ትኩስ ሻይ መጠጣትና የጉሮሮ(esophagus) ካንሰር

በቅርቡ Annals of Internal Medicine በተባለ የሕክምና መፅሔት የወጣ የጥናት ዘገባ ነው፡፡
በጣም ትኩስ የሆነ ሻይ መጠጣት ለምግብ መውረጃ (ኢሶፋገስ esophagus) ካንሰር ጠንቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጥያቄው እንግዲህ  ከዚሁ በጣም ትኩስ ከሆነ ሻይ ከመጠጣት ጋራ ትምባሆ መጠቀምና አልኮል ማዘውተር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው የሚታወቅ ነገር ስላልነበረ፣ ጥናቱን ለማካሄድ ወስነዋል፡፡ ከቻይኖች ጋር ሲወዳደር ኢትዮጵያውያን ሻይ እንጠጣለን ብሎ መግለፅ ይከብዳል፡፡ በአማርኛ አነጋገር፣” የቡና ስባቱ ትኩሳቱ” ነው የሚል አባባል አለ፡፡ ብዙ ሰዎችም ሻይን በተመሳሳይ ሁኔታ በጣም በትኩሱ መጠጣት ይወዳሉ፡፡ ጥናቱ የተካሄደው በቻይና ሲሆን እኤአ ከ2004 -2008 ባለው ጊዜ ውስጥ በአስር ቦታዎች ነው፡፡ የጥናቱ ተካፋይ የሆኑት ቁጥራቸው 456 155 የሚሆኑ ዕድሜያቸው ከ 30 -79 አመት ክልል ውስጥ የሚገኝ ሰዎች ነበሩ፡፡ በዚህ ጥናት ካንሰሩ ያለባቸውና ሻይ፣ ትምባሆና አልኮል በመጠኑ የሚጠቀሙ ሰዎች እንዳይሳተፉ ተደርጓል፡፡ ሻይውን በተለምዶ ትኩስ እንደሆነ መጠጣት ተያይዞም ሲጋራና አልኮል ማዘውተር የመሰሉ ሁኔታዎችን የጥናቱ ተካፋይ የሆኑት ሰዎች ልክ ጥናቱ ሲጀመር ሪፖርት እንዲያደርጉ ተደርጎ እሰከ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ የጉሮሮ ወይም የምግብ መወረጃ ካንሰር መታየቱን መመዝገብ ነበር፡፡

የታየው ነገር

በአማካይ ለዘጠኝ አመት የሚሆን በተደረገው ክትትል፣ 1731በሚሆኑ ሰዎች የምግብ መውረጃ ካንሰር ከጥናቱ ተሳታፊዎች መሀከል እንደታየ ተዘግቧል፡፡ በተደረገው ዝርዘር ጥናት ትኩስ ሻይ መጠጣትና አያይዞም ሲጋራ ማጨስ ወይም አልኮል ማዘውተር  ለመግብ መወረጃ ካንሰሩ መከሰት የበለጠ ጠንቅ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ይህም ትኩስ ሻይ ብቻ ከመጠጣት ጋራ ሲወዳደር ነው፡፡
በዝርዝር ሲታይ፣ ከጥናቱ ተሳተፊዎች መሀከል ሻይ በየሳምንቱ የማይጠጡና በቀን ከ15 ግራም በላይ አልኮል የማይጠጡ ሰዎች ከሌሎቹ በጣም የሚፋጅ ሻይ ከሚጠጡና ከ15 ግራም ወይም ከዛ በላይ አልኮል የሚያዘወትሩ ሰዎች ጋር ሲወዳደር  የኋለኞቹ ለምግብ መውረጃ ካንሰር መከሰት ከፍተኛ ምክንያት እንደሚኖራቸው የሰታቲሰቲክስ ስሌቱ ያስረዳል፡፡ የጥናቱ ደካማ ጎን ሊሆን የሚችለው ሰለ ሻይ አጠጣጥ ተሳታፊዎች ራሳቸው ሪፓርት የሚያደርጉትን ቃል መሰብሰብ ነው፡፡ ማለትም በሌላ መለኪያ ወይም መመዘኛ መዘገብ ስላልተቻለ ነው፡፡
ማጣቃለያ ሃሳቡ፡
የሚፋጅ ሻይን መጠጣትና አብሮም ከመጠን በለይ አልኮል ማዘውተር ወይም ሲጋራ ማጨስ ለጉሮሮ ወይም የምግብ መውረጃ ካንሰር መከሰት በከፍተኛ ደረጃ የሚያጋልጥ ሁኔታ መሆኑን ነው፡፡

ጆሮ ያለው ይስማ!

