋለጡ ደግሞ በቫይረስ የመያዝ ዕድሉ 0.09% ነው፡፡
መድሐኒት ጀምረው በትክክል ከወሰዱ፣ መድሐኒቱ በኤች አይ ቪ እንዳይያዙ ያደርጋል፡፡
    ታዲያ ወደ ሲ/ር መዓዛ ስንመለስ፣ መድሐኒት ወስዳ በቫይረሱ እንድትያዝ አድርገው መፃፋቸው ወይም መተወናቸው አግባብነት ባይኖረውም፣ መያዝ ካለባት ግን፣ በንግግር ወይም በሆነ ቦታ ላይ እውነታውን ቢያስተምሩ ጥሩ ይሆን ነበር፡፡