Health and History

Community health 

education in Amharic 

​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

የናቁት … 08/31/2021

ፀረ ኮቪድ ክትባት ቅስቀሳ ሲያደርጉ ከነበሩት የአሜሪካ ወግ እጥባቂ ወገን ሬዲዮ ተናጋሪዎች ሶስተኛው ሰው ሕይወቱ አለፈ፡፡ በፍሎሪዳ ኗሪ የነበረው የ65 አመቱ ማርክ በርኒር ባለፈው ቅዳሜ ህይወቱ ያለፈው ሆስፒታል ከገባ ሰንበት ብሎ ነበር፡፡ ደጋፊዎቹና የሱን አቋም የሚከተሉ ሰዎች የሀዘን መግለጫም አሰምተዋል፡፡ ሰውየው ራሱን “ሚሰተር ፀረ ክትባት” ብሎ በመጥራት፣ በኮቪድ ክትባት ላይ ቅስቀሳ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ቢጤዎቹን እየጋበዘ ክትባቱን ሲያጥላላ ነበር፡፡

ከወግ አጥባቂ ወገን ከሆኑ ፀረ-ኮቪድ ክትባት አቋማቸውን በሬዲዮ ጣቢያቸው ሲለፍፉ ከነበሩት፣ በናቁት ቫይረስ በኮቪድ ምክንያት ሲሞቱ ሚሰትር በርኒር ሶስተኛው ነው፡፡

ሌላው ቴኔሲ ስቴት ኗሪ የነበረው ፊል ቫለንቲን የተባለ የ61 አመት ዕድሜ የነበረው ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው የኮቪድ ወረርሽኙን የተንኮል ሥራ ነው በማለት ክትባቱም ላይ ሲቀልድ የነበረ ሰው ነው፡፡

ሶሰትኛው ደግሞ ከፍሎሪዳ ስቴት፣ ኒውስማክስ የተባለ የቴሊቪዢን ጣቢያ አስተያየት ይሠጥ የነበረ የወግ አጥባቂዎች ወገን የሆነ ሰው ነበር፡፡ ዲክ ፋረል የተባለው ይህ ሰው የ65 አመት ዕድሜ ደርሶ ነበር፡፡ የዚህኛው የሚገርመው፣ ኮቪድን ማራከስ ብቻ ሳይሆን፣ በአሜሪካና በአለም አቀፍ ደረጃ በተላላፊ በሽታዎች ባለሙያተኛ የሆኑትን ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺን፣ ቀጣፊና ሥልጣን ፈላጊ እያለ ስማቸውን ሲያራክስ የነበረ ሰው ነው፡፡ እሱም ቢሆን በዚሁ ባራከሰው በኮቪድ በሽታ ሕይወቱ አለፈ፡፡ የኋለኞቹ ሁለቱ ቫለንቲንና ፋረል በኮቪድ መያዛቸወን ካወቁ በኋላ አንደ ንስሐም ይሆናል፣ ሰዎች የኮቪድ ክትባቱን እንዲወስዱ ሲገፋፉ ነበር፡፡

መልክቱ፣ ሰለ ኮቪድ የሚናገሩ የሚመክሩ ሰዎችን ሳይሆን ቫይረሱ በተፈጥሮ የመጣ እንደመሆኑ መጠን እንደሌሎች በሽታዎች ሁሉ የሚገባውን አክብሮት ሠጥቶ የሚደረገውን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የኮቪድ ክትባት አንወስድም የማለት መብት ቢኖርም (ወደፊት መብትም ላይሆን ይችል ይሆናል) ቫይረሱን በማጣጣል ሥርጭቱ እንዲገታ መደረግ የሚገባቸውን ነገሮች አለማድረግ በራስም ሆነ በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ አደጋ ያስከትላል፡፡ እሺ ክትባት አንወስድም ይበሉ ነገር ግን ክትባት ከወሰዱና በቂ ጥንቃቄ ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ያለምንም ገደብ ለመቀላቀል የሚሞክሩ ሰዎችም አሉ፡፡ ምን ይባላል፡፡ የግል ወሳኔያቸውን መጠበቅ ሌላ፣ ሌሎች ሰዎችን ለአደጋ ማጋለጥ ደግሞ ሌላ ነው፡፡ ቢችሉ ወረርሽኙ እስከሚያልፍ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገው ሌሎችን ከማጋለጥ መቆጠብ ተገቢ ነው፡፡

በኮቪድ ምከንያት ያላየነው ነገር የለም፡፡ ፖለቲከኞቹ ከሀኪሞቹ በላይ አዋቂ ሆኑ፡፡ በህብተረሰቡ ህይወት ላይ አደጋ ያሰከተለ አቋም በመያዝ ክትባቱን ብቻ ሳይሆን ማስክ ማድረጉን መቃወም ተልኳቸው አደረጉት፡፡ እነሱ እያወቁ፣ አንዳንዶቹም ውስጥ ለውስጥ ራሳቸው እየተከተቡ ህብረተሰቡን ማመስ ቀጥለዋል፡፡

