የኮቪድ-19 ሥርጭትን በተሳካ ሁኔታ ያሰቆመ አገር አለ ወይ? 08/09/2020

 እንዴታ፣ በደንብ፡፡ ግን ያልተጠበቀ፣ ትንሽ አገሮች ከሚባሉት አንዱ ኒውዚላንደ፣ የኮቪድ-19 ሥርጭትን አስቆመናል ሲሉ በቅርቡ በታወቂው የኒው ኢንግደላንድ መፅሔት ገልፀዋል፡፡

ኒውዚላንድ የማስታወሰው፣ የአጼ ቴዎድሮስ ባለሟል የነበረው ባሻ ፈለቀ (ካፒቴን ሰፒዲ)፣ ከቴዎድሮስ ተለይቶ ከሄደ በኋላ፣ ቅጥር ወታደር በመሆን፣ በኒወዚላንድ የማኦሪወች ጦርነት መካፈሉን ነው፡፡ ማአሪዎች በርግጥም፣ የኒውዚላንድ ቀደምት ኗሪዎች ናቸው፡፡

ወደ ኮቪድ-19 ስንመለስ፣ የኒውዚላንድ ሰዎች የሚሉት፣ በቻይና፣ ዉሀን ለመጀመሪያ ጊዜ በጥር 2020 ኮቪድ-19 ተከሰተ ብሎ ሲገለጥ፣ ይህ ሥርጭት አለም አቀፋዊ ሊሆን አንደሚቸል ቀደመን ተገነዘብን፡፡ በተጨማሪም፣ ከቸይናና ከአውሮፓ በየአመቱ ቱሪስቶች ወደ ኒውዚላንድ ሰለሚሚጡ፣ ኮቪድ-19 የሚያሰከትለው ቫይረስ ሳርስ ኮሮና 2 ወደ ኒውዚላንደ መምጣቱ የማይቀር ነገር ነው ብለው አመኑ፡፡ በራሳቸው ባደረጉት ሰሌት ደግሞ ሥርጭቱ ወደ ፓንደሚክ ደረጃ እንደሚያድግ ተገነዘቡ፡፡

የፓንደሚክ ትርጉምን መለስ ብለን ብንመለከት፣ የቫይረሱ ሥርጭት ከአንድ አገር ወጥቶ ወደ ሌላ አገር ከተሸገረ በኋላ፣ አዲስ በገባበት አገር እዛው አገሩ ውስጥ በህብረተሰቡ መሀል መሠራጨቱ ሲረጋገጥ ነው፡፡ ካስታወሳችሁ፣ የአለም የጤና ድርጅት፣ ፓንደሚክ ደረጃ ደርሷል ለማለት ትንሽ ዘግየት ብለው ነበር፡፡ ኒውዚላንደሮቹ ግን በዚህ ጉዳይ የራሳቸውን ስሌት ነው ያመኑት፡፡ ፓንደሚክ ይመጣል፡፡ እንደታየው፡፡ ይህ አንግዲህ ገና በጥር 2020 ነው፡፡

ታዲያ በውቅቱ የነበራቸውን የፓንደሚክ ኢንፍሉዌንዛ ፕላን መተገበር ጀመሩ፡፡ ማንም አስኪነገራቸው አልጠበቁም ማለት ነው፡፡ በዘህ ፕላን፣ ሆስፒታሎች ከፍተኛ ቁጥር ለሚኖረው በሽተኛ እንዲዘጋጁ አደረጉ፡፡ በተጨማሪም፣ በሀገራቸው ደንበር ላይ የፓንደሚክ አገባቡን ለመቀነስ ቁጥጥር ጀመርን ይላሉ፡፡

የመጀመሪያው ኮቪድ-19 በሽተኛ የተገኘው በየካቲት 26 ነበር (እንደ አውሮፓ አቆጣጠር)፡፡ በዚያን ጊዜ. የአለም የጤና ድርጅት የተቀናጀ ኮሚሽን በቻይና ባደረገው ጥናት፣ አዲሱ በሽታ፣ ከዚህ ቀደም ታይቶ እንደነበረው ሳርስ አይነት ባህሪ እያሳየ ነው በማለት ሪፖርት አቀረበ፡፡

