​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

በዚህ በኮሮና ምክንያት “አንድ መቶ ሺ ሰው ብቻ ከሞተ ጥሩ ሥራ ሠርተናል ማለት ነው”​      3/31/2020  
 
 ይህ አባባል የማን እንደሆነ ገምታችሁ ይሆናል፡፡ አዎ፣ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ናቸው እንዲህ ያሉት፡፡ አንድ ሰው ግን፣ ሰውየው እንደልባቸው የመጣላቸውን የሚናገሩ ቢሆንም፣ በዚህኛው ግን፣ ለምን እንዲህ አሉ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ቀደም በጎሽ ገፅና በተለያዩ የቃለ መጠየቅ ፕሮግራሞቸ፣ በቫይረሱ ሊያዙ ይችላሉ የሚባሉ ሰዎችን ቁጥር በኮምፒተር በታገዘ ስሌት አስቀድመው የሚናገሩ ሰዎች አንደነበሩ ለማስገንዘብ ሞክሬያለሁ፡፡ ያንን መድገም አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ለምን ሲባል፣ ሰዎች ያተኮሩት ወይም የሚያተኩሩት፣ በላቦራቶሪ ወይም በምርመራ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ላይ ብቻ በመሆኑና፣ ወደፊት የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ማድረግ የሚገባውን ነገር ሲያዘገዩ ሰለምናይ ነው፡፡ ትክክል አይደለም፡፡

 ለአንድ በቫይረሱ መያዙ በምርመራ ለተረጋገጠ ሰው በጀርባው ሌሎች ሰዎች አሉ፡፡ ተላላፊ ቫይረስ ዘሎ አንድ ሰው ብቻ አይዝም፡፡ እንግዲህ ገና ቫየረሱ ከቻይና ከመሻገሩ በፊት፣ ከወደ ኢንግላንድ የተነገረው የዚህ ስሌት የሚለው፡ ለእያንዳንዱ በምርመራ ለተረጋገጠ የኮቪድ-19 በሽተኛ ሌሎች በምርመራ ያልተገኙ ግን በቫይረሱ የተያዙ 3-4 ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ስሌት፣ አንድ በምርመራ ለተረጋገጠ ሰው፣ በአራት ማባዛት ነው፡፡ ወደ ኋላ ግን ሥርጭቱ እየጨመረ ሲሄድ ሌሎች ሰሌት ተጠቃሚዎች፣ የለም የለም፣ ነገሩ የሚሆነው፣ ለአንድ በምርመራ ለተረጋጠ ሰው፣ ሌሎች ያልታወቁ በቫይረሱ የተያዙ አስር ሰዎች አሉ ብለው ደመደሙ፡፡ በዚህ ስሌት፣ አንድ ሰው ተገኘበት ከተባለ ቁጥሩን በአስር ማባዛት ነው፡፡

ለዚህ ነው እንግዲህ የቫይረሱን የሥርጭት ባህሪ የሚያውቁ ባለሙያተኞች፣ ሥርጭቱን ለመግታት ርምጃዎች አስቀድመው ይወሰዱ የሚሉት፡፡ ሰሚ ያገኙ አይመስልም በአብዛኛው፡፡ ህብረተሰቡም ከቁብ የቆጠረው አይመስልም፡፡ አገር ቤትማ የባሰ ነው፡፡ የሚያሳዝነው፣ እዚህ አገር ያለው የኛው ህብረተሰብ ነገሩን በክብደት ያየው አልመሰለም፡፡ በቁጥር ከመጣ፣ በምርመራ በተረጋገጠ፣ በኔ ግምት፣ እዚህ አሜሪካ የሚኖሩ ጥውልደ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ተይዘዋል ተብሎ ከሚጠራው ቁጥር በላይ እንደሚሆን ነው፡፡ በተገኘበት እየተጠቃን መሆኑ ያሳዝናል፡፡ አሁንም የባሰ እንዳይፈጠር መንቃትና ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ 23 ሰዎች የተባለው ቁጥር በ23 የተወሰነ አይደለም፡፡ ሰሌቱን አስታወሱ ከሱ ጋር ደግሞ ስንት ሰዎች ምርምራ ተደርጎላቸዋል ብሎ መጠየቅ ነው፡፡ ለማሸበርም አይደለም፡፡

 አሁን በርዕሱ ወደ ተጠቀሰው አባባል እንመለስ፡፡ አንድ መቶ ሺ ሰው ቢሞት ምንም አይደለም አይነት ነው አባባሉ፡፡ ሌላ ጊዜ ቢሆን፣ ያንት ያለህ የሚያስብለው ይህ አባባል በዝምታ ነው የታለፈው፡፡ ግን ምክንያቱን ስንረዳ ደግሞ እንደ ሰውየው፣ መቶ ሺ ሰውን፣ እንደ ገንዘብ ስሌት ኪሳራ፣ ይሁንብኝ ብሎ ለመቀበል በዚያ መልክ ባንናገረም፣ ንግግሩ ሊኖረው የሚገባውን ክብደት ላንሠጠው እንችል ይሆናል፡፡

እንግዲህ ይህን አይነት ንግግር እንዲያፈልቁ ያደረገው ምክንያት የሚከተለው ነው፡፡ በቫይረሱ ስንት ሰዎች ተይዘው ይሆናል ለሚባለው የተጠቀሙበትን ስሌት፣ ወደ ስንት ሰዎች ይሞታሉ ወደ ሚለው ጥያቄ ስላዞሩት ነው፡፡ ስሌቱ በሁለት ነው የተከፈለው፡፡

አንደኛ፣ መደረግ የሚገባውን መከላከል ባይደረግ ምን ያህል ሰዎች ይሞታሉ?

ሁለተኛው ደግሞ፣ ማድረግ የሚቻለውን የመከላከያ ድረጊት ቢደረግ ከመጀመሪያው አነስ በማለት ስንት ሰዎች ይሞታሉ ተብሎ የስሌት ውጤት ሰለተነገረ ነው፡፡

ይሀንን የስሌት ውጤት ባለሥልጣናቱ ሲወያዩበት መሰንበታቸው የሚካድ አይደለም፡፡ ችግሩን ያባባሰው ደግሞ፣ የተለያዩ ድርጅቶች ይህን የስሌት ሥራ እየሠሩ የተለያዩ ቁጥሮች ይዘው ብቅ ማለታቸው ነው፡፡ የሠውየው ደጋፊዎች በተገኘው አጋጣሚ ቁጥሩን ተለቅ አድርጎ በተናገረው ድርጅት ላይ ወቀሳና ትችት ሲያስደርጉ ተስተውሏል፡፡ በዚህ የስሌት ውጤት ደጋግሞ የሚጠቀሰው፣ Imperial college ነው፡፡ ከሱ ቀጥሎ ደግሞ IHME የሚባል ቡድን ነው፡፡ የመጀሪያው ቡደን፣ በእንግሊዝ አገር የሚገኝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአሜሪካ ነው የሚገኘው፡፡ ከነዚህ በተጨማሪ፣ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎችና ተቋማት ይህንን የስሌት ትንበያ እየገለጡም ነበር፡፡

አሁን ወደሚያስፈራው ቁጥር እንመለስ፡፡ በህሊናችን ሌላ ቦታም እያሰብን እንደሆነ እረዳለሁ፡፡

ወደ መጀመሪያው ሁኔታ ስንመለስ፣ ምንም ነገር ባናደርግ በተለይም መራራቅ (social distancing) ባይደረግ፣ በአለማችን እሰከ 40 ሚሊዮን ሰዎች በዚህ ቫይረስ ይጠፋሉ የሚለውን የኮምፒተር ሞዴል ውጤት ተናገሩ፡፡ ይህ አነጋገር የሚያስነሳውን አቧራ መገመት አያዳግትም፡፡ በዚህ አገላለጥ፣ መንግሥታቱ ማድረግ የሚገባቸውን ባያደርጉ፣ ግለሰቦችና ህብረተሰቡ የሚገባቸውን ባያደርጉ፣ አርባ ሚሊዮን ሰዎች እንዳልነበሩ ይሆናል፡፡ ጥሪው ለማን እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ በተለይም በማመነታታት ላይ ላሉ መንግሥታት ነው፡፡ በርግጥ፣ ዋናውና ትልቁ ግብ ባቫይረሱ አለመያዝ ከሆነ፣ የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚገታው መንገድ በቀዳሚነት መደረግ የሚገባው ነገር ነው፡፡ ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ቁጥር በሎንደን በኢምፔሪያል ኮሌጅ በይፋ የታተመ ነገር ነው፡፡

ነገር ግን ይላሉ፣ ተገቢው ነገር ቢደረግ፣ የሰዎች እንቅስቃሴ በአዋጅ ቢገታና በከፍተኛ ደረጃ ምርመራዎች ቢካሄዱና የሰዎች እንቅስቃሴ መገታት ለረዥም ጊዜ ቢቆይ፣ እነዚህ አዳኝ ሊባሉ የሚገባቸው ተግባራት ወዲያውን ሥራ ላይ ቢውሉ፣ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በ በ38.7 ሚሊዮን ያንሳል፡፡ ማለትም ያን ያህል ሰው ማዳን ይቻላል ነው፡፡ እንዲሁም እነዚህ ተግባራት ዘግየት ብለው ቢጀመሩም እንኳን፣ የ30.7 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት ማዳን ይቻላል ይላሉ፡፡ በዚህ በይፋ በወጣ መግለጫ፣ ብዛት ያላቸው የጤና ጥበቃ ባለሙያተኞችና የተላላፊ በሽታ ስፔሺያሊስቶች ከጀርባው አሉበት፡፡

እዚህ ላይ ጣልቃ ልግባና፣ ምርመራ መደረጉ ከዚህ ጋር ምን ግንኙነት አለው? የሚል ጥያቄ መነሳትም ሰላለበት ምክንያቱን ልግለፅ፡፡ ምርመራው በስፋት ከተደረገ፣ ማን እንዳለበት ማን እንደሌለበት ከታወቀ፣ የተያዙ ሰዎችን በማግለል ወይም በመለየት ቫይረሱ እንደይዛመት ሰለሚረዳ ነው፡፡ በሥራ ቦታችንም ይህ እንዲሆን ነው የምንማፀነው፡፡ የጤና ባለሙያ በሥራው ምክንያት ተጋልጦ እንኳን ምርመራ ላይደረግለት የሚችል ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ሰለ አሜሪካ ነው የምናገረው፡፡

ቸግሩ፣ የመንግሥት መሪዎች የታያቸው የምጣኔ ሀብቱ ጉዳይ ሰለሆን፣ እነዚህ አዳኝ የሚባሉ ተግባራትን ማድረጉ አይታያቸውም፡፡ ሰለዚህ ለረዠም ጊዜ ሰዎች ባለህበት እርጋ ተብሎ እንቅስቃሴያቸው በህግ ታግዶ እንዲቆይ አይፈልጉም፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ IHME (Institute of Health Metrics Evaluation) የሚባል ድርጅት ድምፁን አጥፍቶ የራሱን ስሌት እያሰላ ነበር፡፡ በዚህም በአሜሪካ ምን ያህል ሰው ሊሞት ይችላል የሚለውን ጥያቄ ሲመልሱ፣ ተገቢው (social distancing) ቢደረግ፣ ከማርች 25 ጀምሮ ነው፣ በሚቀጥሉት አራት ወራት 81 ሺ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ይሞታሉ ብለው ይደመድማሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ተገቢ ርምጃ ነው ተብሎ የተወሰደው (social distancing) ለአራት ወራት ቢራዘም ነው፡፡ ከዛ በኋላ ቢቋረጥ ግን፣ የሞቱ ቁጥር አንደገና ሊያገረሽና ሊጨምር እንደሚችል ነው፡፡

ከነዚህ ከሁለቱ ሞዴሊንግ (ስሌት አድራጊዎች) ውጭ ሌላ ስሌት መካሄዱን የሚጠቅሱት የኮሮና ግብረ ሀይል አመራሮች ደግሞ፣ ቁጥሩን ወደ ኋላ ከገለጠው ከ IHME ወጤት ጋር ተመሳሳይ ነው ብለው በይፋ ተናገሩ፡፡ ይህ ገለልተኛ የተባለው ቡድን ባደረገው ስሌት፡ በነገራችን ላይ ስሌቱ በየቀኑ ይታደሳል፣ እናም በማርች 25 ባደረጉት ገለጣ፣ በአሜሪካ በየቀኑ ሁለት ሺ ሰዎች እንደሚሞቱ ነው፡፡ ያም እንግዲህ ሥርጨቱ በጣም ይገናል በሚባልበት ከአፕሪል ወር አጋማሽ ጀምሮ ባሉት ቀናት ነው፡፡ የዚህኛው ትንተና ከዚህ በፊት በቻይና፣ በኢጣልያና በአሜሪካ የሚገኙ መረጃዎችን ይጠቀማል፡፡

ዶክተር አንቶኒ ፋውቺ፣ የአገሪቱ፣ መሪ የተላላፊ በሸታዎች ስፔሻሊስት በዜና አውታር ቀርበው፣ ሊሞተው የሚችለው ሰው ቁጥር ከመቶ እሰከ ሁለት መቶ ሺ ይሆናል ብለው ተናገሩ፡፡ ዶ/ር ፋውቺ ይህን አሉ ማለት፣ ከባለሙያተኛው እሰከ ፓለቲከኛውና ሌላው ህዝብ ድረስ በአትኩሮት ሰሊሚደመጡ፣ እውነታውን እንደተናገሩት ሆኖ የሚቆጠረው፡፡ ይህ እንግዲህ ተገቢው ነገር፣ በተለይ እንቅሰቃሴ መገደብና በበቂ መጠን ምርመራ ቢካሄድ ነው፡፡ ያም ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ ከተደረገ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ወይም ካልተደረገ ግን፣ የተሰማው፣ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን በላይ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሰውየው በመግቢያው እንደተጠቀሰው፣ የምናደርገውን አድርገን መቶ ሺ ሰዎች ብቻ ቢሞቱብን፣ ጥሩ ሥራ ሰርተናል ማለት ነው ያሉት፡፡

