ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጋር ያገናኘን ነገር

ነብሳቸውን በገነት ያኑረውና በቅርቡ ያረፉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ የተደበቀው ማስታወሻ የተባለውን በእኔና በአቶ ደሳለኝ አለሙ ለህዝብ የቀረበውን መፅሐፍ እንዳነበቡና፣ መፅሐፉን ብዙ ቦታዎች ላይ ምልክት እንዳደረጉበት አንድ ሰው ሹክ ብሎኝ ነበር፡፡ ቆየት ብለው ግን፣ በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ፣ የሚከተለውን አስተያየት ፅፈው አነበብኩ፡፡ መፅሐፉን ያነበበ ሰው፣ ፕሮፌሰሩ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ብዙ ቦታ ምልክት ማድረጋቸው የሚያስገርመው አይመስለኝም፡፡ ያላነበባችሁ ብታነቡት ይመከራል፡፡ በማንበባችሁ እንደምተደሰቱ እርግጠኛ ነኝ፡፡ 

_________________________________

A post from Professor Mesfin's page
Mesfin Wolde-Mariam
December 9, 2015 ·


የወኔ ተስፋ

በኢጣልያ ወረራ ጊዜ በደጃዝማች አያሌው ብሩ የጦር ሰፈር አንድ አማርኛን አቀላጥፎ የሚናገር ስዊድን ሀኪም አብሮ ነበረ፤ ትዝብቱን ጽፎ የተተረጎመውን ሳነብ አንድ ልብን በኩራት የሚያሳብጥ ታሪክ አነበብሁ፤ ስለደጃዝማቹ ጦር ሲናገር በከፊል እንደሚከተለው ነው፤--

‹‹በግምት ከየመቶው ሰው ሰባቱ ጎራዴ ብቻ ወይም በትር የያዙ ናቸው፤ በተለይ የማስታውሰው የአሥራ ስምንት ዓመት ወጣት ልጅ በኩራት መንፈስ ዱላውን በቀኝ ትከሻው ላይ አድርጎ ይንጎራደድ ነበር፤ ዱላው የእንጨት ሲሆን ቀይ ቀለም ያለው ሆኖ እላዩ ላይ ጌጥ ተቀርጾበታል፤ የዚህ ወጣት ልጅ የተለየ ኩራትና አካሄድ የሰዎችን ዓይን የመሳብ ችሎታ ፈጥሯል፤

ደጃዝማች አስጠሩትና
ዕድሜህ ስንት ነው?
አባቴ የሚነግረኝ በንጉሥ ሚካኤልና በሸዋ ገዢዎች መሀከል በተደረገው የሰገሌ ጦርነት ወር ነው የተወለድኩት፤
መልካም በዚህ በሚያምር ዱላህ ምን ልታደርግበት ነው?
በዚህ ዱላ ነጭ ልገልበት ነው፤
እንደሱ እንኳን ማድረግ አትችልም፤ በምትኩ ጠመንጃ ልስጥህ፤
የለም አመሰግናለሁ፤ ለአባቴ የማልኩት ቃለ መሐላ ጣልያን ገድዬ ጠመንጃውን ወስጄ አሳያለሁ፤ አለዚያ በዚህ በጦር ሜዳ እቀራለሁ፤››


የተደበቀው ማስታወሻ ከሚል መጽሐፍ፡፡


እኔ መስሎኝ የነበረውና የማምነው ኢትዮጵያውያን

ምርጫ ካላቸው ቀላሉን እንጂ ከባዱን አይመርጡም

የሚል ነበር፤ ይህ ወጣት የቆየ እምነቴን አነከተው!

አንዳንድ ኢጥዮጵያውያን ከባዱን የመምረጥ ወኔ

አላቸው ማለት ነው፤ አምላክ ዘሩን ያበርክተው!

ልቤን በኩራት አሳበጠው፤ የኢትዮጵያዊነት

ክብሬንም አደሰው! የዚህ ወጣት ወኔ በብዙ

መልኩ የሚታይ ነው፤ የዛሬ ወጣቶች አባባሉን

እንዲመረምሩት እተውላቸዋለሁ፡፡


መስፍን ወልደማርያም       የተደበቀው ማስታወሻ መልካም ልደት ጃንሆይ!!


