​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Health and History

Community health 

education in Amharic 

የሚያልፍ ዝናብ አይምታህ! 
የሚያልፍ ኮቪድም አይያዝህ፣ በሚያልፍ ኮቪድ ሰውን አታስይዝ

የኮቪድ-19 ክትባቶች  11/17/2020
ሰሞኑን ተስፋ የሚሠጡ ግኝቶች የተከሰቱበት የኮቪድ ክትባቶችን በተመለከተ በተከታታይ ዜና ማሠራጫዎች ሲያቀርቡ ታይቷል ወይም እይታየ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ክትባት መከላከያ እንጂ በበሽታው ከተያዙ በኋላ ለህክምና የሚሠጥ ነገር አይደለም፡፡ ሰለ ክትባት ከመግለፄ በፊት ግን ሰሞኑን፣ Herd Immunity የሚባል ነገር ተነስቶ አከራካሪና አስቆጪ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡ ይህንን Herd Immunity ይካሄድ ብለው የመከሩ ሰዎች፣ ሰብዕና የጎደላቸው ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ በመሠረቱ Herd Immunity ማለተ፣ የህብረተሰብ የጋራ የመከላከያ አቅም ማለት ነው፡፡ በዝርዝር ሲታይ፣ እንደ ኮቪድ-19 አይነት ወረርሽኝ ሲከሰት፣ ምንም የመከላከያ ዘዴ ሳይሰተገበር፣ የታመመው ታሞ፣ የሞተው ሞቶ፣ ቀሪው ሰው ለበሽታው መከላከያ የሚሆን አንቲቦዲ ሲኖረው በሽታው መዛመት አቁሞ በዛው ይከስማል ነው፡፡ ምክንያቱም አዲስ የሚያዝ ሰው ከሌለ፣ የሚጋለጠውም ሰው እንቲቦዲ ወይም መከላከያ ካለው በበሽታው ሰለማይያዝ ነው፡፡

ይህ Herd Immunity የማህበረሰብ የመከላከያ አቅም፣ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው፣ ከህብረተሰቡ ውስጥ ምን ያህሉ ሰው ለበሽታው ሲጋለጥና በሰውነቱ ውስጥ የመከላከያ አቅም ወይም እንቲቦዲ መፍጠር መቻሉ በአሃዝ ግብ ሲኖረው ነው፡፡ በአብዛኛው እንደ በሽታው ቢሆንም፣ ከስልሳ አስከ ሰባ በመቶ የሚሆነው ሰው ለበሽታው መጋለጥ ይኖርበታል፡፡ እዚህ ላይ ግን፣ የበሽታው የመሠራጨት አቅምም ወሳኝ ይሆናል እንደ ኮቪድ-19 ያለ በሽታ ከአንድ ሰው ተነስቶ ስንት ሰው ላይ ይሻገራል የሚለው ጥያቄም ይታያል፡፡ እንደምናየው ከሆነ፣ በመሠራጨት አቅም ባለ ዝናና ሪኮርዱን የያዘው ሚዝልስ ወይም ኩፍኝ የሚባል፣ በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት በሽታ ነው፡፡ ከተጋለጡ ሰዎች ዘጠና ፐርስንቱ መከላከያ ከሌላቸው (በክትባት ወይም በተፈጥሮ) በስተቀር በሚዝልስ ቫይረስ እንደሚያዙ ነው፡፡

ይህ አዲሱ ጎበዝ፣ ኮቪድ-19፣ በደረጃ ማለትም በመሠራጨት አቅም ከሚዝልስ ቀጥሎ ይገኛል፡፡ አትጠራጠሩ ከሰው ወደ ሰው የመሸጋገር ችሎታውን ተክኖታል፡፡ እና በዚህ ደረጃ፣ Herd Immunity ለመፈጠር በበሽታው መጋለጥ ያለባቸው ሰዎች እሰከ ሰማንያ ዘጠና ፐርሰንት ድረስ ይሄዳል፡፡ እንግዲህ፣ አኮኖሚው ሞተ ወይም ሊሞት ነው የሚሉ ሰዎች፣ በሽታውን እንዳመጣጡ አንልቀቀውና የዳነው ድኖ ወደ ሥራችን እንመለስ ብለው፣ ያውም ሳይንቲሰት ተብየዎች ፕሮፖዛል አቅርበው፣ አሁን ሽኝቱን አልቀበልም ያሉት የአሚሪካው ፕሪዚዳንት አማካሪ ሳይቀር ይህንን ሀሳብ ከወደቤተ መንግሥት በኩል አሰምተው ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ ቁጣ ያሰነሳው ያለ ነገረ አልነበረም፡፡ ልብ በሉ

