ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ
ማስክ በማድረግ አፍና አፍንጫን መሸፈን ምን ያህል የኮቪደ-19 ሥርጭት ይቀንሳል?
የሚባልላቸውን ያህል ያስጥላሉ ወይ? 6/15/20
በግልፅም ሆነ በሥውር፣ ዋናው የኮቨድ-19 ሥርጭት መከላከያው፣ ከሰው ራቁ የሚለው መልክት ነው፡፡ ከዛ በተጨማሪ፣ አፍና አፍንጫችሁን ሸፍኑ ነው፡፡ አፍና አፍንጫን ለመሸፈን የተለያዩ አይነት ማስኮች (መከለያ ወይም ጭምብሎች) አሉ፡፡ ለህብረተሰብ አገልግሎት የሚውሉት፣ በአንግሊዝኛው አጠራር (Surgical masks) የሚባሉት ሲሆን፣ ከጨርቅ የተሠሩ ማስኮችም ለአገልግሎት ይውላሉ፡፡ ለአገራችን ገበሬ ወይም የገጠሬው ሰው ደግሞ በጋቢው አፍና አፍንጫውን ከሸፈነም ይረዳል፡፡
ታዲያ እነዚህ ምክሮች እየተሠጡ፣ አዳማጭ ህዝብ ባለበት አገር፣ ግለሰቦች ሲጠቀሙባቸው አይተናል፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን፣ እንዲህ አይነት ምክር ሲሰጥና በተግባር ሲውል፣ በውል መሥራቱን፣ ከሠራም ምን ያህል ርዳታ መሥጠቱን በጥናት ማየት እንዴት ጥሩ ነገር ነው፡፡
እንደምኞታችንም፣ ይህንን በሚመለከት የወጣ ዘገባ አለ፡፡ በተደረገ ጥናት፣ መረጃው እንደሚጠቁመው፣ ፌስ ማስኮችን መጠቀም፣ በኒው ዮርክና ከተማና በኢጣልያ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በኮቢድ ከመያዝ አድኗቸዋል፡፡
ጥናቱ የተመለከተው፣ ሰዎች የፌስ ማሰክ ከመጠቀማቸው በፊት የነበረው የሥርጭት መጠን በማየትና፣ ሊከሰት የሚችለውን ቁጥር ስሌት ውስጥ በማስገባት፣ በኒው ዮርክ ከተማ በተደረገው ጥናት፣ ሰዎች ፌስ ማስክ ማድረግ ከጀመሩ በኋላ የታየውን ቁጥር በማየት፣ ከአፕሪል 17 ጀምሮ እሰከ ሜይ 9 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ስሌቱ የሚያሳያው በኒው ዮርክ ከተማ ብቻ 66 000 (66ሺ ሰዎች) ከመያዝ አምልጠዋል፡፡ ይህንን 66ሺ ሰዎች ቁጥር፣ የፊስ ማስክ በመጠቀማቸው በኮቪድ-19 ከመያዝ የተረፉትን ሰዎች፣ ተይዘው ቢሆንስ ኖሮ ብለን ብናስብ፣ በግርድፉ ምን ያህል ሰው ይሞት ነበር ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ያም እንግዲህ 66ሺ ሰዎች መልሰው የሚያራቡትን ወይም የሚያሠራጩትን ቁጥር ለጊዜው ትተን ነው፡፡ አሁን ባለው በኒው ዮርክ ስቴት ከተያዙ ሰዎች ምን ያህሉ ሞተዋል የሚለው አሃዝ በፐርሰንት ብናይ፣ 8% ነው፡፡ እናም፣ 66ሺ ሰዎች ተይዘው ቢሆን ኖሮ በአነስተኛው ግምት፣ ተጨማሪ 5280 ሰዎች ይሞቱ ነበር ማለት ነው፡፡
