የደም ግፊት ህክምና አዲስ መመሪያ

 
ስለ ደም ግፊት(Hypertension) በተለምዶ በሀገር ቤት ደም ብዛት ሰለሚባል በሽታ አብዛኛው ሰው መጠነኛ ግንዛቤ እንደሚኖረው ነው፡፡ ነገር ግን በደም ግፊት ምክንያት የሚደርሰውን የሰውነት ጉዳትና ይህይወት ህልፈት በመመልከት ሰለዚህ ችግር ተደጋጋሚ ግንዛቤ መስጠት ተገቢ ነው፡፡  ይህ በሽታ የደም ግፊት መጠን ከጤናማ በላይ ሲሆን እንደ በሽታ የሚቆጠረው፡፡ የደም ግፊታቸው ከጤናማ መጠን በላይ የሆኑ ሰዎች ደግም መድሃኒት መጀመር እንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን መድሀኒት የሚጀመርበት የደም ግፊት መጠን ለተለያዩ ሰዎች የተለያዪ ነው የሚሆነው፡፡ በተለይም በእድሜ በኩልና ሌሎች ተደራቢ በሽታዎች ባሉባቸው ሰዎች ላይ፡፡

እንደሚታወቀው የደም ግፊት ሲለካ ሁለት ቁጥሮች አሉ በአንግሊዝኛ (systolic ) የላይኛው እና (diastolic ) የታችኛው ቁጥር፡፡ እነዚህ ቁጥሮች አንዱ ወይም ሁለቱ ከመጠን በላይ ሲሆኑ የደም ግፊት አለ ይባላል፡፡ ማሰተዋል ያለብን እነዚህ ቁጥሮች ከመጠን በላይ ሲሆኑ ምንም የህመም ስሜት ወይም ምልክት ላይኖር እንደሚችል ነው፡፡ ዋናው ችግር ይህ የደም ግፊት በጊዜ ካልታወቀ ሊያሰክትል የሚችላቸው የተላየዪ በሽታዎች መኖራቸው ነው፡፡ ዋናዎች ችግሮች

  • ስተሮክ (stroke) የነርቭ ምች(ከህይወት ማለፍ ጀምሮ የሰውነትን ክፍል ሽባ በማድረግ የሚታወቅ


  • ድንገተኛ የልብ ህመም (Heart attack) በሰሜን አሜሪካ ለሕይወት ህልፈት ዋነኛው ምክንያት


  • የኩላሊት መድከም (Kidney failure) ለኩላሊት መድከም ዋና ምክንያቶች አንዱ


ስለዚህ እነዚህን በሽታዎች ለመከላከል የህመም ስሜትም ባይኖር የደም ግፊትን በመድሀኒት አማካኝነት ጤናማ ደረጃ ወይም መጠን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

ይህንን በሚመለከት በአሜሪካ (Joint National Comitte - JNC) የሚባል ብዙ የተለያዪ የህክምናና ሌሎቸ ባለሚያተኞች ያሉበት ኮሚቴ በየጊዜው ለሀኪሞች ለደም ግፊት ህክምና መቼ አንደሚጀምሩ ምን አይነት መድሃኒቶች መጠቀም እንደሚችሉ መመሪያ ያወጣል፡፡ የመመሪያው በየጊዜው የሚወጣው በቁጥር የሚጠራ ሲሆን በቅርቡ የወጣው መመሪያ (JNC 8) ተብሎ ይጠራል፡፡

ይህ መመሪያ ለአሜሪካውያን የወጣ እንደመሆኑ መጠን ሀገር ቤት ለሚኖሩ ሰዎች በትክክል መደረግ አለበት ለማለት በሀገር ቤት በቂ ጥናት መደረግ አለበት፡፡ ነገር ግን ለማንኛውም ወይም ለአብዛኞች በሽታዎች የምዕራባውያኑን የህክምና ትምህርት ስለምንጠቀም ይሕ መመሪያ ደግሞ አገልገሎት ላይ መዋል ይችላል ብለን እናምናለን፡፡ ሌላው ተጨማሪ ነገር ከመድሃኒቶች ጋር ሌሎች የሚደረጉ ነገሮች ለምሳሌ የሚበሉትን ጨው መጠን መቀነስ፤ በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ የመሳሰሉት አስፈላጊ መሆናቸውን ነው፡፡