1ኛ፡ በሽታው እንደልቡ ይሠራጭ የሚሉ ሰዎቸ፣ በማስክ የማያምኑ ለመሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ዋናው ነገር፣ ለምሳሌ የአሚሪካ ህዝብ ሶስት መቶ ሚሊዮን ነው ቢባል፣ አስከ ዘጠና ፐርስንቱ ይጋለጥና Herd Immunity ይፈጠር ሲባል፣ በዚህ ምክንያት የሚሞተውን ሰው ቁጥር እንደ ሂሳብ ማወራረጃ ነው የቆጠሩት፡፡ ገምቱ፣ ከአስር ሚሊዮን ሰው ዕሩብ ሚሊዮን የሚሞት ከሆነ፣ በቀላሉ ከሁለት መቶ ሃምሳ ሚሊዮን ሰው ምን ያህል ይሞታል?

2ኛ፡ አስቀያሚው ነገር፣ አስካሁን በድርሻ ሲታይ ከሚገባቸው ከህብተሰቡ ቁጥር ውክልና ወይም ፐርስንት መጠን በላይ እነማን እንደሚሞቱ ገልፅ ነው፡፡ ይህንን ፅሁፍ ማንበብ የቻላችሁ በሙሉ በዚህ በሚጎዱት ሰዎች ወገን ነው የምትመደቡት፡፡ እነዚህ ሰዎች አንግዲህ ጥቁሮች፣ ሂስፓኒኮች ወይም የነጭ ዠርያ ያልሆኑ ናቸው፡፡ ይሀ ሁኔታ ግልፅ ሆኖ እያለ በሽታው እንደልቡ ይራወጥ ማለት፣ በፖሊሲ ደረጃ፣ አጠያያቂ ነው፡፡

3ኛ፤ በሽታው ያለ ገደብ ከተለቀቀ፣ ኢኮኖሚውን መጉዳቱስ ይቀራል ወይ? ሰው አልባ ኢኮኖሚስ አለ ወይ?

4ኛ፤ Herd Immunity ይፈጠር ሲባል፣ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ለቫይረሱ የተፈጥሮ መከላከያ ማበጀት አለባቸው፡፡ ያ የመከላከያ አቅም ወይም እንቲቦዲ መጀመሪያውኑ መልሶ ከመያዝ ያስጥላል ወይ? የሚያስጥል ከሆነ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል? የሚሉ ጥያቄዎች መልስ ግልፅ ባልሆነበት ሁኔታ፡፡ በሽታውን ልቀቁተን የፈጠረው ይፈጠር ማለት አደጋው ቢጨምር እንጂ አያንስም፡፡

አንግዲህ በHerd Immunity በሚመለከት የተነሳውን ውዝግብ ተከታተላችሁ፡፡ በዚህ ላይ እያወቁ በፖሊሲ ደረጃ መተግበር፣ ወይም አቅም አንሶ መከላከያው መተግበር አለመቻል አለዚያም አገራችን ላይና እዚህም ስፋት ባለው በፖለቲካው የተጠመደ ህብረተሰብ ክፍል በምን ግዴ የመከላከያ መንገዶችን አለመተግበር ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡

ይልቁንስ ወደ ሁለተኛው የHerd Immunity መፍጠር ወደሚቻልበት ሁኔታ እንመለስ፡፡ ይኼኛው ደግሞ፣ በሽታውን ልቅ በመስደድ ሳይሆን፣ በክትባት በቂ የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል በመከተብ፣ ቫይረሱ እንዳይሠራጭ ወይም እንዳይዛመት ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ የሁለቱ ክትባቶች ውጤት ሲገለፅ የተስፋ ስሜት የሠጠው፡፡ የሁለተኛው ክትባት ውጤት ሲነገር፣ ገበያ ደርቶ እንደነበር፣ ወል ስትሪት የሚከታተሉ ሰዎች ያዩት ነገር ነው፡፡