የጥናት ወጤቶች ርዕሶች

  • ትኩስ ሻይና የጉሮሮ ካንሰር
  • ሁካ ወይም ሺሻ ማጨስና ጤንነት
  • የምግብ አይነትና መካንነት
  • ቡና መጠጣትና የጉበት በሽታዎች መሻል
  • ባልታወቀ ድምፅ አማካኝነት  የነርቭ ጉዳት

ባልታወቀ ድምፅ አማካኝነት  የነርቭ ጉዳት የደረሰባቸው የኤምባሲ ሠራተኞች ጥናት ይፋ ወጣ 02/24/2018

አንድ ሰሞን በሃቫና ኩባ በአሜሪካ መንግሥት የዲፕሎማሲ ሠራተኞች ላይ ምንንቱ ያልታወቀ ድምፅ እየተለቀቀባቸው ለህምም መዳረጋቸው ይነሳ ነበር፡፡

ይህን ጉዳይ የህክምና ባላሙያዎች ተከታትለውት ጥናት ካደረጉ በኋላ የጥናቱን ውጤት (JAMA. Published online February 15, 2018. doi:10.1001/jama.2018.1742) በተባለ መፅሔት አውጥተውታል፡፡

የህክምና ውጤት ስለሆነም፣ ጎሽ ድረ ገፅ ለአንባቢዎቹ ለማካፈል ወስኗል፡፡

ዋና ዋና ነጥቦች

ጥያቄው በሀቫና ኩባ በነበሩ የአሜሪካ መንግሥት ሠራተኞች ላይ በአልታወቀ ድምፅ ከመጋለጣቸው ጋር በተያያዘ የተከሰተ የነርቭ ሁኔታ አለ ወይ

ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኝት በተደረገው ክትትል፣ 21 የሚሆኑ ሠራተኞች በዚህ በተጋለጡበት ድምፅና ተጨማሪ ስሜት የሚፈጥር ነገር ምክንያት የነርቭ መዛባት ምልክት የሆኑ በትኩሱ የታዩና ከዛም ያለማቋረጥ የተከሰቱ ሰብሰብ ያሉ ሁኔታዎች ታይተዋል፡፡ ይህንን ድምፅና ሌላም ስሜት የሚፈጠር ነገር ከተጋለጡ በኋላ፣ ህመምተኞቹ የተገኛባቸው ነገር፤ የአእምሮ መታወክ፣ የሰውነት ሚዛን መጠበቅ መታወክ፣ የአይን እንቅስቃሴ መታወክ፣ የድምፅ ማዳመጥ ሁኔታ መታወክ፣ የእንቅልፍ ችግርና የራስ ምታት ናቸው፡፡

ማጠቃለያው፡ በዚህ ባልተለመደ ሁኔታ  የተጋለጡት ሠራተኞችና ያሳዩት የበሽታ ስሜትና ምልክት ያስነሳው አሳሳቢ ሁኔታ የሚጠቁመው በዚህ ባልተለመደ ድምፅ ወይም ሌላ አይነት ስሜት መጋለጥ አዲስ የሆነ የአንጎል ጉዳት የሚያስከትል  ሄደት መኖሩ ነው፡፡

ትንሽ በዝርዝር ለመመልከት

በ2016 እሰከ ነሐሴ 2017 በሀቫና ኩባ የተመደቡ የአሜሪካ መንግሥት  የዲፕሎማሲ ሠራተኞች ለድምፅና ለሌላም ነገር ከተጋለጡ በኋላ የነርቭ መዛባት ሰሜቶች እንዳለባቸው ሪፓርት አደረጉ፡፡

በዚህ አማካኝነት ለዚሕ ላልታወቀ የድምፅ ወይም ሌላ ሀይል ከተጋለጡ በኋላ የታዩባቸው የነርቭ ችግሮች እንዲጠኑ ተወሰነ፡፡  እነዚህ ሠራተኞች ለዚህ ላልታወቀ ድምፅና ሌላም አይነት ሀይል የተጋለጡት በመኖርያ ቤታቸው ወይም በሆቴል ውስጥ ነበር፡፡ ሁሉም ግለሠቦች ተመሳሳይ የሆኑ የአንጎል ጉዳት መከሰቱን የሚያሳዩ ስሜቶችና ምልክቶች መኖራቸውን ነው የገለጡት፡፡ ስለዚህ፣ ሁሉም፣ የአንጎል ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ ክትትል ወደሚደረግበት የተለያዩ ባለሙያዎች ጥናት ወይም ምርመራ ወደሚያደርጉበት ማዕከል ተላኩ፡፡

