መለስ ብለን ስናይ ለምን አዚህ ደረጃ ተደረስ ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ይህ ወረርሽኝ ሲከሰት፣ መጀመሪያ የነበረው አመለካከት፣ አዎ ኮቪድ አለ ግን ብዙ ሰው አይገድልም ነበር፡፡ ወደኋላ ግን ያ አመለካካት፣ እንዳውም ኮቪድ የለም ወደሚለው የተሸጋገረ በሚመስል ሁኔታ መዘናጋትና መሰላቸት ታየ፡፡ ያ እንግዲህ ጥንቃቄዎች ወዳለመተግበር ተሸጋገረ፡፡ ከዛም አልፎ፣ ቫይረሱን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሰራጩ ስብስቦች ያለማቋረጥ ይካሄዱ ጀመር፡፡ ግማሾቸ አስገዳጅና ሰሜታዊ ሁኔታ የተመረኮዙ ቢሆንም ሌሎቹ ሆን ተብለው ታቅደው የሚደረጉ ነበሩ፡፡ ትልቁ ምክንያት ይህ ሲሆን፣ በግለሰብና በቤተሰብ ደረጃ ደግሞ ያለምንም ጥንቃቄ ሰዎች በሠርግ፣ በልደት በቀብር መገናኘታቸውን ቀጠሉ፡፡ አንዳንድ ቦታ በተገላቢጦሽ ማሰክ ማድረግ ነውር ሆነ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ የፖለቲካ መሪዎች ሆነ፣ ሌሎቹም በቴሌቪዢንም ሆነ በሌላ ማዕክል ሲታዩ ማስክ ሳያደርጉ፣ ርቀት ሳይጠብቁ፣ በአዳራሾች ውስጥ ስብሰባ ሲመሩ ይታዩ ጀመር፡፡ ታዲያ አመራሮችና የኮቪድ መከላከያ አይነተኛ የሆነውን ነገር ሳይደርጉ ሲታዩ ኮቪድ የለም ለሚሉ ሰዎች መረጃ እየሰጡ መሆናቸውን የተገነዘቡም አይመስልም፡፡ ይህ በፖለቲካ አመራሮች ብቻ ሳይሆን፣ ሌለቾም የሥነ ጥበብ ሰዎችና ታወቂ ሰዎች አርኣያ መሆን አልቻሉም፡፡ ህዝቡን ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ይታደጋሉ ወይም ያስተምራሉ የሚባሉ የመገናኛ ብዙሀን ሰዎቸና ጋዜጠኞችም ከዚህ ስህተት ኣላመለጡም፡፡ ባጠቃላይ የውሽት ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የታቀደ ይመስል፣ ሰለ ኮቪድ ማውራቱም ተረሳ፡፡ ሰዎች ተዘናጉ፡፡

ሌላው አደገኛ ሃሳብ ደግሞ፣ መጀመሪያ ዙር በመጣው ቫይረስ ተይዘው በቀላሉ የተገላገሉ ሰዎች ደግሞ፣ ተይዤ ምንም አልሆንኩም በማለት መዝናናት፣ ማስክ አለማድረግ፣ እንዳውም መከላከያ አለኝ በማለት የተዘናጉ ይመስላሉ፡፡