በዚህ ክትባት አሠራር ላይ ከስድስት በላይ የሚሆኑ ካምፓኒዎች እየሠሩ ነው፡፡ ሁለቱ ቀድመው ቢወጡም፣ ሌሎች አሉ ማለት ነው፡፡

ከዚህ በፊት ክትባቶች ሲሠሩ፣ ለህብረተሰቡ ከመቅረባቸው በፊት ከጥንስስ እስከ መጨረሻው ውጤት ድረስ ተሸግረው የሚያልፉባቸው ደረጃዎች አሉ፡፡ እነሱም ፌዝ (Phase) 1 – 4 ድረስ ናቸው፡፡ ለውጤት ለመብቃትና አገልግሎት ላይ ለመዋል ረዥም ጊዜ ይወስድባቸውል፡፡ አሁን የብዙዎች ጥያቄ የሆነው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ክትባቶች ውጤታቸው እየተገለፀ ነው ሲባል፣ እንዴት ሆኖ፣ የትኛውን ደረጃ ቢዘሉ ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጤት የበቁት የሚል ነው፡፡ አግባብ ያለው ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ለሰዎች የሚሠጥ ክትባትም ሆነ መድሓኒት ከሁሉም በፊት የሚያደርሰው ጉዳት መታወቅም ሰላለበት ነው፡፡ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን ከሆነ፣ አንዴት ተደርጎ ለህዝብስ ይቀርባል፡፡ ይህንን በሚመለከት፣ ጥናቶች በሚካሄዱበት ጊዜ፣ ጥናቱን ከሚያካሂዱት ሰዎች ብሎም፣ ከጥናቱ ጋር የተያያዘ ሳይነሳዊም ይሁን ወይም የገንዘብ ንክኪ የሌላቸው፣ ነፃ የሆኑ፣ በአበዛኛው ባላሙያተኞች፣ ጥናቱ ከመጀመሪየ ተነስቶ በየደረጃ የሚያሳያውን ጉዳት የሚከታተሉ ይመደባሉ፡፡ ህግ ነው፡፡ የነዚህ ሰዎች ቡድን በምህፃረ ቃል DSMB (Data Safety Monitoring Board) ይባላል፡፡ አደጋ ካዩ ጥናቱን የማስቆም መብት አላቸው፡፡ ታስታውሱ ከሆነ፣ በአንደኛው ጥናት ላይ፣ ክትባቱን የወሰደ ግለሰብ ታሞ፣ በዚያ ግለሰብ ምክንያት ብቻ ጥናቱን የሚያጠናው ካምፓኒ፣ ጥናቱን ለማቆም ተገዶ ነበር፡፡

ሁለተኛ፣ አነዚህ ካምፓኒዎች የጥናታቸውን ውጤት ቢያቀርቡም፣ ሌላ መንግሥታዊ ድርጅት፣ ጥናቱን በዝርዝር ተመልከቶ ፈቃድ ካልሠጠ አገልግሎት ላይ አይውሉም፡፡ ይህ የመንግሥት አካል ደግሞ በምህፃረ ቃል FDA ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡ የዚሀ መሥሪያ ቤት ሠራተኞቸ ደግሞ፣ ከዚህ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች መድሐኒት፣ ክትባት፣ የህክምና መሣሪያ ከሚያመርቱ ኩባንያዎች ጋር ልክልክ እንዳይኖራቸው ጥብቅ ቁጥጥር አለባቸው፡፡ ሰለዚህ ነፃ ናችው ማለት ይቻላል፡፡

የጥናቱን ሂደትና ውጤት የሚከታተሉ ነፃ የሆኑ ሰዎች ቡደኖች መኖራቸውን ከተመለከትን፡፡ የክትባቱ ውጤት ቶሎ እንዴት ለህዝብ ይደርሳል ለሚለው ጥያቄ፤ መታወቅ ያለበት፣ እነዚህ ጥናቶች ቶሎ ለመድረስ ተብሎ አንዱን ደረጃ ዘለው ወደ ሌላኛው እንደማይሄዱ ነው፡፡ ለምሳሌ ፌዝ አንድን ሠርቶ ፌዝ ሁለተን ሳያጠናቅቁ ወደ ፌዝ ሶስት መሄድ አይችሉም እያደረጉም አይደለም፡፡ በአብዛኛው ጊዜ የሚወስደው ነገር፣ ፌዝ አራት ውስጥ የተካተተው፣ ክትባቱን በስፋት ማምረትና ለህዝብ ማድረስ ነው፡፡ ይህም የፌዝ ሶስትን ውጤት ጠብቆ ነው፡፡ አሁን የሆነው፣ ፊዝ ሶስት እየተሰራ እያለ ፌዝ አራት በተደራቢ መሠራቱ ነው ሊያፈጥነው የቻለው፡፡ የፌዝ ሶስት ውጤት ሳያልቅ ወደ ማምረቱ መሄድ አደጋው የገንዘብ ኪሳራ ነው፡፡ ምክንያቱም የፌዝ ሶስት ውጤት የሚያሳየው ክትባቱ ሰው ላይ ጉዳት አለውና ለአግልግሎት አይውልም ቢባል፣ ያ ሁሉ የተመረተ ክትባት ይደፋል ማለት ነው፡፡ እዚሀ ላይ ነው እንገዲህ ባለሀብቶችና መንገሥት በመተባበር፣ ኪሳር ከመጣ ይምጣ በማለት በሚሊዮኖች የሚቀጠር ብር አውጥተው ለሥራ ይዋል በማለታቸው፣ ደረጃ ሶስትና ደረጃ አራት እኩለ አብረው በመሄዳቸው ክትባቱ ለህዝብ የሚቀርበብተን የጊዜ ገደብ በጣም ያሣጠሩት፡፡

