አጠገባችሁ ያለ ሰው በሳርስ ኮሮና ቫይረስ-2 መያዙን ማወቅ ከቻላችሁ…. 4/6/2020

የበሽታ ስሜት የማይታይባቸው ሰዎች ቫይረሱን ማስተላለፋቸው የተረጋገጠ ነገር ነው

ከዚህ ቀደም ፈራ ተባ እያሉ፣ የበሽታ ምልክት የማያሳዩ ሰዎች ቫይረሱን ያስተላልፉ ይሆን የሚል ጥያቄና መልሶች ነበሩ፡፡

እንግዲህ ይህ ሳርስ-ኮቪ-2 የተባለው አዲሱ ቫይረስ፣ ለምን እንዲህ በፍጥነት አለምን አዳረሳት ለሚለው ጥያቄ መልስ ፍለጋ ከተጀመረ ቆየት ብሏል፡፡ አንዱ ጥናት፣ ከዚህ ቀደም በጎሽ ድረ ገጽ እንዳካፈልኳችሁ፣ የተመለከተው ነገር ቢኖር፣ በሁለቱ ቫይረሶች መሀከል በቁጥር 1 እና በዘህኛው በቁጥር 2 መሀከል፣ ቫይረሶች በአየር ላይና በዕቃዎች ላይ የሚቆዩበት ጊዜ የተለያየ ይሆን የሚል ነበር፡፡ ጥናቱ፣ በሰታቲሰቲክ ደረጃ በሁለቱ ቫይረሶች መሀከል ልዩነት አላሳየም፡፡ የጥናቱን ውጤት ማየት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይም ለመከላከል ለሚደረገው ርምጃ፡፡ ታዲያ ምን ይሆን ተብሎ ሲገመት፡፡ አንደኛው ምክንያት፣ ቫይረሱ ከመጠን በላይ በአፍንጫ ውስጥ ሰለሚገኝ ነው፡፡ ሌላኛው ምክንያት ደግሞ፣ በቫይረሱ የተያዙ፣ ገና ምልክት ያልታየባቸው ጤናማ ሰዎች ቫይረሱን ሰለሚያስተላልፉ ነው ብለው ገመቱ፡፡

ነገሩ ግምት ብቻ አይደለም፡፡ እውነት ነው፡፡ የተለያዩ መረጃዎችም እየወጡ ነው፡፡ ከነዚህ ከወጡ መረጃዎች አንድ ሁለቱን ላካፍላችሁ፡፡

የመጀመሪያው፣ በአሜሪካ ኮቪድ ተገኝቶባቸው፣ ለብዙ ህሙማን ህይወት ማለፍ ምክንያት ለሆነው፣ በዋሽንግተን ሰቴት፣ ኪንግ ካውንቲ፣ ውስጥ የሚገኘው የአዛውንቶችና ህሙማን መኖሪያ ቦታ ነው፡፡ በዚህ ቦታ፣ ሀኪሞቹም ሆነ፣ የአሜሪካው የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ሰዎች አጥንተው፣ በሳምንታዊ መግለጫቸው የወጣው ነው፡፡ በመረጃ የተደገፈ ነገር ማንበብና ማካፈል እንልመድ፡፡ መረጃ ሰለተፃፈ ብቻ ሳይሆን፣ እነማናቸው የፃፉት ማለትም ተገቢ ነው፡፡

በዚህ መረጃ መሠረት፣ በዚህ ነርሲንግ ሆም (ወይም የኣዘውንቶች የህክምና ርዳታ እየተደረገላቸው በሚኖሩበት ቦታ)፣ አንድ የጤና ሠራተኛ ኮቪድ-19 ስለተገኘበት፣ በዚህ መኖሪያ ቦታ ከሚኖሩ ከ82 አዛውነቶች በ76 ላይ ምርመራ ይደረጋል፡፡ የግድ ነው፡፡ በዛው በመኖሪያው ውስጥ ሰለሚኖሩ፣ አንደኛው ሰው ከተያዘ ለሁሉም ሰለሚሻገር ነው፡፡ እንግዳ ነገርም አይደለም ምክንያቱም በሌሎች ተላላፊ በሽታዎችም ላይ የሚደረግ አቀራረብ ነው፡፡ ምርመራው ከተደረገላቸው አዛውንቶች መሀከል፣ በዚያን ጊዜ ከመቶ 30 ፐርሰንቱ፣ በዚሁ በሳርስ-ኮቪ-2 መያዛቸው ይረጋገጣል፡፡ አሁን ዋናው ነገር፣ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠው ሰዎች መሀከል፣ ምን ያህሉ የበሽታ ስሜት ነበራቸው የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ከሆነስ፣ በበሽታው ሥርጭትና፣ በሽታውን ለመከላከል በሚወሰደው ርምጃ ላይ የሚያሰከትለው ወይም የሚለውጠው ነገር አለ ወይ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ወሳኝ የሚሆነው፣ ለምን ይመስላችኋል፡፡ ለኮቪድ በሸታ መያዝ ማጣሪያ ጥያቄው (ስክሪኒንግ) በበሸታ ስሜት ያተኮረ ሰለሆን፡፡ የበሽታ ስሜት የለበትም የተባለ አዛውንት በመሀሉ ማጣሪያውን አልፎ የለባቸውም ከሚባሉ ሰዎች ጋር ሰለሚቀላቀል፣ ቫይረሱ መዛመቱ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡

በዕድሜ ገፋ ያሉ ኣዘውንቶች፣ ባቫይረሱ ከተያዙ በዕድሜያቸው ብቻ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ህመም እንደሚሄዱም ይታወቃል፡፡ ሰለዚህ ቫይረሱ ወደ ነሱ እንዳይገባ አስፈላጊው ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ የተያዙትን ካልተያዙ መለየት፣ ተያዙ ከተባሉት ጋር የሚሠሩ የጤና ባሙያተኞች ደግም፣ አስፈለጊውን መከላከያ ለብሰው እንዲሠሩ ማድረግን ይጨምራል፡፡

ነገሩ የመጣው፣ የጤና ባለሙያተኘው፣ እያመመው ሥራውን የቀጠለው ይህ ሠራተኛ፣ ሁለት ቀናት ብቻ ነው የሠራው፡፡ ምርመራ ሲደረግለት፣ በቫይረሱ እንደተያዘ ይረጋገጣል፡፡ እሱ የሠራው፣ በፌብሩዋሪ 26ና 28 ነው፡፡ በማርች 6፣ ሰባት የሚሆኑት አዛውንቶች ይታመማሉ፣ ምርመራው ሲደረግ በቫይረሱ መያዛቸው ይረጋገጣል፡፡ በማርች 13፣ CDC ለኗሪዎቹ ምርመራ ያደርጋል፡፡ ምርመራው የበሽታ ምልክት ማሳየትና አለማሳየታቸው፣ ከዚህም ጋር ደግሞ የላብራቶሪ ምርመራ በማድረግ ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ከ82 ኗሪዎች መሀከል፣ 76 ላይ ነው ምርመራ የተደረገው፡፡ በዚህ መሠረት የበሽታ ምልክቶች (ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ ማጠር ስሜትና ሌሎችን ጨምሮ) የሌለባቸውና ያለባቸው ተብለው ተከፈሉ፡፡ ከ76 ሰዎች መሀከል፣ 23 ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆኑ፣ ከነዚህ ከ23 መሀከል ደግሞ፣ አስሩ የበሽታ ምልክት ሲገኝባቸው፣ ምርመራው በተደረገበት ጊዜ ከ23 ወስጥ 13ቱ ምንም የበሽታ ስሜት አልነበራቸውም፡፡ እንግዲህ አስተውሉ፣ ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች፣ 57% የሆኑት፣ ምርመራው በተደረገው ወቅት ምንም አይነት የበሽታ ምልክት አልነበራቸውም፡፡ እንግዲህ፣ ሰዎችን ለመለየት፣ የላብራቶር ምርመራ ሳይጨመር፣ ዝም ብሎ በበሸታ ምልክት ብቻ ማጣሪያ ቢደረግ፣ እነዚህ አስራ ሶስት ሰዎች፣ የለባቸውም ተብለው ከሌለባቸው ሰዎች ጋር ሲቀላቀሉ የሚከተለውን ጉዳት መገመት አያደግትም፡፡ ከዚህ ቫይረስ ባህሪዎች አደገኛው ይህ ነው፤ በተለይም ሥርጭቱን ለማባባስ፡፡

ሌላው የታየው ነገር፣ ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ ምንም ምልክት ሳያሳዩ ቫይረሱን ተሸክመው አሻጋሪ ሆነው ቢቆዩም፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን፣ የበሽታውን ምልክት ማሳየት ይጀምራሉ፡፡ ያ ግን ጉዳት ከደረሰ፣ ማለትም ቫይረሱን ካሻገሩ በኋላ ነው፡፡ እነዚህ ዘግየት ብሎ የበሽታ ምልክት የሚታይባቸው (ቅድመ ሰሜት አሻጋሪዎች ወይም አስተላላፊዎች) ናቸው፡፡  ማጠቃለያው፣ በበሽታ ስሜትና ምልክቶች ብቻ እከሌ ይዞታል እከሌ አልያዘውም ብሎ መለየት፣ ፈተና የማያልፍ አሰራር ነው፡፡ እንግዲህ ተጧሪዎች እንድ ላይ የሚኖሩበት ቦታ፣ ወይም ሰዎች ሰብሰብ ብለው የሚኖሩበት ቦታ፣ የግድ የላብራቶሪ ምርመራ አስፈላጊ ነው፡፡ ያም በቫይረሱ የተያዘውን ለይቶ ለማስቀመጥ፡፡ ሰፋ ወዳለው ህዝብ ስንመጣ ደግሞ፣ በተለይም ሥርጭቱ ገፋ ባለበት ጊዜ፣ ማን በቫይረሱ እንደተያዘ፣ ማን እንዳልተያዘ መለየት አይቻልም፡፡ ለዚህ ነው ከሰው ጋር የሚደረገውን ግንኙነት አቁሙ፤ አሁን ደግሞ፣ የተያዘውና ያልተያዘው ሰለማይለይ፣ ሁሉም ሰው ጭምብል (ወይም ማስክ) ማድረግ እንደሚኖርበት የተነገረው፡፡ ድሮም ቢሆን የማሰክ ዕጥረት ተፈርቶ ነው አንጂ፣ ማስክ መልበሱ ብዙውን ሰው ከመያዝ እንደሚያድነው ሳይታወቅ ቀርቶ አየደለም፡፡ ማሰክ ሲደረግ ግን፣ አፍና አፍንጫ በደንብ ተሸፍኖ፣ ትንፋሽ በማፈኛ ማስኩ በኩል እንዲወጣና እንዲገባ ተደርጎ ነው እንጂ ለይስሙላ አፍ ላይ ጣል አድርጎ መዞሩ አግባብ አይደለም፣ አያስጥልም፡፡ እንደ ነገሩ ማስክ አድርጎ የሚዞር ሰው ካያችሁ፣ ስድስት ጫማ ወይም ሁለት ሜትር ሳይሆን አራት ሜትር መራቅ ይሻላል፡፡ አራት ሜትር ራቁ ማለቴም አይደለም፣ ነገር ግን ሰውየው ሰለ ኮሮና የገባው ሰለማይመስል፣ ሌላስ ሰዎችን ለቫይረሱ የሚያጋልጥ ነገር ምን ያደርግ ይሆን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ መምከር ግን ጥሩ ነው፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ማስተማር ነው፡፡