አሁን፣ የኮሮና ቫይረስ አዳዲስ ዝርያዎች መፈጠራቸውን ያልሰማ ሰው ያለ አይመስልም፡፡ በወቅቱ፣ አዲስ ከተፈጠሩት ዝርያዎች አምስቴ አሳሳቢ የሚባሉ ናቸው፡፡ ለመጥቀስ ያክል፣ የኢንግላንድ፣ የደቡብ አፍሪቃ፣ የብራዚል(ሁለት)፣ የካሊፎርንያና የኒውዮርክ ናቸው፡፡ እድሜ ለማያቋርጥ ሥርጭት ሌለቾም እንደሚፈጠሩ ጥርጥሬ የለም፡፡ የነዚህ አዲስ ቫይረሶች የጋራ ፀባይ፣ በፍጥነት የመዛመት ችሎታቸው ነው፡፡ ሁሉም ይህን ተክነዋል፡፡ አስፈሪ የሆነው ደግሞ፣ የታማሚዎችን ቁጥር ይጨምራሉ ወይ እናስ ከዚህ ጋር ተያይዞ የመግደል ችሎታቸው ይጨምራል ወይ የሚሉ ጥያቄዎች አሉ፡፡ በመረጃ እንደሚታወቀው ከኢንግላንደ ተገኘ የተባለው ቫይረስ ከድሮው ቫይረስ በተለየ ሰዎችን የማሳመም ችሎታው መጨመሩ ሲታወቅ፣ የመግደል ችሎታው ደግሞ ከድሮዎ ቫይረስ ጋር ሲነፃፀር ከ60 በመቶ በላይ መጨመሩ ነው፡፡ የደቡት አፍሪቃውም ቢሆን በቅርቡ በወጣ መረጃ፣ ከድሮው ጋር ሲነፃፀር፣ ታመው በሆስፒታል በሚረዱ ሰዎች ላይ ሀያ በመቶ የመግደል ችሎታው ጨምሯል፡፡ አንግዲህ እነዚህ ቫይረሶች ምን ያህል በስፋት ተሠረጭተዋል ተብሎ ሲጠየቅ፣ የኢንግላንዱ በ94 አገሮች የተገኘ ሲሆን፣ በአውሮፕ ለሶስተኛ ዙር ለታየው የወረርሽኝ ማዕበል ምክንያት ሆኖ፣ ደንበሮችን ወደማዘጋት ደረጃ ደርሷል፡፡ 94 አገሮች ላይ ከታየ አፍሪካ ላለመግባቱ ማረጋገጫ የለም፡፡ ነገር ግን አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው አዲስ ማዕበል በነዚህ አዲስ ቫይረሶች ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የኢትዮጵያ ባለሙያተኛ ሀላፊዎች የሚናገሩት ነገር ነው፡፡ ሆኖም፣ ኢትዮጵያ በሀገሪቱ ውስጥ የሚዘዋወረውን ቫይረስ ማጥናት አለመቻሏ፣ ከኢንግላንድ በኩል በር እንዲዘጋባት ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ ሌላው በርግጥ የሥርጭቱ መጠን መጨመር ነው፡፡ የሚዘዋወሩ ቫይረሶችን ለማጥናት ባለሙያተኞችና ማጥኛው የተዘጋጀ ቢሆንም በበቂ መጠን ለማጥናት ግን በቂ ገንዘብ የለም፡፡ ድህነት በስንቱ ይጎዳል፡፡ እናም፣ መንግሥት ሳይሆን፣ ባለፀጎቹ፣ አየር መንገዱን ጨምሮ፣ ለዚህ ጥናት የገንዘብ ድጎማ ቢያደርጉ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ የሚሠራጨውን ቫይረስ ማወቅ ይቻል ነበር፡፡ የምታነቡ ሰዎች፣ ይህንን ሀሳባ ወይም ጫና ብታደርጉ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በዚህ ርዕስ ባልነካውም የሚዛወረውን ቫይረስ አይነት ማወቅ ከህክምና ጀምሮ ክትባት ላይ የሚደረገውን እንቅስቃሴ አቅጣጫ የሚያሰቀይስ ነገር ነው፡፡

አሁን ሁላችንም፣ ስለሥርጭት መጨመር እንደ አይነት ደረጃ ያለን ይመስለኛል፡፡ የሥርጭቱ መጨመር ያሰከተለውን ግልፅ ጉዳይ እንመልከት፡፡

አንደኛ፣ በግልፅ የታማሚዎች ቁጥር መጨመር ነው፡፡ በዚህም የኮቪድ ህክምና ማዕከሎች ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ፣ ሌሎች ሆስፒታሎች በዚህ ጉዳይ እንዲረባረቡ ቢደረግም፣ ከአቅም በላይ እየሆነ ከመጣ ቆየ፡፡