ባጭሩም ቢሆን ሰለ ክትባቶቹ እንነጋገር፡፡ የመጀመሪያው ፋይዘር የሚባል ኩባንያ ያቀረበው ክትባት (በነገራችን ላይ ፋይዘር የክትባቱን ጥናት በራሱ ገንዘብ ነው ያካሄደው፣ ማለትም ከመንግሥት አስቀድሞ የወሰደው ነገር የለም)፣ ውጤቱ መቶ ሰዎች ለባይረሱ ቢጋለጡ ዘጠናው ሳይያዙ ቀርተዋልና ስለዚህ ዘጠና በመቶ በሚሆኑ ሰዎች ላይ በሽታውን መከላከል ወይም ማስጣል ይችላል ነው፡፡ አስተውሉ፣ ክትባቱን ወስደው ግን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አሉ፡፡ አነሱም ከመቶ አስሩ ማለት ናቸው፡፡

ይህ ክትባት የሚሠጠው በሶስት ሳምነታት ልዩነት ሁለት ጊዜ ነው፡፡ ሁለተኛው ክትባት ከተሠጠ ከሳምነት በኋላ ዘጠና ፐርሰንት የመከላከል ችሎታ አሳይቷል፡፡ ክትባቱን ከጀመሩ ከውር በኋላ ማለት ነው፡፡  ትልቅ ችግር የሆነው፣ ክትባቱን ለህዝብ ለማድረስ፣ ክትባቱ ማይነስ 70 በሆነ ዲግሪ ሲንቲግሬድ ቀዝቃዘ ሁኔታ መቀመጥ አለበት፡፡ ያ ማለት የአንታርቲካ ክረምት ወራት ማለት ነው፡፡ ይህንን ያህል ቅዝቃዜ መፍጠር የሚችል ማቀዝቀዣ ደግሞ በየቦታው ቀርቶ ትልልቅ ማዕከሎች ላይ የማይገኝ ነገር ነው፡፡ እንግዲህ ታዳጊ አገሮችን ማሰብ ነው፡፡ ያም ሆኖ የሚደረገው ተደርጎ ቅድሚያ በማውጣት ክትባቱን አስቀድመው የሚወሰዱ ሰዎች እንዲያገኙት ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የቅድሚያ ሁኔታ የመጣው ሁሉንም መከተብ የሚገባውን ሰው ለመክተብ በቂ ክትባት ማምረት አለመቻሉ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ አያለ፣ ሌላው የክትባት ጥናት የሚያካሂደው ሞደርና የተባለ ኩባንያ፣ የኔ ክትባት ጥናት ውጤት፣ ከመቶ ዘጠና አምስቱን (94.5) ያስጥላል በማለት የተሻለ ውጤት ይዞ ቀረበ፡፡ ይህ ክትባት እንደ ፋይዘሩ ሁለት ጊዜ የሚሠጥ ነው፡፡ ትልቅ ጠቀሚታ የታየው ግን፣ ክትባቱን ለማስቀመጥ ሆነ ለማጓጓዝ እንደ ፋይዘሩ ክትባት በረዶ ቤት የማያስፈልገው መሆኑ ነው፡፡ ክትባቱ ከ 36 ዲግሪ አስከ 46 ዲግሪ ፋራናይት በሆነ ቦታ መቀመጥ ይችላል፡፡ ያ ማለት የተለመዱ ክትባት በምናገኝባቸው ቦታዎች ሁሉ ክትባቱ መሠጠት ይችላል፡፤ ለታዳጊ አገሮች፣ ክትባቱን በጊዜ ማግኝት ከቻሉ፣ የትራንስፖርት ችግር የለም፡፡ ሆኖም የማምረት ችሎታው መላውን ህዝብ ማዳረስ የማየቻል በመሆኑ ቅድሚያ ክትባት መውሰድ የሚገባቸው ሰዎች በቅድሚያ እንዲያገኙ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ለቀሪው ህዝብ ከመዳረሱ በፊት ወራቶች መጠበቅ ሊኖርብን ነው፡፡ ይህ ወሳኝ ነገር ነው፡፡

