በቅርብ የተከሰተው አዲስ የኮሮና ቫይረስ
ይሄ ነገር ማቆሚያ የለውም ወይ?


 በዚህ ወቅት ደግ ያልሆነ ነገር መናገር በርግጥ ይከብዳል፡፡ ነገር ግን ማወቁም ጥሩ ነው፡፡ ሁሉንም እንዳመጣጡ ማሰተናገድም ጥሩ ነው፡፡ ኮሮናን በሚመለከት ጥሩ ዜናም እናም ሌላ አሳሳቢ መረጃም አለ፡፡ በመጀመሪያ አሳሳቢ የሆነውን እንመልከት፡፡

የዚህ ቫይረስ ሥርጭት በቀጠለ ቁጥር አዳዲስ የቫይረሱ ዝርያዎች አንደሚፈጠሩ ለማንም ግልፅ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ በአለም አቀፍ የጤና ደርጅት ዘገባ መሠረት ከትትል የሚደረግባቸው አስራ አምስት የሚሆኑ አዳዲሰ የቫይረሱ ዝርያዎች አሉ፡፡ ነገር ግን፣ ከነዚህ አዳዲስ ቫይረሶች መሀከል በአሳሳቢነት ደረጃ የሚመደቡ ዴልታን ጨምሮ አራት ቫይረሶች ሲኖሩ፡፡ ሌሎች ትኩረት የሚሠጥባቸው ሁለት አዲስ ቫይረሶች አሉ፡፡ ከነዚህ መሀል አንደኛው ወደ አሳሳቢነት ደረጃ ባይደርስም፣ የባህሪ ክፋት ያለው መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የዛሬ ርዕሳችን ይህ ክፉ ባህሪ ስላለው አዲስ የቫይረስ ዝርያ ነው የምንነጋገረው፡፡

እንደሚታወቀው ቫይረሶችን መጀመሪያ በተገኙበት አገር እንዳይጠሩ ተብሎ በግሪክ አልፋቤቶች ስም መጠራት ከጀመሩ ሰንብተዋል፡፡ ይህ አዲስ ቫይረስ ሚዩ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን መጀመሪየ በደቡብ አሜሪካ ከምትገኝ ኮሎምቢያ ከምትባል አገር መነሳቱ ይታወቃል፡፡ አሳዛኝ ሆኖ፣ ከኮሎምቢያ ወጥቶ ወደ 39 ሌሎች አገራት ተሠራጭቷል፡፡

 ከላይ በሠንጠዡ እንደምታዩት የተነሳበት ወይም የተገኘበት ጊዜ ተዘግቧል፡፡ ይህን ቫይረስ ክፉና አስፈሪ ያደረገው ነገር አለ፡፡ ይሀም ሰዎች በሌላ የኮሮና ቫይረስ ከተያዙ በኋላ በሰውነታቸው ውስጥ የሚፈጠረው የመከላከያ አቅም (እንቲቦዲ) ይህንን ቫይረስ ምን ያህል ያመክነዋል? ከዚህ በተጨማሪም የኮቪድ ክትባት የወሰዱ ሰዎች በሰውነታቸው ውስጥ የሚፈጠረው መከላከያ ሀይል (አንቲቦዲ) ቢሆን ምን ያህል ይንን ሚዩ የተባለ ቫይረስ ያመክነዋል? የሚሉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

እናም ይህን በተመለከተ፣  መጀመሪያ ከቻይና በኩል የመጣ ዘገባ የሚያሳየው፣ ይህ ቫይረስ የኮቪድ ክትባት ከተወሰደ በኋላ ለሚፈጠረው አንቲቦዲ የሚሠጠው ምላሽ በጣም ዝቅ ያለ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ማለት ክትባቱ ይህንን ቫይረስ የማምከን ሀይሉ በጣም ደካማ ነው ማለት ነው፡፡ አንግዲህ ይህ ጥናት የተካሄደው በቻይና ሲሆን የኮቪድ ክትባቱ አይነት ደግሞ አሠራሩ ለየት ያለ ነው፡፡ መግለፅ አለብኝ፡፡ የቻይናው ክትባት የሚጠቀመው ራሱ የኮሮና ቫይረሰን ተመልሶ እንዳየራባ በማሰናከል ወይም መራባት የማይችል በማድረግ በክትባት መልክ መሠጠት ነው፡፡ በአንግሊዝኛው አጠራር Inactivated vaccine ይባላል፡፡ እናም ቻይኖቹ ይህንን ጥናት ሲያካፍሉ፣ ቫይረሱ ከዚህ ክትባት ማምለጥ መቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ በኮቪድ ተይዘው በሰውነታቸው ከሚፈጠረው አንቲቦዲም ማምለጥ የሚቸል ስለሆነ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ ጥሪ አድርገዋል፡፡