የሬዲዮ ሰዎች ደግሞ፣ ፀረ ኮቪድ ክትባት ቅስቀሳና ዘመቻውን ያጧጧፉት በውነት በነገሩ አምነውበት ነው ወይስ የአዳማጭና የተመልካች ቁጥር በጨመረ ቁጥር ገቢያቸው ሰለሚጨምር ይሆን? ፖለቲከኞቹ በግልፅ የሚቀጥለውን ምርጫና ሥልጣናቸውን በማሰብ፣ በደንብ ያልተረዳውን ህብረተሰብ ማስደሰት ሙያቸው አደረጉት፡፡ የሜዲያ ሰዎች፣ ህብረተሰቡን የሚያጓጓና አትኩሮትን የሚስብ ርዕስ ሆነ ሀተታ ሲያቀርቡ ይታያሉ፡፡ አሱም ሳንቲም አለበት፡፡ ዕደሜ ጉግል ለሚባል ድርጅት፣ ማስታወቂያ ለመሸጥ ሲል የእነዚህን አይነት ሰዎቸ በዕቅፉ ይዞ ይነግዳል፡፡ ለማንኛውም ግን አዳማጩ ወይም ተመልካቹ ህብረተሰብ ጊዜ ሠጥቶ አመዛዝኖ የተለያዩ መረጃዎችን ተመልክቶ ውሳኔ ላይ መድረስ ይኖርበታል፡፡

በመጨረሻም፡ ኮቪድ አለ፣ ሰው ያሳምማል፣ ሰው ይገድላል፤ ኢኮኖሜ ይጎዳል፤ የህብረተሰቡን አኗኗር ያቃውሳል፡፡ ገሀድ ነው፡፡ አሁንደ ዴልታ ነው የነገሠው፡፡ ነገ ደግሞ ምን አይነት አዲስ የቫይረሱ ዝርያ ብቅ እንደሚል አናውቅም፡፡ ሥርጭቱን ካልገታን፣ አዲስ የሚከሰተው ቫይረስ ዝርያ ከቀደሙት የባሰ እንደሚሆን ጥርጣሬ አይኖርም፡፡ ህንድ ውስጥ የደረሰውን በደንብ የተከታተለ ሰው፣ ብዙ ትምህርት ማግኘት ይችላል፡፡

በኢትዮጵያ፣ የበፊቱን አቀለለልን ብሎ መዘናጋቱ ከፍተኛ አደጋ ያስከትላል፡፡ ከአቅም በላይ ሆኖ የሚደረጉ የህልውና አንቅስቃሴዎች ቢኖሩም፣ ቫይረሱ በከፈተኛ ደረጃ የሚከሰትባቸው ትልልቅ ከተሞች አዲስ አበባን ጨምሮ፣ አስገዳጅ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ ምንም ነገር እንደሌለ አድርጎ ጥንቃቄ አለማድረግ አደጋ አለው፡፡ አፍና አፍንጫ ላይ ዕራፊ ጨርቅ አለማድረግ ጣጣ አለው፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አገራት ክትባት የሚያገኙበትን መንገድ እየጣሩ ባሉበት ሁኔታ፣ በአሜሪካ የሚኖሩ ወገኖች አማርጠው መውሰድ የሚችሉትን ክትባት አንወስድም ማለት ብቻ ሳይሆን ሌሎቹን ሲቀሰቅሱ ማየት አስገራሚ ከመሆን ተሻግሯል፡፡
መረጃው ከተለያዩ ምንጮች የተሰበሰበ ነው፡፡

በኮቪድ 19  ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከተዘገበው በላይ ዕጥፍ ነው ተባለ

ሰበር ኮቪድ ደግሞ ምን ይሆን?

 ከተከሰተ አንድ አመት ያሳለፈው ወረርሽኝ መለስ ሄደት እያለ አንዳንድ ቦታም አራተኛ ዙር ድረስ እየተመላለሰ መክረሙ ለሁላችንም ግልፅ ነው፡፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን መንግሥታቱ በየሀገራቸው በበሽታው የተያዙ፣ ያገገሙ በሎም የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ ሁላችንም እንደምንከታተለው ይህ አሃዝ በየቀኑ እየታደስ በመገናኛ ብዘሁን ይተላለፋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ በሚኖሩ ወገኖች በኩል፣ በኮቪድ የተያዘ፣ በኮቪድ ምክንያት ሕይወቱ ያለፈ ሰው የማያውቅ የለም ብሎ መናገር ያስደፍራል፡፡

አሰከዛሬው ዕለት ጆንስ ሆፕኪንስ ዩነቨርስቲ በየቀኑ በሚያሳየው ግራፍ፣ በአለም አቀፍ ደረጃ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 3.2 ሚሊዮን ነው፡፡ ቀዳሚነቱን የያዘችው አሜሪካም 580,000 አስመዝግባለች፡፡ ከአሜሪካ ቀጥሎ በወረርሽኙ ክፉኛ የተጎዱት አገራት ደግም የደቡብ አሜሪካና የካሪቢያን ደሴቶች ናቸው አሁን በህንድ የሚታየውን ሳይጨምር፡፡ ታዲያ ተንታኞቹ የሚሉት፣ በኮቪድ-19 ምከንያት የሞተው ሰው ቁጥር 6.9 ሚሊዮን ነው፡፡ ያ ማለት በአሃዝ በአደባባይ ከሚታወቀው ዕጥፍ መሆኑ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ የህክምና ተቋማት በደረሰባቸው ቸግር ምከንያት በህከምና አገልግሎት ማነስ ወይም አለመኖር ምክንያ የሞቱ ህሙማንን ሳይጨምር ነው፡፡

ይህን ቁጠር ያስቀመጠው Institute of Health Metrics and Evaluation (IHME) የተባለ በአሜሪካ University of Washington School of Medicine የሚገኝ ቡድን ነው፡፡