በዚህ ስሌት ወይም ትንበያ ላይ፣ ኢኮኖሚው ይከፈት አይዘጋ የሚሉ የስቴት አስተዳዳሪዎች፣ ስሌቱን ወደማጣጣሉ ይሄዳሉ፡፡

በዚህ ላይ ዋናው ግፊት፣ መንግሥታቱ ህዝቡን አትንቀሳቀስ የሚል ህግ እንዲደነግጉ፣ ህጉም ለረዠም ጊዜ ተግባራዊ ሆኖ እንዲቆይ ነው፡፡ ከዚህ ጋርም ምርመራው በበቂ መጠን ተደርጎ የተያዘው ታውቆ ለየት ብሎ እንዲቀመጥ እንዲደረግ ነው፡፡

እንግዲህ ይህን ያህል የሰዎች ሞት በስሌቱ እየተገለጠ፣ አመራሮች ያለባቸውን ሥጋት በተለይም እንደ ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺና፣ የግብረ ሀይሉ መሪ የሆኑት ዶ/ር በርክስ እያመናቱ ያመኑት ነገር ነው፡፡ ይህ በአሜሪካ ነው፡፡

በሀገራችን በኢትዮጵያ፣ አንዱ ተግባር መቼም መደረግ የሚችልም አይመስልም፣ በበቂ መጠን ምርመራ መካሄዱ፡፡ ሰለ ኢትዮጵያ እንተንብይ ለማለትም አይደለም፤ ነገር ግን ሁኔታውን ወደ አንድ አቅጣጫ ሊገፉት የሚችሉትን ሁኔታዎች በመጠቆም፣ ሥጋትና ፍራቻውን እውን ሊያደርጉ የሚችሉ ሁኔታዎችን እንድናስብ ወይም እንድንገነዘብ ነው፡፡

እንግዲህ በበቂ መጠን ምርመራ ማደረግ ካልተቻለ፣ በቫይረሱ የተያዘው ሰው ካልተለየ፣ የቀረው አንድ አማራጭ ነው፡፡ በዚህ ላይ የህዝቡን አኗኗርና፣ ምክር ያለመስማትና ሁኔታው በአትኩሮት አለመቀበሉን ስንጨምር፣ ያ የቀረውን ብቸኛ አማራጭ አንደ አዳኝ አድርግን መወስድ ይኖረብናል፡፡ የግድም ነው፡፡ የቀረው አማራጭ ደግሞ፣ መንግሥት መውሰድ የሚገባው እርምጃ ነው፡፡ በአሜሪካ፣ ስቴቶች፣ የየራሳቸውን ርምጃ መውሰድ ጀምረው፣ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር በቤታችሁ ተቀመጡ ተብለናል፡፡ በርግጥ የጤና ባለሙያተኞችና ሌሎች አንዳንድ ባለሙያተኞች ከዚህ ህግ ነፃ ናቸው፡፡ የሚገርመው፣ ይህንን ህግ በደስታ ነው የተቀበልነው፤ እንዲያውም ለምን ዘገዩ ነው ያልነው፡፡

ይሀ ቫይረስ ከቦታ ወደ ቦታ የሚራመደው በተያዙ ሰዎች አማካኝነት ነው፡፡ የሰዎች እንቅስቃሴ ካልተገታ፣ ግልፅ ነው፤ ሁሉም ቦታ ይገባል፡፡ ከዚህ በፊት በሥርጭቱ ጥናት ላይ፣ በቻይና የታየው፣ ዋናው የመሠራጫ መንገድ ቤተሰብ ሆኖ የተገኘው፡፡ ይህ ማለት ወደ ቤተሰብ ሲገባ እንዳለ የቤተሰቡን አባለት በመያዝ የተያዦቹን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ነው የጨመረው፡፡ በቻይና ከ85 ፐርሰንት በላይ የተያዙት ሰዎች በቤታቸው ነው የተያዙት፡፡ አሁን ባለን አሠራር፣ በመጋለጥ ደረጃ ከመጣ፣ በቤተሰቡ አንድ ሰው ተይዟል ከተባለ፣ ቀሪዎቹ የቤተሰብ አባለት፣ ሊያዙ ይችላሉ የሚባለው በከፍተኛ ደረጃ ነው፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውንን አስቡ፡፡

ስለዚህ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ አማራጭ ወደ ሌለበት መንገድ መሄድ አለበት፡፡ ካስፈለገ በየከተማዎች አለበለዚያም አገር አቀፍ ተከተት የሚል ሕግ መደንገግ አለበት፡፡ ይህ ርምጃ ካሁኑ ካልተወሰደ ምን ያህል ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ የሚለው ነገር በቁጥር መግለፅ ባይቻልም መገመቱ አያዳግትም፡፡ ከዚህ ቀደም ገና ቫይረሱ አፍሪካ መግባቱ ሳይነገር የፈረንሳይ ተመራማሪዎች፣ ቫይረሱ አፍሪካ ከገባ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቁት በአንደኛ ደረጃ፣ ግብፅ፣ አልጀርያና ደቡብ አፍሪካ ነው ያሉት ውነት ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ በጎሽ ድረ ገፅ ይህንን ትንበያ አስቀምጠናል፡፡ ከነዚህ አገራት ቀጥሎ፣ ከገባ ከፍተኛ ችግር ይፈጠራል ብለው ያሰመሩት ኢትዮጵያንና ሌሎች የአካባቢ አገሮች ነው፡፡ እንግዲህ የግብፅን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርና የሞቱ ሰዎች ቁጥር ብናነፃፅር፣ እስከ ዛሬው እለት ደርስ፣ የሞት ቁጥር በፐርሰንት 6.25 ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ደግሞ፣ በአፍሪካ ውሥጥ በቫይረሱ መያዛቸው በተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር የመሪነቱን ደረጃ ይዛለች፡፡ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ግን በጣም አነስተኛ ነው፡፡ እሰከ ቅርብ ጊዜ ድረሰ ሪፖረትም አላደረጉም ነበር፣ ቆየት ብሎ የሚመጣውን ማዳመጥ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዕጣ የትኛው ይሆን?   ለሥርጭቱ ጥያቄ የለውም፣ አኗኗርና፣ ምክርን ከቁብ አለመቁጠር በራሱ ከፍተኛ ችግር ነው፡፡
እግዚአብሔር ሁላችንም ይጠብቀን

​​​​​እየጨመሩ የመጡት በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ሊኖሯቸው የሚችሉ የበሽታ ስሜትና ምልክቶች 5/30/2020

በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች የሚኖሯቸው የበሽታ ሰሜትና ምልክቶች እየጨመሩ ነው፡፡ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሁሉም አንድ አይነት ሁኔታ አይታይባቸውም፡፡ ማለትም በቀላሉ ከሚለቃቸው ጀምሮ በጠና የሚታመሙና ህይወታቸው የሚያልፍም ድረስ ነው፡፡

ሰሜቶች በቫይረሱ ከተጋለጡ ከ2-14 ቀናት ባሉት ጊዜ ውስጥ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ሁሉም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሰሜቶች አንድ ላይ ላይገኙ ይችላል፡፡

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ስሜቶች ያሉባቸው ሰዎች በኮቪድ-19 ተይዘውም ሊሆን ይችላል፡፡

ብርድ ብርድ ስሜትና ትኩሳት
ሳል
የትንፈሽ ሰሜት ማጠርና ለመተንፈስ መቸገር
የድካም ስሜት
የጡንቻና የሰውነት ህመም
ራስ ምታት
ድንገተኛ የማሽተትና የመቅመስ ችሎታ ማጣት
የጉሮሮ መቁሰል
አፍንጫ መታፈንና ንፍጥ መውረድ
ማቅለሽለሽና ማስታወክ
ተቅማጥ

 
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ይሁኑ እንጂ ሰዎች ሌሎች ተጨማሪ ስሜቶችና ምልክቶች ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ቫይረሱ የማየድርስበት የሰውነት ክፍል ሰለሌለ፣ በቆዳ፣ በአይንም በኩል የበሽታ ምልክት እያሳየ ነው፡፡ ስትሮክና የልብ ህመም ታይቷል፡፡ ልጆች ላይ የተከሰተው በኢንፍላሜሽን አማካኝነት የሚመጣው በሽታም ሌላ መገለጫ ነው፡፡


​​​​​የአዲሱ ኮሮና፣ COVID-19 በትንፋሸ አማካኝነት መተላለፉ ሳያንስ አሁን ደግሞ በአይነ ምድር  3/16/2020

ይህ ግኝት አዲስ ነው፡፡ Gasteroentrology በተባለ መፅሔት ታትሞ ይወጣል፣ ግን ቀድሞ የደረሰኝን ላካፍል ብዬ ነው፡፡ ሁላችንም ማወቅ የሚገባን ነገር ነው፡፡ በተለይም አገር ቤት፡፡

ኮሮና (COVID-2019) መተላለፊያ መንገዶቹ ተደጋግመው ተተልፀዋል፡፡ መድገሙ ሰለማይከፋ
አንደኛ፡ በሳልና በማስነጠስ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች የሚወጡት ለአይን የማይታዩ ጠብታዎች፣ ወደ ሌላ ሰው አፍ፣ አፍንጫ ሲዘልቁ፡፡ በነገራችን ላይ፣ ከዚህ በፊት በተደረገ ጥናት፣ ቫይረሱ በከፈተኛ መጠን የሚገኘው አፍንጫ ውስጥ ነው፡፡

ሁለተኛ፡፡ ሰዎች በሚያስሉበት ወይም በሚያስነጥሱበት ጊዜ፣ እነዚያ ቫይረሱን የተሸከሙ ጠብታዎች፣ ከሁለት ሜትር (ከስድሰት ጫማ) ርቀው አይሄዱም፡፡ ለዛ ነው ከስድስት ጫማ ወይም ሁለት ሜትር ርቀት ሁኑ የሚባለው፡፡ ነገር ግን ጠብታዎች ወደ ታቸ በመውረድ ያገኙት ቦታ ላይ ያርፋሉ፡፡ እንግዲህ ባለፈውም እንደጠቀስኩት፣ ቫይረሱ፣ ለዘጠኛ ቀናት ከሰውነት ውጭ ይቆያል ነው የሚባለው፡፡ ለምን ያህል ጊዜ መልሶ ሌላ ሰው የመያዝ ጉልበቱ ባይታወቅም፣ ቫይረሱ ያረፈበትን ቦታ በእጅ ከተነካ በኋላ፣ እጅ ሳይታጠቡ ወይም በአልኮል ሳይጠርጉ፣ አይንዎን፣ አፍንጫዎን፣ አፍዎን የሚነኩ ከሆነ፣ ቫይረሱን በቀጥታ ወደ ሰውነት ያስገባሉ፡፡ ለዚህ ነው፣ ታጠቡ፣ ታጠቡ፣ የሚለው ተደጋጋሚ መልክት የሚነገረው፡፡ መታጠብ ካልቻሉ፣ በ60ፐርስንት ወይም ከዛ በላይ በውስጡ አልኮል ባለው የእጅ መወልወያ፣ እጅዎን በደንብ፣ የመሻከር ስሜት እስኪሰማዎት ድረስ ይወልውሉ፡፡ ሳልዎን ይስብስቡ፣ እጅዎንም ይሰብስቡ፡፡

አሁን አዲሱ ነገር፣ ቫይረሱ በሌላ በየትኛው የሰውነት ክፍል ይራባል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በሠገራ እንደሚወጣ ተገልጧል፡፡ ግን በዚህ በሠገራ የታየው ቫይረስ፣ አቅም ያለው፣ ሰው መልሶ መያዝ ይችላል ወይ የሚል ጥያቄ ነበረን፡፡ የግድ መታወቅ አለበት፡፡

የቻይና ሀኪሞች፣ በዚህ በኩል፣ በየወቅቱ፣ ለሌሎች ስለቫይረሱ የሚያካፍሉት ጥናት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ አዲስ ቫይረስ ነው፣ አናውቀውም ገና፡፡

ለዚህ የቫይረሱ በሠገራ መገኘት፣ ከላይ በተጠቀሰው መሄት ሊወጣ የተባውን ጥናት ላካፍላችሁ፡፡

ከዛ በፊት ግን፣ ሰለ ቫይረሱ የትኛውን የሰውነት ክፍል ለምን እንደሚያጠቃ ልግለፅ፡፡ ቫይረሶች ወደ ሰው ሰውነት ሲዘልቁ፣ ለይተው የሚያጠቋቸው ሴሎች ወይም የሰውነት ክፍሎች አሉ፡፡ እንግዲህ ሴሎችም ሆነ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች፣ በላያቸው ላይ የሚያሳዩዋቸው ሞሎኪሎች ነገሮች አሉ፡፡ ይህ ቫይረስ የሚያጠቃቸው የሰውነት ክፍሎች፣ ወይም ሴሎች፣ በላያቸው ላይ ACE 2, የተባለ ሞሎኪል የሚያሳዩትን ነው፡፡ እንግዲህ የመተንፈሻ የአካል ክፍሎች፣ ሴሎች ይህን ACE 2 የተባለ ሞሎኪል ሰለሚያሳዩ በቀላሉ እንዚህ ሴሎች በማወቅ፣ ይህንን ሞሎኪል በመጠቀም ወደ ሴሎቹ ይገባል ማለት ነው፡፡ አንደመታወቂያ ካርድ ወይም ኮድ በሉት፡፡