ሁለተኛ፡ የህክምና ተቋማት መጨናነቅ ብቻ ሳይሆን፣ ለኮቪድ በሽታ አይነተኛ ወይም ዋና ርዳታ የሚሠጠው ለህሙማኑ ኦክስጅን በመሥጠት ነው፡፡ በበለፀጉ አገሮች አንደሚታየው፣ አኮስጅን ከግድግዳ በኩል ሳይሆን በሲሊንደር ተሞልቶ ወደየሆስፒታሎቹ የሚወሰድ ነገር ነው፡፡ ያ ደግሞ ለታማሚዎች በበቂ መጠን መድረስ አለመቻሉ ዕጥረቱ በከፍተና ደረጃ እየታየ ነው፡፡ የሚያሳዝነው፣ በኮቪድ በሽታ ለታመሙ ሰዎች አኮስጅን ሲሰጥ በደቂቃ ከፍተኛ የኦክስጅን መጠን መለቀቅ ሰላለበት፣ በሲሊንደር ተሞልቶ የሚላክ ኦክስጅን ወዲያው ነው የሚያልቀው፡፡ በዚህ መሀል እንግዲህ በኮቪድ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ግልፅ ነው፡፡ የአልጋ በተለይም የ አልጋዎች ዕጥረት ሌላ ነገር ነው፡፡ የአርቲፊሻል መተንፈሻ ዕጥረት ደግሞ ሁኔታውን አባብሶታል፡፡

ሌላው በጣም አደገኛው ነገር ደግሞ፣ የህክምና ቦታዎች በኮቪድ በሽታ በሚሰቃዩ ህሙማን ከተወጠረ፣ በሌላ በሽታ የሚሰቃዩ ሰዎችን እንዴት መርዳት ይቻላል፡፡ ሰለዚህ በተዘዋዋሪ መንገድ በኮቪድ በቀጥታ ባይሆንም በኮቪድ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ግልፅ ነወ፡፡

ሌላው ከአዲሶቹ ቫይረሶች የሚታየው ባህሪ፣ በዕደሜ የገፉትን ብቻ ሳይሆነ ጎልማሳና ወጣቶችን መያዝ ብቻ ሳይሆነ ለህመም እየዳረገ መሆኑን ከጀርምን በኩል የዘለቀው ሪፖርት መረጃ ይሆናል፡፡ ያው እንደሚታወቀው በዕድሜ የገፉ ሰዎች አደጋ ላይ መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡

በዚህ ሰአት ኮቪድ አለ ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ጉዳት እያደረስ መሆኑን መገንዘብ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ታዲየ ምን ይደረግ ለሚለው፣ በግልፅ እንደሚታየው ኢትዮጵያ ይህንን ወረርሽኝ በክትባት መወጣት የማትቸለው ነገር መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የተገኘውም መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ትልቁና ደንበኛው ክትባት አለመያዘ ነው፡፡

ሰለዚህ ይህን ችግር በደንብ የተገነዘባችሁ ሰዎች ሌሎችን ከማስተማር አለመቆጠብ አንዱ ትል ቁ ነገር ነው፡፡ ከዛ ውጭ ግን የመከላከያ ተግባራትን መከተል ወሳኝ ነው፡፡ ይህንን በማድረጋቸው በደህና ሁኔታ የሚገኙ አገሮች አሉ፡፡ ለምስክርነት፡፡ ማስክ ማድረግ ወሳኝ ነው፣ ርቀት መጠበቅ ወሳኝ ነው፣ ስብስብ ማቆም በተለይም በቤት ወስጥ ወሰኝ ነው፡፡ እጀን ቶሎ ቶሎ መታጠብ ሌለው ነገር ነው ይህ ነው የተጠየቀው፡፡

እኔ የምማፀነው፣ ከቪድ ከያዛቸው አደጋ ላይ የሚወድቁ የቤተአብ አባላትን ደግሞ መጠበቅነ እንዳይጋለጡ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለቅሶና ሙሾ …