ቡድን ለትንነተና የተጠቀመበትን ዘዴ መመልከቱም ይበጃል፡፡ ያም ሆኖ መንግሥታቱ የሚዘግቡት የሟች ቁጥር ከዐውነታው ያነሰ መሆኑን ሁላችንም ግምቱ አለን፡፡ በኮቪድ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሪፖርት ውስጥ የማይገባበት አንደኛው ምክንያት፣ አገሮቹ ሪፖርት የሚየደርጉት የሟች ቁጥረ በበሽታ ተይዘው በሆስፒታል ውስጥ ሲሞቱ በኮቪድ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎችን ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ብዛት ባላቸው ቦታዎች፣ ደካማ የሆነ የጤና ሪፖርት አሰራር ባለመኖሩ በተጨማሪም ወደ ሆሰፒታል ገብቶ ህክምና ለማግኘት ብቃት አለመኖሩ የሟቾችን ቁጥር በትክክል መግለፅ ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡

እንደ IHME ግኝት፣ በሪፖርት ያልተካተቱ የሟቾች ቁጥር በብዛት የታየው ወረርሽኙ በከፍተኛ ደረጃ የተሠራጨባቸው አገሮች ናቸው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ አገሮች በንፅፅር መጠነኛ የወረርሽኝ ሁኔታ የታየባቸው ቢሆንም ሪፖረት ውስጥ ያልተካተተ ግን ከሌላ ጊዜ በላይ የሟቾች ቁጥር ከፍ ብሎ ማግኘታቸው ይታወቃል፡፡ የሟቾችን ትክከለኛ ቁጥር በብዙ ረገድ ኢኮኖሚውን ጨምሮ ዕቅድ ማውጣት ላይ ይረዳል ይላሉ ሙያተኞቹ፡፡

IHME የሚሉት ትንተናው መሠረት ያደረገው፣ ከ1990 ጀምሮ በአለም ላይ በበሽታ ምክንያት በሰዎች ላይ የሚደረሰውን ጉዳት በመለካት ነው፡፡ በዚህም በአለም አቀፍ ደረጃ በበሽታ ምከንያት በሰው ሕይወት ላይ የደረሰውን አደጋም በመለካት ነው፡፡

ቡድኑ ያደረገው በኮቪድ ምክንያት የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ለመገመት፣ በየአመቱ በማንኛውም ምክንያት በየአመቱ ከወረርሽኙ በፊት የመገመተውን ወይም ከሚጠበቀው የሟቾች ቁጥር ጋር በማነፃፀር ነው፡፡ ከሚጠበቀው በላይ የታየው የሟቾች ቁጥር ትርፍ ሞት (Excess death) ወይም ያልተጠበቀ የሞት ቁጥር ነው፡፡ ይህን ሲያሰሉ ትርፍ ሆኖ ወይም ከተጠበቀው በላይ ከተገኘው የሟቾች ቁጥር መሀል በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ በወረርሽኙ ጊዜ አገልግሎት በማጣት በሌላ ምክንያት የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ቀንሰው ነው፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት ሰዎች እምብዛም ሰለማይንቀንቀሱ በትራፊክ አደጋ የሚሞቱሰ ሰዎች ቁጥር መቀነሱንም ታሳቢ አድርገው ነው፡፡ ይህ ሁሉ ስሌት ከተደረገ በኃላ ቀሪው ሞት በኮቪድ 19 ምክንያት ነው የሚሉት፡፡ እንግዲህ ከዛ ውስጥ ምን ያህሉ ነው በሪፖርት የቀረበው፡፡ በሪፖርት ካልቀረበው ጋር ሲደመር የሟቾች ቁጥር ከሚታወቀው በላይ ከፍ እንደሚል ነው፡፡

ባደረጉት ስሌት የአንዳንድ ሀገሮችን ትክከለኛ የሟቾች ቁጥር ያሰቀመጡበትን ዘገባ ላከፍላችሁ፡፡

ለምሳሌ የአሜሪካን ብንወሰድ፣ በአደባባይ የሚታወቀው የሟቾች ቁጥር 574,043 ሲሆን በነሱ ስሌት ግን በኮቪድ ምክንያት የሞተው ጠቅላላ ቁጥር 905,289 ነው የሚሉት፡፡ ይህ ቁጥር ስሌት ባደረጉበት ቀን የነበረው ነው አንጂ ከስሌቶ በኋላ ቁጥሩ በየቀኑ እንደሚጨምር ይታወቃል፡፡ ህንድ ሪፖርት ያደረገችው 221 181 ሲሆን በነሱ ስሌት 654,395 ነው፡፡ ብራዚል 408 680 ሲሆን በስሌቱ 595,903 ነው፡፡ ሜክሲኮ ደግሞ 217,694 ሪፖርት ቢያደርጉም በስሌቱ 617,127 ነው፡፡ ሩሲያ 109,334 ሲሆን በስሌት ደግሞ 593,610 ነው ይላሉ፡፡ ወደ አፍሪቃ ልውሰዳችሁ ግብፅ ሪፖርት ያደረገችው 13,529 ነው ግን ግምቱ 170,041 ይላሉ፡፡ ደቡብ አፍሪቃ ደግሞ 54,390 ሪፖርት ብታደርግም ጠቅላላ የሟች ቁጥር 160,452 ነው፡፡ የብዙ ሀገራት ቁጥሮች ተዘርዝረዋል፣ የጠቀስኳቸው ግን ሪፖረት ያደረጉት ቁጥር ከጠቅላለው በግማሽ ያነሰ የሚመስሉትን ነው፡፡ ጃፓንም ቢሆን ሪፖርት ያደረገችው 10 390 ሲሆን እነሱ የሚሉት 108 320 ሞቶባታል ነው፡፡ እንደሚታወቀው የሟች ቁጥር የሚመመዘገብ ነገር ነው፡፡ በምን ምክንያት ነው የሞቱት የሚለው ነው ስሌት ውስጥ የሚገባው፡፡ የሚያሳስበውና የሚያሰፈራው ሊደርስ ይቻላል ብለው በሚያሰሉት (ሞዴሊንግ) በመስከረም በአለም ላይ የጠቅላላ ሟቾች ቁጥር 9.4 ሚሊዮን ይሆናል ነው የሚሉት፡፡ የምታስታውሱ ካላችሁ ከዚህ ቀደም ወረርሽኙ እንደጀመረ የተለያዩ ቡድኖች በኮቪድ ምክንያት ሊሞት የሚችለውን ቁጥር ግምት እየገለፁ እንደነበር ነው፡፡ የታየ ነገር ቢኖር የሞት ቁጥር እነሱ ከገመቱት በላይ ነው የሆነው፡፡ አሁንም ከገመቱት በላይ እንዳይሆን ፈጣሪ ይርዳን፡፡ ግን ሀላፊነቱ መልሶ የኛ ነው፡፡ መከላከያ ዘዴዎችን ተግባራዊ አለማድረግ ጣጣውን እየጨመረብን ነው፡፡

