ምግብ ከመካንነት ጋር ይያያዛል ወይ?

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በእንስሳት ላይ በተደረገ ጥናት አትክልቶችን ከተባዮች ለመከላክል የሚረጩ ፀረ ተባይ መድሐኒቶች በአካባቢ በመጠነኛ መጠን በሚገኙበት ጊዜ በእንስሳቱ ላይ የመውለድ ችሎታቸውን እንደሚቀንስ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ታዲያ ጥያቄው ይህ ሁኔታ በሰዎች ላይም ተመሳሳይ ሁኔታ ይፈጥር ይሆን ነው ወይ፡፡ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ፍራፍሬና አትክልቶችን ከተባይ ለመከላከል የሚረጩ እነዚህ መድሐኒቶች በመጠኑም ቢሆን ምግቦቹ ላይ ስለሚቀሩ፣ እነዚህን ፍራፍሬና አትክልት የሚመገቡ ሴቶች ላይ መካንነት ያስከትል ይሆን?

በቅርቡ በጆርናል ኦፍ አሜሪካን ሜዲካል አሶሴሽን (JAMA) በሚባል መፅሔት የወጣ ጥናት ያሰፈረውን እንመልከት፡፡

አላማው ከላይ የተነሳውን ጥያቄ ለመመለስ በሆነው በዚህ ጥናት፣ በማሕፀናቸው እርግዝና መያዝ የማየችሉ በዚሁ ጉዳይም ርዳታ ለመፈለግና ከሰውነት ውጭ ፅንስ በህክምና የሚሠራባቸው የህክምና ቦታዎች የሄዱ 325 ሴቶች አመጋገብ ሁኔታ በዝርዝር ከተመዘገበ በኋላ መደበኛ ክትትል በጥናት መንገድ ተጀመረ፡፡ ጥናቱም ከ2007 – 2016 ባለው ጊዜ ነበር፡፡ ከአመጋገቡ ጥናት በመነሳት ለከፍተኛና ዝቅተኛ ፀረ ተባይ መጠን ተለይቶ ሴቶቹን በሁለት ወገን መደቡ፡፡ የፀረ ተባይ መጠን የተወሰነው ከአሜሪካው የእርሻ መምሪያ ወይም ሚኒሰቴር መስሪያ ቤት በጥናት ካሰፈረው መረጃ በመመርኮዝ ነው፡፡

የጥናቱን ዝርዝር አሰራር ልዝለልና ወደ ውጤቱ ልውሰዳችሁ፡፡

ከ325 ሴቶች በክብደት፣ በዕድሜ ከተዘረዘሩ በኋላ፣ ፀረ ተባይ መጠን የተጋለጡበት ሁኔታ ሲታይ፤ በከፍተኛ መጠን ተጋልጠዋል የተባሉት በቁጥር ሲታይ፣ በቀን 1.7 ጊዜ እነዚህን ፀረ ተባይ ቅሬታ ያለባቸውን የሚመገቡ ከዝቅተኛው መጠን ሲመደቡ፤ እነዚህን ምግቦች ደግሞ በቀን 2.8 ጌዘ በላይ የተመገቡ ሴቶች በከፍተኛ መጠን ከተጋለጡት ወገን ተመደቡ፡፡

በተደረገው ስሌት ከፍጠኛ መጠን የተመደቡት ሴቶች ነብሰጡር ወይም እርግዝና የመያዝ ዕድላቸው ዝቅ ያለ ሆኑ እርግዝናም ቢፈጠር እንኳን ልጅ የመውለድ ዕድላቸው ዝቅ ያለ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ይህ እንግዲህ በዝቅተኛ መጠን ተጋለጡ ከሚባሉት ጋር ሲነፃፀር ነው፡፡

መደምደሚያው እነዚህ በከፍተኛ መጠን የተጋለጡት ሴቶች፣ ለእርግዝና የሚሆን የህክምና እርዳታ ቢደረግላቸውም፣ ከሌሎቹ ጋር ሲነፃፀር የመፀነስ ዕደላቸው ያነሰ ከመሆኑ በተጨማሪ ቢያረግዙም እንኳን ፅንሱን ከነሕይወቱ የመውለድ ዕደላቸው ዝቅ ያለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ሰለዚህ ለፀረ ተባይ መድሐኒቶች መጋለጥ ማለትም ሁልጊዜ ሰዎች ሊጋለጡ በሚችሉበት መጠን እርግዝና ላይ ቸግር ሊያስትል እንደሚችል ነው፡፡ 

መመገብ ብቻ ሳይሆን የምንመገበው ምግብ አመጣጡን ማወቅ መጠኑንም መለየት አስፈላጊ ነው፡፡ በርግጥ ጦም አድረው ለሚውሉ ወገኖቻችን ይህንን ማንሳት ለህሊና የሚከብድ ነገር ነው፡፡ ይህ ነገር ደግሞ በተለይ በታዳጊ አገሮች የማዳበሪያው ጥራትና መጠን፣ የፀረ ተባይ መጠን የሚታወቅም አይደለም፡፡ በጓሮ የሚያደግ አትክልትና ፍራፍሬ ቅድሚያ የሚሠጠውም ለዚህ ነው፡፡ በአደጉ አገሮች፣ እንደምታውቁት በተፍጥሮ ያለምንም መድሓኒትና ማዳበሪያ ተተክለው ያደጉ አትክልትና ፍራፍሬዎች (Natural) ዋጋ ጨመር ያለ ነው፡፡ ከቻልን የምንመገበውን እናስተውል፡፡ በመጨረሻም የምለው፣ እንዚህ ለፀረ ተባይ የተጋለጡ በዝቅተኛ መጠን የተመገቡ ሴቶች ችግር ያልታየባቸው መሆኑን እያስታወስን፣ ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ እነዚሀን የምግብ ክፍሎቸን ከመመገብ መቆጠብ የለብንም፡፡

መልካም ንባብ

አካፍሉ