ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

አስራ አምስት ሺ የፖላንድ የጦር መኮንኖችና ምሁራንን ማን ገደላቸው?

 
በአጋጣሚ ነበር፣ “ዘ ላስት ዊትነስ” የሚባል ሲኒማ እያየሁ ነበር፡፡ እውነተኛ ሁኔታን የተመረኮዘ ነበር፡፡ ሲኒማውን ከጨረስኩ በኋላ፣ ነገሩን በስፋት ለማጥናት መረጃዎችን መቃረም ጀመርኩና፣ ድምዳሜ ላይ ደረስኩ፡፡ እንግዳ ባይሆንም፣ ምዕራባውያን የነሱን ጥቅምን ለማስጠበቅ ሲሉ ይህን ያህል ሰዎች የተገደሉበትን ሁኔታ ያልሰሙና ያላዩ መመስል ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ እንዳይታወቅ ያላደረጉት ነገር አልነበረም፡፡ ጉዳዩ ይፋ እንዳይወጣ ተጨማሪ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ ያደርጋሉ፡፡ አሱንም ነው ያደረጉት፡፡

ወደ ታሪኩ ስንመለስ፣ በሁለተኛው አለም ጦርነት ወቅት አገራቱ በየጎራቸው ተሰለፍው ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ጠላት ሊሆኑ ሩስያና ጀርመን የዋርሶው ፓክት የሚባል ስምምነት ነበራቸው፡፡ በዚህ የተነሳ የፈረደባትን ፖላንድ በሰምምነት ለሁለት ተካፈሏት (የሞሎቶቭና ሪበንትሮፕ ፓክት ይባላል፣ በመስከረም 1939 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር)፡፡ በዛን ጊዜ የሶቨየቱ መሪ ሰታሊን ነበር፡፡ ፓላንድን ለመዋጥ በነበረው ሀሳብ፣ የሶቭየቶችን ሀሳብ ሊቃወሙ ወይም የማይቀበሉ የፖላንድ ተወላጆችን መመንጠር ነበረበት፡፡ የሱ ዕቅድ ነው፡፡

በኛም ሀገር፣ ግራዚያኒ ያደረገው ይህንኑ ነበር፡፡ ኢጣልያን የሚቃወሙ፣ የኢጣልያን ገዥነት የማይቀበሉ ኢትዮጵያውያንን ለመመንጠር ሰበብ ሲፈልግ ነበር፡፡ ለነገሩማ የሚባለው፣ “ኢትዮጵያን ወይም ከህዝቡ ጋር አለዚያም ከህዝቡ ውጭ አሰረክብሀለሁ” ብሎ ነበር ለሞሶሎኒ ቃል የገባው፡፡ እናም በየካቲት 12፣ የሰማዕታት ቀን፣ በተገኘው አጋጣሚ የተማሩ ኢትዮጵያውያንን መጨረስ ነበረበት፡፡ ከነሱ ቀጥሎ ክርሰቲያኖችን መነኮሳትን ጨምሮ መፍጀት ነበረበት፡፡ ደብረ ሊባኖስ ገዳም የተደረገው በምስክርነት በሲነማ ተቀርጾ ለህዝብ ቀርቧል፡፡ ያን ጊዜ፣ ማተብና መስቀል አንገቱ ላይ ያሠረ በታየበት ይገደል ነበር ትዛዙ፡፡ የሆነውን እናውቃለን ብዬ እገምታለሁ፡፡

ወደ ታሪኩ ልመልሳችሁ፡፡ ሰታሊን ፖላንድን ከራሳቸው ከፖላንዶች ለማጥራት የጦር መኮንኖች እንዲሁም የተማሩ ሰዎችን እየጫነ ወደ ሩሰያ እንዲወሰዱ አስደረገ፡፡ ሶቭየቶች ይህን ሲያደርጉ፣ ጀርመኖች በያዙት የፓላንድ ግዛት ወስጥ አይሁዳውያንን እየፈጁ ነበር፡፡ ሶቭየቶቹ ያሠሯቸውን ፖላንዳውያን በምዕራባዊው የሶቭየት ግዛት ውስጥ በካምፕ አጎሯቸው፡፡ ነገር ግን፣ በነበራቸው ዕቅድ፣ ካቲን በሚባል ጫካ ውስጥ ስሞለነስክ በተባለ የሶቭየቶቸ ቦታ አካባቢ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው፣ በካምፕ ታጉረው የነበሩ የፖላንድ ሰዎች ተራ በተራ እየተወሰዱ ተገደሉ፡፡ ይህ የሆነው፣ ሶቭየቶች ያንን አካባቢ በሚቆጣጠሩበት ጊዜ ነበር፡፡የተናገረም የተቃወመም አልነበርም፡፡

