GOSH HEALTH


Community health 

education in Amharic 

በምስሉ የምታዩት ጎልማሳ፣ በቅርቡ ከመሀከላችን የተለየን ገዛኸኝ ወርቁ ካሳ ይባላል፡፡ የ35አመት ጎልማሳ ነበር፡፡ በቤተሰቦቹ ጥያቄና መልካም ፈቃድ፣ ገዛኸኝ ሕይወቱ ሊያልፍበት የቻለበትን በሽታ ለሌሎች ትምህርት እንዲሆን እንድፅፍ ወላጅ አባቱ ለህብረተሰቡ ላለው ቅን አመለካከት በመነሳት ጠየቀኝ፡፡ አኔም በሀሳቡ በጣም የተስማማሁበት ነገር በመሆኑ እነሆ ለህብረተሰቡ ትምህርት እንዲሆንና በተጨማሪ የገዛኸኝ መታሰቢያም አንዲሆን ስለ በሽታው ርዕስ አቀረብኩኝ፡፡ በዚሀም በራሴና በአንባቢዎች አንዲሁም በመላው ህብረተሰብ ስም የገዛኸኝን ቤተሰቦች አመሰግናለሁ፡፡
  ገዛኸኝ ከሰው ጋር የመግባባት ችሎታ ያለው ለማንም ሰው ተጨናቂና አዛኝ የነበረ ሰው ነበር፡፡ ኑሮው በዋሽንግተን ዲሲ ነበር፡፡ አንድ ቀን አመመኝ ቀርቶ፣ ከሥራ እንኳን ቀርቶ አያውቅም ነበር፡፡ ሰው ለመርዳት ባለው ልባዊ ተሠጥኦው፣ ከዚህ ቀደም፣ ገዛኸኝ፣ ከምንም ተነስቶ ከኪሱ ገንዘብ አውጥቶ በጠራራ ፀሐይ ውሃ ለመሸጥ ሲሯሯጥ ያየውን አሜሪካዊ ጥቁር ፣ ለዛሬ የሚሆንህን ገንዘብ እኔ እሰጥሀለሁ ስለዚህ በዚህ ሀይለኛ ፀሐይ ይልቁንስ ዕቃህን ሰብስብና ወደ ቤትህ ሄድ ብሎ ገንዘብ ሠጥቶ ሰውየው ከሙቀት ብዛት ሊደርስበት ከሚችለው አደጋ አድኖት ነበር፡፡ ታዲያ ይህ ጥቁር አሚሪካዊ፣ የገዛኸኝን ሞት ሲሰማ ከቆመበት ወደ መሬት ነው የተዘረረው፣ ማመን አልቻለም፡፡ በድንጋጤ ነበር፡፡ እንግዲህ ይህን የመሰለ ጎልማሳ ሰው ነው ህይወቱ ያለፈው፡፡
   ገዛኸኝ ሰው መርዳት አንጂ ራሱ ሲታምም አስኪደክም ድረስ ለማንም አላዋየም ነበር፡ አንድ ቀን ግን ከሥራ ቀረ፡፡ ከዚያም ወደ ሆሰፒታል ሲወሰድ ምርመራው ውሎ አድሮ ሲጣራ የጨጓራ ካንሰር ሆኖ ተገኘ፡፡

በገዛኸኝ ሞት ብዙ የምናማራቸው ነገሮች አሉ፡፡

አንደኛ ሰለ ጨጓራ ካንሰር፣ የጨጓራ ካንሰር ሰለሚያሰከትለው የ ሄሊኮ ባክተር ፓይሎሪ( Helicobacter pylori) የሚባል የጨጓራ በሽታ ስለሚያስከትለው ባክቴሪያና በመጨረሻም ህይወት ማለፉ የማይቀር ነገር ሆኖ ሲገኝ ለታማሚው ሲባል ስለሚደረጉ ነገሮች ነው፡፡
   ጎሽ ድረ ገፅ ከዚህ ቀደም ሰለ ሄሊኮ ባክተር ፓይሎሪ ፅሁፍ ያሠፈረ በመሆኑ ድረ ገፁን በመጎብኘት እንድታነቡ ምክር እለግሣለሁ፡፡