ታዲያ ከሳንባና ከመተንፈሻ መሰመሮች ውጭ፣ ያንን ሞሎኪል በብዛት የያዙ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች አሉ፡፡ እነሱም ከጨጓራ ጀምሮ ፣ አንጀትን በመጨመር ነው፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ ይህ አዲሱ ቫይረስ፣ ከጨጓራ ጀምሮ አንጀትን በመውረር የሚከሰተው፡፡ አሁን ሚስጥሩ የገባችሁ ይመስለኛል፡፡ በኮረናው ቫይረስ የተያዙ ሰዎችም አንዳንዶቹ ትውከትና ተቅማት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡

ወደ ጥናቱ አንሄድ፤ ይህ ቫይረስ አዲስ አንደመሆኑ፣ ሀኪሞቹ፣ ምርምራ ሲያደርጉ፣ ከጉሮሮ፣ አፍንጫ ጀምሮ፣ ደም ምርመራ፣ ሠገራና ሽንት ምርመራም እያደረጉ ነው የከረሙት፡፡ ኢንዶሰኮፒ የሚባል ነገር ተጠቅመውም ጨጓራና አንጀትን ማየትና ናሙና መሰብሰብ ችለዋል፡፡

እንደተጠቀሰው በሠገራ ወይም በእይነ ምድር ቫይረሱ SARS-Co-V2 (ትክክለኛ መጠሪያው ነው) ሰለታየ፡፡ ተጨማሪ ምርምራ ለማድረግ በሆስፒታል እየታከሙ ያሉ ህሙማን ላይ በ71 በሠገራቸው ላይ የ SARS-Co-V2 ምርመራ ማድረግ ወሰኑ፡፡ በአንድ በሽተኛ ላይ ግን፣ ከጨጓራውና ከአንጀቱና ከፊንጢጣው፣ ናሙና ወሰዱ (በኢንዶሰኮፒ ውስጥ በመዝለቅ)፡፡ ከተወሰደው ናሙና፣ ቫይረሱ መኖሩን የሚያረጋግጡ ምርመራዎችም ተደረጉ፡፡

በዚህ ጥናት በአውሮፓ አቆጣጠር ከየካቲት 1-14፣ 2020፣ በ SARS-Co-V2 ተይዘው ሆስፒታል ሲረዱ ከነበሩት ከ73 ሰዎች መሀል፣ በ39 (25 ወንዶችና 14 ሴቶች) በሠገራቸው ላይ የSARS-Co-V2 ይገኝባቸዋል፡፡ እነዚህ በጥናቱ የተካተቱ ሰዎች፣ ዕድሜያቸው ከ10 ወራት እስከ 78 አመታት ድረስ ነው፡፡ ቫይረሱ በሠገራው የተገኘበት የጊዜ መጠን ከአንድ ቀን አስከ 12 ቀናት ድረስ ነበር፡፤ አሳሳቢው የሚከተለው ነው፡፡ ሰዎቹ በአፍና በአፍንጫ በኩል በሚደረገው ምርመራ ቫይረሱ አለመኖሩ ወይም መጥራቱ ቢረጋገጥም፣ በሠገራቸው ላይ ግን ቫይረሱ ይገኝ ወይም ይታያል፡፡ ያ በኢንዶስከፒ ምርምራ የተደረገለት ሰው፣ በሠገራው ብቻ ሳይሆን፣ ከጨጓራው፣ ከአንጀቱና ከፊንጢጣው በተደረገው የናሙና ምርመራ ቫይረሱ መኖሩን አረጋገጡ፡፡ አጥኘዎቹ የሚሉት በሠገራ የሚወጣው ቫይረስ፣ አቅም ያለው፣ መልሶ ሌላ ሰው መያዝ የሚችል ነው፡፡

ሀሳቡ ምንድን ነው‹ ጥንቃቄ ስናደረግ፣ ሁሉንም ነገር ማድረግ ሊኖርብን ነው፡፡ በሠገራ የሚወጡ ቫይረሶች ሆነ ባክቴሪያ፣ ባልተፀዳዳ ሰው አማከኝነት፣ ምግብና መጠጥ ከተነካካ፣ በሽታው ወደ ሌላ ሰው መዛመቱ ነው፡፡ እን ሄፓታይትሰ ኤ የመሰሉ ቫይረሶች በዚህ መንገድ እንደሚተላለፉ አናውቃለን፡፡ ከባክቴሪየ ደግሚ፣ ኮሌራ፣ ታይፎይደ ፊቨርን ጨምሮ ሌሎችም፡፡ ከጥገኛ ፓራሳይቶቸ፣ አሜባ፣ ጃርዲያ የመሳሰሉትም ይተላለፋሉ፡፡ ይህ አዲሱ ጎበዝም አንግዲህ ይኸው በሠገራ የመተላለፍ ችሎታውን አስመስክሯል፡፡

ይህ የሚያመጣው ነገር፣ አሁን ያለን አሠራር ላይ፣ የግድ ለውጥ ማድረግ ሊኖርብን ነው፡፡ ነገሩ፣ አንድ ሰው በ SARS-Co-V2 መያዙ ከተረጋገጠ በኋላ፣ ለአሥራ አራት ቀናት፣ ተገልሎ እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ ሰለታመመ አሁን quarantine ሳይሆን  isolation ነው፡፡ ታዲያ ከቫይረሱ ነጸ መሆኑን ለማረጋገጥ፣ አሁን ያለው ፕሮቶኮል፣ የሚመራው፣ ታማሚው፣ ከአስራ አራት ቀናት በኋላ፣ በ24 ሰኣታት ልየኑት፣ ሁለት ምርመራ አድርጎ በሁለቱም ምርመራ ቫይረሱ ካልተገኘ ነው ነጻ የሚሆነው፡፡ ምርመረው ደግሞ ከመተንፈሻ አካሎች በኩል ነው፡፡ ነገር ግን፣ በዚህ ጥናት አንዳያችሁት፣ በሽተኞቹ፣ በመተንፈሻ አካላቸው በኩል ቫይረሱ ቢጠራም፣ በሠገራቸው ዘግይት ብሎ መገኘት ቀጥሏል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ከ20% በላይ በሆኑ ሰዎች ታይቷል፡፡ ሰለዚህ አጥኝዎች የሚሉት ደግሞ፣ ሰውየው ጠርቷል ለማለት፣ የሠገራ ምርመራ ይጨመርበት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ግን፣ በተለይም በሆስፒታል የሚገኙ የዚህ ቫይረስ ህሙማን፣ ቫይረሱ እንዳይዛመት በሚደረገው ጥንቃቂ ሠገራ ውስጥ መገኘቱን በመገንዘብ፣ ጥንቃቄው ሰፋ እንዲል ነው፡፡

ወደ ሀገራችን ስንመለስ፣ ቸግሩን ራሳችሁ የምትገነዘቡት ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ነው፣ የንፁህ ውሀ አቅርቦትና፣ የመፃዳጃ ቤቶች መኖር፣ ከምንም ጊዜ በላይ ቅድሚያ ሊሠጣቸው የሚገባ ነገሮች የሚሆኑት፡፡ አሁንም፣ በተለይ አሁን በሚደረገው የቫይረሱን መዛመት ሊገድቡ ይችላሉ ተብለው ከሚወሰዱ እርምጃዎች ጋር አብሮ እንዲታሰብበት፡፡ ህዝቡ ቢሆን ይህንን ነገር የኔ ብሎ መተባበር አለበት፡፡ ንፅህና መጉደል ያንድ ሰው ችግር አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ፣ ነገሩ ያላቸው ሰዎች ቤት መድረሱ አይቀርም፡፡ የሚገርመው ነገር፣ ካስተዋላችሁ፣ ይህ አዲሱ ቫይረስ እያጠቃ ያለው፣ አላቸው የሚባሉ ሰዎችን ነው፡፡ ለምን ለሥራም ይሁን ለመዝናናት ከአገር አገር የሚዞሩትን ነው፡፡

ድሮ ድሮ፣ ተላላፊ በሽታዎች ይከበሩ ነበር፡፡ አሁን ግን ተረሥተው፣ እንደዚህ ብቅ ሲሉ አለምን ያሸብራሉ፡፡ ሰለዚህ ሳልና መፀዳዳትን የመሠሉ ነገሮች አንደ ባህል መያዝ አለባቸው፡፡ የከተማና ውበት መለኪያው የፎቅ ብዛት መሆን የለበትም፡፡ በነገራችን ላይ ያውሮፓ ውብ ከተሞች፣ በፕላን የተሠሩትና ግፊቱም የመጣው በተላላፊ በሸታዎች ምክንያት ነው፡፡ አውሮፓን ያልረገጠ ወረረሽን በሽታ አልነበረም፡፡ ያን ጊዜ፣ ሽንት ቤትም አያውቁም፣ በፖፖ በመሰኮት ሲደፉ ነበሩ፡፡ ትምህርት ወሰዱና አደጉ፡፡

ሌላው እንዲህ አይነት ወረረሽኝ ሲከሰት፣ ያንድን አካባቢ ግጥም አድርጎ መዝጋትና የዛ አካባቢ ሰው እንዳይወጣ ማገድ፣ አሁን ቻይኖቹ የተጠቀሙበት ዋነኛ ነገር ነው፡፡ ልብ በሉ አዲስ እንዳይመስላችሁ፡፡ የቀደምት የኛ ሰዎች፣ አንድ አካባቢ ተስቦ ከገባ፣ በር በሩን በመያዝ የዛ አካባቢ ሰው ከሌላ ጋር እንዳይደባለቅ እየጠበቁና እየከለከሉ ነው የተረፉት፡፡

በዐፄ ቴዎድሮስ ጊዜ፣ ቆራጣ የሚባል ቦታ ሠፍረው እያል፣ የኮሌራ ወረርሽኝ ገብቶ ብዙ ሰው ወታደር ፈጀ፡፡ ያን ጊዜ ኮሌራውን ነፍጠኛ ፈንግል ነበር የሚሉት፡፡ ታዲያ ንጉሡ ያደረጉት፣ የታመመውንና ያልታመመውን ለይተው በማስፈር፣ አንዱ ካንዱ እንዳይገናኝ አድርገው ነው ሠራዊታቸውን ያተረፉት፡፡

ይሀ አይነት ነገር ድንገት ቢደረግ፣ አትደንግጡ፣ ይልቁንስ፣ መንግሥት ከማድረጉ በፊት፣ ሁሉም ሰው በእንቅስቃሴው ቆጠብ ብሎ የቫይረሱን መዛመት በየአካባቢው ቢቀንስ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ለዚህ ነገር በተለይ ፈንጠር ያሉ ትንንሽ ከተሞች፣ በደንብ መቆጣጠር የሚችሉት ነገር፡፡ ለማንኛውም የአገሪቱ መሪዎች የሚሉትን ስሙ፡፡ ከቻይና ብዙ መማር ተችሏል፡፡ የአገሪቱን አቅም ማወቅም ጥሩ ነው፡፡ ኢጣልያ ካለቻለችው፣ ይኸው አሜሪካ ሽብር በሽብር ከሆኑ፣ ረጋ ብሎ ማሰብና መደረግ ያለበትን እንደህብረተሰብ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ መሸበር አያስፈልግም፣ መስገበገብም ጥሩ አይደለም፡፡ በደንብ ሰለ በሽታው ማወቅ፣ ማን በጣም ሊጎዳ እንደሚችል መገንዘብና መደረግ የሚገባውን ማድረግ ነው፡፡ በሁሉም የመጣ ነገር ነው፡፡ እውነት ለህዝብ የሚቆረቆር ድረጅት፣ አሁን ነው መታየት ያለበት፡፡
(ዋቢ)
Evidence for gastrointestinal infection of SARS-CoV-2
Fei Xiao, Meiwen Tang, Xiaobin Zheng, Ye Liu, Xiaofeng Li, Hong Shan



ስለ አዲሱ ኮሮና ቫይረስ(COVID-19) መድሐኒቶች   
03/13/2020 
 
እንደሚታየው አሁን ፓንደሚክ ደረጃ የደረሰው ይህ ቫይረሽ፣ እንደ ዘመዶቹ ሁሉ ለህክምና አስቸጋሪ ነው የሆነው፡፡ በወቅቱ የህክምና ባለሙያተኞችና ሌሎች ሳይንቲሰቶች፣ ለዚህ ቫይረስ መድሐኒት ለማግኝት የማይቆፍሩት ጉድጓድ የለም፡፡ እሰካሁን ምን ደረጃ ላይ እናም ምን አይነት መድሐኒቶች እየተሞከሩ እንደሆነ ልግለፅ፡፡ አትጨነቁ፣ የሕክምና ባለሙያም ሰለሆንኩ በመረጃ የተደገፈ ካልሆነ የማካፍላችሁ ነገር የለም፡፡ ከዚያ በፊት ግን፣ በሶሻል ሜዲያ መድሐኒት አግኝቻለሁ፣ ይህንን ጠጡ ይህንን ብሉ የሚሉ መልክቶች ሲዛመቱ ስላየን፣ ሰለነሱ አንድ ልበል፡፡