የኢትዮጵያን ግምት አቅርብ ከማለታችሁ በፊት፣ በ IHME ሪፖርት አሁን ባለው ከቀጠል በመስከረም 2021 አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 22 293 ይሆናል ነው የሚሉት፡፡ ይህ ቁጥር በራሱ ብዙ ቢሆንም፣ እንደ ሁኔታው ከሆነ ያነሰ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ጠንከር ብሎ የተጀመረውን የመከላክል ተገግባር ሁሉም ቢከተልና የፖለቲካ መሪዎችም ሆነ ታወቂ ሰዎች ማስክ በማድረግና የአካል ርቀት በመጠበቅ አርአያ ቢሆኑ፣ የእምነት ተቋማትም ተከታዮቻቸውን ለማዳን የመከላከያ ዘዴዎችን ቢመክሩ፣ ሁኔታው ሊቀለበስ ይችላል፡፡ አዚህ ላይ ክትባት ወስጃለሁና አይዘኝም ብሎ መዝናናት አደገኛ ነገር መሆኑን ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ በመጀመሪያ የወሰዱት የክትባት አይነት በቫይረሱ ከመያዝ ማስጣል የሚችለው በምን ያህል ፐርስንት አንደሆነ ማወቅ ጥሩ ነው፡፡ ከዛም አልፎ በቫይረሱ እንኳን ቢያዝ ምን ያህል ሰው ከከፋ በሽታ ይድናል የሚለውን አሃዝ ወይም ፐርስንት ማወቅ ጥሩ ነው፡፡ አዚህ አሜሪካ እሰካሁንደ ድረስ በሰበር ኮቪድ፣ ማለትም ክትባቱን ወሰድው በቫይረሱ ከተያዙ መሀል ወደ ሰባ ሰዎች መሞታቸው ይታወቃል፡፡ አንድ የሚያሳዝን ዜና ደግሞ፣ የተላላፊ በሽታዎች ስፔሺያሊስት የሆነ፣ ክትባቱን የወሰደ ሀኪም ወደ ህንዳዊ ሰለነበር ህንድ አገር ሄዶ ለርዳታ ሲሰራ እዛው በኮቪድ ተይዞ ሕይወቱ አልፏል፡፡ በሰበር ኮቪድ ተይዘው የሞቱት ሰዎቸ፣ ከድሮውመ ቢሆን በኮቪድ ቢያዙ አደጋ የሚደርስባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ማለትም በዕደሜ የገፉና ተደራቢ በሽታ ያለባቸው ሰዎች፡፡ ሌላው ችግር እነዚህ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ክትባት ቢወሰዱም እንደ ጎልማሳው ወይም ወጣቱ ጠንከር ያለ የመከላከያ አቀም እንደማይፈጥሩ ይታወቃል፡፡ ሰለዚህ ክትባት ቢወሰድም ለነዚህ ሰዎች ሲባል፣ ጥንቃቄው እንዲቀጥል አጠይቃለሁ፡፡ እኛም ራሳችን ክትባቱን ብንወሰድም ገና አብዛኛው ሰው ክትባት ወስዶ ሥርጭት ቀነሶ ነፃ እስከምወጣ ደርስ መዘናጋት አያስፈልግም፡፡ ከራስ በተጨማሪ፣ ክትባት የሚወሰድብት ሌላው ሰብዓዊ ምክንያት ሥርጭቱን ለመቀነስ ነው፡፡

የአሜሪካው ሲዲሲ ክትባት ለወሰዱ ሰዎች ባወጣው መመሪያ፣ ያለ ማስክ መቀላቀል የሚቻለው ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች ጋር ብቻ ነው፡፡ ያም ሆኖ ጥንቃቄው ጥሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የምናየው ማስክ ያደረገና ያላደረገ ጎን ለጎን ተቀምጦ ነው፡፡ ክትባት በመውሰድ ከቤት ውጭ በሚደረጉ ግንኙነቶች ምክሩ ለቀቅ ቢልም በቤት ውስጥና በአዳራሾች ግን ጥብቅ ምክሩ እንደቀጠለ ነው፡’¨<

በዚህ በኮቪድ ከመጣ ሁሉም ሰው መካሪና አስተማሪ መሆን አለበት፡፡ አናምንምና ምንም ነገር አናደርግም የሚሉ ሰዎች ራሳቸውን ገለል አድርገው እንደፈለጉ ይሁኑ ግን ከአንዱ ወደ አንዱ ቫይረሱን ባያቀባብሉ ጥሩ ነው፡፡ ሌሎችም ቢሆን በሚገድል ነገር ይሉኝታው ቢቀር ጥሩ ነው፡፡ ያልፋል እናሳልፈው፡፡ አሜን፡፡raph here.