አሁን የዚህን ቫይረስ ሥርጭት ያገነነውን አንዱን ትልቁን ምክንያት ተገንዘበናል፡፡ ወደኋላ መለስ ብላችሁ ካያችሁ፡፡ ይህ ቫይረስ በአፍንጫ ውስጥ በብዛት የሚገኝ ከሆነ፣ ስሜት የሌለባቸው የሚያስተላልፉ ከሆነ፣ ሳያስላቸው ወይ ሳያሰነጥሳቸው በሚያወሩበትና በሚተነፈሱበት ጊዜ ቫይረሱን ወደ ውጭ እየረጩት ነው ማለት ነው፡፡ ሰለዚህ ሁሉም ሰው ጭምብል ሲያደርግ እነዚህ ሰዎችም ሰለሚያደርጉ ከነሱ የሚወጣው ቫይረስ በጭምብሉ ተከልክሎ ይቀራል፡፡ በዚህ መንገድ ሥርጭቱ ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ ሰለዚህ አፍና አፍንጫን በጭምብል አፍኖ መውጣት ፋሽን መሆን አለበት፡፡ ይሁን፡፡ ምናለበት እነዚህ ዘፋኞች ይህን እያደረጉ እየወጡ ቢያሳዩ መልካም አርኣያ ይሆኑ ነበር፡፡ ፖለቲከኞቹን አንኳን ወይ ፀበል መንከር፣ ወይ አንድ ላይ ሰብስቦ ሶላት ካላደረጉላቸው የህዝብ ችግር የገባቸው አይመስሉም፡፡ በዚህ ላይ ቢረባረቡ ጥሩ ነበር፡፡

በሠርግ ዕለት ያልተጠራው ተጋባዥ ኮቪድ-19 ሠርገኞችን … 5/25/20202

 ሰው ከሰው ጋር ከተገናኝ መተላለፍ መቻሉን ያስመሰከረው ሳርስ ኮሮና ቁ 2፣ (ሳኮ2) በተለያዩ አጋጣሚዎች መሠራጨቱን አይተናል፡፡ እንግዲህ፣ በልደት፣ በሀዘን፣ በቤተክርሰቲያን ስብስብ ተላለፈ፡፡ ትልልቅ የሚባሉ የህዝብ በአላት ላይ፣ ሠርጭቱ ከመጠን አልፎ የሚሄድበት መሆኑ ታውቋል፡፡ በውሀን ከተማ፣ የቻይኖቹን አዲስ አመት ለማክበር የሄደ ህዝብ ነው ሥርጭቱን ከቁጥጥር ውጭ ያደረገው፡፡ የዛሬ መቶ አመት የታየው የስፓኒሽ ኢንፍሉዌንዛ፣ በኢትዮጵያ የህዳር በሽታ፣ በጣም የገነነው የህዳር ሚካኤል በተከበረ በሳምንቱ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የህዳር በሽታና የኮቪድ አካሄድ ተመሳሳይ ነው ማለት ያስደፍራል፡፡ ለማንኛውም የዚህን ታሪክ ትረካ ክፍል አንድና ሁለትን ብታዳምጡ ብዙ መገንዘብ ትችላላችሁ፡፡

እስካሁን ስለ ሠርግና ኮቪድ ወግ ባለው የፅሁፍ ምንጭ ሰላልቀረበ፣ ማካፈልም አልተቻለም ነበር፡፡ አሁን ግን በአርቲክል መልከ ከጤና ባለሙያኞች በኩል የቀረበ ፅሁፍ ላካፍላችሁ፡፡

ነገሩ የሆነው በጆርዳን ነው፡፡ በማርች 2020፣ በሠርግ የተነሳ፣ ሰፋ ያለ የኮቢድ-19 ሥርጭት ይከሰታል፡፡ እንግዲህ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር፣ የመንግሥት መደበኛ ሥራ መሆን የሚገባው፣ በሠርጉ ለት የተገኙ ሰዎችን ፈልጎ ማግኘት፣ መጠየቅና መመርመር ነው፡፡ ጆርዳንም ይህንን አደረጉ፡፡ የሚገርመው ነገር የዚህ የሠርጉ ሥርጭት እሰኪፈነዳ ድረስ፣ ማለትም አስከ ማርች 15፣ በጆርዳን አንድ በላቦራቶሪ የተረጋገጠ በኮሮኖ የተያዘ ሰው ብቻ ነበር የሚታወቀው፡፡

በማርች 13፣ 2020 ሁለት ሰአታት በወሰደ ሠርግ ላይ ሥርጭት ይከሰታል፡፡ ሠርጉ፣ ለአራት መቶ ሰዎች ተብሎ የተዘጋጀ ነበር፣ የተገኙት ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ባይታወቅም፣ ወደ 360 የሚሆኑ ሰዎች እንደታደሙ ይገመታል፡፡ ከአካባበዊ የጤና ቢሮ ጋር በመሆን፣ አጥኝዎቹ፣ ታመሙ አልታመሙም 360 ሰዎች ላይ ምርመራ ያደርጋሉ፣ በአፍንጫ በኩል በሚደረግ ቫይረሱ መኖሩን የሚያረጋግጥ ምርመራ ነው፡፡ ሠርጉ ላይ የተገኙ ሰዎች ብቻ ሳይወሰን፣ ከነሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ወይም የተጋለጡ ሰዎችም ጥናቱ ውስጥ ተካተዋል፡፡ ተጨማሪ መረጃዎችም ተሰበሰብዋል፡፡

ቫይረሱን ይዞ የመጣና ለመተላለፍ ምክንያት የሆነው ሰው፣ ሌላ ቢሆን ጥሩ ነበር፣ ነገር ግን የሙሽራዋ አባት ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ሰውየው ከሠርጉ ሁለት ቀናቶች በፊት፣ ሳል፣ ትኩሳትና፣ ንፍጥ (ይቅርታ) ነበረው፡፡ ከሠርጉ ከሁለት ቀን በኋለ ወደ ድንገተኛ ክፍል ሄዶ ሲመረመር በኮቢድ-19 ወይም ሳኮ2 መያዙ ይረጋገጣል፡፡ ሰውየው ከስፔይን ነበር የተጓዘው፣ በስፔይን፣ ኮቪድ ካለው ሰው ጋር ለመገናኘቱ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ከሠርጉ ከአራት ቀናት በፊት ጆርዳን ሲመጣ ሙሽራውን ጨምሮ ከቅርብ ቤተሰብ ጋር ተገናኝቷል፡፡

ምርመራው የተደረገው ከሠርጉ አራት ሳምንታት በኋላ ሲሆን፣ ከሙሽራዋ አባት ጋር 85 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ይረጋገጣል፡፡ከነዚህ መሀል 76 በሠርጉ ላይ የተገኙ ሲሆን፣ ዘጠኙ ግን በሠርጉ ላይ ያልነበሩ፣ ነገር ግን ወደ ሠርጉ ከሄዱ ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች ናቸው፡፡ የሚገርመው፣ በጆርዳን ብሄራዊ ፖሊሲ መመሪያ መሠረት ሁሉም በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ሆስፒታል ገብተው ክትትል ተደረገላቸው፡፡

ከ76ቱ ሠርጉ ላይ ከተገኙት እና በሳኮ2 መያዛቸው ከተረጋገጠው ሰዎች መሀል፣ 40ዎች (52.6%) የበሽታው ስሜት ነበራቸው፡፡ 36ቱ (47.4%) የበሽታ ስሜት አልነበራቸውም፡፡ ከተያዙት መሀከል አንደኛዋ ነብሰ ጡር ነበረች፣ ነገር ግን በሰላም ተገላግላለች፡፡ ከ48 ሰኣታት በኋላ አዲሱ ልጅ ምርመራ ተደርጎለት ቫይረሱ አልተገኘበትም፡፡ አነዚህ ሰዎች ሁሉ ክትትል ያደረገው የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ነው፡፡

አብዛኛዎቹ ስሜት የነበራቸው ሰዎች፣ በብዛት የታየባቸው ምልክት ትኩሳት፣ መናፈጥና፣ ራስ ምታት ነበር፡፡ ሌሎችም ተጨማሪ ምልክቶች እንደ ጉሮሮ መከርከር፣ ድካምና ጡንቻ ህመም፣ ትንፋሽ ማጠር ስሜትም ነበሩ፡፡ ከሁለት ሰዎች በስተቀር በሌሎቹ ቀለል ያለ ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ አንድ የ80 አመት የጡት ካንሰር የነበራት አሮጊት፣ እየከፋ የሚሄድ የሳምባ ምች (ኒሞኒያ) ይዟት፣ ሆስፒታል በገባች ከሁለት ሳምንት በኋላ ሞተች፡፡ በዚህ ሥርጭት፣ ከተጋለጡ በኋላ የበሽታ ስሜት ለመከሰት የወሰደው ጊዜ አምሰት ቀናት ነበር፡፡ አማካይ ነው፣ ገደቡ ከ2 አስከ 13 ቀን ድረስ ነበር፡፡

እነዛ ድግስ ሳይበሉ በኮቪድ የተያዙ ዘጠኝ ሰዎች ሁሉም፣ ወደ ሠርግ ሄደው ቫይረሱን ይዘው የተመለሱ ሰዎች ቤተሰቦች ናቸው፡፡ ማመላለስ ይሏችኋል ይህ ነው፡፡ ከዘጠኙ መሀል፣ አራቱ የበሽታ ሰሜት ነበራቸው፡፡ አምስቱ ግን አልነበራቸውም፡፡

ይህ ሪፖርት ብዙ ምክሮች ልናገኝበት የምንችል ነው፡፡
1ኛ. ግልፅ እንደሆነው የሰዎች ስብስብ መፈጠሩ
2ኛ. በሁለት ሰአታት ውስጥ ያን ያህል ሥርጭት መፈጠሩ፣
3ኛ› በአንድ ሰው አማካኝነት ብቻ መሆኑ፡፡ ሰዎቹ ከሰውየው ጋር የነበራቸው ርቀት ወይም ቅርበት አይታወቅም፡፡ ነገር ግን የሙሽራዋና የሙሽራው ወላጆች በር ላይ ቆመው የሚመጡ ሰዎችን ሲቀበሉ ነበሩ ይላል ሪፖርቱ፡፡ እንደዛ ከሆነ ደግሞ፣ በጣም አጭር ጊዜ ነው የነበረው፡፡ ግን መተቃቀፍ መሳሳሙም አለ፡፡
4ኛ. ቫይረሱ ቤት ድረስ ሄዶ ሠርግ ላይ ያልተገኙ ሰዎችን መያዙ
5ኛ. ቁጥራቸው ከፍ ያለ ስሜት አልባ ሰዎች መኖራቸው
6ኛ. መደበኛ ክትትልና፣ የተያዙትን ለይቶ ማወቅና ማግለል፣ እንደ ሪፓርት አቅራቢዎች ዘገባ፣ በቀጠለው ክትትል ሌላ ሰው አለመያዙ ሌላ ትምህርት ነው፡፡
7ኛ. በዚህ ዘገባ በተደረገው ስሌት፣ 1 በቫይረሱ የተያዘ ሰው ከ2 አስከ 3ት ለሚሆኑ ሰዎች እንዳስተላለፈ ነው፡፡ ይህ ስሌት በሽታን ለመቆጣጠር በሚደረግ ዝግጅት ወሳኝ ነው፡፡ ይሀ ቁጥር ግን፣ በጣም በተጣበበ ብዛት ያላቸው ሰዎች ባንድ ላይ በሚኖሩበት ቦታ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ በአሜሪካ ሰሌት አስር ነው ሲባል ነበር፡፡
8ኛ. ቫይረሱ እንደምንም ብሎ የሚገለው ሰው እንዳገኘ መገንዘብ ወሳኝ ነው፡፡