በመጀመሪያ፣ መድሐኒት ወሰደም አልወሰደም፣ በዚህ ቫይረስ የተጋለጠ ወይም የተያዘ ሰው፣ 80 በመቶው (80%) ቀለል ያለ ህመም ተስምቶት ያገግማል፡፡ እንግዲህ ይህ ሰው አንድ ጆንያ (የፈረደበት ነጭ ሽንኩርት)፣ በላ አልበላም፣ በተፍጥሮ ያለምንም ችግር ከህመም ስለሚገላገል፣ ሽንኩርት ነው፣ ወይም ቫይታሚን ሲ ነው ያዳነኝ ብሎ ለህዝብ መናገር ይከብዳል፡፡ ችግሩ ያለው በ20 ከመቶ በሚሆኑ ሰዎች፣ ማለትም በዕድሜ የገፉ፣ ከ 60 አመታት በላይ፣ ተደራቢ በሽታ ያለባቸው ሰዎች፣ እንደ ልብ ድካም፣ ሰኳር፣ ደም ግፊትና፣ የቆየ ሳምባ በሸታ ያለባቸው ሰዎች ላይ ነው፡፡ ከነዚህ ጋር የመከላከያ አቅማቸው የደከሙ ሰዎች፣ በካንሰር፣ በካንሰር ህክምና፣ ወይም ኤይድስ የመሳሰሉት ናቸው አደጋ ላይ ያሉት፡፡ በዕድሜ ከተነሳ፣ ከቻይና ሠፊ ጥናት መገንዘብ የቻልነው፣ ዕድሜያቸው ከ80 አመታት በላይ የሆኑ ሰዎች በጣም ከፍተኛ የሆነ ህመምና ህይወት ማለፍ ይታይባቸዋል፡፡ እንደ ጥናቱ ውጤት፣ እነዚህ በዕደሜ የገፉ ሰዎች፣ በቫይረሱ ከተያዙ ከአምስቱ አንዱ ህይወታቸው እንደሚያልፍ ነው፡፡ እንግዲህ መድሐኒት ሠራ የሚባለው እነዚህን ሰዎች ሲረዳ ነው፡፡
ይህንን የምግልፅበት ምክንያት፣ እንደዚህ ምንም ማረጋገጫ የሌላቸው በሶሻል ሜዲያ የሚለቀቁ ወሬዎች፣ እኛን፣ ማድረግ ከሚገባን ነገር እንዳያዘናጉን ነው፡፡ ዋናው ነገር፣ በቫይረሱ ላለመያዝ ጥረት ማድረግና እናም አንደ ሰብአዊነታችን ሌሎች እንዳይያዙ ማድረግ ነው፡፡
ወደ ሳይንሳዊ ጥናቶች ልመልሳችሁ፡፡

መድሐኒት ተሠራ ሲባል፣ ውጤቱ በብዙ ሰዎች ላይ ተሞክሮና ታይቶ ነው፣ ፍቱን ነው፣ ይሠራል የሚባለው፡፡ አንድ ግለሰብ ይህን አድርጌ ዳንኩኝ ካለ ሰለዚህ ነገር ዕወቀቱም የለውም ማለት ያስችላል፡
ለዚህ አዲሱ ኮሮና ቫይረስ እየተሞከሩ ያሉ መድሐኒቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ለኢቦላ ቫይረስ ህክምና ጥናት ላይ ያለ መድሐኒት እየተሞከረ ነው፡፡ ሰሙም remdesvir ይባላል፡፡ ይህንን መድሐኒት የሚያመርተው ኩባንያ፣ ወደ ቻይና መላኩ ይታወቃል፡፡ ይህ መድሐኒት በቫይረሱ ለተያዘ ሰው ሲሰጥ፣ አማራጭ በሌለበት ሁኔታ compassionate በሚባል ሰበብ ነው፡፡ ጥናቱ እየቀጠለ ነው፤ ውጤቱን አብረን እንጠብቅ
የዎባ መድሐኒት፣ የድሮው፣ ክሎሮኩዊን የሚባል እንዲሁ ጥናት ላይ ነው፡
ሎፒናቪር ሪቶናቪር የሚባል የኤችአይቪ መድሐኒት እየተሞከረ ነው
ከዚህ ቀድም ለሄፓታይትስ ቢና ሲ ህክምና የምንጠቀምበት፣ አልፋ ኢንተርፌሮን
ከመድሐኒቶች ውጭ፣ በቫይረሱ ተይዘው፣ ካገገሙ ወይም ከዳኑ ሰዎች፣ ከደማቸው ፕላዝማው ተወስዶ፣ ለሌሎች በመሥጠት ቫይሱን ለማጥቃት እየተሞከረ ነው፡፡ በአንድ መጠነኛ ጥናት፣ ተስፋ ያለው ነገር ነው ተብሏል፡፡ ይህ ወደ ተፈጥሮ ጠጋ ያለ ህክምና ነው፡፡ የሚሠራ ቢሆን ምኞቴ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ በቫይረሱ ተይዞ የዳነ ሰው፣ በራሱ መከላከያ፣ ሰውነቱ ባለው የተፈጥሮ አንቲቦዲ ነው ቫይረሱን ያፀዳው፣ እናም ያ አንቲቦዲ ሌላ ሰው ላይ የሚሠራ ከሆነ ታላቅ ነገር ነው፡፡
Favipiravir የሚባል ሌላ ኮምፓውንድ፡፡ ከዚህ በፊት ሌሎች ቫይሶች ላይ አገልግሎት የዋሉና፣ አዳዲሰ ኮምፓውንዶች ከተቀመጡበት ሸልፍ እየወረዱ እየተሞከሩ ነው፡፡
እናም ሌሎችንም የጨመሩ፣ ከመቶ በላይ የሚሆኑ ጥናቶች እየተካሄዱ ነው፡፡
ቻይኖች እንደሚታወቀው ባሕላዊ መድሐኒቶችን ሰለሚጠቀሙ፣ ባሕላዊ መድሐኒቶችም እየተጠኑ ነው፡፡
 እናም ይህ ሁሉ ጥረት እየተደረገ፣ በፌስ ቡክና በሌሎች ሜድያዎች መድሐኒት አገኝን ብለው የሚያወሩ ሰዎችን ማዳመጥ ቀርቶ ማሰብ ይከብዳል፡፡ እንዴት ነው? መረጃ፣ ሳይንስ የሚባሉ ነገሮችን አክብሮት እንስጥ እንጂ   ፡፡ ይህ ኮሮና ያሳየን ነገር፣ የፖለቲካ መሪዎች ሁኔታውን ለነሱ አመቺ በሚሆን መንገድ ሲሸፋፍኑና ትክክል ያልሆነ ነገር ሲነግሩ መክረማቸውን ነው፡፡ ስታስቡት አንዴት ነው፣ ቫይረሱ መኖሩን ምርመራ ሳያደርጉ፣ ሥርጭቱ መጠነኛ ነው ብለው ደፍረው ሲነግሩን የከረሙት፡፡ አሁን ግን፣ ቫይረሱ በሚከበርበት መንገድ መጣ፤ ያም ኢኮኖሚውን በማሽመድመድ አዳማጭ አገኘ፡፡ እንደዛ መሆንም አልነበረበትም፡፡
ዋናው መልክት፣ በድጋሚ፣ ላለመያዝ፣ አያደርስና ከተያዙም ወደሌላ እንዳይተላለፍ ማድረግ ሰብአዊ የሆነ ነገር ነው፡፡ መድሐኒትና ክትባት እሰከሚገኝ፣ ሥርጭቱን መቀነስ ሁላችንም ልንረባረብበት የሚገባ ነገር ነው፡፡
ለአመል ያህል እንኳን ቢታሰብ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር እያወጡ፣ ለህክምና ይውላሉ የሚባሉ ኮምፓውንዶቸን የሚያፈነፍኑ የትልልቅ ኩባንያ ሪሰርች እና ደቨሎፕመንት RD ክፍሎች፣ ሶሸል ሜዲያ ላይ መድሐኒት ሲገኝ፣ ዝም ሲሉ ታየኝ፡፡
ፈረንጆቹ “Too Good to be True” የሚሉት ነገር ነው፡፡

ስለ አዲሱ ኮሮና ቫይረስ ምክሮች  

ለመሆኑ በዚህ በአዲሱ ቫይረስ COVID-19 በጣም አደጋ ላይ የሚወድቁ ሰዎች አነማን ናቸው?

 ይህ ጥያቄ በጣም ወቅታዊ ነው፡፡ ጤና ባለሙያተኞችም ሆነ ሌሎቹም በትኩረት የሚጠብቁት ጉዳይ ነበር፡፡ በታወቂው የኒው ኢንግላንድ መጽሔት ባወጣው ዕትሙ፣ ከቻይና በኩል የዘለቀውን ይህን ጥናት ላካፍላችሁ፡፡
ጥናቱ የተሠራው፣ የህ የኮሮና ቫየረስ ተነሳ ከተባለበት የዉሀን ከተማ ነው፡፡ እስከ ጥር 29 ድረስ (እንደ አውሮፓ አቆጣጠር) ባደረጉት ከትትል፣ በ552 ሆስፒታሎች ገብተው ከታከሙት ከ7736 ህሙማን መሀከል የ1099 ሰዎችን መረጃዎች በመሰብሰብ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በቫይረሱ ለመያዛቸው በላቦራቶሪ የተረጋገጠ ነው፡፡  የጥናቱ ትኩረት፣ ምን ያህል ከፍተኛ ደረጃ ታመው በ(Intensive Care Unit) ክትትል ተደረገላቸው፤ ምን ያህሉ በሰው ሰራሽ መተንፈሻ (mechanical ventilation) እርዳታ ተደረገላቸው፤ ምን ያህሉ ሞቱ፡፡ አነዚህ ሰዎችስ ምን አይነት ባህሪ አላቸው የሚል ነው፡፡
የጥናቱ ውጤት የሚያሳየው፤
አማካይ ዕድሜ 47 አመት
41.9 ከመቶ ሴቶች ናቸው
  
ከጠቅላለው ማለትም ከ1099 መሀል፣ 483 በዉሀን ከተማ የሚኖሩ ሲሆን፣ 442 ደግሞ በዉሃን ከተማ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ከጠቅላlaው መሀል 3.5 በመቶ የጤና ባለሙያተኞች ናቸው፡፡ ሆስፒታል ከገቡት ከነዚህ ህሙማ 926 የሚሆኑት ከፍተኛ ያልሆነ የህመም ደረጃ ላይ የነበሩ ሲሆን በ173 ሰዎች ላይ ግን ብርቱ የህመም ስሜት የታየባቸው ነበሩ፡፡ በሽታው የበረታባቸው ሰዎce፣ ካልበረታባቸው ጋር ሲነፃፀር በዕደሜ የገፉ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሽታው የበረታባቸው ሰዎች ሌላ ተደራቢ የቆየ በሽታ ነበረባቸው፡፡ ያም በሽታው ካልበረታባቸው ሰዎች ጋር ሲነፃፀር ነው፡፡ በነዚሀ 173 ሰዎች ላይ ነው እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱት የከፋ የበሽታው ደረጃ የታየባቸው፡፡
  በከፍተኛ ደረጃ የታዩት የበሸታ ምልክቶች ሳልና ትኩሳት ነበሩ፡፡ በአማካይ እነዚህ በሽተኞች በሆስፒታል ውስጥ ለ12 ቀናት ከፍተኛ ህክምና የተደረገላቸው ናቸው፡፡ በዚህ ጥናት፣ የሟቾቹ ቁጥር 1.4 ከመቶ ነበር፡፡ አጥኝዎቹ ያጠቃለሉት፣ ይህ መጠን ከጠበቁት በታች ነው፡፡ በሌላ ጥናት ወይም ዘገባ በቫይረሱ ተይዘው ከታመሙ ሰዎች መሀከል ከ51፣857 1659 ወይም 3.2 በመቶ የሚሆኑት ህይወታቸው ማለፉ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ነው የዚህኛው ጥናት አጥኝዎች የነሱ ግኝት ከዚህ ቀደም ከተገለፀው ያነሰ ነው ያሉት፡፡ ያም ሆኖ በጥናታቸው የተጠቃለሉት ሰዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ስታቲሰቲኩ የተለየ እንደሚሆን ያምናሉ፡፡
የዚህ ጥናት መልክት ዋናው ነገር፣ በሽታው የሚበረታባቸውና ለህይወት አልፈት የሚዳረጉ ሰዎች አንዳሉ ነው፡፡ እንግዲህ ባለሙያተኞቹ እንደሚያስጠነቅቁት፣ አንደኛ በዕድሜ የገፉ ሰዎች (የተጠቀሰው የዕደሜ ገደብ ከ60 አመት በላይ ነው) ሁለተኛ፡፡ ሌሎቸ ተደራቢ በሸታዎች ያለባቸው ሰዎቸ፣ በተለይም እንደ አስምና የቆየ የሳንባ መተንፈሻ ችግር ያለባቸው ሰዎች፣ ሶሰተኛ ካንሰር ያለባቸውና ካንስሩ ለማዳን መደሀኒት (ኬሞ ቴራፒ) የሚወስዱ ሰዎች፣ አራተኛ በተለያዩ በሽታውች ምክንያት ኤይድስን ጨምሮ የመከላከያ አቅማቸው የደከሙ ሰዎች በቫይረሱ ከተያዙ በሽታው ሊበረታባቸው እንደሚችል ነው፡፡
      