በአንድ ጊዜ በሁለት የተለያዩ የኮሮና ቫይረሶች የተያዘችው ሴትዮ 07/12/2021

መቼም ክፉ ነጋሪ አትበሉኝ፤ ነገር ግን እንደ ባለሙያተኛ የማውቀውንና የሚፈራውን ማጋራት ጥሩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ችግሮች የአንድ ህሙም ችግር ሳይሆኑ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ባጠቃላይ በሰው ዘር ላይ ሊከሰት የሚችሉ በመሆናቸው ነው፡፡

በሙያችን፣ አንድ ህሙም የተለያየ ዝርያ ባላቸው ነገር ግን ከአንድ የቫይረስ ቤተሰብ በመጡ ቫይረሶች ሲያዙ ማየት ብርቅ አይደለም፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው በሁሉት ወይም በሶስት የተለያዩ ዝርያዎች በአንድ ጊዜ ሲያዝ አደጋው ብዙ ነው፡፡  ከወደ ቤልጀም በቅርብ ጊዜ የቀረበ ዘገባ ያልተጠበቀ ቢሆንም ማስደንገጡ አልቀረም፡፡ ይህን ጉዳይ የተለያዩ የዜና አውታሮች እየተቀባበሉ ለአንባቢ አቀርበውታል፡፡ በዘገባው የዘጠና አመት ዕድሜ ባለፀጋ የሆነች፣ አንድም የኮቪድ ክትባት ያልወሰደች ሴት ታማ ወደ ሆስፒታል ትዘልቃለች፡፡ ህመሙ እየጠናባት ነበር፡፡ ምርመራ ሲደረግ ኮሮና ቫይረስ እንዳለባት ይታወቃል፡፡ አሁን የሚሠራው ነገር፣ አቅሙ ባላቸው አገሮች፣ ኮሮና  ቫይረስ ሲገኝ የቫይረሱ ዝርያ ይመረመራል፡፡ ይህ ምርመራ ወሳኝ ነው፡፡ የትኛው የኮሮና ቁ 2 ቫይረስ ዝርያ እየተዘዋወረ መሆኑን ማወቅ ያስችላል፡፡ እንደሚታወቀው የኮሮና ቁ 2 ቫይረስ በየጊዜው አዳዲስ ዝርያዎችን እየፈጠረ ነው፡፡ ከነዚህ አዲስ ከተፈጠሩት መሀል በባህሪ ጠንከር ወይም ከፋ ያሉት አሳሳቢ ዝርያዎች ይባላሉ፡፡ እሰከ ቅርብ ቀን የአሳሳቢ ዝርያዎች ቁጥር ወደ አስር ደርሷል፡፡ አሁን በተራው አለምን እያተራመሰ የሚገኘው፣ መጀመሪያ በህንድ አገር የታየው በአዲሱ መጠሪያው ዴልታ የሚባለው ቫይረስ ነው፡፡ በዘጠና ስምንት አገሮች ተሠራጭቷል፡፡ በአፍሪቃም ወደ ሶሰተኛ ዙር ማዕበል እያመራ ያለው ይህ አዲሱ ዴልታ ሳይሆን እንደማየቀር ይገመታል፡፡ ከባህሪዎች አንዱ፣ ከዚህ በፊት ከነበሩት ቫይረሶች በበለጠ በፍጥነት የመሠራጨት ችሎታው ነው፡፡

ወደ ሴትዮዋ ልመልሳችሁ፡፡ በሴትዮዋ ላይ በምርመራ የተገኛው የኮሮና ቫይረስ ሲታይ አንድ ዝርያ ብቻ ሳይሆን ሁለት ዝርያዎች ሆነው ይገኛሉ፡፡ አንደኛው በእንግሊዝ አገር የታየው አልፋ የሚባለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መጀመሪያ በደቡብ አፍሪካ የታየው ቤታ የሚባለው ቫይረስ ነው፡፡ ሴትዮዋ በሁለቱ ቫይረሶች ልትያዝ የበቃቸው ከተለያዩ ሁለት ሰዎች መሆናቸውን ዘግበዋል፡፡ ክትባት እንዳልወሰደች አስታውሱ፡፡ ካልወሰደች ደግሞ በቂ የመከላከል ዘዴ መጠቀም ይኖርባት ነበር፡፡ ሴትዮዋን ያስያዙዋት ሰዎች እነማን እንደሆኑ ግልፅ አይደለም፡፡ የዘጠና አመት ዕድሜ ያላት ይህች ሰው በህክምና ብትረዳም በሽታው በጣም ጠንቶባት ህይወቷ አልፏል፡፡ ለሞት ያበቃት በሁለት ቫይረስ ዝርያዎቸ መያዟ ይሆን የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡ በህክምናው አለም፣ ኮሮና ቫይረስ ቁ 2 በተመለከተ፣ በሁለት የተለያዩ የቫይረሱ ዝርያዎች ለመያዟ በማስረጃ የተረጋገጠ ሁኔታ ቢኖር ሴትዮዋ የመጀመሪያ ናት፡፡