መልካም ንባብ፡፡

በቀብርና በልደት በአል የተገኘ አንድ ሰው ብቻ

ኮሮና አሠራጭቶ ያሰከተለው ችግር 4/11/20 

ለኮሮና ሥርጭት መገታት፣ የሰዎች እንቅሰቃሴ መገደብ መሆኑ አሌ የማይባል ነገር ነው፡፡ ከሁለት መንገዶች አንዱ የሆነው ይህ ሰዎች በየመኖሪያቸው ሰብሰብ ብለው እንዲሰነብቱ የሚሠጠው ምክርና፣ በመንግሥታቱም በኩል በአዋጅ መልክ የሚደረገው ነው፡፡ ሌላው ዋናው ነገር፣ ከዚህ ጋር በማያያዝ፣ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን በምርመራ አረጋግጦ ለይቶ ማስቀመጥ ነው፡፡ በዚህ ረገድ፣ ሥርጭቱን በማቀዝቀዝ የሚታወቁ፣ ይህ አሠራርም በተግባር የረዳቸው አገሮች አሉ፡፡ እነሱም፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓንና ሲንጋፖርን ይጨምራል፡፡ 
     በየቤታችሁ ተሰብሰቡ ሲባል፣ ከዚህ ቁጥር በላይ አንድ ላይ አትሁኑ የሚባልም አብሮ የሚነገር ነገር አለ፡፡ ሲጀመር ከ50 ሰዎች በላይ ነበር፣ በኋላ ግን ይህ ቁጥር ወደ አስር ወረደ፡፡ ያም ሆኖ ቁጥሩ አስር የተባለበትን ምክንያት ያልተገነዘቡ ሰዎች፣ በርከት እያሉ መሰባሰባቸውን ቀጠሉ፡፡ ነገር ግን አስር የተባለበት ምክንያት፣ ድንገት የቤተሰብ አባላት ቁጥር አስር የሚሆንባቸው ቤተሰቦች ላለመነጣጠል ሲባል ነው እንጂ፣ ጭራሽ ሰው በቤቱ ከቤተሰቡ ውጭ ከሌላ ጋር ባይገናኝ ደስታውን ባልቻልነው የነበር፡፡
     ይህንን ለማስረዳት፣ ማለትም ቁጥሩ ሳይሆን ከሌላ ሰው ጋር መገናኘቱ አደጋ እንደሚያሰከተል ለማሳየት፣ MMWR የተባለ የCDC ሳምንታዊ መፅሄት ያሰፈረውን ማጋራት የግድ ነው፡፡
     ከዚህ በፊት አንደተገለጠው፣ አንድ ተላላፊ በሽታ በአንድ ሰው ላይ ሲከሰት፣ ከተያዘው ሰውየ በፊት ማን ሊያስይዘው እንደቻለ፣ ከዚያም የተያዘው ሰው ለማን ሊያሻግረው እንደቻለ፣ በተለይም በመንግሥት የጤና ቢሮዎች በኩል ክትትል ይደረጋል፡፡ Contact tracing ይባላል፡፡ ለኮሮና ብቻ አይደለም፣ ለሌችም ተላላፊ በሽታዎች ይደረጋል፤ የቆየ የተለመደ ሥራ ነው፡፡ አላማውም በሽታው ሳይዛመት የተያዙ ሰዎች ከሌሎች ጋር እንዳይገናኙ ማድረግ፣ ወይም ደግሞ አስፈላጊውን ህክምና በመሥጥት እንዲድኑና ለሌላ ሰው እንዳይሰተላልፉ ለማድረግ ነው፡፡
      በቺካጎ የደረሰውን፣ በክትትል ያገኙትን ውጤት ነው የማካፍላችሁ፡፡ ከጃንዋሪ አስከ ማርች 20 ድረስ ባለው ጊዜ፣ በተለያዩ የላብራቶሪ ተቋሞች ለኮቪድ-19 የተገኘባቸው ናሙናዎችን በማየት ከላይ የተጠቀሰው የንክኪ ምርመራ የግድ መጀመር ነበረበት፡፡ በበሽታው የተያዙት ሰዎች፣ ተፈልገው ከተገኙ በኋላ፣ ሥርአት ባለው መጠየቂያ ፎርም መሠረት ጥያቄ ይደረግላቸዋል፡፡
     በዚህ ባደረጉት ክትትል፣ አንድ ግለሰብ ብቻ ያደረሰውን ጉዳት ይገልጣሉ፡፡
     በፌብሩዋሪ 20፣ በሌላ ምክንያት የሞተ ሰው ቀብር ላይ፣ የቤተሰብ ቅርብ ጓደኛ የሆነ ሰው በቀብር ቦታው ይገኛል፡፡ ይህ ሰው በቅርቡ ከስቴቱ ውጭ ወጣ ብሎ የተመለሰና፣ በዚያን ጊዜ በጣም ቀላል የሆነ የሳል ስሜት ነበረው፡፡ ይህ ሰው፣ ቀብሩ ነገ ሊሆን ማምሻውን፣ ከሟቹ ቤተሰቦች ከሁለቱ ጋር በመሆን በቤታቸው እራት ይበላል፡፡ በእራቱ ላይ ለሶሰት ሰኣታት የቆየ ሲሆን፣ በነጋታው በቀብሩ ላይ ደግሞ ለሁለት ሰኣታት ከቤተሰቦች ጋር ይቆያል፡፡ ከዚህም ጋር የሟቹ ቤተሰቦች ከሆኑ ሰዎች ጋር ሀዘኑን ለመግለፅ መተቃቀፉን ገልጧል፡፡ ይህ ግለሰብ፣ ሌሎች ሰዎች ታመው መረጋገጡ ሲታወቅ፣ እሱም ምርመራ ተደርጎለት በኮቪድ-19 መያዙ ይታወቃል፡፡ ካለፈ በኋላ መሆኑ ነው፡፡
      ሰውየው በቀብሩ ጊዜ፣ ሀዘኑን ለመግለፅ አብሯቸው ከነበሩ ሰዎች መሀከል፣ ሁለት ሰዎች፣ ከሰውየው ከተገናኙ በ2-4 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ የበሽታ ስሜት ሰለነበራቸው፣ ምርመራ ተደርጎ በኮቪድ-19 መያዛቸው ይረጋገጣል፡፡ከሁለቱ አንደኛው በሽተኛ፣ ከተጋለጠ በ11ኛው ቀን በጠና ታሞ፣ ሆስፒታል ገብቶ፣ መተንፈሻ መሳሪያ ቢደረግለትም፣ ከተጋለጠ በአራት ሳምንት ህይወቱ ያልፋል፡፡ ሌላ ተጨማሪ ሶስተኛ ሰውም የበሽታ ስሜት ይታይበታል (በነገራችን ላይ የወንድ ፆታ ተጠቀምኩ እንጂ፣ ፆታቸው አይታወቅም) አነዚህ የተረፉት በተመላላሽ ህክምና ርዳታ ብቻ ቆየተው፣ ሁለቱም ሙሉ በሙሉ አገግመዋል፡፡
      መጋለጡ ከተከሰተ በ11-14 ቀናት ባለው ውሥጥ፣ ከዋናው ሰውዬ ጋር በቀብሩ ጊዜ በጣም ቅርርብ የነበረ ሰው፣ ሆሰፒታል ገብቶ የሚረዳውን ሰው፣ ሆስፒታል ድረስ ገብቶ መጠየቅ፣ አቅፎ ደግፎ ለተወሰነ ጊዜ ርዳታ አድርጎ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ሰው፣ በዚያን ጊዜ ምንም አይነት የመከላከያ ልብስ አልበሰም፡፡ የታመመውን ሰው ከጠየቀና ከረዳ በኋላ በሶስተኛው ቀን፣ የኮቪድ በሽታ ስሜት ይሰማዋል፡፡ ይህ ሰው በቀብሩ ጊዜ የነበረ ቢሆንም፣ በጣም የተጋለጠው ታማሚውን በጠየቀበት ጊዜ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ይህ በሀዘንና በቀብሩ ጊዜ ነው የሆነው፡፡ እንዳያችሁት ለአንድ ሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያትም ሆኗል፡፡
      ከቀብሩ ከሶስት ቀናት በኋላ፣ ይህ ዋናው ሰው፣ አሁንም ቀለል ያለ የጉንፋን ስሜት እየተሰማው፣ የልደት በአል ለማክበር ወደ ሰዎች ቤት ጎራ ይላል፡፡ ይህ የልደት በአል ሌሎች ዘጠኝ የቤተሰብ አባላት የተገኙበት ቤት ውስጥ የተከበረ ነው፡፡ በበአሉ፣ ከዋናው ሰውዬ ጋር ቅርበት ያለው ግንኙነት ነበረ፡፡ ዋናው ሰውዬ ሰው ማቀፍ የሚወድ መሰለኝ፤ በዚህ ልደትም ሌሎችን አቅፎ፣ ሶስት ሰአታት በፈጀ በአል ምግብ አብሮ በልቷል፡፡
      ከልደት በአሉ ከሶሰት እስከ ሰባት ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ፣ በልደት በአሉ ላይ ከነበሩ ሰዎች መሀከል፣ ሰባት ሰዎች የኮቪድ-19 በሽታ ይታይባቸዋል፣ ከነዚህ መሀከል ሶሰቱ በላቦራቶሪ የተረጋገጠ ነው፡፡ አስታውሱ፣ ይህ ክትትል ሁኔታው ከተከሰተ በኋላ የተደረገ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ፣ ምርመራ ሙሉ በሙሉ ሰላልነበር፣ የተለያዩ መስፈርቶችን በመጠቀም ሰዎችን በኮቪድ-19 ተይዘዋል ማለት ይቻላል፡፡ በልደቱ ከነበሩት መሀከል ሁለት ሰዎች ብቻ ከአስራ ቀናት በኋላ ምንም አይነት የበሽታ ስሜት አልታየባቸውም፡፡ ከታመሙት መሀከል ግን ሁለት ሰዎች ወደ ሆስፐታል ገብተዋል፡፡ ሁለቱም በጠና ታመው፣ የመተንፈሻ ርዳታ ቢደረግላቸውም፣ ሁለቱም ህይወታቸው ያልፋል፡፡ ሌሎች ከተረፉት መሀከል፣ የበሸታ ሰሜት ተሰምቷቸው፣ ምርመራ ሲደረግ በኮቪድ-19 መያዛቸው ይረጋገጣል፡፡
     በልደት በአሉ ተገኝቶ የታመመውን ሰው፣ ሌሎች ሁለት በልደት በአሉ ላይ ያልነበሩ ሰዎች፣ ምንም መከላከያ ሳይለብሱ፣ ሰውየውን ሲረዱ የነበሩም፣ ታማሚውን በረዱ በሶሰተኛው ቀን፣ አዲስ ሳል እንደጀመራቸው ተዘግቧል፡፡  እነዚህ በልደቱ በአል ያልተኙት፣ በበሽታው የተያዙት፣ በልደት በአሉ ተገኝቶ ከታመመው ሰው ነው፡፡ ይህ ማለት ሌላ ደረጃ መተላለፍ ማለት ነው፡፡ ያም ከመጀመሪያው ከዋናው ሰው ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ሳይኖራቸው ነው፡፡
      እንግዲህ ሌላው ተጨማሪ ነገር፣ በልደት በአሉ ላይ ከነበሩ ሶስቱ፣ የበሽታ ስሜት ከተሰማቸው ከስድስት ቀናት በኋላ ወደ ቤተክርሰቲያን ይሄዳሉ፡፡ በቤተክርስቲያኑ የነበረ፣ ከነዚህ ሶሰት ሰዎች ጋር በቅርበት የተገናኘ ሰው የበሽታ ሰሜት ይታይበትና ሲመረመር በኮቪድ-19 መያዙ ይረጋገጣል፡፡ ይህ ሰው የጤና ባለሙያተኛ ነው፡፡ ከሶስቱ ሰዎች ጋር፣ በአንድ መደዳ በመቀመጥ ዘጠና ደቂቃ በቆየ ጊዜ ጠጋ ብሎ ወሬ ሲያወራቸው የነበረና፣ የምፅዋት ሙዳዩን ሲቀባበል የነበረ ነው፡፡
      ስለሰዎቹ የሚታወቀው ወይም የተገለጠ ነገር ቢኖር፣ ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 86 አመት መሀከል ያሉ ሲሆን፡፡ ሶሰቱም ከዚህ ንክኪ ጋር በተያያዘ የሞቱት ሰዎች፣ ዕደሜያቸው ከ60 አመታት በላይ ነበር፡፡
     እንግዲህ በዚህ በተጠናከረ መረጃ ያያናቸው ብዙ ነገሮች አሉ
     ከቤተሰብ ውጭ በሚደረግ ግንኙነት ቫየረሱን ለማዛመት አንድ ሰው ይበቃል፡፡ ከአስር በላይ አትሰበሰቡ ለቤተሰብ ነው እንጂ ከማያወቁት ሰው ወይም የቤተሰብ አባል ካልሆነ ሰው ጋር አይደለም፡፡ የሰማሁት በአንዳንድ ቦታ፣ ቁጥራቸው ቀነስ ሳላለ፣ ጓደኛሞች በቡድን በቡድን እየሆኑ የበረንዳ ቡና እንደሚጠጡ ነው፡፡ ከዚህ መማር ይገባቸዋል፡
      ሁለተኛ፣ የህመም ስሜት ከተሰማችሁ አትውጡ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ለሌላ ሰው ታሻግራላችሁ ነው፡፡
     ሶሰተኛ፤ በዚህ ዘገባ እንደተረዳነው፤ ምንም እንኳን ሌሎች ጤነኛ ቢመሰሉ ወይም በቀላሉ በሽታውን ቢወጡ፣ ይህ ቫይረስ ወደሚገለው ሰው መድረሱ አይቀርም፡፡ በዚህ በአንድ ሰው ምክንያት፣ ተገድቦ ካልተያዘ በስተቀር ሶስት ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፣ ሌሎችም ሊጨመሩ ይችላሉ፡፡ ዋናው ሰውዬ ምን አይነት ስሜት ሊሰማው አንደሚችል እግዚአብሔር ነው የሚያወቀው፡፡ 
      አራተኛ፤ ርቀት ጠብቁ ለሚለው ምክር ይህ መረጃ ማረጋገጫ ነው፡፡ ሰውየው በሀዘኑም በደስታውም ጊዜ ሰው ማቀፍ ይወዳል፡፡ ምናልባትም ራቅ ያሉት ይሆናሉ ከመያዝ ያመለጡት
      አምስተኛ፡ ሰው ሲታመም፣ ገለል በል የሚባለው ለሌላ የቤተሰብ አባል እንዳያስተላልፍ ነው፡፡ የታመመውን የሚረዱ ሰዎችም በቂ ጥንቃቄ ማድረግ የሚኖርባቸው ለዚህ ነው፡፡ መከላከያ መልበስ፣ እጅ መታጠብ፡፡ የታመመው ሰው ከክፍሉ ሲወጣ አፍና አፍንጫውን በማስክ መሸፈን አንዱ ትልቁ ነገር ነው፡፡
      ስድሰተኛ፡ ይህ ነገር ገለል እሰከሚል ድረስ፣ ክርስትና ይሁን፣ ልደት፣ ሀዘንም ቢሆን ከቤተሰብ አባላት ውጭ የሚያገናኝ ነገር ከማዘጋጀት መቆጠብ ነው፡፡ የቤተሰብ አባል ሲባል፣ በቤት ውስጥ አብሮ የሚኖረውን ለማለት አንጂ፣ ከቤቱ ውጭ የሚኖሩ ወንደም ሆነ እህት እንደ ሌላ ሰው ነው የሚቆጠሩት፡፡ ነገሩ ከባድ ይመስላል፣ ምክሩ ግን አትገናኙ ነው፡፡ እናንተም ወደ ሰው ቤት አትሂዱ፣ ሰውም ወደቤታችሁ አይምጣ ማለት ነው፡፡
      ከዚህ በኋላ፣ አስር ሰው ነው፣ የለም ስድሰት ሰው ነው የሚባለው ቁጥር እንደማያዋጣ መገንዘብ ነው፡፡ ከዚህ ላይ የምጨምረው ነገር፡፡ የበሽታ ስሜት ያላቸው ሰዎች፣ ለሌሎች ቢያዝኑና ራሳቸው በየቤታቸው ሰብሰብ እንዲሉ የመመፃን ያህል ነው የምጠይቀው፡፡ እዚህ ላይ ግን ለቫይረሱ መሠራጨት ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረጉ ያሉት፣ የበሽታ ስሜት የሌለባቸው ግን በቫይረሱ ተይዘው ቫይሱን የሚስተላልፈ ሰዎች መኖራቸው የተረጋገጠ ሰለሆነ፣ ከዚህ ሁሉ ሰብሰብ ማለቱ ነው የሚያዋጣው፡፡