እነዚህን ተግባራት ሌሎች አስኪነግሩን ድረስ መጠበቁ አደጋ አለው፡፡ የበሽታና የሞቱ መጠን ብዙም ተፅዕኖ ላልፈጠረባቸው ሰዎች ደግሞ፣ በዚህ በሽታ ሥርጭት ምክንያት አኮኖሚው ላይ የሚደርሰው አደጋ ሌላ አስከፊ ነገር ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ደግሞ፣ አውሮፓውያኑ ለጎረቤት አገሮች በር እየዘጉ ባለበት በአሁኑ ሁኔታ በኢንግላንድና በሌሎቹም በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰው በር መዘጋት ከፍተኛ አደጋ ያስከትላል፡፡

በርግጥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆኑ ሌሎች ችግሮች አሉባት፣ ሰዎች በየቦታው በማንነታቸው ምክንያት ብቻ ሰይሆን፣ ሰው በመግደል የፖለቲካ መልክት ማሰተላለፍ በሚመኙ ሰዎችና ቡድኖች የሚፈፀመው ኢሰብኣዊ ድርጊት የሚዘነጋ አይደለም፡፡ እሱም በአግባቡ ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሄ ማግኘት አለበት፡፡ ነገር ግን፣ ይህ ሁኔታ እያለ ሰለ ኮቪድ አታውሩብን የሚሉ ወገኖች ደግሞ እየታዩ ነው፡፡ ሰከን ብለው ካሰቡበት፣ ኮቪድን መቆጣጠር ካልቻልን፣ የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ መፍትሄውን የሚያናክል ሁኔታ የሚፈጠር መሆኑን መዘንጋት ይኖባርቸዋል፡፡ ለማንኛውም ለሰው ህይወት የምንቆረቆርና የምናዝን ከሆነ፣ በቫይረስ ለሚሞተው በተለይም ማስቀረት በሚቻልበት ሁኔታ እኩል መቆርቆር አለብን፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መርዳት የሚችሉት ነገር ቢኖር፣ የመጀመሪያው ቤተሰብን በመምክር፣ በዚህ አደገኛ ጊዜ ጉዞን ማራዘም፣ ከዛ ደግሞ ህዝቡ ማስክ እንዲያደርግ እየመከርን ባለንበት ሁኔታ በቂ ማስክ ሊደርሳቸው የሚችልበትን ሁኔታ ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ፣ በከፍተኛ ደረጃ የኦክስጅን ዕጠርት መታየቱ ግልፅ ሰለሆኔ፣ በውጭ አገራት፣ የአካባቢ አየርን ወደ ንፀኁ ኦክስጅን መቀየር የሚችሉ መሳሪያዎች (concentrators ) ይባላሉ፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚላኩበትን መንገድ ማሰብና በጋራ ርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ በክትባቱ በኩል ካየን፣ ኢትዮጵያ በሚሰጣት ክትባት ጥቅላላ ዜጎቿን ለመከተብ አመታት እንደሚወስድባት ይነገራል፡፡ ሆኖም ሌሎቸ አገሮች አንደሚያደርጉት፣ አገሪቱ በጎን በራሷ ወጭ ክትባት መግዛት ይኖርባታል፡፡ ነገር ግን አቅሙ የለም፡፡ ሰለዚህ በጋራ ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር ጥሪ ሊመጣ ሰለሚችል ለዚህ ጥሪ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጅት ማድረግም ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን፣ ፈጣሪን መለመን የሚያሰፈልግበት እንዲህ ያለ ጊዜ አይኖርም፡፡ ፋሲካን ለማክበር ከመሯሯጥ የፆሙን ጌዜ ማራዘም ይቻል ይሆነ?