ሰለ ጨጓራ ካንሰር በዚህ ፅሁፍ ትንሽ እንነጋገር


የጨጓራ ካንሰር ከጨጓራ ግድግዳ ላይ ካሉ ሴሎች ላይ የሚነሳ ካንሰር ነው፡ በአብዛኛው የጨጓራ ካንሰር መንስኤው ከላይ የተጠቀሰው ሄሊኮ ባክተር ፓይሎሪ የሚባለው ባክተሪያ ነው፡ ዋናው ቸግር የጨጓራ ካንሰር ብዙም ምልክት ላይሠጥ ስለሚችል ሁኔታው በሚታወቅበት ጊዜ በጣም ተስፋፍቶ ነው የሚገኘው፡፡ ገዛኸኝም ይህ ነው የታየበት፡፡ ካንሰሩ ከጨጓራው አልፎ በሆድ ዕቃው ውሥጥ ተሠራጭቶ ነበር የተገኘው፡፡
   የጨጓራ ካንሰር በአለም ውስጥ በካንሰር ምክንያት ለሰው ሕይወት መጥፋት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፤ እኤአ 2008 ወደ 738 000 የሚሆኑ ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት ነበር፡፡
   የጨጓራ ካንሰር መንስኤ ዋነኛ ምክንያቱ ሄሊኮ ባክተር ፓይሎሪ ሲሆን ሌሎች ሰበቦች ደግሞ ሥር የሰደደ የጨጓራ በሽታ፣ የወንድ ፆታ፣ ሽምግልና (በዕድሜ)፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ጨው የበዛበት ምግብ፣ ፍራፍሬና አታክልት አለማዘውተር፣ ከዚህ በፊት በሌላ ምከንያት ጨጓራ  ላይ ቀዶ ህክምና ተደርጎ ከሆነ፣ በቤተሰብ፣ በጨጓራ አሲድ ማነስ ምክንያት የሚከሰት የደም ማነስ በሽታን ይጨምራል፡፡ ይህ ካንሰር በበለፀጉ አገሮች እምብዛም ባይታይም በታዳጊ አገሮች በተለይም በኤስያና በላቲን አሜሪካ በከፍተኛ ደረጃ ይገኛል፡፡
ታዲያ የጨጓራ ካንሰር ዋናው ምክንያት ሄሊኮ ባክተር ፓይሎሪ (Helicobacter pylori) ከሆነ ይህንን ባክቴሪያ ከ10 እሰከ 14 ቀናት በሚሰጥ ፀረ ህዋስ antibiotic መድሐኒት መታከምና ባክቴሪያውን ማስወገድ ካንሰር የመነሳት ሁኔታውን ይቀንሰዋል ወይ?
   ይህ ካንሰር በከፍተኛ ደረጃ በሚገኝበት በቻይና የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ለአጭር ቀናት በሚወሰዱ መድሐኒቶች ባክቴሪያውን ማሰወገድ በካንሰር የመያዝ ዕድሉ እንደሚቀንሰው ያሰገነዝባሉ፡፡  በአንድ ጥናት ለአስራ አምስት አመታት በተደረገው ክትትል፣ መድሐኒት ወስደው ባክቴሪያውን በማሰወገድ ካንስር የመነሳት ሁኔታውን በአርባ ፐርሰንት ቀንሶት ታይቷል፡፡ መደምደሚያው ሃሳብ ባክተሪያውን ማስወገድ በካንሰር የመያዝ ሀኔታውን ይቀንሰዋል ማለት ነው፡፡
   ወደ ካንሰር ስንመለስ በጊዜ ካልታወቀ በስተቀር ካንሰር ከጀመረበት ቦታ በመስፋፋት ወደ ሌላ የሰውነት ክፍል ሲሰራጭ ሜታስታሲስ Metastasis ይባላል፡፡ የጨጓራ ካንሰር መስፋፋት ወይም ሲሰራጭ በአብዛኛው የሚበተንባቸው የሰውነት ክፍሎች ጉበት፣ ሳምባና የሆድ ዕቃ ውስጥ ነው፡፡ በሆድ ዕቃ ውስጥ ሲበተን ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ፈሳሽ በሆድ ዕቃ ውስጥ በማከማቸት የሆድ ዕብጠት ያስከትላል፡፡ ይህ ሁኔታ Ascites ተብሎ ይጠራል፡፡
   ካንሰር ከመነሻ ቦታው ተሠራጭቶ ወደሌላ የሰውነት ክፍል ሲሄድ ከተወሰኑ የካንሰር አይነቶች በሰተቀር በአብዘኛው አሰቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ሥርጭቱን ለመቀነስ መድሀኒቶች ቢሠጡም ብዙ ጊዜ ውጤት አልባ ነው የሚሆኑት፡፡ ገዛኸኝም ምንም አንኳን አንድ ዙር የካንሰር መድሐኒት ቢሠጠውም ካንሰሩ የሚያባራም አልሆነም፡፡ ከዚህ በኋላስ ምን መደረግ ነበረበት? በዚህ የአውነተኛ ታሪክስ ምን እንማራለን?