ስለዚህ ምክሩ፣ በተለይ ከላይ የተጠቀሱት ሰዎች፣ በቫይረሱ ላላመያዝ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ የሚመከረው ምክር፣ በየትም አገር ቢኖሩም፣ ከቤታቸው ባይወጡና ባይጋለጡ ይመረጣል፡፡ ዘመድ ጠያቂም ቢሆን ስብሰብ ማለት አለበት፡፡ እንግዲህ በቫይረሱ ቢያዙም ብዙም ችግር አይደርስባቸውም የሚባሉት ወጣቶቹ ናቸው፡፡ ነገር ግን ብርቱ ህመም ባይዛቸውም፣ ቫይረሱን ወደ ሌሎች ማስተላለፍ ሰለሚችሉ፣ እነሱም ቢሆን ቆጠብ እንዲሉ ይመከራል፡፡ በተለይም በመኖሪያ ቤታቸው፣ በዕድሜ የገፉ ሰዎችና ከላይ የተጠቀሱ በሽታዎቸ ያሉባቸው ቤተሰብ አባላት ወይም ዘምዶች ካሉ፣ ለነሱ ሲሉ ወጣ ወጣ ከማለት መቆጠብና በቫይረሱ ላለመያዝ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደርጉ ይመከራል፡፡ ይህ ቫይረስ፣ ከሰው ወደ ሰው የመሻገር ችሎታው ሀይለኛ መሆኑን እያስመሰከረ ነው፡፡ 114 አገሮች ላይ የደረሰው ይህ ቫይረስ፣ የሚያደርሰውን ጉዳት ሁላችንም እየተከታተልን ነው፡፡ ቫይረሱ የሌለባቸው ይመስል ጭጭ ያሉ አገሮችን እንደሌለባቸው መቁጥር ስህተት ነው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ባልተለመደ ሁኔታ ከጤና ባለሙያተኞች በላይ ርዕሱን ማሽከርከር የፈለጉበት ክስተት አስገራሚ ነው፡፡ አዎ ለኢኮኖሚው አስበው ነው፡፡ ሊባልም ይችላል፡፡ ያልታየቸው የሚመስለው ነገር ግን፣ በሽፍንፍን ሊይዙት ያሰቡት ቫይረስ ገፍቶ ሲሚጣ፣ ኢኮኖሚው አብሮ እንደሚጎዳ ነው፡፡
    
 ሌላው ነገር፣ በማህበራዊ ሜድያ ባህላዊ መድሀኒት ተገኘ ተብሎ ሰዎች እየተቀባበሉ ሲያነቡት አስተውላናል፡፡ በወቅቱ የሚደረጉትን ሙከራዎች በቅርብ አካፍላለሁ፡፡ ነገር ግን፣ መንግሥታትና ካምፓኒዎች በሚሊዮን ዶላሮች ወጭ እያወጡ መድሐኒት በሚያስሱበት ወቅት ሰውን የሚያድን ነጭ ሽንኩርት በቀላሉ የሚሠራ ቢሆን፣ ይሄኔ አፈፍ አድርገው በኪኒን መልክ ይሸጡልን ነበር፡፡ ለማንኛውም ተከታተሉ፣   

በዚህ ገፅ የሚገኙ ርዕሶች

  • እየጨመሩ የመጡት የኮቪድ-19 በሽታ ስሜትና ምልክቶች
  • ይህ ነገር ማቆሚያም የለውም
  • ​​​​​​የአዲሱ ኮሮና፣ COVID-19 በትንፋሸ አማካኝነት መተላለፉ ሳያንስ አሁን ደግሞ በአይነ ምድር  3/16/2020
  • ስለ አዲሱ ኮሮና ቫይረስ(COVID-19) መድሐኒቶች   
  • ስለ ኮሮና ቫይረሶች ማወቅ የሚገባዎት
  • በዚህ በኮሮና ምክንያት “አንድ መቶ ሺ ሰው ብቻ ከሞተ ጥሩ ሥራ ሠርተናል ማለት ነው”​   
  • ስለ አዲሱ ኮሮና ቫይረስ ጠቃሚ ምክር
    ​አስቀድሞ መጠንቀቅ ተገቢ ነው
  • ጥናት አጥኝዎች በአፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ ለኮሮና ቫይረስ COVID-19 የተጋለጡ ናቸው ያሏቸውን አገራት አስታወቁ
  • አዲሱ ቫይረስ COVID-19 ከሰውነት ውጭ በዕቃዎች ላይ ለዘጠኝ ቀናት እንደሚቆይ ተገለጠ 2/23/2020
  • መልከ ጥፉን በስም… 

ስለ አዲሱ ኮሮና ቫይረስ ጠቃሚ ምክር

​አስቀድሞ መጠንቀቅ ተገቢ ነው

አዲሱ ኮሮና ቫይረስ ተብሎ የሚጠራው በምህፃረ ስም COVID-19 ሥርጭቱ እየጨመረ አሰከ ማረች 4 ድረስ በ81 አገሮች መሠራጨቱ ይታወቃል፡፡ አንባቢ እዚህ ላይ ማስተዋል ያለበት፡፡ ሪፖርት ያላደረጉ አገሮች አልደረሰባቸውም ማለት አይደለም፡፡ ይልቁኑ ምርመራ ስላላካሄዱ ነው፡፡ በአሜሪካም ቢሆን እንደ ሌሎቹ ሀገሮች ምርመራው በብዛት ስላልተካሄደ ቁጥርና ሥርጭቱን ማወቅ ከባድ ነው፡፡

ከዚህ በፊት ከቻይና መንገደኞች ጋር ብቻ ግንኙነት አለው የተባለው ይህ ቫይረስ፣ ከቻይና ወጥቶ፣ አስከዚህ ዕለት ድረስ፣ መንገደኞች ከነዚህ አገራት ከመጡ (ወደ አሜሪካ) ልዩ ትኩረት እንደሚሠጣቸው ነው፡፡ አገራቱም፣ ደቡብ ኮርያ፣ ኢራን፣ ጣልያን፣ ጃፓንን ጨምሯል፡፡ የአሜሪካው አስተዳደር ወደነዚህ አገራት በረራዎችን ለማገድ ያሰበ ቢመስልም እስካሁን ድረስ አልወሰነም፡፡ ያ ይቀየር ይሆናል፡፡ ለመንግሥታቱ፣ ዋናው አሳሳቢ የሆነው ነገር፣ ኢኮኖሚው ይመስላል፡፡

ነገር አንደምትከታተሉት፣ ሥርጭቱ ሰፍቶ፣ በየአገራቱ፣ ቫይረሱ በቦታው ከሰው ወደ ሰው እየተዛወረ ባለበት ሁኔታ፣ የአለም የጤና ድርጅት ሆነ መንግሥታቱ ደፍረው፣ አለም አቀፍ ፓንደሚክ ደረጃ ነው ማለት ከብዷቸዋል፡፡ የመንግሥታቱን አቀራረብ መረዳት ከተቻለ፣ በግልና በህብረተሰብ ደረጃ አስቀድሞ በቂ ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡

ሰለ በሽታው ሥርጭት ሌላ ነገር ላካፍላችሁ፡፡ ይህ ለማሸበርም አይደለም፣ ግን በቂ ጥንቃቄ ለማድረግ መረጃ እንዲሆን ነው፡፡ ብዙ ካመናታሁ በኋላ ግን ምክሩ መሠጠተ አለበት ብዬ ሰላመንኩ ነው፡፡ ሱቆችና አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ተገቢወን ጥንቃቄ ሲያደርጉ ሰለተመለከትኩም ነው፡፡

እንደዚህ አይነት ተላላፊ በሸታ ሲከሰት፣ ሰለ በሽታው ወይም ቫይረሱ ሥርጭት፣ በኮምፒውተር በሚደረግ ስሌት አማካኝነት የቫይረሱን የመሠራጨት አቅም አስቀድሞ መተንበይ ይቻላል፡፡ (Computer modeling) ይባላል፡፡ እየሰላና እየተሻሻለ የመጣ ስሌት ነው፡፡ በእንግሊዝ አገር በተደረገ በዚህ ስሌት፣ አንድ ሰው ቫይረሱ ከተገኘበት፣ ሌሎች ሶስት ወይም አራት ሰዎች ቫይረሱ ያለባቸው፣ ነገር ግን ያልታወቁ ወይም በምርመራ ገና ያልተገኙ ሰዎች እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ ውነት ነው፣ ተላላፊ ቫይረስ ብቻውን ዘው አይልም፡፡ ከሰው ወደ ሰው እስከተሻገረ ድረስ፣ አሻጋሪዎች አሉ፡፡ ችግሩ እነዚህ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ታውቀው አስፈላጊው የመከላከያ ዘዴ እስካልተገበረ፣ ቫይረሱን ማዛመታቸው አይቀርም ማለት ነው፡፡ ሌላው አቢይ ችግር፣ የበሽታ ስሜት ሳይኖራቸው በቫይረሱ ተይዘው፣ ቫይረሱን የሚያስተላልፉ ሰዎች መኖራቸው ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው አንግዲህ፣ ቫይረሱ ተገኘባቸው ከሚባሉ ከታወቁ ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች መኖራቸውን መገንዘብና የቫይረሱ ሥርጭት መጠን ከሚታወቀው በላይ መሆኑን መገንዘብ የሚያስፈልገው፡፡ ይህንን በመገንዘብ፣ ሰዎች ማድረግ ሰለሚገባቸው ነገር ምክር ለመሥጠት እወዳለሁ፡፡ ከሙያ አንፃር፡፡


​በቫይረሱ ላለመያዝ

  • ቫይረሱ አለባቸው ወይም ተሠራጭተዋል ወደሚባሉ ቦታዎች የሚያደርጉትን ጎዞ መሠረዝ
  • ከነዛ አካባቢዎች ሄደው ተመልሰው ከሆነ፣ ራስዎን ለአስራ አራት ቀናት ማግለል
  • ሰውነትዎን ማዳመጥ፣ ማለትም፣ ሳል፣ ትኩሳት፣ የደረት ህመም፣ የትንፋሽ ማጠር ሰሜትና ምልክቶች
  • እነዚህ ምልክቶች ከታየብዎት፣ መጀመሪያ ወደ ህክምና ቦታዎች መደወልና ስለ ሁኔታዎ በማስረዳት ተገቢው ጥንቃቄና እንክብካቤ እንዲደረግልዎት ማድረግ

በሚኖሩበት አካባቢ ሊገባ የሚችል ከሆነ ወይም ገብቶ እየተሠራጨ ከሆነ

  • አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚያገናኙ ሁኔታዎችን መቀነስ (Social distancing)
  • ውጭ ከወጡም፣ ከተገኘ እጅዎች በውሃና በሳሙና ለሃያ ሰከንዶች በደንብ አሽተው ማጠብ፡፡ እዚህ ላይ አላማው እጅዎን በመፈተግ እጅዎ ላይ ሊኖር የሚችለውን ቫይረስ ለማስወገድ ነው፡፡ ሳሙናው ብቻውን አይገለውም፡፡
  • ውሀ የማይገኝ ከሆኑ፣ ከ60 ፐርስንት በላይ አልኮል ያለባቸው የእጅ መወልወያዎችን መጠቀም፡፡ አነዚህን ማፅጃዎች በኪስዎ ይዘው መዞር ይመከራል፡፡
  • ከመንገደኛ ጋር የሚያገናኝ ሥራ ካለዎት ደግሞ፣ በተለይም መኪና የሚጠቀሙ ከሆነ፣ የእጅ ጓንት በማጥለቅ፣ መኪናዎን በየጊዜው ማፅዳት ተገቢ ነው፡፡ ቫይረሱን ይገላሉ የሚባሉ ኮምፓውንዶች የሚከተሉት መሆኑን ያስተውሉ፡፡

62–71% ethanol አልኮል፣ (62-71 ጥንካሬ ያለው)
0.5% hydrogen peroxide ሀይድሮጅን ፐርኦክሳይድ
0.1% sodium hypochlorite ሶድይም ሀይፖ ክሎራይት

  •  ወደ ቤትዎ ሲመለሱ፣ ከውጭ እጅዎን በአልኮል ካፀዱ በኋላ፣ የቤተሰብ አባል ጋር ከመቀላቀልዎ በፊት፣ እጅዎን ታጥበው፣ ልብስዎን ይቀይሩ፡፡ በታዋቀዊ የኒው ኢንግላንደ ጆርናል፣ በተፃፈ ደብደቤ፣ ከታይላንድ በኩል፣ የቻይና መንገደኛ የጫነ ሰው በዚሁ ቫይረስ ተይዞ ማገገሙን አስፍረዋል፡፡
  • ውጭ ለሥራም ሆነ ለገበያ ከወጡ፣ አፍንጫና አይንዎን ከመነካካት ይቆጠቡ፡፡ ሌሎች አስፈላጊ ያልሆኑ ዕቃዎችን ከመንካት ይቆጠቡ፡፡ ድንገት ከነኩ፣ አልኮልዎን መዘዝ አድረገው እጅዎን ይወልውሉ፡፡
  • ግድ የለም፣ ለጊዜው የአንገት ሠላምታ ይበቃል፡፡ መጨባበጥና መሳሳሙ ለሌላ ጊዜ ይሁን፡፡
  • ቤትዎ ውሥጥም ቢሆን፣ የሰው እጅ ይደርስበታል የሚባሉ ዕቃዎችን ከበር መክፈቻ ጀምሮ ማፅዳት ተገቢ ነው፡፡
  • የፊት ማሰክ ጠቃሚነቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አፍና አፍንጫ በማስነጠስ ሆነ በመሳል ቫይረሱ በአየር ላይ እንዳይውል ሰለሚቀንስ ነው እንዲያደርጉ የሚደረገው፡፡ ያልተያዙ ሰዎች እንዳይያዙ የሚያደረጉት፣ ለአእምሮ ይረዳ እንደሆን እንጂ ላይስጥል ይችላል፡፡ የጤና ባለሙያዎች የሚያደርጉት ማስክ የተለየ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አሱም N-95 የተባለ የተለየ ነው፡፡ ይህንን ማስክ ለማድረግ ግን፣ ባለሙያተኞቹ መጀመሪያ የሚደረግላቸው Fit testing የተባለ ነገር አለ፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው ሳይለካና ሳይፈተሸ የሚያደርገው ነገር አይደለም፡፡ ዋናው ነገር በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች በስድስት ጫማ ርቀት ውስጥ ላላመገኘት ነው እንግዲህ ከሰዎች ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት ቀንሱ የሚባለው፡፡
  • ድንገት በአካባቢዎ ወይም በአገሩ፣ የፓንደሚክ ፕላን ከታወጀ፣ እንቅስቃሴዎች ሊገደቡ ሰለሚችሉ፣ በቤትዎ ውስጥ ቢያንስ ቢያንስ ለሁለት ሳምንታት የሚሆኑ፣ ውሀ፣ ደረቅ ምግቦች የመሳሰሉትን ማዘጋጀት፡፡
  • መድሐኒቶች የሚወስዱም ከሆነ፣ እንዳይቋረጥብዎት በበቂ መጠን እንዲኖር ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

