GOSH HEALTH


Community health 

education in Amharic 

እህል አጥቂውን ያጠቃል

ስለ ቅድመ ስኳር ወይም (Prediabetes ) ስለሚባል ክስተት ከዚህ በፊት በጎሽ ድረ ገፅ ፅሁፍ አስቀምጠን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በቅርብ ጊዜ በእንግሊዝ አገር የህክምና መፅሄት የቀረበን የጥናት ውጤት ለማከፈል እንወዳለን፡፡ ከዚህ ቀደም በቀረበ ፅሁፍ የስኳር ኢንዱሰትሪ ረቀቅ ባለ መንገድ ነብሳቸውን ከሸጡ ሳይንቲሰቶች ጋር በመሆን ለልብ ህመምና ሌሎች ችግሮች ተጠያቂ ምግብ ጮማ ነው በማለት ለአመታት በየመጠጡና በየምግቡ በፋብሪካ የተመረተ ስኳር በመጨመር ሲሽጡ መክረማቸው ግልፅ ነው፡፡ እንደ ትምባሆ ሁሉ ይህ በፋብሪካ የሚመረት ከመጠን በላይ የሆነ ስኳር ለስኳር በሽታ መንስኤ መሆኑን በድረ ገፃችን አስፍረናል፡፡ ሰሞኑን በቴሌቢዢን ከትልልቆቹ ለስላሳ መጠጥ አምራቾች የአንዱ ሥራ አስኪያጅ ያለ ሀፍረት እንዲህ ሲሉ ታይተዋል፡፡ ወደፊት የምናመርታቸው መጠጦቻችን የስኳር መጠናቸውን ቀንሰን አነስ ያለ መጠን ያለቸው እንዲሆኑ እየተዘጋጀን ነው በማለት አንድ ጥሩ ወሬ እየነገሩን ነው፡፡ ልብ ብሎ ላዳመጠና ለተመለከተ ሰው፤ ማክዳኖልድ ፍሩክቶስ የተባለው የስኳር አይነት በብዛት ያለባቸውን የምግብ አይነቶች ከሽያጭ መደርደሪያ እንደሚያወርዱ አስታውቀዋል፡፡ እንግዲህ የለስላሳ መጠጥ ሥራ አስኪያጇም የስኳር መጠን እንቀንሳለን ሲሉ፤ ፊት ለፊት ባያምኑም ስኳር ጉዳት እንደሚያሰከትል ያውቃሉ፡፡

ለማንኛውም በአማርኛ አባባል፡ ሶዳ የሚባል ቅጠል በደጃፊ አይበቀል ማለት ጥሩ ሳይሆን አይቀርም

ወደ ጥናቱ ልመልሳችሁና፡፡ የስኳር በሽታ ከመከሰቱ በፊት ቅድመ ስኳር የሚባለ ሁኔታ አለ፡፡ ሰዎች ካልተጠነቀቁና አስፈላጊውን ርምጃ ካልወሰዱ የስኳር በሽታ በገሀድ መከሰቱ አይቀርም፡፡ ከበሽተኞቻችን ጋር ስንወያይ፣ ጥያቄው ምን አይነት ምግብ ቢሆን ይሻላል ነው፡፡ ሀኪሞችም ብንሆን ስንቱን ምግብ ከልክለን እንችላለን? ይህ ጥናት ታትሞ ሲወጣ በጥሩ መንፈስ ነው የተቀበልነው፡፡

ባጠቃላይ ከፍተኛ የፕሮቲን መጠንና መጠነኛ የሆነ የካርቦሀይድሬት ምግብ የቅድመ ስኳር ሁኔታን ያሻሻለ መሆኑን ጥናቱ ይዘግባል፡፡

ይህ ጉዳይ ለምን አሳሳቢ እንደሆነ ለመረዳት በአሜሪካ ብቻ ወደ 86 ሚሊዮን የሚሆነ ሰዎች ቅድመ ስኳር ሁኔታ አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን አሳሳቢ በሆነ ደረጃ የስኳር በሽታ ሲከሰት ነው የሚታየው፡፡

ጥናቱ መጠነኛ ቁጠር ያለቸው ሰዎች የተሳተፉበት ቢሆንም ውጤቱ በጣም ገላጭ ነው፡፡ የተደረገው ነገር 24 አዋቂዎችን ከሁለት ወገን በመክፈል፤ አንዱ ወገን ከፍተኛ ፕሮቲን መጠን ያለበት (30 ፐረሰንት ፕሮቲን፣ 30 ፐርሰንት ጮማ ፣ 40 ፐርሰንት ካርቦሀይድሬት) ሌላው ወገን ደግሞ ከፍተኛ ካሎሬ ያለበት (15 ፐርሰንት ፐሮቲን፣ 30 ፐርሰንት ጮማ፣ 55 ፐርስንት ካርቦሀይድሬት) የተዘጋጁ ምግቦችን ለስድስት ወራት መመገብ ተጀመር፡፡ ጥናቱ ከመጀመሩ በፊትና ከስድስት ወር በኋላ የደም ምርመራዎች ተደረጉ፡፡

ቅድመ ስኳር የመሻል ወይም መሻር ምልክት የተባሉት ፤ ምግብ ሳይበሉ (ሰምንት ሰአት ፆም) በሚደረግ ደም ምርምራ የስኳር መጠን ከ100 mg/dl በታች መሆንና፤ ግሉኮስ ጠጥተው ከሁለት ሰአት በኋላ በሚደረግ ምርመራ መጠኑ ከ140 mg/dl በታች ሲሆን ነው፡፡

የጥናቱ ውጤት ያሳየው፡ ከፍተኛ ፕሮቲን ያለው ምግብ የተመገቡ ሰዎች በአስራሁለቱም ሙሉ በሙሉ የቅድመ ስኳር ሁኔታ መሻር ታይቷል፡፡ በቀሪዎቹ አስራ ሁለት ሰዎች ውስጥ አራቱ ብቻ ላይ ነው ይህ የመሻሻል ሁኔታ የታየው፡፡ በስታቲክሳዊ ስሌት ይህ ውጤት መሠረት ያለው ነው፡፡

ሌላው ደግሞ ሄሞግሎቢን A1c(HbA1c) በሚባል ምርመራ ከፍተኛ ፕሮቲን የተመገቡ ሰዎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ መጠኑ ዝቅ ሲል ተከስቷል፡፡ ይህ ምርመራ በደም ውስጥ የስኳር መጠን ለዘጠና ቀናት እንዴት አንደነበር የሚገልፅ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ ፕሮቲን የተመገቡ ሰዎች ኢንሱሊን የተባለው ሆርሞን በደንብ መስራት የሚችልበት ሁኔታ ተሻሽሎ የታየ ሲሆን፤ ለልብ ህመም አደጋ የሚያገልጡ ሁኔታዎች መሻሻልን ጨምሮ የኮለስትሮልና ሌላ የጮማ መጠን መቀነስና፤ ለልብ ህምም የሚዳርጉ በሰውነት የሚፈጠሩ አስጊ ኬሚካሎች መቀነስ ከፍተኛ ካሎሪ ከተመገቡት ሰዎች በላይ በተሻለ ሁኔታ ታይቷል፡፡

መርጠን ካልተመገብን እህል አጥቂውን ያጠቃል ወደሚለው አባባል መመለሳችን ነው፡፡ ሰለዚህ ኩኪዎች፣ ለስላሳ መጠጦች፤ ከፋብሪካ የሚመጡ ጭማቂዎችን ደህና ሰንብቱ ብሎ ወደ ፍራፍሬና አታክልት፣ ሥጋ፣ አሳ የመሳሰሉትን መመገብ ጥሩ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ዳቦ ከካርቦሀይድሬት ወገን ነው የሚመደበው፡፡ በየቀኑ የምንወስደውን የስኳር መጠን መቀነስ አስፈላጊ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አልኮሆል ማለት የመጨረሻ ውጤቱ ስኳር ነው፡፡ ስለዚህ ስሌቱ ውስጥ ማሰገባት ተገቢ ነው፡፡ ስኳር ተወደደ ማት ጥሩ ወሬ ነው፡፡ ቢቀርስ፡፡ መልካም ንባብ፡፡ አካፍሉ