ካንሰር ተስፋፍቶ ከቁጥጥር ውጭ ሲሆን ህምምተኛውና ቤተሰብ መነጋገር የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ 
   ባለፈው ፅሁፍ እንደተጠቀሰው ገዛኸኝ ወርቁ ካሳ ህይወቱ ያለፈበትን ምክንያትና ሁኔታ ወላጅ አባቱ በቅን አመለካከት ሌላው ህብረተሰብ ትምህርት እንዲያገኝ በማለት ሁኔታዎን እንድናካፍልና መማር የምንችልበት አጋጣሚ እንዲፈጠር ጠይቆ ይኸው ሁለተኛው ክፍል ቀርቧል፡፡
   በመጀመሪያው ርዕስ እንደተጠቀሰው ወንድማችን ገዛኸኝ በጨጓራ ካንሰር ምክንያት የጉዞው ፍፃሜ መሆኑን ተጠቅሷል፡፡ ግን ቀላል አልነበረም፡፡ ሁኔታው እየከፋ ሲሄድ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹ ጉዳት ደርሰባቸው፡፡ ከነዚህም አንዱ ኩላሊቶቹ ነበሩ፡፡ ፍፁም መሥራት የማይቸሉበት ደረጃ ደርሰው፣ ዳያሊሲስ በሚባል ሰው ሰራሽ የደም ማጣሪያ ሲረዳ ሰነበተ፡ በኋላም እንደምንም ኩላሊቶቹ መረጋጋት ጀመረው ዳያሊሰሱ ቆመ፡፡ ይህን እየተከታተለ እያለ ደግሞ፣ የደም መርጋት በሰውነቱ ውስጥ ስለተፈጠረ፣ የግድ የደም ማቅጠኛ መድሀኒት መውስድ ነበረበት፡፡ ሰለ ደም መርጋት ጎሽ ድረ ገፅ የተቀመጠውን ይመልከቱ፡፡ ትልቁ ችግር፣ ምግብ የሚባል ነገር በአፉ ገብቶ መርጋት አልቻለም፡፡ ሰለዚሀ በደም ስር በኩል የተመጣጠነ ፈሳሽ ምግብም ይሠጠው ጀመር፡፡ ይሁ ሁሉ ሲሆን ገዛኸኝ፣ ደህና ነኝ የሚል መልስ ይሠጥ ነበር፡፡ በጣም ያሰቸገረው ነገር ደግሞ የልብ ምቱ ከቁጥጥር ውጭ በፍጥነት ስለሚመታ የግድ መድሀኒት ተሠጥቶት ልቡ ብፍጥነት እንዳትመታ ተደረገ፤ መድሐኒቱን ግን ማቆም አልተቻለም፡፡ ከዚህ ቀድም በዚሁ በካንስሩ ምክንያት የሆድ ዕቃው በፍጥነት በፈሳሽ እየተሞላ ፈሳሹ በየጊዜው በመርፌ ይቀዳም ነበር፡፡ ሌላው ተጨማሪና ዋነኛው