እነዚህን ምክሮች የኛ ህብረተሰብ የሚከተላቸው ባይመስልም፣ ሌሎቹ በዝግታና በፀጥታ እያደረጉት መሆኑን ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ መንግሥትና ሳይንቲስቶቹ ምክሩን ከሰጡ ሰንብተዋል፡፡
አያድርስና በቫይረሱ ከተያዙን ምልክትና ስሜት ካለብዎት፣ ማድረግ የሚገባዎትን ነገር በዚሁ ድረ ገፅ በኮሮና ገፅ ላይ ያንብቡ፡፡
እባክዎን ይህንን መልክት ለሁሉም አካፍሉ!! መልክት ሲወጣ እንዲደርስዎት በኢሜይልዎ ብቻ በዚህ ገፅ ይመዝገቡ፡፡ ኢሜይልዎን ለሌላ አገልግሎት ለማዋል አይደለም፡፡ ስምዎን መፃፍም አያስፈልግም፡፡


ጥናት አጥኝዎች በአፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ ለኮሮና ቫይረስ COVID-19 የተጋለጡ ናቸው ያሏቸውን አገራት አስታወቁ

እንደምትከታተሉት፣ ይህ አዲሱ ኮሮና ቫየረስ እየተዛመተ አስከ ፌብሩዋሪ 25 ድረስ ከቻይና ውጭ በ35 አገሮች መከሰቱ ይታወቃል፡፡ ከአፍሪካ አገራት አስከ አሁን ድረስ በግብፅ ብቻ አንድ ሰው አስመዝግበዋል፡፡ ሌሎቹ ያልደረሰባቸው ይመስል ጭር ብለዋል፡፡
በቅርቡ ከፈረንሳይ አጥኝዎች ጉዳዩን ተመልክተው ከአፍሪካ ውስጥ ለዚህ COVID-19 ቫይረስ በከፍተኛ ደረጃ የተጋለጡ ናቸው ያሏቸውን አገራት አስታውቀዋል፡፡ እነዚህ ከቻይና ተነስቶ ይዛመትባቸዋል ተብለው በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አገራት፣ አልጄሪያ፣ ግብፅና ደቡብ አፍሪካ ናቸው፡፡ አለመታደል ሆኖ፣ በጣም ከፍተኛ ደረጃ ባይሆንም፣ እንደነሱ አገላለጥ፣ ናይጄሪያና ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ሲሆኑ፣ የሚያሳዝነው ነገር፣ ሁለቱም ለዚህ ወረርሽኝ በሚገባ ሰላልተዘጋጁ፣ ለከፈተኛ ወረርሽኝ የተጋለጡ ናቸው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ ይህ መረጃ፣ ሄልዮ የተባለ የተላላፊ በሽታዎች መፅሄት ላይ ነው የቀረበው፡፡ ከአጥኝዎች፣ (Vittoria Colizza, PhD, research director at Inserm and Sorbonne Universite in Paris) እንደገለጡት ከሆነ፣ ብዛት ያላቸው የአፍሪካ አገሮች ይህንን ከውጭ የመጣ ቫይረስ በወቅቱ ለማወቅና ሥርጭቱን ለመግታት ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ ጥናታቸው ያተኮረውም፣ በቂ ዝግጅት ያላደረጉ አገሮችን ለይቶ በማወቅ አስፈላጊው እርዳታና ዝግጅት እንዲደረግላቸው ለማስጠንቀቅ ነው፡፡ አለዚያ እነዚህ አገራት፣ ከቻይና ከሚመጣው ከዚህ ቫይረስ በከፍተኛ ደረጃ ሊጠቁ እንደሚችሉ ነው፡፡

የነዚህን አገራት የዝግጅት ችሎታ የመረመሩት የአለም ጤና ጥበቃ ድርጅትን ሁለት መመዘኛዎች በመጠቀም ነው፡፡ የዚህ ግኝታቸው ደግሞ ላንሴት በተባለ መፅሔት በይፋ ወጥቷል፡፡

ሰፋ አድርገው ሲያቀርቡ፣ በጣም ከፍተኛ ደረጃ አደጋ ላይ ያሉት ዝግጅት በማድረጋቸው በወረርሽኙ ብዙ ላይጎዱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በከፍተኛ ደረጃ  ለቫይረሱ ሊጋለጡ ይችላሉ የተባሉት አገሮች ማለትም፣ ናይጄሪያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ አንጎላ፣ ታንዛንያና ጋና የዝግጅት መጠናቸው በተለያዬ ደረጃ ሲሆን፣ ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በቂ ባይሆንም ዝግጅት ያደረጉ መሆኑን አጥኝዎቹ ይጠቅሳሉ፡፡ ያም ሆኖ ሁለቱም አገሮች ለበሽታው ሥርጭት በከፈተኛ ደረጃ ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው፡፡ ይህንን የማቀርበው፣ ሰውን ለማስጨነቅ ሳይሆን፣ ህዝቡ አስቀድሞ በመጠንቀቅ የበኩሉን ዝግጅት እንዲያደርግም ነው፡፡ ለተጨማሪ ንባባ ከዚህ በፊት የወጡትን ፅሁፎች መመለክት ይረዳል፡፡ በተለይም በጎሽ ድረ ገፅ GOSHHEALTH.ORG የወጡትን ተከታታይ ፅሁፎች ማንበብ ይጠቅማል፡፡

ከኢትዮጵያና ከናይጄሪያ ውጭ፣ ሌሎቹ፣ ሱዳን፣ አንጎላ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ታንዛንያ በተመሳሳይ ደረጃ ከቻይና የሚመጣውን ቫይረስ የማስገባት አደጋቸው እኩል ቢሆንም፣ በዝግጅት ማነስ ብቻ አንዴ ከገባ በከፍተኛ ደረጃ ሊሠራጭ በሚችልበት አስጊ ሁኔታ ላይ ናቸው፡፡

ያም ሆኖ እንደ ጥናቱ ባለቤት አገላለፅ፣ የአለም የጤና ድርጅት፣ የጉዞ ወይም የመንገድ ግንኙነት እንዲቋረጥ መመሪያ አልሠጠም ይላሉ፡፡ አከራካሪው ነገር ይህ ነው፡፡

አዲሱ ቫይረስ COVID-19 ከሰውነት ውጭ በዕቃዎች ላይ ለዘጠኝ ቀናት እንደሚቆይ ተገለጠ 2/23/2020


በስፋት እየተሠራጨ ያለውን የዚህ ቫይረስ ባህሪ ለማወቅ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ ባሕሪውን ማወቅ ሥርጭቱን ለመግታት ይረዳል፡፡ በቅርቡ በጤና ጆርናል የተገለጠው፣ ሌሎች ከዚህ በፊት የተደረጉ ጥናቶችን በመመልከትና ከዚህ ቀድም የታዩ Severe Acute Respiratory Syndrome (SARS) coronavirus ቫይረስ፣ Middle East Respiratory Syndrome (MERS) coronavirus ሜርስ ቫይረስና ሌሎች የሰው ኮሮና ቫይረሶችን ባህሪ በመመልከት፣ ቫይረሱ ከሰውነት ውጭ በዕቃዎች ላይ፣ እንደ ብረት፣ ፐላስቲክና ጠርሙስ ላይ ለዘጠኝ ቀናት ሊቆይ እንደሚችል ነው፡፡ ልብ በሉ፣ ዋናው መተላለፊያ መንገድ ከታማሚዎች በሳል ወይም በማስነጠስ ከትንፋሻቸው በሚወጡ በአይን የማይታዩ ጠብታዎች ወደ ሌሎች ሰዎች መተንፈሻ አካላት ሲዘልቁ ነው፡፡ ሆኖም፣ ቫይረሱ ያረፈበትን ዕቃ በአጅ ከነካኩ በኋላ አይንና አፍንጫን በመንካትም ሊተላላፍ እንደሚችል ነው፡፡ ይህ ማለት ያሳለው ወይም ያስነጠሰው ሰው ቦታውን ለቆ ከሄደ በኋላ ነው፡፡ እነዚህ ዕቃዎች ላይ የሰነበተው ቫይረስ በምን ያህል ጥንካሬ ወደ ሰው መተላለፉ ግልፅ ባይሆንም አደጋው ለሁላችን ግልፅ መሆን አለበት፡፡

እነዚህ እቃዎች ላይ የሚሰነብተውን ቫይረስ ማፅዳት ይቻላል፡፡ ለዚህ ጉዳይም የሚከተሉት ማፅጃ ኬሚካሎች ተጠቅሰዋል፡፡
62–71% ethanol አልኮል፣ (62-71 ጥንካሬ ያለው)
0.5% hydrogen peroxide ሀይድሮጅን ፐርአኮሳይድ
0.1% sodium hypochlorite ሶድይም ሀይፖ ክሎራይት ይህ በ1 ደቂቃ ውስጥ ያፀዳል

ስለዚህ ሌሎች ያልተጠኑ ማፅጃ ኮምፓውንዶችን መጠቀም ቫይረሱን ለመግደላቸው እርግጠኛ መሆን ሰለማይቻል፣ በሚታወቁት ተጠቀሙ፡፡
በነገራችን ላይ፣ እጅ መታጠብ ሥርጭቱን ለመከላክል እስዎም እንዳይያዙ የሚረዳ ሲሆን፣ ውሀ ከሌላ እጅዎን በአልኮል (ከላይ በተጠቀሰው ጥንካሬ መጠን) ይወልውሉ፡፡
አሃ! ሌላው ጥናት የሚያሳያው፣ ይህ አዲስ ቫይረስ አፍንጫ ውስጥ ከመጠን በላይ እንደሚገኝ ነው፡፡ አፍንጫን እንደልምድ የሚነካኩ ሰዎች ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ከተነፈጡ በኋላ የተነፈጡበትን ወረቀት ወዲያውኑ ሌላ ሰው እንዳይነካው በጥንቃቄ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ቢቻል በፕላሲቲክ ጠቅልሎ ማስቀመጥ ይረዳል፡፡
ይህ አዲስ መረጃ ለሁሉም ለጤና ባለሙያተኞችም ጭምር አዲስ ነው፡፡ እባካችሁ አካፍሉ.


መልከ ጥፉን በስም… 
ይላሉ ያገራችን ሰዎች፡፡ ከዚህ ቀደም አዲሱ ኮሮና ቫይረስ ተብሎ የሚጠራው አዲስ ስም ተሠጥቶታል፡፡ ሌላ ጉዳይ ማለትም ህዝብን ወይም አገርን በማይጎዳ መልክ ነው የወጣው፡፡ አስታውሳለሁ፣ ዌስት ናይል ቫይረስ ለምን ዌስት ናይል ተባለ ብዬ ተከራክሬያለሁ፣ የዛሬ ምን አምን አመት፡፡ አሁን ቢሆን በፖለቲካል ኮሬክትነስ ዘመን ይህንን ስም አያወጡም ነበር፡፡ ግን ለአፍሪካ ያውም ለኛ ግድ ያለው ይኖር ይሆን?