በህዝብ በኩል የሚደረጉ መከላከያዎች የኮቪድ-19 ሥርጭትን ማቀዝቀዛቸውን የሚገልፅ ጥናት 4/23/2020

ይህ ፅሁፍ፣ የኮቪድ-19 ሥርጭትን ይገታሉ ወይም ይቀንሳሉ የሚባሉ የመከላከያ ተግባራትን ውጤት በጥናት መልክ ያቀረበ ነው፡፡ የተሠሩ ሥራዎችን ውጤት መገመት ቢቻልም፣ በርግጠኛነት መናገር የሚቻለው ግን፣ እንደዚህ በጥናት ወጥቶ በአሃዝ ተደግፎ ሲቀርብ ነው፡፡

ይህንን በሚመለከት፣ የአሜሪካ የህክምና መፅሄት አንዱ ከሆነው JAMA (Journal of Medical Association) በአፕሪል ዕትሙ ጥናት አውጥቷል፡፡

የኮቪድ-19 ሥርጭት በቻይና በውሃን ከተማ ነው የጀመረው የሚለውን ዘገባ ብዙዎቻችን ተቀብለነዋል፡፡ በዚህ ከተማ ሲጀምርም፣ ዘግይተዋል ይባል እንጂ፣ ቻይኖቹ የወሰዷቸው ርምጃዎች ነበሩ፡፡ ከነዚህ ርምጃዎች በኋላ፣ ሥርጭቱ በጣምና እንደዘገባው ከሆነ አንደምሳሌ ሊጠቀስ የሚገባው አቀናነስ ነው የታየው፡፡ ታዲያ የጥናቱ ጥያቄ፣ ውነት እነዚህ የተወሰዱ ርምጃዎች፣ ሥርጭቱን ከመቀነሱ ጋር ግንኙነት አላቸው ነው ወይ፡፡

ይህን ጥያቄ ለመመለስ፣ አጥኝዎቹ፣ በኮቪድ-19 መያዛቸው በላቦራቶሪ የተረጋገጠ የ32 583 ሰዎችን ዝርዝር መረጃ ተመለከቱ፡፡ ጥናቱ ያተኮረው ከታህሳስ 8 አስከ መጋቢት 8 ድረስ በነበረው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ የነዚህ ሰዎች መረጃ፣ ከከተማው የተለላፊ በሽታዎች ሪፖርተ ተሰበሰበ፡፡ መረጃው፣ የልደት ቀን፣ዕድሜን፣ ፆታን፣ መኖሪያ አካባቢን፣ የሥራ ቦታን ያካተተ ሲሆን፣ የበሽታውን ጥናት በደረጃ መከፋፈልንም ይጨምራል፡፡ የበሽታው ሰሜት መጀመሪያ የተሰማበትን ቀንና፣ በላቦራቶሪ የተረጋገጠበትን ቀንም ይጨምራል፡፡

የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት በህዝብ ደረጃ የተወሰዱ ርምጃዎች ደግሞ፡ አካባቢን በማገድ ሰው እንዳይወጣ እንዳይገባ ማድረግ፣ የትራፊክ ዕገዳ፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር በርቀት መሆን፣ በቤት ውስጥ ብቻ ተወስኖ መቀመጥ፣ ከዚያ በተጨማሪ ደገም፣ ማዕከላዊ የሆነ የመገለያ ቦታ ማስገባት፣ እንዲሁም አጠቃላይ የሆኑ በበሽታው ስሜት የተመረኮዘ አሰሳ ማድረግ ነበሩ፡፡

የታዩ ውጤቶችና የተወሰዱት ርምጃዎች፡ የሥርጭቱን ጊዜ፣ ማለትም ከታህሳስ 8 አስከ መጋቢት 8 ያለውን በአምስት ወቅቶች እንዲከፈሉ ተደረገ፡፡ በነዚህ ወቅቶች፣ በኮቪድ መያዛቸው በላቦራቶሪ የተረጋገጠ ሰዎች በአሃዝ ለማስቀመጥ፣ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በቀን በአንድ ሚሊዩን ህዝብ እንዲሰላ ከተደረገ በኋላ፣ ይህ ስሌት በዕድሜ፣ በፆታ፣ በሠፈር ወይም የመኖሪያ ቦታን በመጨመር አንድ ላይ እንዲሰላ ተደረገ፡፡

አንግዲህ በነዚህ በአምስት ወቅቶች የነበረውን ሁኔታ አንመልከት

ከታህሳስ 8 እሰከ ጥር 9 ባለው ጊዜ ውስጥ ምንም አይነት ከላይ የተገለጡን በህዝብ ደረጃ የሚደረጉ የመከላከያ ርምጃዎች አልተወሰዱም፡፡ ይህ ወቅት የመጀመሪያው ወቅት የተባለ ሲሆን፣ የቻይኖቹን አዲስ አመት ለማክበር ብዛት ያለው የህዝብ አንቅስቃሴም ነበር

ከጥር 10 እሰከ ጥር 22 ባለው ጊዜ፣ የቻይኖቹን አዲስ አመት ለማክበር የህዝብ እንቅስቃሴ በገፍ ነበር የታየው፡፡ በዚህ ሁለተኛው ወቅት በሚባለው ጊዜ፣ ያን ያህል የህዝብ እንቅስቃሴ በመካሄዱ የኮቪድ-19 ሥርጭትን እንደሚያፋጥነው ይጠበቅ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ጠንከር ያለ በህዝብ ደረጃ የተደረገ መከላከያ አልነበረም፡፡ በዚህ ጊዜ፣ የመጀመሪያው ከሰው ወደ ሰው መተላለፉ ከተነገረ በኋላና፣ የጤና ባለሙያተኞች በበሽታው መያዛቸው ከታወቀ በኋላ፣ ሆሰፒታሎች፣ ትኩሳትና የመተንፈሻ አካለት ህመም ሰሜት ባላቸው ሰዎች መጨናነቅ ጀመሩ፡፡

ከጥር 23 አስከ የካቲት 1 ባለው ጊዜ፣ አካባቢን ከልሎ መዝጋት፣ በቤት ውስጥ ገለል ብሎ መቆየት፣ እና የትራፊክ እገዳ ተደረገ፡፡ በዚህ በሶሰተኛው ወቅት፣ ከውሀን ከተማ የሚወጣ ማኘውም ትራንስፖርተ እንዲዘጋ ተደረገ፤ ከዛ ቀጥሎም የህዝብ መመላለሻ አገልግሎት ታገደ፣ ተከትሎም በከተማው ውስጥ ምንም አይነት የትራንስፖረት እንቅስቀሴ እንዳየደረግ ተወሰነ፡፡ በዚህ ጊዜ፣ በሰዎች መሀል መራራቅ፣ ከቤት ውጨ ወይም ሰዎች ባሉበት አካባቢ ማስክ መልበስ ማስገደድና፣ ማንኛውም የሰዎች መገናኛ የሆኑ ቦታዎች ወይም ሁኔታዎች አንዲሰረዙ ተደረገ፡፡ በቻይናም ቢሆን፣ በዚህ ወቅት፣ የህክምና ቁሶች ከፍተኛ ዕጥረት ስለነበር፣ ብዙ የታመሙ ሰዎች በቤታቸው ሆነው እንዲገለሉ ተደረገ፡፡