ሌላው ማየት የምንችለው ነገር ደግሞ፣ አቅጣጫ ነው፡፡ በግረፍ ሲታይ የበሽታው ሥርጭት ወደየት እየሄደ ነው የሚለውን ማለት ነው፡፡ በግራረፉ እንደምታዩት ተመሳሳይ የምርምራ ቁጥር እየተደረገ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር መጨመሩን የሚያስረዳው የግራፉ አቅጣጫ ወደ ላይ መሄዱ ነው፡፡

የሞትን ጉዳይ ካነሳን፣ የሚታወቀው ምርመራ ተደርጎ የተረጋገጠላቸው ሰዎቸ ቁጥር፣ በየሳምንቱ ሪፖረት ላይ ሲታይ፣ ከቀደመው ሳምንት የተከታዩ ሳምንት ሪፖርት የሚየሳየው የሟቾች ቁጥር በዕጥፍ መጨመሩ ነው፡፡ ነገር ግን፣ በሪፖርቱ ላይ የቀረበው ሪፖርት በውነት ትክከለኛውን ሁኔታ ያስረዳል ወይ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ መልስ አይደለም ነው፡፡ በየቤቱ የሚሞተውን ሰው በኮቪድ ምርመራ በማይደረግበት በአሁኑ ወቅት በኮቪድ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን ትክክለኛ አሃዝ ማወቅ ያስቸግራል፡፡ ይህ ልዩነት ደግሞ የኢትዮጵያ የተለየ ችግር ብቻ ሳይሆን በአሜሪካም የሚታወቅ ችግር ነው፡፡ በአደባባይ የተለጠፈው የሟቾች ቁጥር፣ ሰለዚህ፣ ከሚታወቁት ነው እንጂ ሁሉንም አይወክልም፡፡ በዚሀ ጊዜ፣ ትርፍ ሞት የሚባል ነገር አለ፡፡ ከዚህ ቀደም በየአመቱ ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ከዛ አማካይ ቁጥር በላይ ያልተጠበቀ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሲታይ፣ ትርፍ ሞት ይባላል፡፡ በእንግሊዝኛ  Excess death ይሉታል፡፡ አናም፣ ያ ትርፍ ሞት ከየት መጣ ነው፡፡ በአሜሪካ ስሌት ሲደረግ ከሚጠበቀው በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወቃል እናም ያ ትርፍ ሞት 61 ከመቶ በላይ የሆነው በኮቪድ አማካኝነት ነው ይላሉ፡፡ ሰለዚሀ ከግማሸ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሞቱበት አሜሪካ በደንብ ክትትል ቢደረግ የሟቾች ቁጥር በሪፖርት ከሚጠቀስው በላይ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሰንመለስ፣ ህብረተሰቡ ራሱ ሰዎች በብዛት እየሞቱ አንደሆነ እየተገነዘበ ነው፡፡ ይህንን መንግሥት ከፈለገ፣ መከታተል የሚችለው ነገር ነው፡፡ ሰዎች ሲሞቱ አብዛኞቹ በቤተክርስቲያኖች ወይም በመስጊዶች በኩል አልፈው ስለሆነነ በነሱ በኩል የሚቀበረውን ሰው አሃዝ በመከታተል፣ ከአምናና ከዛ በፊት እንዲያው ከወራት በፊት ከነበረው የሟቾች ቁጥር ጋር ማወዳደር ይችላልና፡፡ ተጨማሪ ወይም ከተለመደው በላይ ሰዎች እየሞቱ መሆኑን በቀላሉ ማወቅ ይቻላል፡፡

ኮቪድ በኢትዮጵያ ከአሳሳቢነት ወደ አስፈሪነት መሸጋገር

ለተወሰነ ጌዜ ሁኔታዎችን እየተከታተልን ትምህርት ከመስጠት ባንቆጠብም፣ አሀዝ ጠቅሶ ኮቪድ በኢትዮጵያ ወደ የት እንደሄደ እንደሆነ ለመግለፅ ዘግት ብለን ነበር፡፡ አሁን ግን፣ ህብረተሰቡ በራሱ የበሽታውን ሥርጭት ብቻ ሳይሆን የታማሚዎች ቁጠር መጨመሩን ከዛም ደግሞ የሟቾች ቁጥር መጨመሩን እየተረዳ መጥቷል፡፡ በወቅቱ በኮቪ የታመመ፣ ወይም የሞተ ሰው ያልሰማ ወይም የማያውቅ ሰው የለም፡፡ እንግዲህ ወደ አውሮፓ በኩል ሶስተኛ ዙር የወረርሽኝ ማዕበሉን እያናፈሰ ያለው ይህ ሞገደኛ ቫይረስ በኢትዮጵያም፣ ከዚህ በፊት ከነበረው በጨመረ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ ይህን ደግሞ በአሀዝ ለማስረዳት ቀላልም ነው፡፡