ችግር ደግሞ በካንሰሩ ምክንያት የቆሰለው ጨጓራው ደም ማፍሰስ መቀጠሉ ነው፡፡ በትውኪያ በኩል የጠቆረ ደም ይወጣል፡፡ ጎልማሳው ገዛኸኝ ምን ያህል እንደሚሰቃይ መገመት የሚያስቸግር አይደለም፡፡ በሆዱ በኩል እንደ ዕብጠት የተቀመጠው ካንሰር ህመሙንና ስቃዩን አባበሰው፡፡ ከፍተኛ የህመም መድሀኒት ቢወስድም ህመሙ ከመድሀኒቱ በላይ እየጣሰ ስቃዩን ጨመረበት፡፡
   ይህ ሁሉ ሲሆን ገዛኸኝ የመዳን ፍላጎቱ ሀይለኛ ነበር፡፡ በቤተሰብና ዘመዶችም ተስፋ ነበር፡፡ የካንሰር ሀኪሙ ነገሩን የተመለከቱት በራሳቸው በህክምና በኩል ነበር፡፡ ሁኔታው እየከፋ መሄዱ ግልፅም ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የካንሰር መድሀኒቶች (ኬሞ ቲራፒይ) በራሳቸው ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ ከሀኪሙ ጋር በተደረገ ውይይት፣ ከቤተሰብ አባል አንድ ጠንከር ያለና የህክምና ሙያ ዕውቀቱ የነበራት ሰው ሁኔታውን በትክክለኛ መንገድ ተገንዝባለች፡፡ ታዲያ ሀኪሙ አንድ ዙር እንኳን ቢሆን የካንሰር መድሀኒቱ እንዲሠጠውና የሚመጣውን ለውጥ በተስፋ ለማየት በመስማማት፣ ሀኪሙ አንድ ዙር ኬሞ ቴራፒ እንዲሰጠው አደረጉ፡፡ ያም በስንት ችግር፣ ገዛኸኝ ካለበት ክፍል ወጥቶ እንደተመላላሽ ህምመተኛ በተመላላሽ ክፍል ነው የተሠጠው፡፡ ይህ የተደረገበት ምክንያት ሆሰፒታሉ ኬሞ ቴራፒውን በውስጥ ህክምና ላይ ላሉ ሰዎች መሰጠት ስለማይፈቀድ ነበር፡፡ 
   መድሂኒቱን እንደወሰደ ግን በነበረው ሁኔታ ወደ ሆስፒታል እዛው ተመልሶ ገባ፡፡ ከዚያ በኋላ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች በሙሉ ምንም ለውጥ አላሳይ አሉ፡፡ ደም መፍሰሱም በተንቀሳቀሰ ቁጥር በአፍ በኩል የሚመጣ ነገር ሆነ፡፡