ከየካቲት 2 አስከ የካቲት 16 ባለው ጊዜ፣ ማዕከላዊ ማግለያ ቦታና ህክምና ተካሄደ፡፡ የህክምና መገልገያዎች ዕጥረት ሰለተስተካከለ፣ አጠቃለይ የማግለያ (ኳራንቲን) ቦታ ተዘጋጅቶ፣ የህመም ስሜት ያላቸው ሰዎች ህክምና እንዲያገኙ ተደረገ፡፡ በዚህ ጊዜም፣ ለሁሉም የከተማው ኗሪዎች በየቤታቸው እንዲቀመጡ የሚል ፖሊሲ ተግባራዊ ተደረ፡፡

ከየካቲት 16 አስከተ መጋቢት 8 ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ፣ አጠቃላይ የሆኑ የኮቪድ-19 የበሽታ ስሜቶችን የተመረኮዘ አሰሳ ተደረገ፡፡ በዚህ ወቅት፣ መንግሥት፣ ለሁሉም ነዋሪዎች፣ ከቤት ወደ ቤት በመዘዋወር፣ ግለሰቦችን የበሽታው ስሜት ያላቸው ወይም የሌላቸው መሆኑን የሚዘግብ አሰሳ ተደረገ፡፡ ለዚህ አንግዲህ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ዕገዛም ነበረበት፡፡

ከዚህ ጋርም፣ የሳርስ ኮሮና ቫይረስ-2 የመባዛት መጠን ከላይ በታዩት ወቅቶች ውስጥ እንዲሰላ ተደረገ፡፡ ይህ የቫይረሱ የመራባት መጠን የሚጠቁመው፣ በሌሎች ተጋልጠው በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ መልሰው ለሌሎች ማዛማታቸውን ነው፡፡

 ከላይ የተጠቀሱት ዕገዳዎች መሥራታቸውን አለመሥራታቸውን መለኪያ ያደረጉበት ስሌት፣ በቀን፣ በአንድ ሚሊዮን ሰዎች መሀል፣ ምን ያህል በበሽታው መያዙ የተረጋገጠ ሰው ተገኘ ለሚለው ቁጥር፣ በፆጻ፣ በዕደሜ፣ በሥራ ቦታ፣ ጤና ባለሙያተኞችን ጨምሮ፣ በሚኖሩበት አካባቢ እንዲመዘን ተደረገ፡፡

ይህ ስሌተ በጀርባው፣ ቀናትን፣ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር፣ በአካባቢው ያለውን ህዝብ ቁጥር ያካተተ ነው፡፡ ሰለሱ ብዙም ሳንነጋገር፣ ወደ አሃዞቹ አንግባ፡፡ ለእንደዚህ አይነት ጥናት መግለጫነት በሳይንስ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ስሌት ነው ብለን እንቀበለው፡፡ አለዚያ አይታተምም ነበር፡፡

 ብዙ ዝርዝር መረጃዎች ቢኖሩበትም፣ ለዚህ ፅሁፍ እንዲተኮርበት የተፈለገው፣ የሥርጭቱን ግራፍ ነው፡፡

አብዛኛው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር የተከሰተው ከጥር 20 አስከ የካቲት 6 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያሰመዘገበውም በየካቲት 1 ነበር፡፡ ሥርጭቱ ከመሀል ከተማ ተነስቶ ወደ ዳር ዳር ቦታዎች አንደሄደም፣ በዳር ቦታዎችና በመሀል ከተማ የሥርጭት መጠን ልዩነት ያለው ሲሆን፣ የመሀል ከተማው በብዛት በበሽታው የታያዙ ሰዎች የታዩበት ክፍል ነው፡፡ በየቀኑ የሚታየው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥረ በእያንዳንዱ ሚሊዮን ሰዎች ሲሰላ፣ ከጥር 10 በፊት 2.0 የነበረው ቁጥር፣ በቀጥታ ወደ 162.6 ከፍ ያለው ከጥር 23 እስከ የካቲት 1 ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ መቀነስ ጀመረ፡፡ ከየካቲት 2 አስከ የካቲት 16 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ 77.9 ወረደ፣ ከየካቲት 16 በኋላ ደግሞ ወደ 17.2 ወረደ፡፡

ጥናቱ፣ የዚህን ስሌት ቁጥር አወራረድ በተለያየ ገፅታዎች ተመልክቷል፡፡ ዝርዝሩን ማስፈርም አልተፈለገም፡፡ ዋነው መልክት ግልፅ ነው፡፡ ቻይኖቹ ያንን የሚያህል ህዝብ ባለበት ከተማ የወሰዱት ርምጃ፣ ምን ያህል ሥርጭቱን እንደገታው መመልከት ይቻላል፡፡ ይህንነ በማድረጋቸው፣ ወደ መላው ቻይና ሥርጭቱን መግታት ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ውጭ ሊወጣ የሚችለውን የሥርጭት መጠን በ80ፐርስን ቀንሰውታል ይላል ከሌላ በኩል የተገኘው መረጃ፡፡ ሥርጭቱን መቀነስ ብቻ ሳይሆን የቀናት ፋታ እንዲኖርም እድረገዋል፡፡

ያንን ያህል የመከላከያ ተግባር በተለያየ መንገድ ፖሊሲ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በተግባር መፈፀሙ፣ አቅም የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ፣ መንግሥት አለም አላለም፣ ከዚህ መማር የሚቻለውን ወስዶ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ከላይ ከጠቀሱት ተግባራት፣ ህዝቡ በራሱ ማድረግ የሚችለው፣ በየቤተ መከለልን፣ ማህብረሰባዊ ርቀትን መጠበቅ ይገኙበታል፡፡

ማስታውስ ያለብን ቫይረሱን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚወስደው ራሱ ሰው ነው፡፡ ሰለዚህ የሰው እንቅስቃሴ መገታት የቫይረሱን በፍጥነት መዛመት ያሳንሰዋል፡፡

ሌለው ትምህርት ደግሞ፣ ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች መሀል በቀን በበሸታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በጣም ዝቅተኛ በነበረበት ጊዜ፣ ቁጥሩ 2.0 ነው፣ ድንገት ወደ ላይ አንዲነሳ ያደረገው፣ ቁጥር ስፍር የሌለው ሰው፣ የቻይኖቹን አዲስ አመት ለማክበር በዚያው በውሀን ሲርመሰመስ ሰለነበረ ነው፡፡

በኢትዮጵያ እንግዲህ በየቀኑ በመጠኑ ዝቅተኛ የሆነ ሰው ቁጥር በበሽታው ሊያዝ ይችል ይሆናል፡፡ ይህንን ቁጥር ግን ልክ በቻይኖቹ እንደታየው ወደ ላይ ከፍ ሊያደርገውና ስፋት ያለው ሥርጭት እንዲከተል ሊያደረጉት የሚችሉተ ድርጊቶች ሰዎች በአንድ ላይ በብዛት መገናኘት ነው፡፡ የአምልኮ ወይም የፀሎት ቤቶች በዚህ ይካተታሉ፡፡

ሰለዚህ፣ እያንዳንዱ ግለሠብ ወደ ነዚህ ቦታዎች በመሄድ ስብሰቡን ሲያደምቅ በዛው ልክ ደግሞ የበሽታውን ሥርጭት ሊያፋፍም ወይም ሊያደምቅ አንደሚችል መገንዘብ አለበት፡፡

በየቀኑ የምንከታተለው የአለም አቀፍ ሥርጭት የሚያስተምረን ነገር አለ፡፡ አሱም፣ ቫይረሱ አንድ ሀገር ወይም አካባቢ ሲዛመት፣ ሌላ ቦታ አለ ወይስ የለም በሚባልበት ደረጃ ፀጥ ያለ ይመስልና፣ እነዚህ ፀጥ ያሉ የሚመስሉ አገሮች ሥርጭቱ እየጨመረ እየሰፋ ሲሄድባቸው ይታያል፡፡ ፀጥታ የሚመስለው ነገር፣ ብዙ ጊዜ፣ ለበሽታው ከሚደረገው ምርመራ ጋር መያያዙ ግልፅ ነው፡፡ ሌላ ተጨማሪ ነገር ቢኖር፣ የበሽታውን ምልክት የማሳዩ ግን በቫይረሱ የተያዙና ቫይሱን ወደ ሌላው የሚያስተላለፉ ሰዎች ነው፡፡ ካልታመሙ በሸታው መኖሩ አይታወቅም፡፡ ነገር ግን፣ እንደልቡ የሚሆንበት ሰፈርና ሰዎች ቤት ውስጥ ሲገባ ነው፡፡ የቻይኖቹ የውሃን ሁኔታ የሚያሳየን፣ ከመሀል ከተማ ወደ ዳር ዳር መውጣቱን ነው፡፡ ከተሜዎች ልብ ቢሉ ምናለበት፡፡

እንግዲህ አያድርስ ነው፣ ሌሎች በአፍሪካ ሊደርስ ይቻላል ብለው የሚተነብዩትን ነገር መስማት ባንፈልግም፣ ማስተዋልና ለሚደረገው ዝግጀት አስፈላጊውን ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ እነሱ አንደሚሉት፣ አሁን በአፈሪካ የሚታየው በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር፣ ማዕበል ከመምጣቱ በፊት ቀደም ብለው እንደሚታዩት የዝናብ ጠብታዎቸ ነው፡፡ባይሆን መልካም ነበር፡፡ እንግዲህ የበሽታውን ሥርጭት ለማቀዝቀዘ የሠራውነ ነገር አንድ ላይ ተመልከተናል፡፡ ይህ መልክት፣ ለግለሰቦች፣ በአስተዳደር ሥራ ላይ ላሉ፣ ለፖሊሲ አውጭዎችም ጭምር ነው፡፡

በዚህ ገፅ የሚገኙ ርዕሶች


  • በሠርግ ዕለት ያልተጠራው ተጋባዥ ኮቪድ-19 ሠርገኞችን … 5/25/20202
  • ከሌሊት ወፍ አምጥቶ ኮሮና ቫይረስ ቁጥር ሁለትን ወደ ሰዎች አሻገረ የሚባለው ተጠርጣሪው እንስሳ ይህ ሳይሆን አይቀርም
  • በዋሽንግተን ዲሲ በኮሮና በመያዝ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው ሰው የቤተክርስቲያን ቄስ ነው
  • አሳዛኝ ዜና፣ በኮቪድ-19 ምክንያት የመጀመሪያው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ህይወት ማለፍ  (3/30/20)
  • ከኮሮና እንድናለን ብለው ያልተፈቀደ መድሐኒት የወሰዱ  ባልየው ሲሞት ባለቤቱ በጠና ታማለች፡፡
  • በቀብርና በልደት በአል የተገኘ አንድ ሰው ብቻ ኮሮና አሠራጭቶ ያሰከተለው ችግር 4/11/20 
  • በህዝብ በኩል የሚደረጉ መከላከያዎች የኮቪድ-19 ሥርጭትን ማቀዝቀዛቸውን የሚገልፅ ጥናት 4/23/2020
  • አጠገባችሁ ያለ ሰው በሳርስ ኮሮና ቫይረስ-2 መያዙን ማወቅ ከቻላችሁ…. 4/6/2020


