ሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

ተአምር! የጋምቤላ ትውስታ

የሞርጋን ፍሪማን “Finding God” የሚባል ፐሮግራም በናሽናል ጂኦግራፊክ ፕሮግራም እያየሁ እያለ፤ በጨረፍታ ከ9/11 ተረፍኩ የሚል ሰው አየሁኝ፡፡ በአውሮፕላኑ ከጋዩት ህንፃዎች አንደኛው ላይ የነበረ ሰው ነው፡፡ መደምደሚያው እግዚአብሔር አለ ነው፡፡ ድንገት ጋምቤላ ያጋጠመኝ አንድ ሁኔታ ብልጭ አለብኝ፡፡ ልፃፋው አልፃው እያልኩ አመናታሁና ግን ይኸው፡፡


ከህክምና እንደተመረቅሁ ጋምቤላ ተመድቤ ስሰራ በድንገት የስራ ጓደኞቼ በሰበብ አስባቡ ወደ አዲስ አበባ ሄዱና 100 አልጋ ላለው ሆስፒታል ብቸኛ ሀኪም ሆንኩኝ፡፡ ይህ ሁኔታ መቱ(ኤሊባቡር) ባሉ አለቆች ስለታወቀ ከጎሬ አንድ ሀኪም ለርደታ ተላከልኝ፡፡ አብሬው የተማርኩ በጣም የምወደውና የማከብረው ልጅ ነበር፡፡ ደስታዬ መጠን አልነበረውም፡፡ እንግዲህ ጋምቤላ ሆስፒታል ለኗሪው ብቻ ሳይሆን በሰፈራ መንግሥት ጋምቤላ ላመጣቸው ከሰማንያ ሺ በላይ የሚሆኑ ሰፋሪዎችና ግፋ ሲል ደግሞ ከሁለት መቶ ሺ በላይ ለሚሆኑ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች አገልግሎት መሰጠት አለበት፡፡ ስደተኞቹ እንኳን ኢታንግ የሚባል ቦታ የራሳቸው አልጋ ያለበት ጤና ጣቢያ ይረዳሉ፡፡


ለሠፋሪዎቹ ግን ሀላፊነቱ የኛ ነበር፡፡ በደርግ ጊዜ ነበር፡፡ አንድ የማይረባ ህግ ነበር፡፡ በጣም አሰቃቂ ውጤት ነው ያስከተለው፡፡ በምንም መንገድ ቢሆን ሠፋሪዎች ቢታመሙና ከፍተኛ ህክምና ርደታ ቢያስፈልጋቸው ከጋምቤላ ውጭ መላክ አይቻልም፡፡ በጭራሽ፡፡ ቀጭን ትዕዛዝ ነበር፡፡


ታዲያ ከጎሬ የመጣው ጓደኛዬ ጋር ሆነን የምንችለውን ያህል ሠርተን ልንወጣ ስንል ድንገት ወሊድ ክፍል ምጥ ላይ ነች የተባለች ሴትዮ አለች ተብሎ ተጠራን፡፡ ደም እየፈሰሳት ነው፡፡ ምጥ ላይ አልገባችም ግን ቀኑ ደርሶአል፡፡ ምርመራ ስናደርግ ማንም ሀኪም ሊያጋጥመው የማይፈልግ ሁኔታ ነው ያየነው፡፡ እንደቆምን ደነዘዝን፡፡ ነገሩ የእንግዲህ ልጅ ተብሎ የሚጠራው በህክምና ፕላሴንታ የሚባለው ነገር ከልጁ ፊት ለፊት የማህፀን መውጫው ላይ ተቀምጧል፡፡ ይህ በጣም አደገኛ ሁኔታ ነው፡፡ ምክንያቱም በተፈጥሮ መጀመሪያ ልጁ ይወለድና ከዚያ የእንግዲህ ልጁ ተከትሎ ነበር መምጣት ያለበት፡፡ አለበለዚያ ገና ልጁ ሳይወለድ የእንግዲህ ልጁ ከማህፀኑ ግድግዳ ከተላቀቀ እናትና ልጁ በደም መፍሰስ ምክንያት ህይወታቸው ያልፋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ደግሞ መነካካት ያባብሰዋል፡፡ የነበረው አማራጭ በኦፕራሲዮን ማሰወለድ ነው፡፡ እኔና ጓደኛዬ መሥራት እንችል ይሆናል፡፡ ስንማር ይህን ሁሉ ተምረናል፡፡ ባይሆን አስተማሪ በሌለበት ብቻችን አድርገነው አናውቅም፡፡ ለዚያም ቢሆን ማደንዘዣ የሚሠጥ ባለሙያ የለም፡፡ ነገሩን ሲያከፋው ደግሞ ሴትዮዋ ደም ማነስ አለባት፡፡ የደም ማነሱ መጠን ደግሞ ከጤናማው መጠን ከግማሽ በታች ነው፡፡ ወደ መቱ እንዳንልክ አምቡላንስም የለም፡፡ የደርግ ቀጭን ትዕዛዝ ደግሞ ከላይ እንደተጠቀሰው ነው፡፡ የፈለጋችሁትን በሉ እንጅ ባናለቅስም የተሰማን ጭንቀት ይህ ነው አይባልም፡፡ አዎ ሀኪሞች አንጨነቃለን ግን እንድታውቁብን አንፈልግም፡፡

