​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

ፕሮስቴት ካንሰር (Prostate Cancer)

ፕሮስቴት ካንሰር በአሜሪካ ወንዶች በብዛት በመከሰት በአንደኛ ደረጃ የሚገኝ ካንስር ሲሆን በካንስር ምክንያት ሕይወታቸው ለሚያልፉ ወንዶች ሁለተኛው ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሰለዚህ በወንዶች ላይ በብዛት ስለሚከሰተው ካንሰር መነጋገር አስፈላጊ ነው፡፡

ፐሮስቴት በወንዶች የሰውነት ክፍል የሚገኝ ዕጢ ሲሆን፡፡ ከሽንት ፊኛ ስር ተጠግቶ የሚገኝ አካል ነው፡፡ ከሽንት ፊኛ ሽንት ይዞ የሚወርደው ቱቦ በዚህ በፕሮሰቴት ዕጢ በኩል አልፎ ነው የሚሄደው፡፡ የዚህ ዕጢ ዋናው ተግባር ሲመን (semen) የተባለ ፈሳሽ ማመንጨት ነው፡፡ ይህ ፈሳሽ ደግሞ የወንዶች የዘር ሴሎችን (sperm ) ለመመገብና ለማመለስ ይረዳል፡፡ እንግዲህ በግብረ ስጋ ግንኙነት ጊዜ ከወንዶቸ በኩል የሚዘልቀው ፈሳሽ ከዚህ ዕጢ ነው የሚመነጨው፡፡
ፕሮስቴት ካንሰር የሚመጣው ከዚህ ፐሮስቴት ከተባለ ዕጢ የሚገኙ ሴሎች ከመጠን በላይና ከቁጥጥር ውጭ በሚያድጉበት ጊዜ ነው፡፡ የእድሜ ክልል 80 አመት ባላፋቸው በአብዛኛዎች ወንዶች ፕሮስቴት ካንሰር የሚከሰት ቢሆንም ከዕጢ ውጭ ተስፋፍቶ ካልተሠራጨ በስተቀር ከፍተኛ ጉዳት አያደርስም፡፡
በኢትዮጵያ የዚህ በሽታን መጠን ለጊዜው ማወቅ ባይቻልም ከካንሰር ውጭ ይሕ ዕጢ ከመጠን በላይ በማደጉ ምክንያት በውስጡ የሚያልፈውን የሽንት ቱቦ በመጫን ሽንት እንደልብ እንዳይወርድ በማድረግ ዕድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ የሽንት ማጥ የተባለ ችግር ሲያሰከትል ይታያል፡፡ የሽንት ማጡ በዕጢ ከመጠን በላይ ማደግ ምክንያት ሲሆን ከመጠን በላይ ያደገው ዕጢ ካንሰር ይኑረው ወይም ካንስር አልባ የሆነ (Benign prostatic hypertrophy- BPH) የተባለ ሁኔታ መሆኑ ተለይቶ መታወቅ አለበት፡፡

የፕሮስቴት ካንሰር ለማወቅ የሚደረጉ ምርመራዎች

ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ፕሮስቴት ካንሰር ከመከሰቱ በፊት የሚደረግ ቅድም ምርመራ ነበር ሆኖም ባለሙያተኞች በዚህ ጉዳይ ላይ ሙሉ ስምምነት ላይ ሰላልደረሱ ቅድመ ምርመራው በማንኛውም ተገቢ እድሜ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች ላይ እንዲደረግ ጥብቅ መመሪያ የለም፡፡ ሰለዚህ ይህ ቅድመ ምርመራ በሀኪምዎና በእርስዎ መሀከል በሚደረግ መነጋገር የሚደረግ ነው፡፡ ለመሆኑ ምርመራዎች ምንድናቸው፡፡

በፊንጢጣ በኩል የሚደረግ ምርመራ፡፡ ሐኪሞች በፊንጢጣ በኩል አንድ ጣት በማስገባት ዕጢውን በመዳሰስ በዕጢው ላይ እብጠት ወይም ጠጠር ያለ ጤናማ ያልሆነ ነገር ማደጉን ማወቅ ይችላሉ፡፡ (Digital Rectal Exam –DRE)

ሌላው ደግሞ በደም ምርመራ የሚታዘዝ ከዚህ ዕጢ የሚወጣ በምህፃረ ቃል (PSA – Prostate-specific-antigen) ተብሎ የሚጠራ የፕሮቲን አይነት ነው፡፡ ይህ ፐሮቲን ከመጠን በላይ ከተገኘ የፕሮስቴት ካንሰር መከሰቱን የሚጠቁም ነው፡፡ ሆኖም ይህ ምርመራ የራሱ ድክመት አለበት ይኸውም ዕድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ በእድሜ ምክንያት ብቻ ካንሰር ሳይኖረባቸው የዚህ  PSA የተባለ መጠን ከፍ ብሎ ሊገኝ ሲችል በሌላ በኩል ደግሞ የ ፕሮስቴት ካንሰር ባለባቸው ሰዎች ላይ ደግሞ በጤናማ መጠን ሊገኝ ይችላል፡፡ ስለዚህ አሰተማማኝነቱ አከራካሪ ነው፡፡  ሰዎች ከፈለጉ ሀኪማቸውን ይህ ምርመራ እንዲታዘዝላቸው መጠየቅ ይችላሉ፡፡