ወደ ኮሮና ልመላሰችሁና አዲሱ ስም አወጣጡን ልንገራችሁ
አዲሱ ስም COVID- 2019
CO= Corona
VI= Virus

D= Disease
2019= የተነሳበት ጊዜ
አስተውላችሁ ከሆነ ቻይና የሚል ቃል የለበትም፡፡ ስም አውጭዎቹ የመረጡት ሌላ ነበር፣ ከSARS ጋራ የተያያዘ፡፡ ወሳኞቹ ሽብሩን አልፈለጉትም፡፡

ባለሙያተኞቹ፣ ቻይኖቹን በሙሉ ልብ ያመኑ አይመስሉም፡፡ መጀመሪያ የተሠጠው ቁጥር በጠና የታመሙትን ነበር፡፡ ወደኋላ የተጋለጡትን ጨመሩ፡፡ ሥርጭትን በሚመለከት ቀለል ያለ ህመም ያለውም ሰለሚያሠራጭ ያንን ቁጥር ማስታወቅ ነበረባቸው፡፡ ለምን? በኢንግላንድ በተደረገ ሞዴሊንግ፣ አንድ ለተያዘ ሰው፣ ከሱ ወይም ከሷ ጋር ሌሎች ያልታወቁ ግን የተያዙ ሶስት ወይም አራት ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያሳያል፡፡
ሰለዚህ የቻይናው አንዳለ ሆኖ፣ አትኩሮት ወደ ሲንጋፖር ሆኗል፡፡
ግን ለምን?
አንደኛ፤ በሲንጋፖር በራሱ በቦታው ቫይረሱ ሰው ከሰው መተላለፉ፣ ከቻይና ውጭ የሆነ ነገር በመሆኑ
ሁለተኛ ሲንጋፖር ምንም ሳትሻሽ ሪፓርቱን ቅልብጭ አድርጋ በመስጠቷ ታማኝነት
ሶሰተኛ፤ የበሽታው ክፋት አሳሳቢ መሆኑ፣ ሃምሳ ከተያዙት መሀከል ስምንቱ በጠና ታመው ከፍተኛ ደረጃ ላይ መሆናቸው፡፡
አራተኛ፤ የኛን ሀገር ባለሙያዎች መልካም ምኞት የሚበላሸው፣ ሙቀት የቫይረሱን መዛመት ይገታዋል የሚል ዕምነት ወይም ተስፋን ያጨለመው፡፡ የሲንጋፖር የአየር ፀባይ ሞቃታማ ሆኖ ያውም 80 ዲግሪ ፋራናይት፣ ቫይረሱ መተላለፉ ነው፡፡

በዚህ መሀል አንድ ጥሩ ነገር የታየው፡ በዘጠኝ ነብሰ ጡሮች (እርጉዞች) ላይ በተደረገው ጥናት፣ እናቶቹ ወደ ወሊድ መቃረቢያቸው ጊዜ በቫይረሱ ተይዘው ግን የተወለዱት ህፃናት ምርመራ ሲደረግ፣ ከቫይረሱ ነፃ ሆነው መገኘታች ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ባለፈው በSARS ጊዜ ነብሰ ጡሮች ከባድ ህምም ላይ ነበሩ፡፡ ቢዝህኛው COVID- 2019 የተያዙት ግን ከባድ ህመም አልታያባቸውም፡፡ ተመስገን፡፡ ልብ በሉ በሽታ ከሚጠናባቸው ወገኖች ነብሰጡሮች ይገኙበታል፡፡

እንግዲህ ባለፈው በፅሁፍም በቪዲዮም ለመከላከል መወሰድ የሚገባቸውን ርምጃ መግለጤ ይታወሳል፡፡ አሁን አንድ ልጨምር፣ እሱም Self Quarantine ይባላል፡፡ እራስዎነ ማግለል ማለት ነው፡፡ የተሠጠው ጊዜ ገደብ 14 ቀናት ነው፡፡ በተቻለ መጠን ላለመያዝ መሞከር፣ የተያዙ ከመሰለዎት ደግሞ ቤተሰብና ህብረተሰብን ላለማጋለጥ ሰብሰብ ይበሉ፡፡ እጅ ታጠቡ ብዬ ተናግሬያለሁ፣ ነገር ግን ውሀው ከየት ይመጣል ለምትሉ፣ አጅ ላይ የሚወለወለውን አልኮል መያዝና ውሀ ከለለ እጅዎን እንዲወለወሉ ይመከራሉ፡፡ እዚህ ላይ ከአንድ ታናሽ ወንድሜ ጋር ያደረኩትን ሙግት ላስታውስ፡፡ እሱ የሚለው፣ ሳኒታይዘር እጠቀማለሁ ነው፡፡ ለዕቃ ማፅጃ የሚሆን ሳኒታይዘር ለእጅ አይሆንም፡፡ ለእጅ አገልግሎት የሚውለው የአልኮሉ ጥንካሬ መጠን ደግሞ 60% መሆን አለበት፡፡ የትኛው ተባይ በየትኛው ኬሚካል በምን ያህል ኮንሰንትሬሽን እንደሚሞት የሚታወቅ ነገር ሰላለ ነው፡፡ ሳኒታየዘሮች ላይ የሚፃፈውን የማሻሻጫውን “99.9 %” ፖለቲከኞቹን በምትሰሙበት ጆሮ ስሙ፡፡
ሰለዚህ ባካችሁ ጥንቃቄው ላይ አተኩሩ፡፡
የቀረው ነገር፣ እንደ ሲንጋፖር ቫይረሱ ከቻይና ንክኪ ውጭ መተላለፉ አለመረጋገጡ ነው እንጂ፣ ፓንደሚክ የሚባል ደረጃ ላይ እንገባለን፡፡ አሁን በመሽኮርመም ፓንደሚክ ሲትዌሽን እያሉት ነው፡፡ ባልዘረዝርም ለምን እንደዚያ እንደሚያደርጉ ሊገባን ይገባል፡፡ የክፋት አናድርገው፡፡




ስለ ኮሮና ቫይረሶች ማወቅ የሚገባዎት

 በጤና በኩል፣ አለምን ውጥረትና ጭንቀት ውስጥ እያስገባ ስለሚገኘው ኮሮና ቫየረስ ማወቅ የሚገባንን ያህል ለማስገንዘብ ይህን ጽሀፍ አቅርቤያለሁ፡፡ መጀመሪያ ስሙን ካስተዋልን፣ አዲስ ኮሮና ቫይረስ ነው የሚለው (Novel Corona virus of 2019)፡፡ አዲስ ነው ከተባለ የድሮዎቹ እነማናቸው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ ደግሞ ስመጥር ቫየረሶች ስለሆኑ መታወቅም ይገባቸዋል፡፡ ክፉ አውሪ አትበሉኝ እንጂ፣ ከሙያና ከታሪክ አንፃርም፣ የሰውን ልጅ ላልታሰበ ዕልቂት ከሚዳርጉት ነገሮች ቫይረሶች ትልቅ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

 ኮሮና ቫይረሶች በብዛት በቁጥራቸው በርከት ያሉ የቫይረስ ቤተሰቦች ሆነው ከቀላል ጉንፋን እሰክ ለሕይወት አስጊ የሆኑ በሽታዎች ያስከትላሉ፡፡ እነዚህ ቫይረሶች በአይነት ሰባት ሲሆኑ፣ አራቱ በብዛት የሚገኙ ቀላል ጉንፋን የሚያስይዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ከ1960 ጀምሮ በህክምናው አለም የሚታወቁ ናቸው፡፡ በየጊዜው ቀላል ጉንፋን ህመም የሚያሰከትሉትን ትተን ከዘህ ቀደም በጣም በአሳሳቢ ደረጃ ተከስተው የነበሩትን ስናስተውል፡፡

እኤአ በ2002 ተከስቶ የነበረው ሳርስ ( SARS: Severe Acute Respiratory Syndrome) የሚባለው SARS-CoV
በህብረተሰቡ ዘንድ ብዙም ያልታወቀው፣ ነገር ግን በመካከለኛው ምሥራቅ ችግር ያስከተለው ሜርስ-ኮቫይረስ (Mers-co: Middle Easte Corona virus )ተብሎ የሚጠራው
አሁን በአለም አቀፉ የጤና ድርጅት፣ አለማቀፋዊ አደጋ ያስከትላል ተብሎ የታወጀለት የ2019-nCoV አዲሰ ኮሮና ቫይረስ ይገኙበታል፡፡

 ሥርጭትን በተመለከተ
ኮሮና ቫይረሶች ከአንስሳት ወደሰዎች የሚተላለፉ ቫይረሶች ሲሆን ከዛም ከሰው ወደ ሰው በሚያደርጉት ሥርጭት ነው ጭንቀት የሚያስከትሉት፡፡ የሳርስ ቫይረስን ብንመለከት፣ ከድመት ዝርያዎች አንዱ ከሆነው ሲቬክ ድመት ወደ ሰው የተላለፈ ሲሆን የመካካለኛው ምሥራቁ ቫይረስ ደግሞ ከግመል ወደ ሰው ነው የተሸጋገረው፡፡ እንግዲህ ከእንስሳት ወደ ሰው መተላለፍ በእንግሊዘኛው አጠራር ዞኖቲክ zoonotic የሚባል ሲሆን፡፡ ገና ወደ ሰው ያልተሻገሩ በእንስሳቱ ላይ የሚዘዋወሩ ብዙ ቫይረሶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በአብዛኘው ወደ ሰው ሲዘሉ ቸግር የሚያስከትሉ ቢሆንም ከአንስሳቱ ጋር ተላምደው የሚኖሩ ይመስላሉ፡፡ ይህ አዲሱ ኮሮናቫይረስ፣ በቻይና ተከሰተ ሲባል፣ ዉሃን በሚባል ክፍለ ሀገር በአሳ መሸጫ ገበያ አካባቢ ነው የተነሳው ነው የሚባለው፡፡ አሁን ግን፣ እንደምንመለከተው ከዚያ ሰፋ ብሎ ወጥቷል፡፡

 የሚያስከትሉት የበሽታ አይነትና ለህይወት ማለፍ ደረጃ
አዲሱን የ2019 ኮረኖቫይረስ በመጠኑም ቢሆን ከከፍተኛ ስጋት ወረድ ያለ እንዲሆን ያደረገው፣ በቫይረሱ ከተለከፉ ሰዎች ምን ያህሉ ህይወታቸው ያልፋል የሚለው ጥያቄ መልስ ነው፡፡ ይህንን ለመገንዘብ በሶስቱ ቫይረሶች መሀል ያለውን ልየኑት እናነፃፅር

  •  የሳርስ ቫይረስ፡ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ከመቶ አሥሩ ሕይወታቸው ያልፋል (9.6)፣ በ2002 በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ በዘጠኝ ወራት ውሥጥ 8096 ሰዎች በቫይረሱ የተለከፉ ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት ሞተዋል ተብሎ የተዘገበው የሰዎች ቁጥር 774 ነበር፡ በዚያን ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ነገር እንደነበር፣ ከሙያ አንፃር የማይረሳ ትዝታ ነበር፡፡ ይህ ከቻይና ተነስቷል የተባለው ቫይረስ ከ2004 ወዲህ ድምፁ አልተሰማም፡፡
  • ቀጥሎ የተከሰተው ደግሞ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የታየው ሜርስ-ኮቫይረስ ነው፡፡ ይህ ቫይረስ አሁንም ድረስ ችግር የሚያሰከትል ነው፡ ይህ ከሳውድ አረቢያ ተነስቶ ወደሌሎች አገሮች የተዛመተው ቫይረስ በስፋት ባይሠራጭም በአይነ ቁራኛ የሚጠበቅ ቫይረስ ነው፡፡ በአረብ የባህር ሠላጤ አካባቢ ሰለሚታይ ነው የመካከለኛው ምሥራቅ ኮሮናቫይረስ የሚባለው፡፡ ይህ ቫይረስ ከግመል ጋር በሚደረግ ንክኪ የሚመጣ ሲሆን፣ ከሳውዲና ሌሎች የአረብ አገሮቸ ተነስተው በሚጓዙ መንገደኞች ወደሌላው አለም ይዛመታል፡፡ ከመጠነኛ ሳል አዘል በሽታ አስከ ከባድ የሕይወት ህልፈት ምክንያትም ነው፡፡ አስከ ጃንዋሪ 2019 በቀረበው ሪፖርት በቫይረሱ በላቦራቶሪ የተረጋገጠ 2298 ሰዎች በ27 አገሮች ውስጥ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስት 811 ህይወታቸው አልፏል፡፡ በሂሳብ ሲሰላ፣ ከተለከፉት መሀል 35 ፐርስነቱ ህይወታቸው አልፏል፡፡ ከአንድ ሶሰተኛ በላይ ማለት ነው፡፡ ለዚህ በሽታ ሠርጭት ምክሩ፣ ከግመሎች መራቅ፣ የግመል ጥሬ ወተት አለመጠጣት፣ ከግምል ሽንትም ጋር ንክኪ አለማድረግ ነው፡፡ አሁንም በአይነ ቁረኛ ሰለሚጠበቅ ነው ሰፋ አድርጌ ያቀረብኩት፡፡ የባሰ አለ ለማለትም ነው፡፡  ከላይ የተጠቀሱት ቫይረሶች የመጀመሪያ ምንጫቸው ናቸው የሚባሉት የሌሊት ወፎች ናቸው፡፡
  • ይህ አዲስ ኮሮና ቫይረስ ደግሞ አስካሁን ድረስ በተደረገው ዘገባ ከተያዙ ሰዎች መሀከል አስከ 2.9 በመቶ የሚሆኑት ህይወታቸው ያልፋል፡፡ ቸግሩ ግን ይህ የህይወት ማለፍ ደረጃ እንደተያዘው ሰው የጤንንት ደረጃ ነው፡፡ የሚበረታባቸው ሰዎች እንዳሉ መገንዘብ ያሻል፡፡
  • ከኮሮና ቫይረስ ውጭ ግን፣ ሰልተለመደ እንጂ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለው የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ነው፡፡ በሰሜን አሜሪካ በየአመቱ በቀዝቃዛው ወራት መታወቂያውን እየቀየረ ብቅ የሚለው ይህ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ በ2019 አስከ 600ሺ ሰዎች ድረስ የለከፈ መሆኑ ሲታወቅ፣ ለምርመራ ከተላከው ናሙና ወደ 107ሺ የሚሆነው የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ተግኝቶበታል፡፡ በነገራችን ላይ በከፍተኛ ደረጃ ህመም ከሚያስከትሉ ቫይረሶች፣ ኢንፍሉዌንዛ A ና ኢንፍሉዌንዛ B ይገኙበታል፡፡ የዚህ በሽታ መክፋት መለኪያዎች፣ በቫይረሱ መለከፍ ምክንያት ምን ያህል ሰዎች ሆስፒታል ገብተው የታከሙ መሆናቸውና ከዚህ ጋር በተያያዘም የምን ያህል ሰዎች ህይወት እንዳለፈ ማወቅ ነው፡፡ በዚህ መሠረት፣ ዕድሜያቸው ገፋ ያሉ ሰዎች በብዛት ሆሰፒታል ውስጥ ተኝተው የሚታከሙ ሲሆን ባጠቃላይ ከ100ሺ ሰው 29.7 የሚሆኑት ሆስፒታል እንዲገቡ ምክንያት ነው፡፡ ዕደሜያቸው ከ65 አመት በላይ ከሆነ፣ ይህ ቁጥር ወደ 71.3 ያድጋል፡፡ ከኢንፍሉዌንዛና የሳንባ ምች ጋር በተያያዘ፣ በአሜሪካ፣ 6.7 ከመቶ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ይሕ ቁጥር፣ ከ7.2 በመቶ በታች በመሆን በከፍተኛ ደረጃ ተዛምቷል አልተባለም፡፡ ካስተዋልን ግን፣ ኢንፍሉዌንዛ፣ ከአዲሱ ኮሮና ቫይረስ በላይ ገዳይ ነው፡፡ ደግነቱ፣ ለኢንፍሉዌንዛ ክትባትም አለ፣ መድሀኒተም አለ (ወዲያውኑ መወሰደት አለበት)፡፡