ሰውየውን አውሮፓውያንና ባላንጣዎቻቸው እንደሚስሏቸው ጨካኝ በማለት ብዙ ሰው ያስተጋባል፡፡ ቆራጥ ነበሩ፣ የማያወላውል ርምጃ ይወሰዳሉ ግልፅ ነው፡፡ ፈሪሀ እግዚአብሔር የነበረው ንጉሥ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ያለ የለም፡፡ ሀይለኛ የሆኑት፣ ለህዝቡ የፈለጉትን ያህል ቢጥሩም ምላሹ ሽፍትነት፣ ዘረፋ ሆነ፡፡ የዛን ጊዜው ሽፍታ ደግሞ፣ ንጉሡ ዞር ሲሉ፣ እሳቸውን አምነው የተቀመጡ ገበሬዎችን ቤት ንብረት እያቃጠለ፣ እየዘረፈና እየገደለ ይሸሻል፡፡ እባካችሁ ተውኝ አትሸፍቱ እያሉ ይለምኑ ነበር፣ ያውም በቴዎድሮስ ኩራት ፡፡ ነገር ግን ሰሚ አላገኙም፡፡ በመጨረሻም እንዲህ አሉ ፈጣሪ የላከኝ ህዝቡን እንደረዳ መስሎኝ ነበር ለካስ ተሳስቻለሁ፣ የላከኝ ለቅጣት ነው ብለው ከልባቸው አመኑ፣ ቅጣቱንም ከፈጣሪ የተላከ አደረጉት፡፡ ለዚህ ምስክር፣ አንደኛው መድፋቸው ላይ፣ “ቴዎድሮስ የርጉማኖች መቅሰፍት” የሚል ፅሁፍ አስቀርፀውበት ነበር፡፡ ህዝቡ ከመቶ ሃምሳ አመታት በኋላም ያው ነው፡፡ ያላየ ሰው በቴዎድሮስ ይፈርዳል፡፡


ለድሆች የተለየ እንክብካቤ በማድረግ፣ ችግራቸውን ማዳመጥና፣ ሥራቸውን ከመጀመራቸው በፊትም ምፅዋት ይሰጡ ነበር፡፡ በሰብአዊ ርህራሄ ስሜትና እንደ አሰተዳደራቸው ፖሊሲ በመቁጠር በዘመቱበት ቦታ ሁሉ ለድሆች ገንዘብ ይሰጡ ነበር፡፡ በዶክተር ክረፕ ሚሲዮናዊ ጥናት ውስጥ የተገኘ መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ቴዎድሮስ፣ “እኔ ራሴ ድሃ ነበርኩ፤ ድሆችን ባልረዳ፣ ለፈጣሪ ስሞታ ያቀርባሉ” ይሉ ነበር፡፡ ለናፒየር በፃፉት በመጨረሻው ደብዳቤ፣ “ራሴ የምጦራቸው ሰዎች” በማለት፣ የሚያስተዳድሯቸው ባልቴቶች፣ ሴቶችና ህፃናት እንደነበሩ ይጠቅሳሉ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የሚሠጡት ፍርድም በሰው መወደድንና መደነቅን አትርፎላቸው ነበር፡፡ ለመጥቀስ፣ ሁለት ሰዎች ተካሰው ንጉሡ ፊት ቀረቡ፣ አንደኛው ላንዱ ፈረስ በትውስት ሠጥቶት ኖሮ፣ ተቀባዩ ግን ይክዳል፡፡ ሠጭው ሰጥቸዋለሁ ብሎ ሲምል፣ ተቀባዩ እግዚአብሔርን በመፍራት መቀበሉን ያምናል፡፡ ይህን የሰሙ ቴዎድሮስ፣ ሰውየው በነበረው ፈሪሀ እግዚአብሔር ምክንያት፣ እዳውን አኔ እከፍልሃለሁ በማለት ለከሳሹ ፈረስና ብር ሠጥተዋል፡፡
መቅደላ የቴዎድሮስ ዕጣ ከተባለው መፅሐፍ የተጠቀሰ


ይህን መፅሐፍ ያነበበ ሰው፣ ቴዎድሮስ ማን እንደነበሩ ማወቅ ይችላል፡፡ ሰለፃፍኩት አይደለም፣ ብዙ የማይታወቁ፣ በተለይም ደግ ሥራዎቻቸው እየተመረጡ ለአንባቢ ያልቀረቡ መሆናቸውን አስተውያለሁ፡፡ ቴዎድሮስን የምትወዱ የምታከበሩ አንብቡት፡፡ ትርጉምና ተጨማሪ ሥራዎች ያሉበት ነው፡፡ አርቆ በማሰባቸው የተጎዱ ሰው፣ ግን ይችን አገር መልሰው የሠጡን ሰው ናቸው፡፡


ሥዕሉ የሚያሳያው፣ ቴዎድሮስ አባይን ተሻግረው ሰዎቻቸውን ሲመለከቱ ነው፡፡ የሥዕሉ ምንጭ መልክተኛው ራሳም ነው፡፡
መልካም ልደት ጃንሆይ!!