ከኮሮና እንድናለን ብለው ያልተፈቀደ መድሐኒት የወሰዱ
 ባልየው ሲሞት ባለቤቱ በጠና ታማለች፡፡


ይህ መልክት ለሁሉም ነው፡፡ ከዚህ ቀድም በተለያዬ ሜድያዎችም ሆነ በጎሽ ድረ ገፅ ለማሰተማርም ለማንሰጠንቀቅ ተሞክሯል፡፡ ይህ ይሠራል ወይም አይሠራም የሚለው ነገር፣ ከጀርባው በመረጃ የተደገፈ መሆን አለበት፡፡
    በዛሬው ዕለት ሜድያው እየተቀባበለ ያቀረበው አሳዛኝ ክስተት አለ፡፡ ለኮሮና ቫይረስ ከሚሞከሩ መድሓኒቶች አንዱ የዎባ መድሐኒት ክሎሮኪን የሚባል ነው፡፡(chloroquine phosphate)፡፡ ይህ መድሀኒት ለኮሮና ህክምና ጥናት ላይ ነው፡፡ ፍቱህ መሆኑም አልታወቀም፡፡ የሙያ ባልደረቦቻችን በየሆስፒታሉ የሚያደርጉትን ጥረት ብትመለከቱ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ይህ ነው የሚባል መድሐኒት አስካሁን አልተገኘም፡፡ የመድሐኒቶቹን ዝርዝር በጎሽ ድረ ገፅ አሰቀምጫለሁ፡፡ ጎብኙ አንብቡ፡፡
    ወደ ዜናው ስንምለስ የአሜሪካው መራሄ መንግሥት፣ የዚህን መድሐኒት ስም እየጠሩ ልክ እንደተረጋገጠ የሚሠራ ነገር አድርገው ሲገልፁ የተመለከቱ የአሪዞና ነዋሪ የሆኑ ባልና ሚሰት፤ የመድሐኒቱን ስም፣ የአሳ ገንዳ ማፅጀው ኮምፓውንድ ላይ ተፅፎ ያዩታል፡፡ የአሳ ማፅጃው ውስጥ የሚገኙ ተባዮችን ነው የሚገለው፡፡
     ባልየው ምን ብሏል፣ ይሕ ኮምፓውን በቴሊቪዢን የሚያወሩት አየደለም እንዴ፡፡ ታዲይ ሁለቱም ብድግ ያደርጉና ከጨማቂ ጋር ደባልቀው መጠጣት፡፡ በ30 ደቂቃዎች ውስጥ ሁለቱም በጠና ታመው ሆሰፒታል ይገባሉ፤ ባልየው ይሞታል፣ ሴትዮዋ በጠና አንደታመመች ነው፡፡
        ብዙ መማር አለብን፡ ኮምፓውንዱ ተመሳሳይ ቢሆንም የጉልበት መጠኑ ይለያያል፡፡ ለሰው የሚሰጠው የጉልበት መጠን ለአሳ ገንዳ ማፅጃው መጠን ጋር የሰማይና ምድር ነው፡፡ሁለተኛ ለኮሮና ፍቱንነቱም አልተረጋገጠም፡፡
        እንግዲህ ባራኪና ለማፅጃነት ያገለግላል ብየ ስፅፍ፣ ለማጽዳት እንኳን መጠኑ ተበርዞ ወደ አንድ አምስተኛ መውረድ አለበት፡፡
      አንደኛ ለኮሮና የሚሞከሩ መድሐኒቶች ኮምፓውንዶች የታወቁ አሉ፣ ከዚህ በፊት የጠቀስኩላችሁ ሎፒናቪር ሪቶናቪር የሚባል ለኤች አይ ቪ ህክምና የምንጠቀመበት መድሐኒት ለኮሮና አይሠራም ተብሎ ከምርምሩ ገለል ተደርጓል፡፡
         ሰለዚህ ሰዎች፣ ተስፋ በመቁረጥም ይሁን፣ ባለማወቅ፣ ወይም ከሰው የበለጡ መስሏቸው የማይታወቅ ነገር ወስደው ለአደጋ እንዳይጋለጡ ለመምከር ነው የምጥረው፡፡ በበአሁኑ ሰአት፣ የህክምና ሙያ ቀርቶ ሰለ ህክምና አንዳች ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች የሚፅፉትነ አታንብቡ፣ ሼርም አታደርጉ፡ ሼር ያደረጋችሁት ነገር፣ ያልታሰበ ሰው ላይ ደርሶ ተግባራዊ ሊሆንና አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ አንድ ነገር ብቻ ወይም አንድ በሽተኛ ብቻ አየተው ሰለ ሁኔታው በሶሻል ሜድያ የሚለጥፉ ባለሙያ የሚመስሉ ሰዎችም አሉ ከነሱም ተጠንቀቁ፡፡
       አንድ የተሠራጨ ነገር ቢኖር፣ ቫይረሱ በጨጓራ አሲድ ይሞታል ነው፡፡ ጎሽ ላይ ይህንን በሚመለከት በአጥኝ ሀኪሞች የተፃፈውን ተመልከቱ፡፡ በሠገራ ይገኛል በሚል፡፡ እንዲያውም አሜሪካ ውስጥ እየታየ ያለው፣ በዛ ያሉ ሰዎች ተቅማጥ እንደለባቸው ነው፡፡ ምነው አሲዱ በገደለው፡፡
        ሰለዚህ ሰለኮሮና የምታገኙትን ዜና ምንጭ አረጋግጡ፡፡ አታራቡት፡፡ ለዝናና ለገቢ ሲባል፣ ሰዎች ምን ያህል አሳዛኝ ነገር እንደሚፅፉ መረዳት አለባችሁ፡፡ ባለፈው ሰሞን፣ ድፍን የአሜሪካ የኤይድስ ህሙም ግማሹ ኢትዮጵያው ነው ብለው እየተቀባበሉ ሲያናፍሱ አይተናል፡፡ አግባብ ያለው የሰከነ ምላሽ ሠጥተናል፡፡ በዘህ ጉዳይ፣ ባለሙያ ባልሆን ደፍሬ አልፅፍም ለመምከርም አልሞክርም ነበር፡፡ ግን ሁሉም ነገር፣ እንደ ፖለቲካ ማንም እንደፈለገ እየተናገረና እየፃፈ የሚያስክትለውን አደጋ እያየሁ ዝም ማለትም አልችልም፡፡ ሰዎች ሰከኑ በሉ፣ ይህ ነገር በሽታ ነው፡፡ እየተደማመጥን የሚቻለንን እናድርግ፡፡ በዚህ ወቅት ትልቁ ግብ፣ አለመያዝና ከተያዙም አለመሠራጨት ነው፡፡ ሆስፒታል ውስጥ የሚደረገው ግብግብ እያወጣን ብንነግራችሁ፣ የሚመች አይደለም፡፡ ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ነው፡፡ ለዛውም እኮ እኛም ራሳችን አደጋ ላይ እየወደቅን ነው፡፡
      የዛሬ ስንት አመት፣ አንድ የወንድሜ ልጅ ካሊፎርንያ እንደመጣ የማያደርገው ነገር አልነበረም፡፡ ታዲያ የክፍል ደባሉ የሆነ ልጅ ሲመክረው፤ “አንተ ልጅ የማታወቀውን መርዝ ውጠህ እንዳትሞት” ብሎ ነበር፡፡ ያ አባባል አሁንም ትዝ ይለኛል፡፡ ተመርምሮ ተጠንቶ በሰው ልክ ይሆናል ተብሎ የሚሠራ መድሐኒት እንኳን ሰው ላይ ዳርቻ ጉዳት(side effect) ያስከትል ይሆን ብለን በምንጨነቅበት አለም፣ ያገኘውን መውሰድ ተገቢ አይደለም፡፡
      አንዲየው ኮሮኖ በሜዲያ ሰለተነገረ፣ የመንግሥት ባለሥልጣኖችም እናውቃለን እያሉ እንደሌላ ጉደይ ለመሸፋፈን የሞከሩት ነገር ያስከተለውን ጣጣ ተመልከቱ፡፡ 

አሳዛኝ ዜና፣ በኮቪድ-19 ምክንያት የመጀመሪያው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ህይወት ማለፍ  (3/30/20)
       
            ወሳኝ መልክት ሰላለው ባካችሁ አካፍሉ 
በተለይም በዲሲ፣ ቨርጂኒያና፣ ሜሪላንድ አካባቢ የምትኖሩ

የ57 አመት ጎልማሳ የነበረ ሰው በዚህ በኮቭድ-19 ምክንያት ሕይወቱ ያለፈ መሆኑን ጓደኞቹና ቤተዘመዶቹ አስታወቃል፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ኑዋሪ የነበረው ትውልደ ኢትዮጵያዊን ሞት አስመልከቶ፣ ከቤተሰቦቹ በኩል ዜናው እንዲነገርና ለሌሎች ማስገንዘቢያ እንዲሆን ፈቃድ መሠጠቱ ምስጋና የሚያሰጥ ነገር፡፡ ያም ሲሆን ማንነታቸው በተጠበቀ መልክ እንዲቆይም አሳስበዋል፡፡ ከሁሉም በፊት በሰውየው ህይወት ማለፍ ሀዘን የተሰማን መሆኑን እየገለጠን፣ ለቤተሰቦቹም ብርታቱንና መፅናናቱን ፈጣሪ እንዲሰጣቸው እንመኛለን፡፡

ተጨማሪ ሁኔታ ደግሞ፣ ባለቤቱና ልጁም በዚሁ በኮቪድ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡ እነሱንም ከበሽታው እንዲያገግሙ በፀሎት እንርዳቸው፡፡ ሕይወቱ ያለፈው ይህ ኢትዮጵያዊ፣ ከአውፕላን ማረፊያ መንገደኞችን የሚያመላለስ የታክሲ ሥራ ላይ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ይህን አጋጣሚ በመጠቀም፣ ተጨማሪ ምክሮች መሥጠት የግድ ነው፡፡ በመሠረቱ እንዲዚህ ያልተለመደ አዲስ ተላላፊ በሽታ ቀርቶ፣ ሌሎች ብዛት ያላቸው በሽታዎች፣ በአንድ ሰው ላይ በሚገኙ ጊዜ፣ ሀኪሙ ለአካባቢው መንግሠት ወዲያውኑ እንዲያስታውቅ የሚያስገድድ ህግ አለ፡፡ ሰለዚህ ሀኪሞች ሪፖረት ያደርጋሉ፡፡ ከቆዩት በሽታዎች አንዱ የሳንባ ነቀርሳ ነው፡፡ ሌለችም የአባለ ዘር በሽታዎች ሲከሰቱ፣ ሪፓርት እንዲደረጉ ህጉ ያስገድዳል፡፡ ሪፓርት ከተደረገ በኋላ፣ በሽታው የተገኘበት ሰው የሚኖርበት መንግሠት የጤና ቢሮ ክፍል፣ በሽታው የተገኘበትን ሰው በመጠያቅ፣ የንክኪ ምርመራ ይጀምራል፡፡ በአንግሊዝኛ (Contact Investigation) ይባላል፡፡ ሰለዚህ የመንግሥት ሠራተኞች በር ቢያንኳኩ እንዳይገርማችሁ፡፡ ህግ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሀኪሞች የበሽተኛን ስም ሆነ ሌላ መረጃ አሳልፈው አይሰጡም፡፡ የሚሰጡ ከሆነ ከበሸተኛው ፈቃድ ተቀብለው ያውም በፊርማ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ፣ ለበሽተኛው ተከታይ ህክምና ወይም የስፔሻሊሰት ምክር ሲያስፈልግ ግን ሰለ በሸተኛው ያለው መረጃ ምክር ለተጠየቀው ይነገራል፡፡