በተጨማሪ ይህን መመሪያ የምናካፍለው አብዛኞች ሰዎች በየቤታቸው ወይም በሌላ አጋጣሚ ደም ግፊታቸው ለክተው ቁጥሮችን የሚያውቁ ከሆነ ወደ ሀኪም ቀርበው ህክምና እርደታ እንዲጠይቁ ለመርዳት ነው፡፡ ከመመሪያው በተጨማሪ ሀኪምዎ የሚወሰንልዎትን ነገር ለመሻርም አይደለም፡፡ እንግዲህ ወደ ቁጥሮቹ እንሂድ

  1. ለአዋቂዎች እድሜያቸው ከ60 አመታት በላይ ለሆኑ ሰዎች መድሃኒት መጀመር የሚገባው (systolic ) የላይኛው ቁጥር ከ150 ወይም ከ 150 በላይ ከሆነ ወይም (diastolic ) የታችኛው ቁጥር 90 ና ከዛ በላይ ከሆነ


  1. እድሜያቸው ከ60 አመት በታች ለሆኑ አዋቂዎች ደግሞ መድሃት መጀመር የሚገባው የላይኛው ቁጥር 140 ወይም ከዛ በላይ ሲሆን የታችኛው ቁጥር ደግሞ 90 ወይም ከዛ በላይ ሲሆን ነው፡፡


  1. የኩላሊት በሽታና የስኳር በሽታ ላለባቸው ሰዎች ግን በማንኛውም እድሜ ክልል ቢሆኑም የደም ግፊት መድሓኒት የሚጀመረው የላይኛው 140 ወይም ከዛ በላይ ከሆነ የታችኛው ደግሞ 90 ወይም ከዛ በላይ ከሆነ ነው፡፡


  1. ሰዎች መድሃኒቶች ከጀመሩ በኋላ አስፈላጊ ክትትል ማድረግ የሚኖርባቸው ሲሆን የሚፈለገው የደም ግፊት መጠን በአንድ ወር ውስጥ አስፈላጊ መጠን ካልወረደ የመድሃኒቱ ጉልበት መጨመር ወይም ሌላ ተደራቢ መድሃኒት መታዘዝ ይኖርበታል፡፡ እዚህ ላይ ግን ደም ግፊታቸው አደገኛ ደረጃ የሆነባቸው ሰዎች አንድ ወር ድረሰ ይቆዩ ማለትም አይደለም፡፡ ሰለዚህ ነው ሀኪምዎ የሚወስኑልዎ ነገሮችን በትክክለ መከተል አስፈላጊ የሚሆነው፡፡


እንግዲህ ከላይ እንደተጠቀሰው የደም ግፊት መጠን ከፍ ሲል ስሜትና ምልክት ስለማይሰጥ በጊዜ ካልታወቀና ቁጥጥር ስር ካልሆነ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ጉዳት ስለሚያደርስ ማንኛው እድሜው 18 አመት የሞላው ሰው የደም ግፊቱን መጠን እንዲለካ እንመክራለን፡፡ ከተለኩ በሁዋላ ቁጥሮች ከፍ ያሉ ከሆነ የግድ ሀኪም ማማከር ተገቢ ነው፡፡ ማን ደም ግፊት ሊኖረው እንደሚችል የሚያመለክት ነገር የለም የደም ግፊትን መጠን ከመለካትና ከማውቅ ውጭ፡፡

መልካም ንባቡ ካነበቡ ለሌሎች ያካፍሉ፡፡