የተለያዬ የቫይረስ ዝርያዎች በአንድ ሰው ላይ መገኘት ከፍተኛ አደጋ አለው፡፡ ብታምኑም ባታምኑም (የቫይረስ ሴክስ) ይሉታል፣ የተለያዩ ዝርያዎች በአንድ ቦታ ሲኖሩ በሚራቡበት ጊዜ በመዳቀል ሌላ አዲስ ቫይረስ ዝርያ መፍጠር ይችላሉ፡፡ ይህንን እንኳን በኤች አይ ቪ የምናወቀው ነገር ነው፡፡ ፍራቻው ምንድን ነው፣ አዲስ የተደቀለው ቫይረስ ምን አይነት ክፉ ባህሪ ይዞ ይመጣል ነው፡፡ ፖለቲካ አወራህ አትበሉኝ እንጂ፣ ከዚህ በፊት እንዳየነው የዘር ፖለቲካ የሚያራምዱ ጥቂት ሰዎች ያውም በከፍተኛ ደረጃ፣ ራሳቸው ከተለያዩ ዘሮች የመጡ ናቸው፡፡ አንድ ሰው “ድብልቁ ነው ያስቸገረን” ሲል ሰምቻለሁ፡፡ ያም ሆኖ አብዛኛው ከተለያዩ ብሄረሰቦች ወይም ማህበረሰቦች የመጣው ህብረተሰብ ሰላም ወዳድና አብሮ መኖርን ናፋቂ ነው፡፡

ሌላው ደግሞ ከአንድ ቫይረስ የወጡ የተለያዩ ዝርያዎች ሳይሆን፣ የተለያያ የቫይረስ ዝርያዎች በአንድ ላይ ቢገኙስ የሚለው አስፈሪ ጥያቄ ነው፡፡ ለምሳሌ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስን ብትወስዱ፣ የወፎች፣ የአሳማዎች እናም የሰዎች የኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶች አሉ፡፡ እነዚህ ርስ በራሳቸው የመዳቀል ባህሪ አላቸው፡፡ ለምሳሌ የሰው ኢንፍሉዌንዛ ከሰው ወደ ሰው የመሻገር ችሎታው ከፍ ያለ ነው፡፡ በሌላ ጎን የወፍ ኢንፍሉዌንዛው ደግሞ ከሰው ወደ ሰው መሻገር ላይ ደካማ ሆኖ ነገር ግን የማሳመምና የመግደል ችሎታው ከፍ ያለ ነው፡፡ አይጣልና እነዚህ ሁለቱ ተዳቅለው፣ የመሻገር ችሎታውን ከሰው፣ የመግደል ችሎታውን ከወፍ ዝርያው ኢንፍሉዌንዛ ያደቀለ አዲስ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ብቅ ቢልስ? ገምቱ፡፡ ለዚህ ነው፡፡ ተላላፊ በሽታ የዛ ማዶ መንደር ሰዎች ችግር ብቻ አይደለም፡፡ የሁላችንም ነው፡፡ አሁን ከህንድ ተነስቶ አለምን እያተራመሰ ያለው ዴልታ የህንድ ችግር ብቻ ሆኖ አልቀረም፡፡

ኮሰትር ወዳለ ነገር ስንመለስ፣ ክትባት አንወስድም የሚሉ ብዙ ዜጎች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ መብታቸው ነው እንበል፡፡ ነገር ግን በቫይረሱ ተይዘው ቫይረሱን ወደ ሌሎች ሰዎች የማሻገር መብት ግን ሊኖራቸው አይገባም፡፡ አንከተብም ካሉ ከቢጤዎቻቸው ጋር ይቀላቀሉ፡፡ ያም አደጋ አለው፡፡ ምክንያቱም ቫይረሱ በተራባ ቁጥር አዳዲስ ዝርያዎች ሰለሚፈጥር መልሶ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አደጋሰለሚያስትል ነው፡፡ የሚገርመው እነዚህ ፀረ-ክትባት አቋም ያላቸው ሰዎች፣ ጉዳዩን የጤና ችግር ከማድረግ ይልቅ፣ የፖለቲካ ካደረጉት ስንብቷል፡፡ ደጋፊ ለማምረት የሚጥሩ ሰዎችም እየተጠቀሙባቸው ነው፡፡ አሁን በዚህ በአሜሪካ የወግ አጥባቂ ፖለቲካ አራማጅ የሆኑ ሰዎች ባደረጉት ስብሰባ ላይ፣ የአሜሪካ መንግሥት በሚፈለገው መጠን ሰዎችን ማስከተብ አልቻለም ተብሎ ሲነገር በደስታና በጩኸት ማጨብጨባቸውን ስንሰማ በጣም የሚያስደንግጥ ሳይሆን የሚዘገንን ሁኔታም ነው የሆነው፡፡ በምንም መልኩ ወገንተኝነት ዳኝነት አያውቅም፣ በፖለቲካውም እንዲሁ ነው፡፡

ለማንኛውም፣ የዚህን ቫይረስ ሥርጭት ለመቀነስ ሁላችንም እንረባረብ፡፡ ክትባት ባለበት ክትባቱን፣ ከዛ ጋር ተያይዞም በዕራፊ ጨርቅ አፍና አፍንጫን ሸፍኖ ከዚህ ጣጣ ማምለጡን ተመስገን ማለት ተገቢ ነው፡፡ በነገራችን ላይ፣ ከዚህ ቀደም፣ በኮቪድ በጣም የሚጎዱ ሰዎች ዕድሜያቸው ከ65 አመት በላይ የሆኑ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በአሜሪካ፣ በዚህ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ክትባቱን በብዛት ከወሰዱ የህብረተሰብ ክፍል እንደመሆናቸው፣ በኮቪድ ተይዘው ወደ ሆስፒታል የመግባት መጠኑ በጣም ቀንሶላቸዋል፡፡ የተከተቡ ሰለሆነ፡፡ በተራው ግን ሆስፒታሎችን እያጣበቡ ያሉት ዕድሜያቸው ከ18-49 አመት ያሉ ጎልማሶች ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው፣ ክትባት አንወሰድም የሚለው ወገን በብዛት በነዚህ ዕድሜ ገደብ ውስጥ ያለው ነው፡፡ 

