ወንዶችም ቢሆን Menopause አለባቸው
የትዳር ጓደኛዎን ከመጠርጠርዎ በፊት ይህንን ያንብቡ
አምብዛም በህብረተሰቡ የማይታወቀው ይህ የወንዶች Menopause በዕድሜ በገፉ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በወጣቶች ላይም እየታየ ነው፡፡ በተለምዶ አጠራር ይህ ሁኔታ በሴቶች ላይ ሲታይ በአማርኛ “ደም መቁረጥ” ይባላል:: ሁኔታው ሲከሰት፣ በተለይም በሴቶች የተለያዩ የባህሪና የሰውነት ለውጦች ጋር ታጅቦ ነው፡፡ ሴቶች እህቶችና እናቶቻችን ይህንን ሁኔታ አስቀድመው በአእምሮ ተዘጋጅተው ሰለሚጠብቁ ብዙም ሲያማርሩ አይታዩም፡፡
የነጮቹን ነገር ለጊዜው ተወት እናድረገውና፡፡ እንግዲህ በተመሳሳይ ሁኔታም ቢሆን ወንዶች ላይ ይህ Menopause ይከሰታል፡፡ ነገሩ እንደሴቶቹ ብዙም የሰውነት ምልክትና የባህሪ ለውጥ በከፍተኛ ደረጃ ባይታይበትም የራሱ የሆኑ ስሜትና ምልክቶች አሉት፡፡ ይሕ የሚከሰተው ቴስተስተሮን (Testerone) የተባለ የወንድነት ባህሪ የሚፈጥረው ሆርሞን መጠን እየወረደ ሲሄድ ነው፡፡ በተፈጥሮ፣ ከዕድሜ ጋር ይህ ሆርሞን መጠኑ በዝግታ ቢሆንም እየቀነሰ የሚሄድ ነገር ነው፡፡
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የወንዶች ዕድሜ 40 አመት ካለፈ በኋላ በየአመቱ የዚህ ቴስተስትሮን የተባለ ሆርሞን በ3 ፐርሰንት እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ በሌላ መረጃ ዕድሜ 30 አመት ካለፈ በኋላ የቴስተስተሮን መጠን በአመት በአንድ ፐርሰንት እየወረደ ይሄዳል፡፡ እንግዲህ በዚህ ግምት፣ የ80 አመት ሽማግሌ ወይም የዕድሜ ባለፀጋ ከወጣቶች ጋር ሲወዳደር የቴስተስተሮን መጠኑ በ50 ፐርሰንት ዝቅ ያለ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ በተፈጥሮ ሂደት የሚሆን ሰለሆነ በሽማግሌዎቹ ላይ ሲከሰት እንግዳ ነገር አይሆንም፡፡ አሁን ግን ችግሩ ወጣቶች ላይ መታየት ሰለጀመረ ነው፡
ለመሆኑ የዚህ የቴስተስተሮን መጠን መቀነስ የሚያሳያቸው ምልክቶች አሉ ወይ?
በነገራችን ላይ የዚህ ሆርሞን መጠን ዝቅተኛ መሆን የሚታወቀው በደም ምርመራ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ወንዶች በተፈጥሯቸው አነስ ያለ የቴስተስተሮን መጠን ቢኖረቸውም ምልክት ወይም ሰሜት ላያሳዩ ወይም ላይኖራቸው ይችላል፡፡
ከምልክቶች ዋነኛው
በግብረሥጋ ግንኙነት ላይ የሚታዩ ለውጦች ናቸው
ማለትም ለግብረሥጋ ግንኙነት ያለ ወይም የነበረ ፍላጎት መቀነስ (ሚስቶች ሌላ ሴት ጀመረ እንዴ ይሉ ይሆናል)
የወንድ ብልት መወጠር መቀነስ፣ በግብረሥጋ ግንኙነት ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ በመኝታ ጊዜ ወይም በጠዋት ከእንቅልፍ ሲነሱ የሚታየው የወንድ ብልት መወጠር መቀነስ(Erectile dysfunction)፣ ከዚህ ጋር በተያያዝም የወንድ መካንነት ሊከተል ይችላል፡፡ የወንድ ዘር ፍሬ ኳስ (testes) መጠንም ያንሳል፡፡
የዕንቅልፍ መዛባት፤ የቴስተስተሮን መጠን ሲቀንስ የዕንቅልፍ ማጣት ወይም መረበሽ አለዚይም ከመጠን በላይ እንቅልፋም መሆን ይከሰታል
በሰውነት ላይ የሚታዩ ለውጦች፤ የሰውነት ውፍረት፣ የጡንቻዎች መስለል ወይም መቀነስ፣ የአጥንት መሳሳት ይጨምራል፡፡ በሰውነት ላይ የፀጉር መጠን ማነስም ሌላው ምልክት ነው፡፡ እንዳንድ ወንዶች ላይ ደግሞ ጡት ማጎጥጎጥም ይታያል፡፡ የሰውነት መስነፍን ጨምሮ አንዳንድ ጊዜ አንደ ሴቶቹ የሰውነት ሙቀት መጨመርም ሊከሰት ይችላል፡፡
የባህሪ ለውጥ፤
ይህ ደግሞ በሀገር ቤት ወንዶቹ መነጫነጭ ሲጀምሩ እንግዲህ አረጀ እየተባለ ይነገራል፡፡ ምናልባትም በቂ ምክንያት አለው፡፡ በባህሪ ላይ የሚታዩት ለውጦች
የቴስተስተሮን መቀነስ የሚያስክትላቸው፣ ለስራ መትጋት ማነስ ወይም ስንፍ ማለት፣ በራስ መተማመን የመቀነስ ሁኔታም ይፈጥራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ምክንያቱ የማይታወቅ የሀዘን ስሜት መሰማት፤ ነገሮችን የማስታወስ ችሎታ መቀነስና በሥራ ላይ የሚኖር አትኩሮት መቀነስንም ይጨምራል፡፡
መታወቅ የሚኖርበት ነገር ቢኖር እነዚህ ሁኔታዎች በሌሎች ምክንያቶችም ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
ታዲያ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች በወጣቶችም ላይ እየተከሰተ ነው፡፡ በሰል ያሉ ህሙማን ወይም ሰዎች ሀኪሞቻቸውን የቴስተስተሮን መጠናቸውን እንዲለኩላቸው ይጠይቃሉ፡፡ እኔም ብሆን በብዛት አይሁን እንጂ የዚህን ደም ምርመራ እንዳዝላቸው የጠየቁኝ ሰዎችም አሉ፡፡
በሚቀጥለው ፅሁፍ ይህንን ጉዳይ እንዴት ማስተናገድ እንደሚቻል እሰከማቀርብ በዚህ ፅሁፍ ተዝናኑ፡፡ የማስበው ነገር ቢኖር ሚስቶች ያነበቡ ለታ ባሎቻቸው ላይ ምን ሊሉ እንደሚችሉ ነው፡፡ ከቻላችሁ አካፍሉን፡፡
ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ
Community health
education in Amharic