አዲሱ ቫይረስ መነሻው

በተለያዩ የህክምናና የጤና መፅሄቶች እንደተዘገበው፣ ይህንን ችግር ለአለም ህዝብ ያካፈለቸው ራሷ ቻይና ስትሆን፡፡ በሽታው ተነሳ የተባለበት ቦታ፣ ሁቤ በሚባል ክፍለ ሀገር፣ ነገሩ አንዲህ ነው በተህሳስ ወር አጋማሽ፣ በሁቤ፣ ዉሀን በሚባል ከተማ ያልታወቀ በቫይረስ አማከኝነት የሚከሰት የሳንባ ምች በሽታ የተያዙ ሰዎች ሰብሰብ ባለ ቁጥር ይታያሉ፡፡ የነዚህ ሰዎች አክታ በላቦራቶር ሲመረመር፣ ከዚህ በፊት ያልታየ አዲስ ቫይረስ መኖሩ ይረጋገጣል፡፡ ዝርያው ግን የኮሮና ቫይረስ ነው፡፡ ለዚህ ነው የ2019 አዲሰ ኮሮና ባይረሰ የተባለው 2019 n-cov፡፡ ይህ ምርመራ ሲደረግ በወቅቱ፣ የጤና ባለሙያተኞችን ጨምሮ ወደ 800 ሰዎች መያዛቸው ይታወቃል፡፡ ቻይኖቹ በፍጥነት ሁኔታው ለአለም ህዝብ ማስታወቃቸው እንዲመሰገኑ አድርጓቸዋል፡፡ ችሎታቸውም የሚገርም ነው፡፡ አያድረገውና በኛ…(አልጨርሰውም)፡፡

ታዲያ ይህ ቫይረስ ከእንስሳት ወደ ሰው ተሻግሮ ይሆን በማለት ክትትሉ፣ በከተማው ውሥጥ ባለው የአሳ መሸጫ ሱቅ አካባቢ ነበር፡፡ ነገር ግን ወደኋላ እንደታየው ከአሳ መሸጫ ገበያው ሰፋ ብሎ በሌሎች ቦታዎች መገኘቱ ታወቀ፡፡

መሸጋገሪያ መንገድ

ትልቁ ፍራቻ ደግሞ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል ወይ ነው፡፡ ዘግየት ብሎም ቢሆን ከሰው ወደ ሰው መተላለፉ ተረጋገጠ፡፡ ሌለው ችግር፣ እንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የሚያስተላልፈው በህመም ላይ እያለ ነው ወይስ የህመም ስሜት ሳይሰማው ነው የሚለው፣ ለጤና ባለሙያተኞችና ለሌሎችም ቢሆን አብይ ጥያቄ ነው፡፡ ያልታመመ ሰው፣ ግን ለቫይረሱ የተጋለጠ፣ ቫይረሱን ሌላ ሰው የሚያስተላልፍ ከሆነ፣ ለቁጥጥርና ወይም ሥርጭቱን ለመገደብ ይከበዳል፡፡ እንደተፈራውም፣ ከጀርመን በኩል በቀረበ ሪፖርት፣ የበሽታው ስሜት በውቅቱ ያልነበራት ሴት ለሌሎች ማስተላለፏ ይረጋገጣል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከቻይና ወደ ጀርመን ለሥራ የሄደች ሴትዮ ከጀርመን ኑዋሪዎች ጋር ስብሰባ አድርጋ ወደ አገሯ ትመለሳለች፡፡ ከተስበሳቢው አንዱ ቀለል ያለ የሳል በሽታ ይዘውና ወዲያው ግን ያገግማል፡፡ ሲትዮዎ ግን ወደ አገሯ ስትመለስ፣ ትታመምና ምርመራ ሲደረግ፣ ቫይረሱ እንዳለባት ይታዋቃል፡፡ ይህ ሲሆን ሁል ጊዜ የሚደረግ፣ contact investigation የሚባል ከትትል ይደረጋል፡፡ ይህ ከአባለዘር በሽታዎች ጀምሮ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ሳንባ ነቀርሳን ጨምሮ፣ ለአካባቢው የመንግሥት አካል ሪፖርት ሲደረግ፣ መንግሥት፣ ተጋለጡ የሚባሉ ሰዎችን ስም ዝርዝር በመያዝ ክትትልና ምርመራ የሚያደርግበት የተለመደ አሠራር ነው፡፡ እስዎም ቢሆኑ፣ የጤና ቢሮው ሰዎች በርዎን ድንግት ቢየንኳኩ እንዳይገርምዎት፣ ማለቴ ድንገት ተጋልጠዋል ከተባለ ነው፡፡ ታዲይ ጀርመኖቹ ይህንን ክትትል ሲያደርጉ፣ ያ ቀለል ጉንፋን የያዘውና ያገገመው ሰው፣ አክታ ምርመራ ያሳየው ይኸው አዲሱ ቫይረስ መኖሩን ነው፡፡ ተጨማሪ ባደረጉት ምርመራ አራት ሰዎች መጋለጣቸው ይረጋገጣል፡፡ ይህ ዜና በታወቂው የኒው ኢንግላንድ መፅሄት ሲቀርብ፣ ባለሙያተኞቹ በፍራቻ ነው ያነበበብነው፡፡ የምንሠራውን ሥረ አቀራረብም ያከብድብናል፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ አንድ ሰው አመመውም አላመመውም ቫይረሱ አለበት ከሚባል ቦታ ከመጣ ተገልሎ እንዲቆይ የሚደረገው፡፡

መሸጋገሪያው ዋናው መንገድ፣ ቫይረሱ ካለበት ሰው ስድስት ጫማዎች ጠጋ ብሎ በትንፋሽ የሚወጣውን ቫይረስ መቋደስ ነው፡፡ በተለይም በቫይረሱ የተያዘ ሰው ሲያስለው ወይም ሲያስነጥሰው ለአይን የማይታዩ ቫይረሱን የያዙ ጠብታዎች አጠገብ ባለው ሰው አፍና አፍንጫ በሚዘልቁበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ በተጨማሪ፣ ቫይረሱ ያረፈባቸውን ዕቃዎች በመነካካት ወደ ሰው ሊተላለፍ እንደሚችል ነው፡፡ ይህ በርግጥ ባይረጋገጥም፡፡ አያድርስ፡፡ በህክምናው አለም፣ በዚህ ምክንያት፣ ቫይረሱ አለበት ለተባለ ሰው አፍና አፍንጫ ላይ የሚደረግ ማስክ ተሠጥቶ ለብቻው በተለየ ክፍል ውስጥ እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ የሕክምና ባለሙያው ወደ በሽተኛው ክፍል ሲገባ ግን፣ ከራስ ፀጉር እሰከ ጫማ ድረስ ተሸፍኖ፣ ጓንት አድርጎ፣ ለዚህ ጉዳይ ለህክምና ባለሙያተኞች የሚሠት የትንፋሽ ማስክና አይን የሚሸፍን መከለያ አድርጎ ነው የሚገባው፡፡ ያው ኢቦላ ላይ እንዳያችሁት ማለት ነው፡፡

መከላከልና ህክምና
አስከሁን ድረስ፣ አማራጭ የሆነው መንገድ ለቫይረሱ አለመጋለጥ ነው፡፡ አዲስ እንደመሆኑም፣ ከትባትም የለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን፣ እንደ ባህል አድርግን ልንይዘው የሚገባ፣ በተለይም ከላይ የጠቀስኩት የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስንም ታሳቢ በማድረግ የሚከተሉትን ነገሮች ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

  • እጅዎን በሳሙና ለ20 ሰከንዶች መታጠብ፡፡ ይህንን የሚያደርጉትም፣ ከሳሉ፣ ካስነጠሱ፣ አፍንጫዎን ከጠረጉ በኃላም ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን መፀዳጃ ቤት ደርሰው ሲመለሱ፣ ምግብ ከመብላትዎ በፊትም ማድረግ የሚገባዎት ነገር ነው፡፡ አጋጥሟችሁ ከሆነ፣ መፀዳጃ ቤት ገብተው ከተገለገሉ በኋላ እጃቸውን ሳይታጠቡ የሚወጡ ብዙ ሰዎች እይተው ይሆናል፡፡ ይህንን ሳይ፣ በበኩሌ፣ አንዳገሬ የአንገት ሰላምታ ብቻ ሠጥቼ የእጅ ጨበጣውን መተውን እመኛለሁ፡፡ በተለይ በኢንፍሉዌንዛ ወራቶች፡፡


  • ውሃ ከሌለ ደግሞ፣ እጅ ላይ የሚወለወሉ አልኮሎችን መጠቀም ይችላሉ፡፡ ይህ ለንፅህና የሚጠቀሙት አልኮል 60% አልኮል ያለው መሆኑን ያረጋግጡ፡፡


  • ካልታጠቡ ግን፣ አይንዎን፣ አፍንጫዎንና አፍዎን ከመነካካት ይቆጠቡ


  • ከታመሙ ሰዎች ጋር አለመገናኘት ይምረጡ፡፡ ያመመዎት ከሆነም፣ ለሌሎች ሲሉ ከቤት አይውጡ፣ ቤትም ውስጥ ቢሆን፣ ከተቻለ የተወሰነ ክፍል ውስጥ ብቻ ይቆዩ፡፡ ልብ ማለት የሚገባዎት፣ እነዚህ የቫይረስ በሽታዎች የሚጠናባቸው ሰዎች በዚህ ምክንያትም ህይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችል መገንዘብ ጥሩ ነው፡፡


  • የሚያስልዎትና የሚያስነጥስዎት ከሆነ፣ ቲሺው ካለ በዛ ሸፈን ያድርጉ፣ የተጠቀሙበትን ወዲያው ወደ ቆሻሻ መጣያ ያስገቡ፡፡ ከሌለ ደግሞ በእጅጌዎ ሸፈን አድርገው ይሳሉ ወይም ያስነጥሱ፡፡ ልብ ማለት ያለብዎት ስድስት ጫማ ርቀት አጠገብዎ ያለ ሰው ለቫይረሱ እንደሚጋለጥ ነው፡፡


  • በቤት ውስጥ ወይም ድንገት ቢሮ ከሄዱም፣ በእጅ የነኳቸውን ነገሮች በማፅጃ ማፅዳት ይኖርብዎታል፡፡ ብዙ ጊዜ የሚረሳው፣ የበሮች መክፈቻና መዝጊያ ነው፡፡ ተደጋግሞ የሚነካውም ነገር አሱ ሰለሆነ፣ እጀታዎቹን ማፅዳት ተገቢ ነው፡፡


ከዚህ በተጨማሪ እንግዲህ፣ የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል የሚመክረው ወደ ቻይና እንዳይጓዙ ነው፡፡ ይህ ባሁነ ሰአት ሲሆን ወደፊት የትኞቹን አገሮች እንደሚጨምር አይታወቅም፣ በተለይም በሽታው በስፋት ከተዛመተ፡፡

ሕክምናን በሚመለከት፡፡ ለዚህ ቫይረስ ተብሎ የተዘጋጀ ምንም አይነት መድሐኒት የለም፡፡ በአብዛኛው ድጋፍ ሰጭ ህክምና ነው የሚደረገው፣ ሌላ ተጓዳኝ በሽታ ካለ ለሱም ህክምና ይደረጋል፡፡ ብዙ ጊዜ የበሽታው ምልክት ከታየ ከሁለት ሳምንት በኋላ ከበድ ያለ የሳንባ ምች በሽታ የሚታይባቸውና እየከፋ ሲሄድም ሌሎች የስውነት ክፍሎች መድከም ይታያሉ፡፡

በቅርብ ጊዜ በወጣ ሪፖርት፣ ለኢቦላ ቫይረሰ የሚሠጠው መድሃኒትን መጠቀም የቻሉ ሀኪሞች ጠቆም ያደርጋሉ፡፡ አሱም ቢሆን በአሁኑ ጊዜ አማራጭ ከማጣት የተነሳ የሚደረግ ነው፡፡

እንግዲህ ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ከመታመምዎ ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ቻይና ተጉዘው ከሆነ፣ ወይም በዚህ ቫይረስ ተለከፈ ከሚባል ሰው ጋር ተገናኝተው ከሆነና፣ አሁን የህመም ስሜት የሚሰማዎት ከሆነ፣ ወደ ሆስፒታል ከመሄድዎ በፊት ደውለው እንዲያስታውቁ ይመከራሉ፡፡ ባለሙያተኞቹ ተዘጋጅተው እንዲጠብቁዎት ነው፡፡ መገንዘብ ያለብን ሁሉም ታማሚ የግድ ሆስፒታል መሄድም አያስፈልገውም፡፡ በቤት ሆነው ክትትል ሊደረግሎትም ይችላል፡፡