ሌላው ጥናቱ የተመለከተው ቦታ ደግሞ ኢጣልያ ነው፡፡ በተመሳሳይ ስሌት ያስተዋሉት ነገር፣ በህግ ሁሉም ሰው ማሰክ እንዲያደርግ በመደረጉ፣ ከአፕሪል 6 እሰከ ሜይ 9 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ78000 (78ሺ) ሰዎች በላይ በቫይረሱ ከመያዝ አምልጠዋል፡፡ እንደ ኒው ዮርኩ ሁሉ፣ ያን ያህል ሰዎች ተይዘው ቢሆን ኖሮ፣ ምን ያህል ተጨማሪ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ ለሚለው ጥያቄ፣ ሳይንሳዊ ባይሆንም፣ በቀላሉ በኢጣልያ በቫይረሱ ከተያዙት መሀከል የሞቱትን ሰዎች ፐርስንት ስናይ፣ 14.5% ነው፡፡ በርግጥ በኢጣልያ ብዙ ሰዎች እንደሞቱ ይታወቃል፡፡ በነገራችን ላይ፣ በኒው ዮርክ የተሠራጨው ቫይረስ ዝርያ፣ ከኢጣልያ እንደመጣ ነው የሚነገረው፡፡ ያውም አንድ ግለሰብ፡፡ ወደ ስሌቱ ስንመለስ፣ 78ሺ ሰዎች ተይዘው ቢሆን ኖሮ፣ ተጨማሪ 11310 ሰዎች ይሞቱ ነበር ማለት ነው፡፡
ይህንን ውጤት ከተመለከትኩ በኋላ፣ በሜሪላንድ ሰቴት፣ በዋና ጎዳናዎች ላይ የተፃፈውን ፅሁፍ አስታወስኩና እውነት ነው አልኩኝ፡፡ ፅሁፉ የሚለው “Face masks save lives” ነው፡፡
እንግዲህ መረጃ አገኘን፡፡ ማስታወስ ያለብን የኮቪድ-19 ቫይረስ መተላለፊያው ዋናው መንገድ፣ በትንፋሽ ነው፡፡ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች፣ ስሜት ይኑራቸውም ወይም አይኑራቸው በትንፋሻቸው የሚወጣው ቫይረስ የሌላ ሰው አፍ፣ አፍንጫ፣ አይን ላይ ካረፈ ነው፡፡ ለዚህ ነው ማስኮቹ ይሀን ያህል ጥሩ ውጤት ሊያሳዩ የቻሉት፡፡ መቼም በድሮፕሌትና በኤርቦርን መተላለፍ መሀከል ያለው ውዝግብ እንደቀጠለ መሆኑን ጠቆም ላደርግላችሁ እወዳለሁ፡፡ ውዝግቡ ቢቀጥልም፣ በቫይረሱ ለተያዙ ሰዎች ወይም መያዛቸውን ለማያውቁ ሰዎች፣ ትንፋሻችሁን አታጋሩ ነው መልክቱ፡፡ በማስክ ገድቡትና ሌሎችን ከመያዝ አድኑ፡፡ ሰብአዊነት ነው፡፡
ለዚህም የጤና ባለሙያተኞችና፣ የሆስፒታል ሌሎች ሠራተኘቾ፣ በሽተኞችም፣ በተለይ በሆስፒታሎችና የጤና ርዳታ መስጫ ቦታዎች፣ አፍና አፍንጫን በማሰክ እንዲሽፍኑ የሚደረገው፡፡ ችግሩ በቂ መጠን አላቸው ወይ ነው፡፡
አሁን አያየን ያለነው፣ የምን ግዴ የማስክ አጠቃቀም ጉዳት አለው፡፡ አፍን ሸፍኖ፣ አፍንጫን ክፍት ማድረግ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ ከተሸፈኑ ሁለቱንም መሆን አለበት፣ እንዲያውም እኮ አይንም ሸፍን እንዲል እንፈልጋለን፡፡ አጠገብዎ አንድ ሰው ቢያስነጥስና በአፍ የወጣው ረጨት አይን ላይ ቢያርፍ፣ ቫይረሱ መግቢያ አገኘ ማለት ነው፡፡ ሰለዚህ ሁላችንም ስንወጣ ማሰክ ብናደርግ ከዚህ አደጋ ይከላከልልናል፡፡ የአይን መነፀር ወይም መከለያ ቢያደርጉ፣ እኔ በበኩሌ የምደግፈው ነገር ነው፣ በተለይ አፍና አፍንጫውን ሳይሸፍን የሚንጎራደድ ሰው ካሉ፡፡ ከዚህ ላይ፣ ያችን የስድስት ጫማ ርቀት መጠበቁ ይረዳል፡፡
ዋናው መልክት ትንፋሻችን እንገድብ፣ ማስኩ ለታየታ አይደለም፣ መንግሥት አድርጉ ሰላለም ብቻ አይደለም ማድረግ ያለብን፡፡ እንዲዚህ አይነት መረጃ ካየን፣ ከልባችን አምነን መሆን አለበት፡፡