እንደፈሩት አልቀረም፣ በመጋቢት፣ በኒውዚላንድ ህብረተሰብ መሃል የኮቪድ-19 ሥርጭት ይካሄድ ጀመር፡፡ እንግዲህ ኒውዚላንደሮች የሚሉት፣ በሳይንሳዊ መረጃ በመመርኮዝ፣ የጤና ባለሙያተኞችን ምክርም በመስማት፣ ውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡ በመጋቢት 26፣ ባንድ ጊዜ በጠቅላላው ባገሩ የተከተት አዋጅ አወጁ፣ በነሱ ደረጃ ጥብቅ የሆነ ደረጃ አራት ነው የሚሉት፡፡ እንደሱም አደርጋው ሥርጭቱ ከፍ ብሎ እየተካሄደ ሰለነበር፣ ያገሬው ሰዎች፣ አዋጁ ይሠራ ይሆን የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ አደርጓቸዋል፡፡

በትግሥት፣ ለአምስት ሣምንቶች፣ የሰዎች አንቅስቃሴ በጠቅላላ በተገደበበት ወቅት፣ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት መቀነስ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ከደረጃ አራት ተከተት፣ ወደ ደረጃ ሶስት ተከተት በመቀነስ ለተጫመሪ ሁለት ሳምንታት ባጠቃላይ ለሰባት ሳምንታት በየቤታችሁ ተወሰኑ የሚለው ትዛዝ በተግባር ዋለ፡፡ ሰባት ሳምንታት ብቻ!

በግንቦት መጀመሪያ ላይ፣ የመጨረሻው በኮቨድ-19 የተያዘ ሰው ተገኘ፡፡ አሱም ወዲያውኑ ወደ መለያ ቦታ (Isolation) ተወሰደ፡፡ በነገራችን ላይ፣ የኳራንቲንና የአይሶሌሽን ትርጉም እየተምታታ በመሆኑ፣ ሰለ ሁለቱ ትርጉም መናገር አስፈላጊ ነው፡፡

ኳራንቲን የሚደረገው፣ በቫይረስ ወይም በበሽታ ያልተያዙ ወይም የበሽታው ስሜትና ምልክት የሌለባቸው ሰዎች ነገር ግን በቫይረሱ ከተያዘሱ  ሰዎች ጋር ተጋልጠው የነበሩ ሰዎች፣ በመገለል የሚቀመጡበት ሁኔታ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ድንገት ተይዘው ከሆነ ለሌላ ሰው እንዳየስተላልፉ፣ ከዛም ደግሞ ምልክት ይታይባቸው ይሆን ተብሉ በቅርብ ክትትል የሚደረግላቸው ናቸው

አይሶሌሽን ግን፣ በግልጽ በቫይሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች፣ ወይም የበሽታው ስሜትና ምልክት ያለባቸው ሰዎን በማግለል የሚቀመጡበት ሁኔታ ነው፡፡ እነዚህ በጥብቅ ሁኔታ ከማንም ጋር በማይገናኙበት ሁኔታ ነው የሚገለሉት፡፡ በተጨማሪም ግን፣ በሽታው ይጠናባቸው ይሆን በማለት በጣም ቅርብ ክትትል ይደረጋል፡፡ እንደምታውቁት አብዛኞ በዚህ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች፣ በጠና ሳይታመሙ ከበሽታው ሰለሚያገግሙ ወደ ሆሰፒታ መዝለቅ የላበቸውም፡፡ ይህ ግን በሽታው ሊጠናባቸው የሚችሉ በዕድሜ የገፉና ሌላ ተደራቢ በሽታ ያለባቸው ሰዎችን አይጨምርም፡፡ ለዚህ ነው እንገዲህ ትልቁና ዋናው ጥረት ቫይረሱ እነዚህ አደጋ ላይ ሊወድቁ የሚችሉ ሰዎች አጠገብ እንዳይደረስ ወይም እነሱ እንዳይጋለጡ ማድረግ ነው፡፡

ወደ ኒውዚላንድ ስንመለስ፣ በሰኔ ስምንት፣ ተከተት ያሉትን ነገር ወደ ደረጃ አንድ አውርድው፣ ቫይረሱ አገራቸው በገባ ከ103 ቀናቶች በኋላ፣ ከፓንደሚክ ነፃ መሆናቸው ገለጡ፡፡