በመጀመሪያ ኢትዮጵያ የኮቪድ ምርመራ የምታደርገው በሳምንት 49ሺ የሚሆን ነው፡፡ በዚህ መጠን ምርመራ ከቀጠሉ ቆየት ብሏል፡፡ እንግዲህ በዚህ አነስተኛ መጠን ምርመራ ሲደረግ ኮቪድ የተገኛበቸው ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር አነስተኛ እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡ እንደዛም ሆኖ፣ በአፍሪካ ቀንድ በኩል ሲታይ፣ በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ብቻ ሳይሆን በሚሞቱ ሰዎች ቁጥር የመሪነቱን ደረጃ ይዛለች፡፡ ከጠቀላላው አፍሪካ ሲታይ ደግሞ በአምስተኛና በስድስተኛ ደረጃ ነው የምትገኘው፡፡

የሚያሰፈራው ነገር የታየው፡፡ ምርመራ ከሚደረግላቸው ሰዎች መሀከል ምን ያህሉ እየተገኘባቸው ነው የሚለውን ጥያቄ መልስ በአሀዝ ስንመለከት ነው፡፡ ለማሸበር አይደለም ግን በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ በቀላሉ እንደ አካባበዊ፣ ምርመራ ከሚደረግላቸው ሰዎች ከአራቱ አንዱ አንዳንድ ቦታም ደግሞ ከሶሰቱ አንዱ ቫይረሱ እየተገኘባቸው ነው፡፡ ይህ እንግዲህ የቫይረሱን ሥርጭት በትክክል የሚገልፅ ብቻ ሳይሆን፣ የመሠራጨት ችሎታው ከፍ ያለ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ለማንኛውም የኢትዮጵያ የህብረተሰብ የጤና ኢንስቲቲዩት በየሳምነቱ የሚያወጣውን ሪፓርት መመልከት ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ሪፖርት መሠረት በሚቀጥለው ግራፍ ላይ እንደሚታየው፣ በሲዳማ፣ በኦሮሚያ የሚታየው ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች በፐርስነት ሲታይ በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ የሲዳማው፣ ከሀዋሳ ከተማ የሚመጣ የምርመራ ውጤት ሪፖርት ነው፡፡ ከሶስት ሰው አንዱ ቫይረሱ አለባቸው ማለት ነው፡፡ አንግዲህ ኢትዮጵያ በየቀኑ በመቶ ሺ የሚቀጠር ምርመራ ብታደርግ፣ በጠቅላላ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር እንደሚጨምር ግልፅ ነው፡፡ እዚህ ላይ ለማወዳደር፣ በአሜሪካ፣ ከሚመረመሩ ሰዎች ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች በፐርሰንት ሲታይ ከ6-10 ፐርሰንት ነው፡፡ አንድ ስቴት ብቻ ነው አስከ ሀያ ፐርሰንት የታየበት፡፡ በዚህ ፐርሰንት፣ በየቀኑ ቫየረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር 65ሺ ነው፡፡ ለምን ሲባል፣ አሜሪካ በብዛት ምርመራ ሰለምታደርግ ነው፡፡ አስሉት እንግዲህ፡፡ መልክቱ ምንድን ነው፣ በኢትዮጵያ ተገኘባቸው ተብሎ የሚታወቀው ቁጥር እውነተኛ የቫይሱን ሥርጭት አይገልፅም ማለት ነው፡፡

ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic