​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

“ነቅሎ ተከላ” ከየት መጣ?

ይህን አባባል ስሰማ በጣም ገርሞኝም ነበር፡፡ ለመሆኑ ማን ነው እንዲህ አይነት አባባል ያመጣው ብዬ ራሴንም ጠየቅሁ፡፡ አንግዲህ በዚህ ርዕስ ሥር፣ የብዙ ታወቂ ግለሰቦች ህይወት ህልፈት ምክንያት ሰለሆነው ስለኩላሊት በሽታ ትንሽ ምክር ልስጥ ብየ እያሰብኩ፣ እንደ ልማዴ መረጃዎችን ለመስበሰብ ስጥር ጥሩ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ይህም  People to People, የተባለ የህክምና ባለሙያተኞች ድርጅት፣ አመታዊ ስብሰባውን በቨርጂኒያ በአሜሪካ ያካሂዳል፡፡ እኔም የዘንድሮውን ልካፈል ብዬ ጎራ አልኩኝ፡፡ የተገጣጠመው ነገር፣ የድርጅቱ የዘንድሮ የስብሰባ Theme (“Endstage Renal Disease in Resource Malaligned Countries; Issues of Ethics and Equity”) በሚል ርዕስ ስለ ኩላሊት በሸታ መሆኑም ገረመኝ፡፡ ከኢትዮጵያ የመጡ ባለሙያተኛ ሀኪሞች ብዙ ነገር አካፈሉን፡፡ እንደ ጋዜጠኛ ማስታወሻ መያዝ ጀመርኩ፡፡ ደሃና ገበያ ሲገጣጠም እንደሚባለው፡፡

በመጀመሪያ፣ መግቢያው ላይ ሰለጠቀስኩት፣ ተገቢ ያልሆነ አጠራር አንድ ልበል፡፡ በመሠረቱ ከዚህ ቀደም አንድ የሰውነት ከፍል በሌላ (ከሌላ ሰው) በመጣ ሲተካ፣ በአንግሊዝኛ transplant ይባል ነበር፡፡ ያ ግን ተቀይሮ፣ አሁን replacement ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ እናም በዚህ በአዲሱ አጠራር መሠረት፣ ትክክለኛው አባባል ትክ የሚለው ነበር፡፡ ለምሳሌ Renal Replacement Therapy የኩላሊት ትክ ህክምና፣ ወይም Liver Replacement Therapy የጉበት ትክ ህክምና ተብሎ ቢጠራ ለጆሮም ይስማማlል፤ ትክክለኛውም እሱ ነው፡፡ “ነቅሎ ተከላ”፣ የችግኝ ነው የሚመስለው፡፡ መቼም፣ በአሁኑ ጊዜ፣ የማህበራዊ ሜዲያውን፣ ያልታረመ አንደበት ያላቸው ሰዎች ሰላጥለቀለቁት፣ አነጋገርን የሚያርም የለም፡፡

የኩላሊት በሽታ መንስኤዎች እንደየሀገሩ የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዋናው አቢይ ነገር፣ ይህ በሽታ በአብዛኛው፣ የመጨረሻው ደረጃ እሰከሚደርስ ምንም ምልክት ወይም ስሜት ሰለማይሠጥ፣ ሰዎች ጉዳቱ የከፋ ደረጃ ከደረሰ በኃላ ነው የሚታዩት፡፡ ኩላሊት በመሠረቱ ዋናው ሥራው፣ ደምን ማጣራትና፣ ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በደም ውስጥ በሚገባው መጠን እንዲቆዩ ማድረግ ሲሆን፤ አስፈላጊ ያልሆኑ ኮምፓውንዶች በሽንት በኩል እንዲወጡ ያደርጋል፡፡ ለህክምና የምንወስዳቸው መድሐኒቶችን የመጨረሻ ውጤቶች በአብዛኘው ኩላሊቶቻችን ናቸው አጥበው በሽንት በኩል የሚያስወግዱልን፡፡ ይህ የተገለፀው ሥራ በከፊል ነው፡፡ አንድ ሰው ሁለት ኩላሊቶች ይኖረዋል ወይም ይኖራታል፡፡  