ጉዳዩ ለአደባባይ የበቃው፣ ጀርመኖች ሩስያን ሲወሩና ያንን ቦታ ሲቆጣጠሩ የአካባቢ ተወላጅ የሩሰያ ዜጎች የሆነውን ሁሉ ለጀርመኖች ሪፖርት በማድረጋቸው ነው፡፡ ጀርመኖችም ምንም እንኳን እነሱም ዘር ጨፍጫፊ ቢሆኑም በዚህኛው ነገር ላይ አጃቸው የሌለበት መሆኑን ለማስመሰከር፣ አለም አቀፋዊ የሆነ የሜዲካል ኮሚሺን አቋቁመው ቁፋሮውን ቀጠሉ፡፡ በዚህም የወታደር መኮንኖችና የፓላንድ መሪ ምሁራን አስከሬኖችን ያወጣሉ፡፡ እነዚህ የተገደሉ ሰዎች በምዕራባዊው የሩስያ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዛ ካምፖች ደግሞ በሶቭየቶች ቁጥጥር ሥር ነው የነበሩት፡፡ ጀርመኖቹ ሌሎች ታዛበዎችን እንዲሁም በነሱ ቁጥጥር ሥር የነበሩ የአሜሪካ የጦር ምርኮኞችን ሳይቀር ወደ ቦታው ወሰድው አሳዩ፡፡ ሲጣራ ይህ የጀምላ ግድያ የተካሄደው በ1940 እንደነበር ያረጋግጣሉ፡፡ በዛን ጊዜ ቦታው በሶቭየቶች ቁጥጥር ሥር ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ የምዕራባውያን የሸፍጥ ሥራ የሚጀምረው፡፡

ጀርመኖቹ ወዲያውኑ፣ ይህንን የጀምላ ጭፍጨፋ ያካሄዱት ሶቭየቶች ናቸው ብለው አስነገሩ፡፡ ሀሳቡ የነበረው፣ ሰታሊን ከምዕራባውያን ጎን ሆኖ ጀርመኖቸን እየተከላከለ ሰለነበር በተጨማሪም የተሰደደው የፖላንድ መንግሥት ከሶቭየቶች ጋር እየተባበረ ሰለነበር፣ በሶቭየቶችና በፖላንዳውያን መካከል ክፍፍልም ለመፍጠር ነበር፡፡ ሶቭየቶች ደግሞ፣ እኛ አይደለንም ገዳዮቹ የጀርመን ናዚዎች ናቸው ብለው ድርቅ አሉ፡፡

ታዲያ፣ ምዕራባውያኑ ራሳቸው ባደረጉት ጥናት እነዛን የፖላንድ ዜጎች ማን እንደፈጃቸው እያወቁ፣ ከሶቭየቶች ጋር ተባብረው ገዳዮቹ የጀርመን ናዚዎች ናቸው አሉ፡፡

ግን ለምን? ምዕራባውያኑ፣ አሜሪካን ጨምሮ፣ ጀርመንን ለማጥቃት የሶቭየትን ወይም የሰታሊንን ርዳታ ይፈልጋሉ፡፡ ሰለዚህ በምንም መንገድ ሰታሊንን የሚያስከፋ ነገር ላለማድረግ ወሰኑ፡፡ ከሶቭየቶች ጋር ተባብረው ፖላንዳውያንን የፈጁት ጀርመኖች ናቸው ከማለት በተጨማሪ፣ ቁርጠኛ በመሆን፣ ይህ ሚስጥር እንዳይወጣ ከፍተኛ ጥረት አደረጉ፡፡ ይህንን ሚስጥር የሚያውቁ ሰዎችም ማን እንደገደላቸው ሳይታወቅ ይገደሉም ነበር፡፡ ያ የግድያ ቦታ የካቲን ጫካ ጀምላ ግድያ ተብሎ ይጠራል፡፡ በቦታው የአራት ሺ ሰዎች አስከሬን ሲገኝ፣ የሌሎቹ ግን የት እንደሆነ ሳይታወቅ ባጠቃላይ አስራ አምስት ሺ ፓላንዳውያን ምሁራንና የጦር መኮንኖች ደብዛቸው ጠፍቷል፡፡

በ1943፣ ሶቭየቶች መልሰው ያንን ቦታ ሲቆጣጠሩ፣ እነሱም የራሳቸው ቁፋሮ አስደርገው፣ ፖላንዳውያኑ የተገደሉት በወራሪ ጀርመኖች ነው የሚል ማጠቃለያ ተናገሩ፡፡ ማን ትንፍሽ ይበል? ጀርመን እየተሸነፈ በነበረበት ወቅት አዳማጭም የለውም፡፡ ምዕራባውያኑም ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ፣ የሶቭየቶችን ሀሳብ ተቀብለው እያስተጋቡ ነበር፡፡ በሱ በቆሙ ጥሩ ነበር፡፡ ሚሰጥሩን ለማፈን ተጨማሪ የብዙ ሰዎች ህይወት ጠፋ፡፡