ትልቁ ጥያቄ

ሀኪሞች ቤተሰብ አስጠሩና ከዚሕ በኋላ መደረግ የሚችል ነገር የለም፡፡ የካንሰር ሀኪሙም ቢሆን በዚህ ሁኔታ ሌላ ኬሞ ቴራፒ መስጠት ኢሰባዊ ነው አሉ፡፡ ቤተሰብ እንዲወስን ተጠየቀ፡፡ ይህ ከባድ ፈተና ነበር፡፡ አባቱም ይህንን ፈተና ሰው እንዲማርና እንዲዘጋጅ በማለትም ነው የውድ ልጁን የህክምና ሁኔታ በአደባባይ እንዲወጣ የጠየቀው፡፡ በፅሞና ላጤነው ሰው፣ ቤተሰቡ ከዚህ በላይ ለገዛኸኝ ማሰታወሻ ወይም መታሰቢያ አላደረጉም፡፡ ትልቅ አስተዋፅኦ ነው፡፡
   ታዲያ በዚህ በሀኪሞች የመጨረሻ የውሳኔ ጥያቄ ላይ የግድ መነጋገርና መወሰንም አስፈላጊ ነበር፡፡ ሁኔታው ሁለት አማራጭ ነው የነበረው፡፡
   ለገዛኸኝ የሚታሰብ ከሆነ፣ ስቃዩና በስቃይ መቀጠሉ በውን ትክክል  ይሆን? ይህ ማለት የሚደረገው ሁሉ እየተደረገ ይቀጥል ብሎ መፍረድ ነበር፡ በሌላ በኩል እንደቤተሰብ በተስፋና በምኞት የሚሆነው ሁሉ ይቀጥል ብሎ ለራስ ከማሰብም የሚመጣ ሊሆን ይችላል፡፡
   ሁለተኛው አማራጭ፣ ከፈጣሪ በታች የሚደረገው ነገር ሁሉ ተደርጓል፣ አካሄዱም ወይም ሁኔታው ግልፅ ነው፤ አስከዚያ ድረስ ግን ገዛኸኝ መሰቃየት ነበረበት ወይ? እንግዲህ ሁኔታው ባለበት ከቀጠለ፣ ሰውነቱ ላይ የተሰኩ ቱቦዎችና ሌሎቸም በየጊዜው የሚደረጉ ነገሮች ስቃዩን ቢያባብሱበት እንጂ የሚረዱት አልነበረም፡፡

የግድ መወሰን ነበረበት፡፡

ይህ ፈተና በማንም ቤተሰብ ላይ ሊደርስ የሚችል ነው፡፡ በነገራችን ላይ፣ የገዛኸኝ ቀብር በሚያምር ሁኔታ ያለፈው ቅዳሜ ተከናውኗል፡፡ በቀብሩ ሥነ ሥርአት ሌላ ሰው የገዛኸኝ ቤተሰቦች የደረሰባቸው ፈተና እነሱም ላይ እንደደረሰ አጫወተኝ፡፡

እንግዲህ በዚህ በገዛኸኝ መታሰቢያ ዋና ዋና ትምህርቶች
1.      የጨጓራ በሽታ የሚያስከትለው ኤች ፓይሎሪ ባክቴሪያ በህብረተሰባችን በስፋት የሚገኝ ስለሆነ መመርመርና መድሃኒት በመውስድ ባክቴሪያውን ማስወገድ፡፡ ይህ ባክቴሪያ ነው እንግዲህ ለጨጓራ ካንሰር ሰበብ ወይም ጠንቅ በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀሰው( ጎሽ ድረ ገፅ ይመልከቱ)
2.     የጨጓራ ህምም ያለማቋረጥ የሚከሰት ከሆነ ደግሞ ወደ ባለሙያ ቀርቦ ጨጓራና አንጀት በኢንዶስኮፒ እንዲታይ ማድረግ፡፡
3.     በፅሁፉ የመጨረሻ ክፍል እንደተጠቀሰው፣ ህይወት በሚያልፍበት በመጨረሻዋ ሰአት፣ የህመምተኛውን ስቃይ ከግንዛቤ በማስገባት የሚቆመው ነገር ሁሉ ቆሞ፣ ህመምተኛው በሰላም ቤበተሰብ እንደተከበበ ፈጣሪ እንደወሰነው እንዲሆን ለማድረግ አስቀድሞ በአእምሮ ማንሰላሰል ተገቢ ነው፡፡
   ታዲያ ቤተሰብ የወሰነውን ውሳኔ ከማጋራታችን በፊት እሰኪ አንባቢ የራሱን አስተያየት ይውሰድ በሚል መደምደሚያውን ሌላ ጊዜ እናቀርባለን፡፡ ሀሳብ ሲሰጥ በስሜት ሳይሆን፣ በፅሞና፣ በቤተሰብ እግር ራስን ተክቶ በማሰብ ቢሆን መልካም ነው፡፡