በአገራችን ይህ የኩላሊት በሽታ እየተበራከተ መምጣቱን ባለሙያተኛ ሀኪሞቹ ገልፀዋል፡፡ እኔን በጣም ያሳሰበኝና፣ ይህን ፅሁፍ፣ በሌለ ጊዜ ተበራትቼ እንድፅፍ ያደረገኝ አንድ ነገር ነው፡፡ ባደጉ በሚባሉ አገሮች የኩላሊት በሽታ የሚከሰትባቸው በዕድሜ የገፉ ሰዎች ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ ግን፣ በዕድሜ ያልገፉ ሰዎች ላይ መሆኑ ነው፡፡ በአብዛኛው ይህ የዕድሜ ክልል፣ የማህበራዊ ሜድያ ተጠቃሚዎችን ያካትታል፡፡ ሰለዚህ ልብ ብላችሁ ብታነቡ መልካም ነው፡፡ ወደ ኩላሊት ችግር ከመሻገሬ በፊት፣ መሠረታዊ መረጃዎችን ላካፍል፡፡

ኩላሊት ሥራውን በደንብ መሥራት ሳይችል ሲቀር፣ ማለትም ደም የማጣራት አቅሙ እያነሰ ሲሄድ ቸግር ያስከትላል፡፡ ሙሉ በሙሉ የደም ማጣራቱን ሥራ ማቆም ወይም በሕይወት ለመቀጠል በቂ ያልሆነ ደረጃ ሲደርስ፣ End Stage Renal Disease (ESRD) ይባላል፡፡ በአማርኛ፣ የኩላሊት ውድቀት ቢሆን ይቀራረባል፡፡ ከዚያ በፊት ግን በማዝገም የሚሄድባቸው የኩላሊት ድክመት፣ Chronic Kidney Disease (CKD) ይባላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ባንዳንድ ችግሮች ወይም በሽታዎች ምክንያት፣ ኩላሊት ከጤናማ ደም ማጣራት፣ ባጭር ጊዜ ውስት ወደ ኩላሊት ውድቀት ወይም ድክመት (Acute Kidney failure or Acute kidney injury) ሊሻገር ይችላል፡፡ በአንግሊዝኛ የሚባለው ነው፡፡

ለኩላሊት ድክመት ዋናኛ ምክንያቶች የሚባሉት፣ የደም ግፊት በሽታና የስኳር በሽታ ናቸው፡፡ የውጩን ልተወውና፣ በኢትዮጵያ ሲታይ፣ የኩላሊት ድክመት ካለባቸው ሰዎች 15.8 ፐርሰንት በደም ግፊት በሽታ አማካኝነት ነው፡፡ 3.2 ፐርሰንቱ ደግሞ በስኳር በሽታ ምክንያት ነው፡፡ የስኳር በሸታ እንደ መንስኤ መሆን ካደጉ አገሮች ጋር ሲነፃፀር በጣም አነስተኛ ደረጃ ነው፡፡ እኛን ያሳሰበን፣ ለኩላሊት መድከም ምክንያት የሆነው በአብዛኛው የሚታወቅ አለመሆኑ ነው፡፡ አጠገቤ ከነበረው ሀኪም ጋር ስንቀላለድ፣ “ዘይቱ” ይሆናል አልን፡፡ እንደውነቱ ከሆነ፣ ያ መረጃ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ምክንያቱ ካልታወቀ፣ እንዴት አድርጎ መከላከል ይቻላል?

ሌላው የቀረበው መረጃ የሚያሳየው፣ በአገሪቱ በዚህ የኩላሊት መድከምና ውድቀት የሚታይባቸው ሰዎች  ዕድሜ በ 20 -50 አመት መሆኑ ነው፡፡ ይህ እንደ አሜሪካ ካሉ ሀገሮች ለየት ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ በአሜሪካ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ላይ ነው የሚታየው፡፡ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ፣ ይህ የመጨረሻ ደረጃ እሰኪደርስ ድረስ ስሜት ወይም ምልክት የማይታይበት የኩላሊት መድከምና ውድቀት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደገርበት የሚገባው፡፡ 