በአሁኑ ወቅት፣ ኒውዚላንደ ፓንደሚኩን ካገራቸው አስወገድው የሚኖሩበት ሁኔታ ላይ ነው ያሉት፡፡ የሚገባ ቢኖር ከውጭ የሚመጡ ሰዎች መሆኑን ሰለተረዱ፣ ከውጭ የሚመጡ ሰዎችን ለ14 ቀናት እንደሁኔታው ወይ ኳራንቲን አለዚያም አይሶሌሽን ወስጥ ያሰገቧቸዋል፡፡ ብልጦቹ ኒውዚላንደሮች፣ ሌሎች የቫይረሱን ሥርጭት ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ የመከላከል ተግባራቸውን ላላ በማድረጋቸው እንደገና ሥርጭት የተነሳባቸውን አገሮች፣ እንደ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሆነግ ኮንግ፣ ሲንጋፖር እና አውስትራሊያ ላይ የደረሰውን በደንብ ተገንዝበዋል፡፡ ለዚህም በቂ ዝግጅት አድርገዋል፡፡ እዚህ ላይ የምንረዳው፣ የተወሰኑ አገሮች ብቻቸውን የቫይረሱን ሥርጭት ተቆጣጥረው መኖር አይችሉም፡፡ ችግሩ አለም አቀፋዊ ነው፡፡

ባደረጉት ቆራጥ የሆነ እርምጃ፣ የቫይሱን ሥርጭት በጥቂት ቀናት ውስጥ መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን፣ ባጠቃላይ በአገራቸው በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1569 ብቻ ሲሆን በዚህ ቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥርም በ22 ሰዎች ብቻ ነው የተወሰነው፡፡ ይህን በማድረጋቸውም ኑሯቸው ወደ ድሮው እየተመለሰ፣ የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴም፣ ኮቨድ-19 ከመግባቱ በፊት ወደ ነበረበት ደረጃ ተመልሷል፡፡ ሳይንስ ተመርኩዘው በወሰዱት ርምጃና ሁለት ወራቶች ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የበሽታውን ሥርጭት መቆጣጠራቸው በተግባር ሲታይ በመንግሥትና በህዝቡ መሀል መተማመን እንዲኖር ነው ያደረገው፡፡ የሚገርመው ነገር፣ ኒውዚላንድ ይህንን ሥርጭት ድል መንሳት የቻሉት፣ ማስክ ሳይጠቀሙ ነበር፡፡ ድንግት ካገረሸ ግን፣ ማስክ እንደሚጠቀሙ ነው፡፡

ይህን ቫይረስ የሚያመላልሰው ሰው ከሆነ፣ በየቤት በመቀመጥ ሰው ከሰው ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት መቀነስ  ዋናው የመከላከያ መንገድ መሆኑን መመልከት እንችላለን፡፡ ከቤት ከተወጣም ደግሞ፣ ርቀት መጠበቅና፣ በትንፋሽ እንደመተላለፉ ሁሉ ትንፋሽን መሸፈን ሌላው መንገድ ነው፡፡ ይህም ባንድ ጊዜ ባንድ ላይ ሁሉም በተግበር ቢያውለው ውጤት ላይ ይደረሳል፡፡ ሌላው ቢቀር፣ በማን አለብኝነት፣ ቫይረሱ ምንም አያደርገኝም በማለት የመከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ ሳያደርጉ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች፡፡ ቫይረሱ ቢያገኛቸው ሊገላቸው ወደሚችል ሰዎች ቫይረሱን ማድረሳቸውን እንኳን ቢዘነጉ፤ ሥርጭቱ በቀጠለ ቁጥር በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረውን ቸግር ቢገነዘቡ መልካም ነው፡፡ እንደምናየው ከሆን፣ ይህ ቫይረሱ ብዙ ሰው አይገድልም በሚል ስሜት፣ የሰዎች ስብስቦች ሲፈጠሩ እያየን ነው፡፡ የዛሬ መቶ አመት የታየውን የህዳር በሽታን ከተከታተልን፣ ያሁኑ ቫይረስ ተመልሶ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ከመጣም ደግሞ፣ እንደምናየው በየጊዜው ዝርያና ባህሪውን እየቀየረ በመሄድ ላይ ያለው ይህ ቫይረስ፣ ተዳቅሎም ይሁን በራሱ ገዳይ ከመሆን የሚያግደው ያለ ነገር አይመስልም፡፡

መልካም ንባብ

Community health 

education in Amharic 

ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