ራሳቸው የሠጡትን ክትባት የወሰዱ ሰዎችን አትገቡም አሉ
የአውሮፓ ግሪን ፓስ (ይለፍ) ያስነሳው ጣጣ 
07/01/2021

የኮቪድ ክትባት በስፋት በአለም ደረጀ እየተሠጠ ነው፡፡ ቁጥሩ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ተሻግሯል፡፡ ነገር ግን ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጋውን በኮቪድ መሞታቸው የሚታወቁትን ሰዎች ቁጥር አልደረሰበትም፡፡ አሁን ጥያቄው የትኛውን ክትባት የትኛው አገር ወሰደ የሚለው ነው፡፡

አዎሮፓና ያደጉ አገሮች በኮቫክስ አማካኝነት ወደ አፍሪካ የላኩት አስትራ ዜኔካ የሚባለውን ክትባት ነበር፡፡ አማራጭ የሌላቸው የአፍሪቃ አገሮችም ለዜጎቻቸው አዳረሱ፡፡ ሆኖም የሚቀጥለው ዙር ክትባት ይደርሳል ሲባል፣ ህንድ በወረርሽኙ በክፉ ደረጃ ሰለተመታች፣ የህንድ ዜጎች እኛ ሳንከተብ እንዴት ተብሎ ወደ ውጭ ይሸጣል በማለታቸው አፍሪቃውያኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁለተኛውን ዙር ክትባት ለዜጎቹ ማድረስ አልቻሉም፡፡

እዚህ ላይ የመጀመሪያውን ክትባት ብቻ ወሰዶ የሚጠበቀው ውጤት ላይመጣ ቢችልም፣ ነገር ግን የሁለተኛው ክትባት መዘግየቱ ክፋት የለውም ሰለዚህ ዜጎች መደናገጥ የለባቸውም፡፡ እንደ አንዳንድ ዘገባዎች፣ ሁለተኛው ክትባት በዘገየ ቁጥር ለክትባቱ የሚሠጠውና የሚጠበቀው የመከላከያ ምላሽ የበረታ ነው፡፡ ሰለዚህ ዜጎች ሊረጋጉ ይገባል፡፡ ተገቢውን የመከላከያ ተግባር መቀጠልም የግድ ነው፡፡

ወደ ክትባቱ ስንመለስ፣ በዚህ ሳምንት አውሮፓውያኑ ያደረጉት ነገር አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ይህም የሆነው፣ የአውሮፓ ህብረት ዜጎቻቸው አንደልብ እንዲንቀሳቀሱ በማለት የክትባት የይለፍ ካርድ አዘጋጁ፣ አርንጓዴው ማለፊያ ወይም በአንግሊዝኛ Green pass ይባላል፡፡ ይህ ማለፊያ ዲጂታላይዝድ የሆነ በራሱ ላይ ኮድ ያለው ስለሆነ ሰዎች መከተባቸውን ማረጋገጥ የሚቻልበት ዘዴ መፍጠራቸው ነው፡፡ ታዲያ ካርዱን ሲሰጡ አንደኛ የኮቪድ ክትባቶችን ሁለቱን የወሰዱ፣ ሁለተኛ ከዚህ በፊት በኮቪድ ተይዘው የነበሩ ሰዎች እንደሚነሱበት ሀገር አንድ ወይም ሁለት ክትባት የወሰዱ፣ ሶሰተኛ ደግሞ ኮቪድ ይዟቸው ያገገሙ፣ ከዚያ ውጭ ግን የኮቪድ ምርመራ ተደርጎላቸው ቫይረሱ ላልተገኘባቸው የሚሠጥ ነው፡፡

ችግር የመጣው የኮቪድ ክትባት ተብለው የተዘረዘሩት፣ በአውሮፓ ፈቃድ ያገኙትን ክትባቶች ብቻ እንጂ በአውሮፓ ፈቃድ ያላገኙትን ክትባቶቸ የተከተቡ ሰዎች ተቀባይነት አይኖራቸውም የሚለው መግለጫ ነው፡፡ በተለይ ከአውሮፓ ውጭ ለሚመጡ ሰዎች ወደ አውሮፓ አትገቡም የሚል ነው፡፡ ይሁን፡፡ ችግር የተፈጠረው፣ በአውሮፓ የተሠራውን የአስትራ ዜኔካ ክትባት የሚቀበሉ ሲሆን፣ ይህንን የራሱን የአስትራ ዜኔካ ካምፓኒ የሚሠራውን ክትባት ግን በህንድ አገር የሚመረተውን አንቀበልም አሉ፡፡ ጉድ ፈላ፡፡ በህንድ አገር ሲረም በሚባል ካምፓኒ የሚሠራውን ይህንን የአስትራ ዜኔካ ክትባት ወደ አፍሪካ ያደሉት ራሳቸው አውሮፓውያኑ ናቸው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ያንን ከህንድ የተሠራውን ተመሳሳይ ክትባት አንቀበልም የሚሉት፡፡ ይህ ነገር ያስቆጣቸው ህንዶች፣ መልስ ሲሰጡ አንደዛ የምታደርጉ ከሆነ፣ እኛ ደግሞ በተራችን የአውሮፓውን አረንጓዴ ወይም ግሪን ፓስ ዕውቅና አንሠጥም አሉ፡፡ በዚህ መሀል፣ ርግጠኝነቱ አልታወቀም እንጂ አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች፣ ግድ የለም የህንዱን የአስትራ ዜኔካ ክትባት አንቀበላለን አሉ፡፡ ቁጥራቸው ወደ ዘጠኝ ይደረርል ይባላል ግን ሁሉም ዘጠኙም የህንዱን ክትባት ዕውቅና መሥጠታቸው አልተረጋገጠም፡፡