ፕሮስቴት ካንሰር ህክምና 

 እንግዲህ ከምርመራ በሁዋላ ፕሮስቴት ካንሰር ከተገኘ ህክምናው ካንሰሩ እንደተገኛበት ደረጃ እንደበሽተኛው እድሜ ፤ እንደ እድሜ ዘመን እና ጠቅላላ በሽተኛው የሚገኝበት የጤንንት ደረጃ ወይም ሁኔታ የሚደረግ ነው፡፡

  • ሀኪሞቹ ምንም አይነት ህክምና ሳያደረጉ ዕጢውን ወይም ካንሰሩን በየጊዜው በመከታተል ሊወስኑ ይችላሉ
  • በጣም ጥሩ ውጤት ያለው ህክምና ደግሞ ቀዶ ህክምና ነው፡፡ ጠቅላላ ዕጢውን እንዳለ ቆርጦ ማውጣት ከዕጢ ውጭ ላልወጣው ካንሰር ዋና ህክምና ዘዴ ነው፡፡ በእንግሊዝኛ Radical prostatectomy ይባላል፡፡ ሆኖም ይህ ዘዴ ደግሞ የራሱ ችግሮች አሉበት አነዚህም ሽንት መቆጣጠር አለመቻል እና የወንድ ብልት ቀና ማለት አለመቻል ነው፡፡ ይህ ግን በሁሉም ሰዎች ላይ የሚከሰት አይደለም፡፡ ይህ አይነት ቀዶ ሕክምና በአንዳንድ ሆሰፒታሎች በሮቦት አማከኝነተ ይደረጋል፡፡
  • ለተስፋፋ ካንሰር ደግሞ የጨረር ህክምና ይደረጋል (Radiation Therapy)፡፡ የጨረር ሕክምናው ደግሞ በሁለት መንገድ ሊደረግ ይችላል፡፡ አንደኘው መንገድ ከሰውነት ውጭ ጨረር አስፈላጊ ወደሆነው ስውነት ክፍል በመላክ ሲሆን ሁለተኛው ዘዴ ደግሞ ጨረር መልቀቅ የሚችል ነገር በፕሮስቴት ዕጢው ውስጥ በመቅበር የሚደረግ ነው፡፡


ከላይ የተጠቀሱት ህክምናዎች ከመደረጋቸው በፊት ግን የተለያዩ ምስል ማንሻ ዘዴዎች በመጠቀም ካንሰሩ በዕጢ ውስጥ ብቻ ተወስኖ ያለ ወይም ከዚያ ውጭ የተስፋፋ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ከዚህም በመነሳት ሀኪሞቹ ደረጃ የካነሰሩን ደረጃ በማውጣት ወደ አስፈላጊው ህክምና ያመራሉ፡፡

 ወደ ሁዋላ መለስ ብለን ስንመለከት ፕሮስቴት ካንሰር የሚያሰክትሉ ወይም የሚያጋልጡ ሁኔታዎቸ መኖራቸውን መጠቆም አንወዳለን፡፡ እነዚህም

  • ዕድሜ

  • ሲጋራ ማጨስ

  • አፍሪካን አሜሪካን ወይም ጥቁር አሜሪካዊ መሆን አደጋውን በዕጥፍ ይጨምራል
  • በቤተሰብ ውስጥ የህ ካንሰር ተከስቶ ከሆነ
  • ጤናማ ያልሆነ ስኳር እና ጮማ የበዛበት አመጋገብ ከመጠን በላይ ውፍረትም አጋላጭ ሁኔታዎቸ ሊሆኑ ይችላሉ


 ሰዎች ከላይ የተጠቀሱት አጋላጭ ሁኔታዎቸ ካለባቸው አስቀድሞ ወይም ቅድመ ምርመራ ማድረጉ ጥቅሙ ያመዝናል፡፡

ለመሆኑ የበሽታው ስሜትና ምልክቶች ምንድናቸው

ከእምብርት በታች የህመም ስሜት

ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት

ሽንት ሲሸኑ የህመም ስሜት፣ ቶሎ አለመውረድ ወይም ማስማጥ፣ ማቃጠል ወይም መለብለብ፤ ደካማ የሆነ የሽንት አወራረድ

ደም በሽንት ወይም በዘር ፈሳሽ ወስጥ መታየት

በግብረስጋ ጊዜ ዘር ፈሳሽ በሚመጣበት ጊዜ ሕመም ስሜት (ሲጨርሱ)

ከወገብ በታች ህመም ስሜት ጭኖችናአሟሂት ጨምሮ

የምግብ ፍላጎት መቀየር ክብደት መቀነስ

የማያቋርጥ የአጥንት ህመምን ይጨምራል፡፡

ከላይ አንደተገለፀው ይህ በእድሜ የገፉ ወንዶች ቸግር ስለሆነ በጥሞና ስውነትን ማዳመጥ እና በጊዜ ወደ ህክምና መዝለቅ አስፈላጊ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ በሽታ ላይ ባለሙያተኞች በእንግሊዝኛ Urologist ተብለው ይጠራሉ፡፡