ዋቢ Proceedings of the National Academy of Sciences
በኮቪድ-19 የሞቱት ሰዎች እነማን ናቸው? 7/11/2020
በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው፣ በአሜሪካ በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱ ሰዎች እነማን አንደሆኑ የሚገልፅ ዝርዝር መረጃ ወጣ፡፡ ይህ ዝርዝር አስፈላጊ የሆነውም፣ እንደሚነገረው፣ በኮቪድ-19 ምክንያት ማይኖሪቲ የሚባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ከድርሻቸው በላይ በኮቪድ መያዝ ብቻ ሳይሆን በኮቢድ ምክንያትም እንደሚሞቱ ሲነገር ሰለከረመ ነው፡፡
የአሜሪካው የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ባውጣው ሪፖረት፣ ከጃንዋሪ 1፣ 2020 እስከ ሜይ 18፣ 2020 በነበረው ጊዜ ውስጥ 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በኮቪድ 19 መያዛቸው ይታወቃል፡፡ ያ ቁጥር አሁን ከ 3.1 በላይ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የሟቾች ቁጥር 83ሺ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ከ134 ሺ በላይ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ወደ ሲዲሲ ከሚላከው ሪፖርት፣ ከ50ዎች ስቴቶችና ዲስትሪክት ኦፍ ኮሎምቢያን (ዲሲ) ጨምሮ 52166 በኮቪድ-19 መያዛቸው በላቦራቶሪ የተረጋገጠና ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች መረጃ የተጠናከረውን ዝርዝር ነው ያቀረቡልን፡፡ የነዚህ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች የተሰበሰበው ከየካቲት 12 አስከ ግንቦት 18 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡
ከነዚህ 52 166 ሰዎች መሀከል
55.4% ወንዶች
79.6% ዕድሜያቸው ከ65 አመት ወይም ከዛ በላይ የሆኑ ነበሩ
በዘር ሲታይ ደግሞ
13.8% ሂስፓኒክ
21.0% ጥቁሮች
40.3% ነጮች
3.9% ኤስያኖች ነበሩ
በተጨማሪም፣ ከዘር ውጭ ተደራቢ በሽታ ያለበቸው ሰዎችን ለማወቅ ተጨማሪ መረጃ ከተገኘባቸው ሰዎች፣ ቁጥራቸው እድሜያቸው ከ65 አመት በታች የሆነ 8134 ሰዎች ተጨማሪው መረጃ በሚያሳየው መሠረት ቢያንስ ቢያንስ አንድ ተደራቢ በሽታ ነበረባቸው፡፡ ተደራቢ በሽታ ወይም የቆየ በሽታ ሲታይ፣
በብዛት የታየው የልብና የደም ዝውውር በሽታ በ60.9%
የስኳር በሽታ 39.5%
የቆየ የኩላሊት በሽታ 20.8%
የቆየ የሳምባ በሽታ 19.2%
ዕድሜያቸው ከ65 አመታት በላይ ከሆነ የሞቱት ሰዎች መሀከል፣ 69.5% የሚሆኑት አንድ ወይም ከዛ በላይ የቆየ ወይም ተደራቢ በሽታ ነበረባቸው፡፡ በዕድሜ ተከፋፍሎ ሲታይ ዕድሜያቸው ከ65 አመት በታች በሆኑ ሰዎች በብዛት የታየው ተደራቢ በሽታ የስኳር በሽታ በ49.6% ነበር፣ ዕድሜያቸው 85 አመትና ከዛ በላይ በሆኑት ሰዎች፣ የስኳር በሽታ የነበረባቸው 25.9% ነበር፡፡
ሪፖረቱን በዝርዝር ስንመለከት፣ ተጨማሪ መረጃ ከተሰበሰበላቸው 8976 ሟቾች መሀከል፣ 84.3% ሆስፒታል ገብተው ነበር፡፡ እንግዲህ ሆስፒታል ሳይደርሱ የሞቱም አሉ፡፡ በተጨማሪም ሆስፒታል ሳይደረስ በነረሲንግ ሆም ወስጥ እያሉ የሞቱም ይገኙበታል፡፡ ድንገተኛ ክፍል አያሉ ወደ ውስጥ ወደ ሆሰፒታል ሳይቡም የሞቱም አሉ፡፡ ህመም ከተሰማቸው ጀምሮ ሕይወታቸው እሰካለፈበት ድረስ በአማካይ አስር ቀናት ነው የወሰደው፡፡ ይህ እንግዲህ ሕመም የጀመረበት ቀን መረጃ በተሰበሰበ ሟቾች ቁጥር ውስጥ ነው፡፡
ሆሰፒታል ገብተው ከሞቱት መሀል፣ በአብዛኛው በአምስት ቀናት ውስጥ ነው የሞቱት፡፡ ባጠቃላይ ሲታይ፣ ዕድሜያቸው ከሟቾቹ መሀከል 75% የሚሆኑት ወይም አንድ ወይም ከዛ በላይ ተደራቢ በሽታ አለባቸው አለዚያም ዕድሜያቸው ከ65 አመታት በላይ ነበር፡፡ አነዚህ የህብረተሰቡ ክፍሎች ናቸው እንግዲህ በቫይሱ እንዳይያዙ ከፍተኛ ጥረት የሚደረገው፡፡ ለዚህም ነው እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ከራስ በላይ በማሰብ በቫይረሱ ላለመያዝ ጥረት ማድረግ ያለበት፡፡ ከምንም ጊዜ በላይ ለሌላ የቤተሰብ አባል፣ ጓደኛ፣ ቤተዘመድ ወይም የሥራ ጓደኛ ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ ለቫይረሱ መጋለጥ የሚየበቁ ቦታዎችን ለይቶ ማወቅ፤ በቤት ውስጥ ማን እንደሚኖር ቫይረሱ ቢይዛቸው ከፍተኛ አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችሉ ይሆን ብሎ መጠየቀት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን፣ ይህ ቫይረስ ባህሪውን እየቀየረ የወጣቶችንም ዕድሜ እየቀጠፈ መሆኑን ማወቅም ተገቢ ነው፡፡ ዋናው፣ በምንኖርበት አካባቢ፣ ወይም የህብረተሰብ ክፍል የቫይረሱ ሥርጭት ምን ያህል መሆኑን ለይቶ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን፣ በቫይረሱ ተይዘው፣ ግን የበሽታ ስሜት ወይም ምለክት የሌለባቸው ሰዎች ቫይረሱን እያስተላለፉ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ ደግሞ እንደ ሲዲሲ ሪፖርት አርባ ፐርስንት ይሆናሉ፡፡ ቫይረሱን አደገኛ ካደረጉት ነገሮች አንዱ ይህ ነው፡፡
የመረጃ ምንጭ MMWR / July 10, 2020 / Vol.69
ከሚጠበቀው በላይ ሞት ሲከሰት ትርፍ ሞት የሚባል ነገር አለ ወይ? 10/20/2020