ይህን የምጠቅሰው፣ በቅርቡ ሕይወቱ ያለፈው ወንድማችን በቫየረሱ መያዙ እንደታወቀ፣ የሚኖርበት አካባቢ መንግሥት፣ የንክኪ ምርመራ አድርጓል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን፣ በአሁን ጊዜ በጤናው መስክ ያሉ ሥራዎች ሰለተወጣጠሩ፣ ይህ ባይደረግስ ብየም አሰብኩ፡፡ አንግዲህ ልብ ማለት ያለብን፣ ሰውየው ከነማን ጋር፣ በምን መልክ ለምን ያህል ጊዜ፣ በምን ያህል ቅርበት ግንኙነት አድርጓል ተብሎ ይጠየቃል፡፡ በተለይም የህመም ስሜት ከጀመረው ጊዜ ጀምሮ፡፡ ይህ ሲደረግ ከሰውየው ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች ይታወቁና እያንዳንዳቸው ራሳቸውን እንዲያገሉና ሰውነታቸውን እንዲያዳምጡ ይደረጋል፡፡ ይህ የሚደረገው፣ የተጋለጡት ሰዎች ድንገት ተይዘው ከሆነ እነሱም በተራቸው ወደ ሌላ ሰው እንዳያስተላለፍ ለመግታት ነው፡፡ እንደሰማነው፣ ባለቤቱና ልጁ በዚህ ቫይረስ መያዛቸው ግልፅ ተደርጓል፡፡ ይህ ሌሎች በዚህ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ያሉ የጤና በላሙያኞችን ለመርዳት፣ በቡድን ከሚንቀሳቀሱ የህከምና ባለሙያዎች በኩል የተገለጠ ነው፡፡ የንክኪ ምርመራው ደግሞ፣ ሰውየው ከማን ተገናኘ ተብሎ ሲመረመር እርሱ ራሱም ከማን እንዳገኘው ለማወቅ ጥረት ይደረጋል ማለት ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚደረገው በሸታው በስፋት ከመሠራጨቱ በፊት የተጋለጡ ሰዎችን በማግለል ወደሌሎች እንዳይዘመት ለመከላከል ነው፡፡

ከዚህ ጋር አያይዞ፣ ከሰውየው ጋር በተለይም የህመም ስሜት እየተሰማው አያለ በቅርበት ከሱ ጋር ጊዜ ያሳለፋችሁ የቅርብ ጓደኞችና የቤተሰብ አባለት፣ የመንግሥት ምክር ሳትጠብቁ፣ ራሳችሁነ በማግለል ሥርጭቱን ለመግታት ሞክሩ፡፡ አዚህ አካባቢ በሚኖሩ ኢትዮጵያውን፣ ከሟቹ ቤተሰቦች በተጨማሪ ሌሎች የተያዘሁ መሆናቸው የታወቀ ሶሰት ሰዎች መኖራቸውን እኔ ራሴ የማውቀው ጉዳይ ነው፡፡ በኛ አኗኗር ሁኔታ፣ ምክርን ቸል የማለት ባህሪ፣ ቫይረሱ በፍጥነት በመሠራጨት ብዛት ያለቸው የህብረተሰቡን አባላት ሊይዝ እንደሚችል መታወቅ አለበት፡፡ ራሳችሁ ከሰውየው ጋር ግንኙነት ባይኖራችሁ፣ ሌሎች ከሱ ጋር ተገናኝተው ሊሆኑ ይችላሉ ለምትሏቸው ሰዎች ይህንን ምክር አካፍሉ፡፡

አንግዲህ ጥርጣሬው ያላቸው ሰዎች፣ መጀመሪያ የሚያደርጉት ነገር ራስን ማግለል (self-quarantine)ነው፡፡ ያም ለአስራ ቀናት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ከቤት አካበቢ ተውስነው በመቀመጥ ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚያደርጉትን ግንኙት ማቆም አለባቸው፡፡ ወደ ቤታቸውም ሌላ እንግዳ እንዳይመጣ መከልከል አለባቸው፡፡

ራሳቸውን አግልለው በሚቆዩበት ጊዜ፣ በአንድ ክፍል ይወሰናሉ ማለት አይደለም፡፡ ራሳቸውን አዳምጡ ሲባል፣ በቀን ሁለት ጊዜ የትኩሳት መጠን መለካት፡፡ ሳል መከሰቱን ማወቅ፣ ራስ ምታትም እየታዬ ነው፣ የጉሮሮ መቁሰልም እይታየ ነው፡፡ ባጠቃለይ ከነበራቸው ሁኔታ ለየት ያለ ነገር ሲከሰት፣ ምልክት እንደጀመራቸው በመገንዘብ፣ ከዚህ በኋላ ራስን ከማግለል ራስን (self-isolation) መለየት ይጀምራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ግን፣ በአንድ ክፍል በመወሰን፣ ከሌሎች የቤተሰብ አባላት ጋር በማይገናኙበት ሁኔታ ነው፡፡ የህምም ስሜቱ ጠንከር በማለት፣ ትንፋሽ የማጠር ስሜት፣ ትንፋሽ መፈጠን ሲጀምር፣ ስልክ ደውለው ሰለ ሁኔታው በመግለፅ ወደ ህክምና ቦታ እንዲሄዱ ይመከራል፡፡

ሆስፒታል በማያደርስ ደረጃ ቤት ከቆዩ፣ ምልክት ከጀመራቸው ከሰባት ቀን በኋላ፣ ትኩሳቱም ምንም የትኩሳት ማብረጃ መድሐኒት ሳይወሰዱ በራሱ ከወረደ ከ72 ሰዓታት በኋላ፣ ከማግለያ ይወጣሉ፡፡ ይህ በወቅቱ ያለ አሠራር ነው ወደ ፊት ግን ሊለወጥ ይችላል፡፡ በተለይም ምርመራው ለሁሉም የሚደርስ ከሆነ፣ ከአፍና ከአፍንጫ በሚወሰድ ምርመራ ቫይረሱ አለመኖሩ ሁለት ምርመራዎቸ በ24 ሰኣት ልዩነት ከተደረጉ በኋላ ከተረጋገጠ፤ አገግመዋል ከቫይሱም ነፃ ሆነዋል ሰለሚባል ከመለያ ክፍላቸው መውጣት ይችላሉ ማለት ነው፡፡

በዋሽንግተን ዲሲ በኮሮና በመያዝ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው ሰው የቤተክርስቲያን ቄስ ነው

ቄሱ ለሁለት ጊዜ አገልግሎት የሠጠ ሲሆን፣ እንደ ቤተክርስቲያኑ ሥርአት ምዕመናኑን ማቁረብና እጃውን እንደጨበጠ የታወቃል፡፡

በዚህ የቄሱ በኮረና መያዝ ከታወቀ በኋላ፣ ይህ 550 ምዕመናን አባላት ያሉበት ቤተ ክርስቲያን፣ በሁለቱ ቀናት ወደ ቤተክርስቲያኑ የሄዱና የተጋለጡ ሰዎች በሙሉ በቤታቸው ገለል ብለው ለአስራ አራት ቀናት እንዲቆዩ ተነግሯቸዋል፡፡ ይህንን ጉዳይ፣ የዋሽንግተን ከተማ ከንቲባ በይፋ ለህዝብ አሰምተዋል፡፡

እሰካሁን ድረስ፣ ከዚህ ቤተ ክርስቲያን ጋር በተያያዘ ሶሰት ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ መሆናቸው በላቧራቶሪ ተረጋግጧል፡፡ የሚገርመው፣ የታወቁት ሰዎች፣ አንደኛው ከሜሪላንደ፣ ሌላኛው ከቨርጂኒያ የመጡ ናቸው፡፡ በሜሪላንድ በኩል የታወቀው ከናይጄሪያ የመጣ ሰው መሆኑን ተገልጧል፡፡ ከሶሰቱ አንደኛው የቤተክርስቲያኑ ኪይ ቦርደ ተጫዋች ነው፡፡

በዋሽንግተን ከተማ በቫይረሱ ለመያዙ በመታወቅ የመጀመሪያው ይህ ቄስ በህክምና ላይ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ መረጃ በተለያዩ ታማኝ በሆኑ ታላላቅ የዜና አውታሮችም ተደጋግሞ የተገለጠ ነው፡፡ ይህ ሪፓርት ለህዝብ ይፋ የሆነው በማርች 9፣ 2020 (እኤአ) ነው፡፡  

ከሌሊት ወፍ አምጥቶ ኮሮና ቫይረስ ቁጥር ሁለትን ወደ ሰዎች አሻገረ የሚባለው ተጠርጣሪው እንስሳ ይህ ሳይሆን አይቀርም

 ከዚህ ቀደም ሰለ ሳርስ ኮሮና ቫይሶች ሲገለጥ፣ ሶስቱም አደገኛ የሆኑት የኮሮና ቫይሶች መነሻቸው የሌሊት ወፍ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆኖም፣ ከሌሊት ወፍ ተነስቶ በቀጥታ ወደ ሰው እይሻገሩም፡፡ ያ ማለት አሻጋሪ ሌላ እንሰሳ ያስፈልጋቸዋል፡፡

በ2002-2003 የተነሳው የሳርስ ኮሮና ቫይረስ አሻጋሪ እንሰሳ ሲቬክ ድመት የሚባል እንሰሳ መሆኑ ከታወቀ ቆይቷል፡፡ ከሳውዲ ተነስቷል የሚባለው፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ኮሮና ቫይረስ በምህፃር ሜርስ ኮሮና የሚባለው፣ አሻጋሪ እንሰሳው ግመል መሆኑ ታወቋል

ይህ፣ በታህሳስ ድንገት ብቅ ብሎ አለምን እያስጨነቀ ያለው ሳርስ ኮሮና ቫይረስ ቁጥር ሁለት፣ በዝርያው ከሌሎቹ ቀደም ካሉት ጋር የሚመሳሰል ቢሆንና ከሌሊት ወፍ መነሳቱ ቢገለጥም፣ እንዴት ብሎ ወደ ሰው እንደደረሰ ከመላ ምት በላይ ብዙም የሚታወቅ ነገር አልነበረም፡፡ ቻይናም ቢሆን በዚህ በኩል፣ ፈታ ብላ የገለጠቸው ነገር የለም፡፡ ለነገሩ፣ በሽታው የተከሰበት በውሃን ከተማ፣ የአሳና የሌሎች የጫካና የቤት እንስሳት የሚሸጡበት ገበያ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በቅርብ ጊዜ ሹልክ ብሎ የወጣ ጥናት የሚጠቁመው፣ ፀሀፊዎቹ፣ ከላይ በምስሉ የምታዩት ፓንጎሊን የሚባል እንሰሳ ነው የሚል ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

ለምን ግን ይህ እንስሳ ሊሆን ይችላል? ማለትም ምን ያህል ከሰዎች ጋር ግንኙነት አለው ለሚለው መልሱ ቀላል ነው፡፡ ይህ ዕንስሳ በጣም የሚፈለግና በብዛት በተለያየ መልክ ለገበያ የሚቀርብ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሰውነቱ እንደምታዩት ቅርፊት በመሰሉ ብዛት ባለቸው ጠጠር ወይም ጠንከር ባሉ መደረቢያዎች የተሸፈነ ነው፡፡ ለካስ፣ እነዚህ ቅርፊቶች ናቸው፣ ይህንን እንስሳ ተፈላጊነቱን የጨመሩት፡፡ ቅርፊቶቹ ከምግብነት በላይ ለመድሐኒትነት ያገለግላሉ ሰለሚባል ይህንን እንሰሳ ፈላጊና አዳኙ እንዲበዛበት አድርጓታል፡፡ እንግዲህ ከዚህ በላይ ከሰው ጋር ንክኪ የት አለ፡፡

በጥያቄና መልስ ጊዜ ከአንባቢ ወይም ከአዳማጭ አንድ ሰው፣ ሰለ ኮሮና ቫይረሶች ተጨማሪ መግለጫ ይሰጠን ብሎ መጠየቁን ሰለተመለከትኩ፣ እነሆ ስለ ኮሮና ቫይረሶች

በመጀመሪያ ኮሮና የሚለው ስም የመጣው፣ (ኮሮና ማለት ዘውድ ማለት ነው)፣ ቫይረሱን በኤሌክትሮኒክ ማይክሮስኮፕ ሲመለከቱት የዘውድ ቅርፅ ስላለው ነው፡፡ ከዘውድ ጋር የተያያዘ ስም ያላችሁ ሰዎች ይቅርታ፣ ትንሽ ለመቆጠብም አስቤ ነበር፡፡

የኮሮና ቫይረሶች በጣም ስፋት ያለው የቫይረስ ቤተሰብ አባላት ናቸው፡፡
ባላቸው የዘር ስንስለት ልዩነት ምክንያት ከአራት ምድብ ይከፈላሉ፡