ዕወነትና ንጋት እያደር ይላሉ ያገራችን ሰዎች፡፡ ነገሩን የሚያውቁ ጥቂት ሰዎች ጉዳዩን ቀጥለውበት፣ በመስከረም ወር፣ በ1951 የአሜሪካው ምክር ቤት ይህንን ጉዳይ የሚያጣራ ኮሜቴ አቋቋመ፡፡ እንደሚመስለኝ፣ በዛን ጊዜ ቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ ሰለነበሩ፣ ሶቨየቶችን ለማጋለጥ ሲሉ ነው፡፡ አለዛማ በመዝገብ ቤቶቻቸው ትክክለኛው መረጃ ነበራቸው፡፡ እንግዲህ ከስታሊን ጋራ አስኪጣሉ ጠብቀው መሆን አለበት፡፡ የኢንዲያና ስቴት ተወካይ በነበረው በሪፓብሊካኑ በሬይ ማደን ስም፣ የማደን ኮሜቴ ተብሎ ተሰየመ፡፡ በርግጥ፣ ኮሚቴው ጉዳዩን ማጣራት ብቻ ሳይሆን፣ የአሜሪካ ባለሥልጣኖች ግድያውን በመሸፋፈን ተሳታፊ እንደነበሩም ለመመርመርም ነበር፡፡ ኮሚቴው በሙሉ ድምፅ ግድያውን ያካሄዱት ሶቭየቶች ናቸው አለ፡፡ የአሜሪካውያን ጉዳዩን የመሸፋፈን ሁኔታ ላይ ግን ኮሜቴው ግልፅም አልነበረም፡፡

በመስከረም ወር በ2011 የወቅቱ የአሜረካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በላኩት ደብዳቤ መሠረት፣ ፋይሉን ይዞ የነበረው የአሜሪካው ናሽናል አርካይቭ፣ ጉዳዩን ለህዘብ በይፋ እንዲያወጣ በመጠየቁ በሺዎች የሚቀጠሩ ገፆች ለህዝብ እንዲለቀቁ ተደረገ፡፡ ከሰባ አመት በኋላ የካቲን ጭፍጨፋ ውነተኛው ዘገባ ለሕዝብ ይፋ ወጣ፡፡

ከዛ ቀድም ብሎ በ1992 የሩስያ መንግሥት ጭፍጨፋውን ያካሄደው የሶቭየት የፖሊት ቢሮ ነው ብላ ይፋ አወጣ፡፡ ቁጥሩንም ወደ ሀያ ሺ ከፍ አደረገው፡፡ በዚህ ምክንያት የተቀጣ ሰው አልነበረም፡፡ የሚያሳዝነው፣ የፖላንድ መንግሥት እንኳን ራሱ፣ ከሶቨየቶች ጋር በነበረው ቅርበት፣ ጭፍጨፋውን ያካሄዱት ጀርመኖች ናቸው እያለ ቆየቶ ነበር፡፡ በህዳር 2010፣ የሩሰያ ፓርላማ ጭፍጨፋው የተካሄደው በሰታሊን ትዛዝ ነው ብሎ በይፋ አረጋገጠ፡፡

የካቲን ጫካ ጭፍጨፋ መታሰቢያም ተሠርቶ በሚያዝያ ወር በዚያኑ አመት የሩሰያው መሪ ፑቲን ከፖላንድ ጠቅላይ ሚኒሰትር ጋር በመሆኑ የመታሰቢያው ቦታ ተገኝተው አከበሩ፡፡ የሩስያ መሪ በግልፅ መታሰቢያው ቦታ ሲገኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር፡፡ የሚያሳዝነው ነገር የፖላንዱ ፕሬዚደንትና ባለቤቱ ከሌሎች የፖላንድ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን በሌላ የመታሰቢያ ፕሮግራም ለመገኘት በአውሮፕላን ሲበሩ፣ በዚሁ በካቲን አቅራቢያ አውሮፕላኑ ተከስክሶ ፕሬዚዳንቱ ከነባለቤቱና አብረው የነበሩ ባለሥልጣነት ህይወታቸው አልፏል፡፡

ጭፍጨፋ መካሄዱ፣ የሰዎች ህይወት በጀምላ መጥፋቱ ትልቅ ጥፋት ሆኖ፣ በተጨማሪ ግን መንግሥታቱ ለጥቅም ሲሉ እውነታውን መደበቅ ብቻ ሳይሆን በተቃራኒው ማስወራታቸው እንግዳ ነገር አለመሆኑን ሁላችንም የተገነዘብን መሰለኝ፡፡ አንዲህ ሲሆን፣ ማን ምን ሊጠቀም ነው? ማንስ ማንን ሊጠቅም ነው? የሚለውን ጥያቄ አስቀድሞ መመርመርና ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ የሚያሳዝነው የፖላንዳውያን ህይወት ዋጋም ሳይሠጠው መጠቀሚያ ሆኖ ቀረ፡፡ የራሱን ጥቅም የሚያስቀድም ሀይል ወገንተኛነቱ ጊዜያዊ ነው፡፡