ስለ ህክምናው ትንሽ እንበል፡፡ የኩላሊት ድክመት ከሆነ፣ ጥንቃቄ እየተደረገ፣ መንስኤ የሆነውን በሽታ በማከም፣ ኩላሊቱ ወደ ውድቀት እንዳይሄድ ይሞከራል፡፡ የኩላሊት ውድቀት ደረጃ ከደረሰ ግን፣ አማራጮቹ ውስን ናቸው፡፡ የመጀመሪያው፣ ደምን ማጣራት ነው፡፡ ሁለት አይነት አለ፣ ደም በቀጥታ በሚያጣራው መሣሪያ በኩል አልፎ ተመልሶ ወደ ሰውነት እንዲገባ ይደረጋል፡፡ ይህም፣ የውሀ መጠኑን፣ የኤሌክትሮላይትና ሌሎች ኮምፓውንዶች መጠን እንዲሰተካከል ያደርጋል፡፡ ሌላው በሆድ በኩል፣ ፈሳሽ ልውውጥ ማድረግ ነው፡፡ ባጠቃላይ፣ ይህ አሠራር፣ Dialysis ይባላል፡፡ ደም ማጣራቱ hemodialysis በሆድ በኩል የሚደረገው ደግሞ peritoneal dialysis ይባላል፡፡ እነዚህ ማጣራት ሥራዎች፣ በአብዛኛው በሳምንት ሶሰት ቀን ይደረጋሉ፡፡ እንግዲህ ትልቁ ችግር፣ ደሙን ለማጣራት የሚያሰፈልጉ ፈሳሾችና መሣሪያዎች መወደድ ነው፡፡ አንደ ሀኪሞቹ አገላለፅ፣ ለአንድ ጊዜ ደም ለማጣራት ከአንድ ሺ እሰከ አራት ሺ ብር ድረስ ያስከፍላሉ፡፡ በሳምንት ሶሰት ቀን ከሆነ ደግሞ፣ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሊከፍለው ቀርቶ ሊያስበው የሚችል ነገር አይደለም፡፡ ለዚህም ነው፣ ብዙ ሰዎች ይጀምሩና ያቋርጣሉ፡፡ እንግዲህ፣ ደም በወቅቱ ካልተጣራ፣ በሰውነት የሚቀረው፣ መውጣት የሚገባው ኮመፓውንድ፣ መስተካከል የሚገባው አሌክትሮላይት፣ እንዲሁም መቀነስ የሚገባው የውሀ መጠን ተደማምሮ የሕይወት ማለፍን ያስከትላል፡፡

ይህ ደግሞ በጣም አሳሳቢ የሚሆነው፣ በአለም የኩላሊት ድክመት ያለባቸው ሰዎች ወደ 105 ሚሊዮን የሚጠጉ በመሆናቸው፤ አብዛኛቹ ደግሞ በታዳጊ አገሮች ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ ሌላው አስፈሪው ነገር፣ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030፣ የኩላሊት ድክመት ያለባቸው ሰዎች ቁጥር በዕጥፍ ስለሚጨምር ነው፡፡ ከላይ እንዳየነው፣ ለረዥም ጊዜ ደም ማጣራቱ በገንዘብ አቅም ምክንያት የሚቻል ወይም የሚያዋጣ ነገር አይደለም፡፡ ሌላው አማራጭ የኩላሊት ትክ ህክምና ነው፡፡ ሲነፃፀር፣ ለረዥም ጊዜ በሚታይ የዋጋ መጠን፣ ይህ የኩላሊት ትክ ህክምና ረከስ ያለና የሚያዋጣ ነው፡፡ በተለይም በኛ ሀገር የሰው ጉልበት ሰለሚረክስ፣ ከውጭው አለም ጋር ሲወዳደር ርካሽ ነው፡፡ እሱም ቢሆን የራሱ ቸግር አለው፡፡ የኩላሊት ትክ ሲደረግ፣ የሌላ ሰው ኩላሊት በሌላ ሰው ሰውነት ውስጥ በሚተካበት ጊዜ፣ ሰውነት እንደ ባዳ አካል ቆጥሮ፣ Reject ለማስወጣት ይሞክራል፡፡ ያ እንዳይሆን rejection ለመከላከል መድሐኒት ይወሰዳል፡፡ መደሐኒቶቹ ደግሞ ውድ ናቸው፡፡ በአለም ሲታይ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የኩላሊት ትክ የተደረገላቸው ሲሆን፣ 90 ፕርሰንቱ ባደጉ ሀገሮች ነው፡፡ በድሀ አገሮች፣ እንኳን የኩላሊት ትክ፣ ደም ማጣራቱ ቢሆን ማግኘት የሚችሉት ከ10 ፐርስነት በታች የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡

እንግዲህ እንደምንም ብለው፣ በብዙ ጥረት፣ በኢትዮጵያ የኩላሊት ትክ ህክምና ተጀምሯል፡፡ ደም ማጣራቱም በተለያዩ የግል ሆሰፒታሎች የሚደረግ ሲሆን፤ ወደ 800 ሰዎች ደም ማጣራት ይጀምሩና፣ በወጭው ምክንያት አብዛኞቹ ከሶሰት ወራት በላይ መቀጠል እንዳልቻሉ መረዳት ተችሏል፡፡ የትክ ህክምናው ደግሞ በ126 ሰዎች ላይ ተደርጎ፣ 91 ፐርሰንቱ የተሳካ እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ትክ ኩላሊት የመጣው በህይወት ካሉ ዘመዶች የተሠጠ ነው፡፡ አንድ ሰው ሁለት ኩላሊት ቢኖረውም፣ ጤናማ ከሆነ በአንድ ኩላሊት መኖር ሰለሚችል ነው፣ አንደኛውን ሌላ መሥጠት የሚችለው፡፡ የአገሪቱ ህግ፣ ህገ ወጥ የአካል ንግድ እንዳይፈጠር ትክ ኩላሊት መሥጠት የሚችለው የተረጋገጠ ዝምድና ወይም ግንኙነት ያለው ሰው ይላል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሀገር፣ ባለው ደካም ኤኮኖሚና የሰዎች ገቢ መጠን፣ ለዚህ ነገር በጀት ማውጣት እንደሚያስቸግረው ግልፅ ነው፡፡ ካለው በጀትም ለሌሎቸ በሽታዎቸ ማብቃቃት ይኖርበታል፡፡ ሰለዚህ የኩላሊት ድክመት ወይም ውድቀት ከመፈጠሩ በፊት መደረግ ሰለሚገባው ነገር እንነጋገር፡፡

  • በሸታው በዕድሜ ለጋ የሆኑ ሰዎች ላይ እንደሚከሰት
  • ውድቀት ደረጃ እሰከሚደርስ ምንም ምልክትና ስሜት ሰለማይሠጥ
  • ውድቀት ደረጃ ከደረሰ ደግሞ፣ ህክምናው በበቂ መጠን  ሰለሌለ
  • ህክምና ቢኖር እንኳን፣ ወጭው የሚቻል ስላልሆ


የኩላሊት ድክመትና ውድቀትን ለማስቀረት፡
የበሽታው መንስኤ የሆኑት ሌሎች በሸታዎችን በጊዜ ማወቅና በቂ ህክምናና ክትትል ማድረግ
ከላይ እንደተጠቀሰው፣ የደም ግፊት ከዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ስለሆነ፣ የደም ግፊቱን መጠን ወደ ጤናማ ደረጃ ማውረድና መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡ መድሀኒት በትክክል መውሰድና በሀኪም ክትትል ማድረግ፡፡
በአሜሪካ፣ የስኳር በሽታ ከዋና ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ ሰለዚህ የስኳር በሽታን ችላ ሳይሉ፣ ተገቢውን የምግብ መጠንና አይነት በመመገብ የስኳር መጠኑን ጤናማ መጠን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡
እንዳንድ መድሀኒቶች፣ በተለይም ለህመም የሚሠጡ እንደ ሞትሪን፣ ናፕሮሲን የመሳሰሉትን አጠቃቅም በጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ መድሐኒቶች በተለያዬ ስም ለተገልጋዩ ስለሚቀርቡ፣ ያለ ሀኪም ትዛዝ መገዛት ስለሚችሉ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡
ዋናው ነገር ግን፣ የኩላሊት ቸግር መኖሩን ለማወቅ መጠነኛ ጠቋሚ ምርመራዎች ይደረጋሉ፡፡
አንደኛው፡ የሽንት ምርመራ ሲሆነ፣ በሽንት ውስጥ ተገቢ ያልሆነ የፕሮቲን መጠን የሚወጣ ከሆነ ቸግር መኖሩን ይጠቁማል፡፡
ሁለተኛው ምርመራ ደግሞ በደም የሚደረግ ሲሆን፣ የኩላሊት ደም የማጣራት አቅሙን በአሀዝ ወይም በቁጥር ማወቅ ይቻላል፡፡ በአንግሊዝኛ Estimated Glomerular filtration rate (eGFR) ይባላል፡፡

እንደኔ ከሆነ፣ ሁሉም ሰው ከላይ የተጠቀሱትን ምርመራዎች ቢያደርግ መልካም ነው፡፡ ይህንን ያልኩበት ምክንያት፣ ለአብዛኛው የኩላሊት ድካም ምክንያት መንስኤ አይታወቅም ሰላሉ ነው፡፡ ካልታወቀና በሽታው ስሜት የመይሠጥ ከሆነ፣ አስቀድሞ ቀላል ምርመራ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ግን የደም ግፊትን መጠን ማወቅም ጥሩ ነው፡፡ እሱም ቢሆን በአብዛኛው ስሜት አይሰጥም፤ እንደገናም ካልተከታተሉት ለኩላሊት ድክመትና ውድቀት ምክንያት ይሆናል፡፡

መልካም ንባብ

ለሌሎች አካፍሉ