በቅርብ ጊዜ ደግሞ በታወቂው በኒው ኢንግላንድ ጆርናል በወጣው ዘገባ፣ የዚህን ቫይረስ ባሕሪ ለመረዳት፣ በኮቪድ ከተያዙ በኋላ በሰውነት ለሚፈጠረው አንቲቦዲና፣ mRNA vaccine ለእንደኛው (ለፋይዘር) ከትባት የሚያሳየውን ምላሽ በመረጃ ያጋራሉ፡፡

ወደ ሚዩ ቫይረስ ከመሄዴ በፊት፣ ከዚህ ቀደም ከደቡብ አፍሪቃ በኩል የመጣው ቤታ የሚባለው የኮሮና ቫይረስ፣ በተፍጥሮም ሆነ በክትባት ለሚፈጠረው አንቲቦዲ ደካማ ምለሽ እንደሚሠጥ ይታወቃል፡፡ እንዲያውም ደቡብ አፍሪቃ ይህንን ጉዳይ በመገንዘብ፣ የአስትራ ዜኔካ ክትባት እንዳይሠጥ አድርጋለች፡፡ ምክንያቱም ቤታ የተባለው ቫይረስ ላይ አይሰራም፡፡ ከዚህ ከቤታ ቫይረስ ያመለጥነውም፣ በከፍተኛ ደረጃ በመሠራጨት ችሎታው የሚታወቀው የዴልታ ቫይረስ ሥርጭቱን በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር ሰላደረገ እነ ቤታና ጋማ ቫይረሶችን ከሥርጭት (ከጨዋታ ውጭ) ሰላደረጋቸው ነው፡፡

ወደ ሚዩ ስንመለስ፣ ሪፖርቱ የሚገልፀው፣ አንቲቦዲዎች ይህንን አዲስ ቫይረስ ምን ያህል ማምከን ይችላሉ ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመሥጠት ያደረጉት ጥናት ነው፡፡

በመጀመሪያ የደረጉት ከዚህ ቀድም መጀመሪያ በተከሰተው ቫይረስ ከሚያዝያ እሰክ መስከረም 2020 ባለው ጊዜ ተይዘው ያገገሙ ሰዎች በተፈጥሮ ያፈሩትን አንቲቦዲ በመውሰድ ይህንን ሚዩ የተባለ ቫይረስ ምን ያህል ማምክን ይቻላል ብለው ሲመለከቱ ያዩት ነገር፣ አዲስ መጪው ሚዩ ቫይረስ ከቀደመው ቫይረስ ጋር ሲወዳደር በ10.6 ዕጥፍ ክትባቱ የማይጎዳው ወይም በእንግሊዝኛ resistant ሆኖ የተገኘው፡፡

የፋይዘር ክትበት ከወሰዱ በኋላ ለተፈጠረው አንቲቦዲ ደግሞ፣ ከቀዳሚው ቫይረስ ጋር ሲወዳደር፣ ሚዩ በ9.1 ዕጥፍ ለእንቲቦዲው ሬሲስታንት ሆኖ ነው የተኘው፡፡ ይህ በርግጥ በጣም ኣሳሳቢ ነው፡፡ በተለይም በክትባቱ ለተፈጠረው አንቲቦዲ መምከን የማይችል በመሆኑ፡፡

ይህን ሚዩ ቫይረስ ቀደም ብዬ ከገለፅኩላችሁ ከቤታ (የደቡብ አፍሪቃው) ቫይረስ ጋር ሲያወዳድሩ፣ በተፈጥሮ ለሚመጣው እንቲቦዲ ከቤታው በበለጠ በሁለት ዕጥፍ ሬሲስታንት ሲሆን፣ በክትባት ለሚፈጠረው አንቲቦዲ ደግሞ በ1.5 ዕጥፍ ከቤታው ቫይረስ በላይ ሬሲስታንት ነው፡፡ ሚዩ እንግዲህ ከእንቲቦዲ በማምለጥ መድረኩን ለብቻው ይዞታል ማለት ነው፡፡ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከተከተቡ በኋላ በኮሮና ሲያዙ (ሰበር) ወይም breakthrough infection ይባላል፡፡ እናም የዚህ ሪፖርት አቅራቢዎች ሚዩ ቫይረስ ላይ የበለጠ ትኩረት እንዲሠጥበት ያሳስባሉ፡፡