ዋናው ነገር ደግሞ የጥናቶቹ ውጤት የሚያሳዩት፣ ክትባቱን በወሰዱ ሰዎች ላይ የታየ አሳሳቢ ችግር የለም ነው፡፡ የሞደርናው ክትባት ያሳያው (No safety concern) የሚል ማጠቃለያ እንዲሠጥ አድረጎታል፡፡ የቀደመው አገላለጥም በፋይዘር የተጠናው ክትባት ላይመ የታየ ነው፡፡ የፋይዘሩ ክትባት፣ ዕደሜያቸው ከ12 አመታት በታች ለሆኑ ልጆች ገና ጥናት ሊያደርግ አቅዷል፤ አስከዛ ድረስ ግን ለነዚህ ልጆች አይሠጥም ማለት ነው፡፡

እንግዲህ ተስፋው፣ በክትባት አማካኝነት፣ ህዝቡ መከላከያ አበጅቶ በቫይረሱ እንዳይያዝ፣ መልሶም እንዳየሠራጭ ለማድረግ የመጠውን ወረርሽኝ ለመመለስ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ይህን ጥቁር ደመና መሻገር የምንችልበት ሁኔታ ይመጣል ማለት ይሆናል፡፡ ለዚህ ነው የሚያልፍ ወረርሽኝ አይያዝህ ያልኩት፡፡

ነገር ግን ልብ ካላችሁ፡፡ ክትባቱ ባንድ ጊዜ ለመላው ህዝብ መዳረስ አለመቻሉ፣ ጊዜው እየረዘመ ሰለሚሄድ ብዙ ሰዎች አደጋ ላይ ይወድቃሉ፡፡ ለዚህ ነው ክትባቱ ቢጀርም፣ ኮቪድ -19 ለመከላከል ማድረግ የሚገባንን ጥንቃቄዎች መቀጠል ያለብን፡፡ ክትባቱን የወሰደ ሰውም ቢሆን፣ በሽታው ባካባቢው በቁጥጥር ስር ውሎአል ቢባልም ጥንቃቄውን ማቆም አይኖርበትም፡፡ ክትባቶች መቶ ፐርስነት የሚከላከሉ አለመሆናቸውን መገንዘብ ያሻል፡፡ ትልቁ ጥያቄ ደግሞ፣ በክትባቱ አማካኝነት በሰውነት ውስጥ የተፈጠረው በቫይረሱ እንዳንያዝ የሚረዳን አንቲቦዲ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አለማወቃችን ነው፡፡ ውሎ አድሮ መታወቁ አይቀርም፡፡ 

እናም አልፎ የሚሄድ ከሆነ፣ አልፎ በሚሄድ ባይረስ መያዝ ከዛም ለሌሎች አሳልፎ መሰጠቱ በብዙ መልክ ተገቢ አይደለም፡፡ ከመከላከያዎች ሁሉ ዋነኞቹ ማስክ ማድረግና የአካል ርቀት መጠበቅ ነው፡፡ የሰዎች ስብስቦችን ማስቀረት፡፡ በቤትዎ ውስጥ በአንድ ጣራ አብሮት የማይኖር ከሆነ፣ ቤተሰብም ሆነ ጓደኛ ጋር አለመገናኘት፤ በተለይ በቤቶች ወይም በክፍሎች ውስጥ፡፡ በአሜረካ ለምትኖሩ፣ የዘንድሮ የምስጋና ቀን (Thanks Giving) በቤቱ ውሰጥ አብረው ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ብቻ እንዲሆን ነው የሚከረው፡፡ ህዝቡን ለማረጋጋት በማለት፣ ግድየለም ሁለት ወይም ሶስት ቤተሰብ፣ ከአስር ሰው ያልበለጠ የሚባለው ምክር ትክክልም አይደለም፡፡ ይልቁንስ ቁጥር ሳይጎድል ለመጭው ምስጋና ቀን መገናኘት አይሻልም ወይ?