አልፋ ኮሮና ቫይረስ
ቤታ ኮሮና ቫይረስ
ጋማ ኮሮና ቫይረስ
ዴልታ ኮሮና ቫይረስ

የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ፣ አልፋና ቤታ ኮረና ቫይረስ የሰውና የእንስሳት ሲሆኑ
ተከታዮቹ ጋማና ዴልታ የአእዋፍ ቫይረሶች ናቸው፡፡

በዝርያ በተጨማሪ መከፋፈል ከተፈለገ፣ የቤታ ኮሮና ቫይረሶች አንደገና በአራት ይከፈላሉ፡፡ ኤ፣ ቢ፣ ሲ፣ ዲ፡፡

አሁን የምናተኩረው የሰው ኮሮና ቫይረሶች በሆኑት በአልፋና በቤታ ቫይረሶች ነው፡፡

እሰካሁን ድረስ፣ የሰው ኮሮና ቫይረስ ተብለው የሚጠቀሱ ወይም የሚታወቁ ሰባት ኮሮና ቫይረሶች አሉ፣ አዲሱን ጉልበተኛ ጨምሮ ነው፡፡

ቀደም ብለው የተነሱ አብረውን ተላምደው ቀለል ያለ በሸታ፣ ጉንፋን የሚያሰከትሉት አራቱ፣ ከሁለቱም ወገን ይመጣሉ ማለትም ከአልፋና ከቤታ ቫይረስ ወገን፡፡ እነዚህ ቫይረሶች ቀደም ብለው የሚታወቁ ሲሆን፣ ከነዚህ አንደኛው ገና በ1960፣ ጉንፋን ከያዘው ሰው አፍንጫ ተገኝቶ ማንነቱ ከታወቀ ሰንብቷል፡፡ ግምቱ ምንድነው፣ እነዚህ፣ አራቱ ቀለል ያለ ጉንፋን ብቻ እያሰከተሉ ከሰው ጋር አብረው ቢኖሩም፣ ከመጀመሪያ ሲነሱ ሌሎች ከነሱ ጋር የመጡ ቫይረሶች ገዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እና ይህን አባባል ሰፋ ብናደርገው፡፡ ገዳይ ቫይረሶች ከነበሩ ለምን አሁን የሉም ብሎ አንድ ሰው መጠየቅም ይችላል፡፡ መላ ምቱ ምንድን ነው፣ በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎቸ ከነቫይረሱ አብረው ሰለጠፉ ነው፣ እነዚህ በአንፃራዊ አነጋገር ለማዳ የሆኑት አራቱ፣ ተራ ጉንፋን የሚያስይዙት የቀሩት፡፡ (የዳርዊንን ነገር ካስታወሳችሁ)፡፡ እንግዲህ ገዳይና ሟች አብሮ ሰለጠፋ፣ የቀረው ህዝብ ደግሞ ከዛ የተረፈ በመሆኑ፣ የቀረው ቫይረስም ደግሞ እንደ አጥፍቶ አጥፊ አብሮ በመጥፋቱ የቀሩትን አራቱን ቫይረሶ ይዘን ኖረናል፡፡

ያ ግን እሰከ አውሮፓ አቆጣጠር 2002-03 ድረስ ነበር፡፡ ምን ብቅ አለ? የመጀመሪያው ሳርስ ኮሮና ቫይረስ፡፡ ይህ ቫይረስ እራሱ መነሻው ከቻይና ጉዋንዶግ ከሚባል ፕሮቪንስ ነው፡፡ (2002)፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ አለምን አናውጦ፣ ወደ 8ሺ ሰዎች መያዛቸው የተረጋገጠ፣ ካዳረስ በኋላ፣ (10%) አስር ፐረስንቱን ገድሎ፣ ጥፍት አለ፡፡ ለሱ የተዘጋጀው ክትባትም ጥቅም ላይ ሳይውል ቀረ፡፡ እኔ ራሴ አስታውሳለሁ፣ በዚያ ጊዜ የተላላፊ በሽታዎች ስብሰባ በሙሉ በአብዛኛው ሰለ ሳርስ ነበር፡፡ ለእንደኔ አይነቱ ባለሙያተኛ ገና የሳርስ ስም ሲጠቀስ ብዙ የምናስታውሰው ነገር አለ፡፡ ይህ ቀዳማዊ ሳርስ በዝርያው ከቤታ ኮሮና ቫይረሶች ነው የሚመደበው፡፡

ሁሉም ሰላም መሰለ፣ ዝም ዝም ተባለና፣ ከአስር አመት በኋላ በ2012 ደግሞ ሌላ ኮሮና ቫይረስ ከሳውዲ በኩል ብቅ አለ፡፡ ይሀ ቫይረስ የሚያስከትለው በሸታ ለየትም አለ፡፡ ሁሉም ቫይረሶች ዋና የበሸታ ማዕከል ያደረጉት የመተንፈሻ አካለትን ሲሆን፣ ይህ ግን ዘሎ ኩላሊት ላይ ጉብ በማለት የኩላሊት ድክመት ወይም ውድቀት ያስከትላል፡፡ አስከፊነቱም የታየው፣ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች፣ ከሶስቱ አንዱን በመግደል ነው (34 ፐረስንት)፡፡ ይህ ቫይረስ የሚድል ኢስት ኮሮና ቫይረስ ተብሎ ይታወቃል፡፡ ሜርስ ኮሮና፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ መሽጎ፣ አንዳንዴ በመንገደኛ ምክንያት ሾለክ እያለ አውሮፓም ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ በ2015 በደቡብ ኮርያ በኩል ብቅ ብሎ 186 ሰዎችን መያዙ ይታወቃል፡፡ እስከ የካቲት 2020 ድረስ፣ ባጠቃላይ፣ 2500 መያዛቸው በላቦራቶሪ የተረጋገጠ ሰዎች ይታወቃሉ፣ ከነዚህ መሀል 34.4 ፐርስነቱ በበሸታው ምክንያት ህይወታቸው አልፏል፡፡ ለዚህ ነው ይህ ቫይረስ በነብሰ ገዳይነተ ቀዳሚውን ደረጃ የሚይዘው፣ ከኮሮና ማለት ነው፡፡ ይህ ቫይረስም ከቤታ ኮሮና ቫይረሶች ወገን ነው፡፡ ይህ ቫይረስ ያነሰው ነገር ቢኖር፣ ከሰው ወደ ሰው እንደልቡ ወይም በበቂ መንገድ አለመተላለፉ ነው፡፡ እንዳው በዛው ይቅር ሳትሉ አትቀሩም፡፡ ለሱም፣ አሜን ነው መልሱ፡፡ ይህ በጠመንጃና በገንዘብ አቅም ራሱን ከፍ ከፍ ያደረገ አለም፣ በኮቪድ ሲንበረከክ ስላየን፣ ያኛውን እዛው በቤቱ ያስቀረው ማለት የግድ ነው፡፡

ከቤታ ወገኖች፣ ሶሰተኘው ቫይረስ ደግሞ ይህ አዲሱ ጎረምሳ ነው፡፡ እንደ አዲስነቱ ያስመዘገበው ልዩ ባህሪ ምንድነው ቢባል፣ ከሰው ወደ ሰው በፍጥነትና በቀላሉ መሸጋገር መቻሉ ነው፡፡ የሚገለውም ሰው ቁጥር እንደ ዘመዶቹ ከፍ ያለ ባይመስልም፣ መግደል ከፈለገ፣ በአሜሪካ የነርሲነግ ሆምስ (አሮጊትና ሽማግሌዎች መጦርያና የህክምና ርዳታ መስጫ ማዕከል) ሲገባ የሚያደርሰው ጉደት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ አስካሁን ድረስ በአሜሪካ በጠቅላላ በኮቪድ ምክንያት ከሞቱ ሰዎች ሀያ ፐርሰንቱ ከነርሲነግ ሆም ነው፡፡ ይህ ግን በአሜሪካ ብቻ አይደለም፣ በአውሮፓ፣ በኮቪድ ምክንያት ከሚሞቱ ሰዎች ግማሹ ከነዚህ ነርሲንግ ሆም ካሉ ሰዎች መሆኑን የአለም ጤና ድርጅት ገልጧል፡፡ አዲስ እንደመሆኑ ሁሉም ሰው በዚህ ቫይረስ የመያዝ ዕድል አለው፡ አነሰ ቢባል፣ ዕድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑት ላይ መጠኑ አነስተኛ ነው፡፡ እንደዛ ሆኖ ይዘልቅ ይሆን የሚታወቅ ነገር አይደለም፡፡ ዕድሜያቸው ከ19-44 አመት የሆኑት፣ “አይነካንም” ብለው የሚያስቡ በጣም ተሳሰተዋል፡፡ በአሜሪካ ዳታ እንዳየነው፣ በቫይረሱ ከሚያዙ ሰዎች አንድ ሶሰተኛውን የሚይዙት እነሱ ናቸው፡፡ ሰለዚህ ሥርጭቱ እንዳይሰፋ ማድረግ የሚገባቸውን ነገር ቢያደርጉ መልካም ነው፡፡ ይህ ቫይረስ አፍሪካ፣ ከገባ ምን አይነት ባህሪ እንደሚያሳይ የሚያውቅ የለም፡፡ አፍረካ፣ በኤች አይ ቪ፣ በሳንባ ነቀርሳ ብዛት የሚታወቅ ከፍተኛ ቁጥር እንዳለ ግልፅ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ቢያዙ ምን እንደሚያሳዩ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ሰለዚህ ለራስም፣ ለህብረተሰብም፣ ለደጋጎቹም በማሰብ፣ ወጣቱና ጎልማሳው ቢጠነቀቅ መልካም ነው፡፡

ለማጠቃለል፣ አንደዚህ አይነት የቫይረስ ወረረሽኝ ሲነሳ፣ ቫይረሱን ብቻ ነጥሎ ማየትም ጥሩ አይሆንም፡፡ የአካባቢ አየር ለውጥ፣ የሰው ባህሪ እራሱ (ማለትም በምስሉ አንደተጠቀሰው አይነት አንስሳና ሌሎችም አሻጋሪ ሊሆኑ ከሚችሉ አንስሳት ጋር የሚደረገው ግንኙነት ሊታሰብበት ይገባል)፡፡ በአለም በአንድ ጠርዝ በኩል የሚደረግ ነገርና የሚያሰከትለው ውጤት በሌላው አለም ጫፍ መድረሱን ተመልከተናል፡፡

ኮሮና ቫይረስ የሚያሰተምረን አንድ ትልቅ ነገር ነገር ቢኖር፣ የሰው ልጅ አንድ ዘር፣ ቫይረስ ሌላ ዘር መሆኑን ነው፡፡ በሌላ መንገድ፣ በትንሹም በትልቁም ሰውን የሚያክል ፍጡር መከፋፈሉን ቆም ብለን ማሰብ ይገባናል፡፡ ይኸው ጥቃት ሲመጣ፣ ቫይረስ የሰው ዘር ነው እያጠቃ ያለው፡፡ ይልቁንስ፣ አንድ ላይ እየተጋገዝን ወደ ዕደገቱ መራመድ፣ በተጨማሪም፣ መንግሥታቱ እንደ አንጀራ ልጅ የሚያዩትንና በቂ በጀት የማይመድቡለትን የጤናውን ዘርፍ ወይም መስክ ቅድሚያ እንዲሰጠው ማድረግ የግድ መሆኑ ታይቷል፡፡ የሲንጋፖር ሰዎች አንዳደረጉት፣ የምታወቋቸውንም ሆነ፣ የማታውቋቸውን የጤና ባለሙያተኞች ባገኛችሁበት አጋጣሚ አመስግኑ፡፡ የቀራቸው ነገር ቢኖር የህዝቡ ከበሬታ ነው፡፡

መልካም ንባብ


GOSH HEALTH


Community health 

education in Amharic