ቫይረሶቹን ወደ አሳሳቢነት ደረጃ ከሚያስገቧቸው መመዘኛዎች አንዱን አይተናል፡፡ ሌላው፣ ደግሞ አዲስ የተከሰተው ቫይረስ ሰዎች ላይ የበለጠ ህመምና ሞት ያመጣል ወይ የሚል ነው፡፡ በዚህ በኩል የቀረበም ጥናት የለም፡፡

ሌላው ሶሰተኛ መመዘኛ ደግሞ፣ አዲሱ ቫይረስ የመሠራጨት ችሎታው ከዚህ ቀደም ከታዩት የበለጠ ነው ወይ የሚለው ነው፡፡ በዚህ በኩል ከላይ እንደጠቀስኩት ዴልታ የነገሠበት ባህሪ ነው፡፡ ይህ ሚዩ የተባለው ቫይረስ ግን፣ ወደ ሰዎች ሰውነት ውስጥ (ሴሎች) የመግባት ችሎታው አንዳለ ሆኖ፣ በፍጥነት የመራባትና ከዛም በፍጥነት የመሠራጨት ችሎታ እንደሚጎድለው፣ የተዘገቡት ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ የዲልታን ያህል ወይም የዴልታን ግማሽ የመሠራጨት ችሎታ ቢኖረው፣ ችግር ላይ እንደምንወድቅ ግልፅ ነው፡፡

ክፉና ገዳይ የሆኑ ቫይረሶች ይህ የመሠራጨት ችሎታ ሰለሚያንሳቸው በሰው ዘር ላይ የበለጠ ጉዳት ከማየት ለጊዜው እያመለጥን ነው፡፡ ለምሳሌ ከሳርስ ኮሮና ቫይረስ ወገን የሚመደበው የመካከለኛው ምሥራቅ ኮሮና ቫይረስ ተብሎ የሚታወቀው ቫይረስ ከተከሰተ አስር አመታት በላይ ቢያልፈውም ከሰው ወደ ሰው የመሠራጨት ችሎታው ደካማ በመሆኑ በተወሰነ ቦታ ተከልሎ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን ይህ ቫይረስ ከያዛቸው ሰዎች መሀከል አንድ ሶሰተኛ በላይ የሚሆኑትን እንደሚገድል ይታወቃል፡፡

እንግዲህ ለዚህ ነው የዚህን ቫይረስ ሥርጭት ለመግታት ሁሉም መረባረብ የሚኖርበት፡፡ ምንድን ነው? ቫይረሱ በተሠራጨና በተራባ ቁጥር አዳዲስ ቫይረሶች መፈጠራቸው አይቀርም፡፡ ከነዚህ መሀል ክትባቱን ማምለጥ የሚችል፣ ብሎም በከፍተኛ ፍጥነት መሠራጨት የሚችልና አይጣል እንጂ በከፍተኛ ደረጃ ለህመም መዳረግና መግደል የሚችለ ቫይረስ ቢፈጠርስ?

ሰለዚህ አሁን በስፋት እየተሠራጨ ያለውን ቫይረስ ቢቻል ማስቆም አለዚያም መግታት የሁሉም ሰው ሀላፊነት መሆን አለበት፡፡ የመከላከያ ዘዴዎችን መተግበር፣ በተለይም ማስክና ርቀት መጠበቅ፣ ከዛም ደግሞ ክትባቱን የማግኘት ዕድል ያላቸው ሰዎች ደግሞ ክትባቱን በመውሰድ ለግል ጤንነት ብቻ ሳይሆን ለጋራ ጤንነት ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ተይዣለሁ ብለን መዘናጋት እንደሌለብን ሁሉ፣ ክትባት ወስጃለሁ ብሎ መዘናጋትም አደጋ አለው፡፡ በነገራችን ላይ ሚዩ ቫይረስ አሚሪካም ውስጥ ተገኝቷል፡፡

አመሰግናለሁ

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History