ይህ ጉዳይ በሰፊው ያሳሰበው የአፍሪካ ህብረት በተለይም የአፍሪካ ሲዲሲ ነገሩን ትክክል አይደለም አለ፡፡ በአንድ ካምፓኒ የሚሠራ ክትባትን አንደኛው አውሮፓ ሰለተሠራ ሌላኛው ደግሞ ህንድ ሰለተሠራ፣ መርጦ የህንዱን አልቀበልም ማለት ትክክል አይደለም ሲል መግለጫ አወጣ፡፡

ለምን ህንድ የተሠራውን ከለከሉ ሲባል ምክንያት የሚሠጡት፣ ህንድ የሚሠራው ክትባት በአውሮፓ ፈቃድ አላገኘም ነው የሚሉት፡፡ ጠያቂዎች ደግሞ፣ እንደዛ ከሆነ ክትባቱን ወደ አፍሪካ ከመላካቸው በፊት ለምን ፈቃዱ እንዲጠየቅ አላዳረጉም ይላሉ፡፡ ነገሩን ወደሌላ ነገር ያሰፉት ሰዎችም አሉ፡፡ ሆን ተብሎ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ምክንያቱም ቢዘህ ጉዳይ አውሮፓ መግባት የማይችሉ አገራትን ማስተዋል ነው፡፡

እዚህ ላይ፣ በአሜሪካም ቢሆን፣ ክትባት የወሰዱና ያልወሰዱ የሚባል መለያ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ምን ያህል ርግጠኛ እንደሆነ ባይታወቅም፣ በዚህ በዋሽንግተን ዲሲ፣ የነፃነት ቀን ሲከበር የሚተኮሰውን ርችት ለማየት ሰዎች በሁለት በኩል ይሰባሰባሉ፤ ያም ክትባት የወሰዱና ያልወሰዱ በሚል የሚል ዜናም አለ፡፡ በዚህ በአሜሪካ የሚሠጡ ክትባቶችን የወሰደ አውሮፓ ችግር የለበትም፡፡ ግን አሜሪካ እየኖሩ አማራጭ እያላቸው ክትባት ላለመውሰድ ሰበብ የሚፈጥሩ ሰዎች ልብ ቢሉ ጥሩ ነው፡፡ በአገር ቤት የተሠጠውን ክትባት የወሰዱ ሰዎች በጉዞ ላይ ይህንን ያህል ነገር በአውሮፓውያን መፈጠሩ ምን ያህሉ ኢትዮጵያዊ አውሮፓ እንዳልሄደ ነውና ትልቅ ችግር ባይፈጥርም ክትባቱን የማጣጣል ስሜት ይፈጥራል የሚል ፍራቻ አለ፡፡ ሆኖም አውሮፓውያኑ በአውሮፓ የሚሠራውን የአስትራ ዜኔካን ክትባት ራሳቸው ሰለሚጠቀሙ የጥራት ጥያቄ ካልተነሳ በስተቀር ክትባቱ ጠቀሜታ ላይ የተለየ ቸግር አይኖርም፡፡ በዚህ ጉዳይ፣ አስትራ ዜኔካ ክትባት ወስዶ አጋጣሚውን አግኝቶ ወደ አሜሪካ የሚመጣ ሰው ካለ፣ እዚህ አሜሪካ የሚሠጡ የፋይዘር ወይም የሞደርናን ክትባት መውሰድ ይችላሉ፡፡ ምናልባትም በኛ በባለሙያተኞች በኩል፣ ሞደርና ወይም ፋይዘር ወስደው አስትራ ዜኔካ ወይም ጆንሰን ጆንሰን በተከታይ መውሰዱን አንመክርም፡፡

ለዚህ እንግዲህ ለዘለቄታው፣ ዞሮ ዞሮ አገር ማሳደግ መፍትሄ ነው፡፡ ያደገ አገር የራሱን ክትባት መሥራት ይችላል፡፡ ኢትዮጵያም ቢሆን በዚህ ሁሉ ችግር መሀል ክትባትን በሚመለከት የራሳችን ክትባት መሥራት አለብን የሚል አቀረቀረብ ከተዘረዘሩ ዕቅዶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እንደምታዩት በርዳታ በሚሠጡ ነገሮች ታዳጊ አገሮችን እንደልባቸው ማወዛወዝ እንደሚፈልጉ ግልፅ ነው፡፡ በኮቪድ ክትባት ምክንያት በምዕራባውያኑና በሌሎቹ መሀከል የቫክሲን ዲፕሎማሲ ዘመቻ በማለት ፉክክር እንዳለ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ስናድግ ወላጆቻችንና ዘመዶቻችን “ከሰው እጅ አትጣለኝ” ብለው ሲፀልዩ እናስታውሳለን፡፡ ከሰው እጅ ላለመውደቅ አገርን ማጠነከር አስፈላጊ ነው፡፡ አስከ መቼ ነው እየተቆራቆስን ራሳችን እያደከምን ለዚህ ሁሉስ የምንጋለጠው?

መልካም ንባብ