በዚህም መሠረት ሰዎቹ ሪፖርት ያደረጓቸው የአእምሮ መዛባት ምልክትና ስሜቶች ከተዘገቡ በኋላ፣ የህክምና ፋይላቸው ተሰብስቦ፣ በሀኪሞች ቃለ መጠይቅና ምርመራ ተደርጎላቸው በተጨማሪም የተለያዬ የነርቭ ክፍሎች ምርመራዎች ተደረገላቸው፡፡ በተጨማሪም አንጎልና ነርቭን ሁኔታ የሚያሳዬ የምስል ምርመራዎቸም ተደረጉ፡፡

ውጤቱ፡ ለዚህ ላልታወቀ ሀይል ተጋልጠዋል ከተባሉት 24 ሠራተኞች መሀከል 21 203 ቀናት የፈጀ ከላይ የተጠቀሰው ምርመራ ተደርጎላቸዋል፡፡ በዚህም መሠራት ከሶሰት ወራት በላይ የሆነ የማያባራ ስሜት ያላቸው መሆኑን ሰዎቹ ሪፖርት አድርገዋል፡፡ 17 ሰዎች፣  የማሰብ ችሎታቸው እንደታወከ፤ 15 ሰዎች፣ የሰውነት ሚዛን መጠበቅ መዛባት እንዳለባቸው፤ 18 ሰዎች፣ የዕይታ ችግር እንዳለበቸው፤ 15 ሰዎች፣ የማዳመጥ ችግር እንዳለባቸው፤ 18 ሰዎች የእንቅልፍ መዛባት፤ 16 ሰዎች፣ የራስ ህመም እንዳለባቸው ሪፖርት አድርገዋል፡፡

በምርምራ ከተገኙት መሀከል ደግሞ፣ የማሰብ ችሎታ መዛባት በ16 ሰዎች፤ የሚዛን መጠበቅ አለመቻል በ17 ሰዎች፣ የአይን እንቅስቃሴ መታወክ በ17 ሰዎች ተገኝቷል፡፡ በ3 ሰዎች ደግሞ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚሆን የማዳመጥ ሁኔታ መታወክ ታይቶባቸዋል፡፡ ከሰዎቹ መሀከል የህክምና ዕርዳታ ያሰፈለጋቸው አሉ፡፡ እነሱም 15 ሰዎች በነበረባቸው የማያባራ የዕንቅልፍ መዛባት ምክንያት መድሐኒት ታዞላቸዋል፡፡ 12 የሚሆኑት ደግሞ ለራስ ምታታ መድሐኒት ታዞላቸዋል፡፡ 14 ሰዎች በነበረባቸው ችግር ሥራ እንዳይሠሩ ሲደረግ፣ ከነሱ መሀከል 7 ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በከፊል የሆነ ሥራ እንዲሠሩ ተደርጎ ተመልሰዋል፡፡

ማጠቃለያው፡ ከላይ የተዘረዘሩትን የነርብና አዕምሮ መታወክ ስሜትና ምልክቶች ባሳዩ ሰዎች ላይ በተደረገው በዚህ ጥናት ፣ ለዚህ ላልታወቀ የድምፅና ሌላም አይነት ሀይል መጋለጣቸው በአንጎልና በነርቮቻቸው ላይ ስፋት ያለው ጉዳት እንደደረሰባቸው ጥናቱ ያስረዳል፡፡ እነዚህ ሰዎች ከዚህ በፊት የራስ ቅላቸው ላይ ምንም አይነት ጉዳት ታሪክ እንዳልነበራቸው ተገልጧል፡፡

የሰው ልጅ ረቀቅ ባላ መንገድ ሌላውን ሊጎዳ የሚችል ሀይል ሊፈለስፍ እንደሚችል ግልፅ ቢሆንም፡፡ የዚህ ያልታወቀ ሀይል ምንጩ እናም እንዴት የዲፕሎማሲ ሠራተኞች ላይ እንዳነጣጠረ የወጣ መረጃ የለም፡፡ የህክምና ጥናት ውጤት ስለሆነና በጣም ስለሚያስገርም ነው ያጋራናችሁ፡፡

መልካም ንባብ ፤ ለሌሎችም አካፍሉ፡፡

ምግብ ከመካንነት ጋር ይያያዛል ወይ?

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በእንስሳት ላይ በተደረገ ጥናት አትክልቶችን ከተባዮች ለመከላክል የሚረጩ ፀረ ተባይ መድሐኒቶች በአካባቢ በመጠነኛ መጠን በሚገኙበት ጊዜ በእንስሳቱ ላይ የመውለድ ችሎታቸውን እንደሚቀንስ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ታዲያ ጥያቄው ይህ ሁኔታ በሰዎች ላይም ተመሳሳይ ሁኔታ ይፈጥር ይሆን ነው ወይ፡፡ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ፍራፍሬና አትክልቶችን ከተባይ ለመከላከል የሚረጩ እነዚህ መድሐኒቶች በመጠኑም ቢሆን ምግቦቹ ላይ ስለሚቀሩ፣ እነዚህን ፍራፍሬና አትክልት የሚመገቡ ሴቶች ላይ መካንነት ያስከትል ይሆን?