ከሴትዮዋ አልጋ ስር የተደገነው ሰሀን ላይ የሚንጠባጠበው ደም ድምፅ እሰካሁን ድረስ ይህ ሁኔታ ትዝ ባለኝ ቁጥር ጠብ ጠብ ጠብ ሲል ይሰማኛል፡፡

እኔና ጓደኛዬ ተያየን፡፡ ንግግር አላስፈለገንም በሚገባ አውቀናል፡፡ ሴትዮዋ ከነልጇ መሞታቸው ነው፡፡ ድንገት ደም ቢያስፈልግ ደም የሚሠጥ ሰው ጠፋ፡፡ ባል ተብየው ሲጠየቅ ሚሰት ቢሞት ሌላ ይተካል እንጅ ደም አልሠጥም አለ፡፡ በባህላቸው ደም መሥጠት አይወዱም፡፡ ጭራሽ ተሠወረ፡፡ ሴትዮዋና ባለቤቷ ጋምቤላ እንዲሠፍሩ ከተደረጉት ወገኖች ናቸው፡፡

ምን እናድርግ?

ቆየን፡፡ ተጠማዘዝን፡፡ መጨረሻ ወደ መኖሪያ ቤታችን ሄድንና፤ ሆስፒታሉ አጠገብ ነበርን፡፡ አንደ አዲስ ነገር ቢፈጠር ጥሩን አልን፡፡

ግን ቤት እንደገባን ሳንነጋገር ሁለታችንም እኔ አልጋ ሥር ተንበረከክንና ወደ እግዚአብሒር ፀለይን፡፡ ለሴትዮዋ፡፡

ምንም ጥሪ ስላልመጣና ሰለደከመን የሚቀመሰውን የወንደላጤ ምግብ በልተን ጋደም እንዳልን እንቅልፍ ለቀቀብን፡፡ ሌሊቱኑ በሙሉ ምንም ጥሪ አልመጣም፡፡

በጥዋት ሁለታችንም እየሮጥን ወደሴትዮዋ ሄድን፡፡ ነርሷ በፈገግታ ተቀበለችን፡፡ ተመስገን፡፡ ሌሊቱን ሴትዮዋ የእንግዲህ ልጁንና ልጁን አንድ ላይ ገፍታ ወልዳ ከሞት ተርፈዋል፡፡ ማህፀን የእንግዲህ ልጁ እንደወጣ ወዲያውኑ ሰለሚኮማተር ደም መፍሰስ ይቆማል፡፡ ግፋ ቢል ማህፀኑ እንዲኮማተር የሚያደርግ መድሀኒት መሥጠት ነው፡፡ ግን ሁለቱም ማለትም ልጁም የአንግዲህ ልጁም መውጣት አለባቸው፡፡

እንግዲህ ተዐምር ማለት ይህ ነው፡፡ ሴትዮ ከነ ልጇ ከነደም ማነሷ በዚህ የህይወት መጥፊያ ሁኔታ ተረፈች፡፡

ተመስገን፡፡