አለም አቀፍ የዳያቤትስ ፌዲሬሽን ሰለ ጤናማ አመጋገብ ያወጣው ምክር

ይህ ምክር ስኳር በሽታን ለመከላከልም ታስቦ ነው፡፡

 1. መጠጥን በተመለከተ፡ ከፍራፍሬ ጭማቂ፣ ከሶዳ (ለስላሳ መጠጥ) እና ከሌሎችም በስኳር ከጣፈጡ መጠጦች ፋንታ ውሀ፣ ቡና፣ ሻይ ይምረጡ
 2. በቀን ከተቻለ ሶስት ጊዜ አትክልቶችና ያም አረንጓዴ ቅጠላ ቅጠሎችን ይመገቡ
 3. ከተቻለ በቀን ሶሰት ጊዜ የሚሆን አዲስ (fresh) ፍራፍሬዎች ይመገቡ
 4. መክሰስ ቢጤ ካስፈለገም፣ እንደ ኦቾሎኒ፣ የፍራፍሬ ቁራጭ ወይም በሰኳር ያልጣፈጠ እርጎ
 5. የአልኮል መጠን ቢሆን በቀን ከሁለት መጠጥ በላይ አይጠጡ
 6. ሥጋን በተመለከተ፣ በፋብሪካ ከተዘጋጀ ሥጋ ይልቅ የተመተረ ወይም የተቆረጠ የከብት ሥጋ፣ የዶሮ ሥጋ እና የአሳ ዝርያዎችን ይመገቡ
 7. ዳቦ ላይ የሚቀቡ ነገሮችን በሚመለከት በቾኮሌት የተቀመመ ማባያ ይልቅ፣ የኦቾሎኒ ወይም ለውዝ (Peanut butter) ይጠቀሙ
 8. ከነጭ ሩዝ፣ ነጭ ዳቦና ነጭ ፓስታ ከመመገብ Whole grain bread, Brown rice, or whole grain pasta, ይምረጡ
 9. ዘይትን በሚመለከት Unsaturated oil (የወይራ ዘይት olive oil, canola oil, sunflower oil) እንጂ ቅቤ፣ አይብ፣ የእንስሳት ጮማ፣ የኮኮናት ዘይት፣ ወይም Palm Oil) አይጠቀሙ


የሰውነት እንቅስቃሴን በተመለከተ የአለም የጤና ድርጅት ለተለያዬ ዕድሜ ላላቸው ሰዎች ያወጣው ምክር


 • ዕድሜያቸው ከ 5- 17 አመታት ውስጥ ያሉ ልጆች፣ በቀን ቢያንስ የ60 ደቂቃ ጠንከር ያለ የሰውነት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ


 • አዋቂዎች ከ18 – 64 ዕድሜ ክልል የሚገኙ ደግሞ በሳምንት ውስጥ፡ ከ150 ደቂቃዎች ያላነሰ ጠንከር ያለ የሰውነት እንቅስቃሴ ለምሳሌ (ፈጠን ያሉ እርምጃዎች፣ ሶምሶማ ሩጫ፣ ወይም አትክልት ሥራ) እነዚህ ባንድ ቀን ሳይሆን በሳምንቱ ውስጥ በተለያዩ ቀናት መሆን አለባቸው፡፡ ከልሆነም ቢያንስ ቢያንሰ በሳምንት ውስጥ 75 ደቂቃዎች የመሆን ጠንከር ያለ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖባቸዋል፡፡ ጠንከር ያለ ሲባል አንግዲህ በአብዛኛው ጊዜ ላብ እስከሚወጣቸው ድረስ የሚሆን ለማለት ነው፡፡


 • በዕድሜ ለበለፀጉ አዋቂዎች ደግሞ ተመሳሳይ ለሆነ ጊዜ ተመሳሳይ የሰውነት እንቅሰቃሴ ይመከራል ነገር ግን በዚህ ዕድሜ ክልል ላሉ ሰዎች ግን እንደ ችሎታቸው መጠን ጡንቻ የሚያጠነክሩ እንቅስቃሴዎች ጋር ተደባልቆ መሆን አለበት፡፡