በቅርቡ በጆርናል ኦፍ አሜሪካን ሜዲካል አሶሴሽን (JAMA) በሚባል መፅሔት የወጣ ጥናት ያሰፈረውን እንመልከት፡፡

አላማው ከላይ የተነሳውን ጥያቄ ለመመለስ በሆነው በዚህ ጥናት፣ በማሕፀናቸው እርግዝና መያዝ የማየችሉ በዚሁ ጉዳይም ርዳታ ለመፈለግና ከሰውነት ውጭ ፅንስ በህክምና የሚሠራባቸው የህክምና ቦታዎች የሄዱ 325 ሴቶች አመጋገብ ሁኔታ በዝርዝር ከተመዘገበ በኋላ መደበኛ ክትትል በጥናት መንገድ ተጀመረ፡፡ ጥናቱም ከ2007 – 2016 ባለው ጊዜ ነበር፡፡ ከአመጋገቡ ጥናት በመነሳት ለከፍተኛና ዝቅተኛ ፀረ ተባይ መጠን ተለይቶ ሴቶቹን በሁለት ወገን መደቡ፡፡ የፀረ ተባይ መጠን የተወሰነው ከአሜሪካው የእርሻ መምሪያ ወይም ሚኒሰቴር መስሪያ ቤት በጥናት ካሰፈረው መረጃ በመመርኮዝ ነው፡፡

የጥናቱን ዝርዝር አሰራር ልዝለልና ወደ ውጤቱ ልውሰዳችሁ፡፡

ከ325 ሴቶች በክብደት፣ በዕድሜ ከተዘረዘሩ በኋላ፣ ፀረ ተባይ መጠን የተጋለጡበት ሁኔታ ሲታይ፤ በከፍተኛ መጠን ተጋልጠዋል የተባሉት በቁጥር ሲታይ፣ በቀን 1.7 ጊዜ እነዚህን ፀረ ተባይ ቅሬታ ያለባቸውን የሚመገቡ ከዝቅተኛው መጠን ሲመደቡ፤ እነዚህን ምግቦች ደግሞ በቀን 2.8 ጌዘ በላይ የተመገቡ ሴቶች በከፍተኛ መጠን ከተጋለጡት ወገን ተመደቡ፡፡

በተደረገው ስሌት ከፍጠኛ መጠን የተመደቡት ሴቶች ነብሰጡር ወይም እርግዝና የመያዝ ዕድላቸው ዝቅ ያለ ሆኑ እርግዝናም ቢፈጠር እንኳን ልጅ የመውለድ ዕድላቸው ዝቅ ያለ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ይህ እንግዲህ በዝቅተኛ መጠን ተጋለጡ ከሚባሉት ጋር ሲነፃፀር ነው፡፡

መደምደሚያው እነዚህ በከፍተኛ መጠን የተጋለጡት ሴቶች፣ ለእርግዝና የሚሆን የህክምና እርዳታ ቢደረግላቸውም፣ ከሌሎቹ ጋር ሲነፃፀር የመፀነስ ዕደላቸው ያነሰ ከመሆኑ በተጨማሪ ቢያረግዙም እንኳን ፅንሱን ከነሕይወቱ የመውለድ ዕደላቸው ዝቅ ያለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ሰለዚህ ለፀረ ተባይ መድሐኒቶች መጋለጥ ማለትም ሁልጊዜ ሰዎች ሊጋለጡ በሚችሉበት መጠን እርግዝና ላይ ቸግር ሊያስትል እንደሚችል ነው፡፡ 

መመገብ ብቻ ሳይሆን የምንመገበው ምግብ አመጣጡን ማወቅ መጠኑንም መለየት አስፈላጊ ነው፡፡ በርግጥ ጦም አድረው ለሚውሉ ወገኖቻችን ይህንን ማንሳት ለህሊና የሚከብድ ነገር ነው፡፡ ይህ ነገር ደግሞ በተለይ በታዳጊ አገሮች የማዳበሪያው ጥራትና መጠን፣ የፀረ ተባይ መጠን የሚታወቅም አይደለም፡፡ በጓሮ የሚያደግ አትክልትና ፍራፍሬ ቅድሚያ የሚሠጠውም ለዚህ ነው፡፡ በአደጉ አገሮች፣ እንደምታውቁት በተፍጥሮ ያለምንም መድሓኒትና ማዳበሪያ ተተክለው ያደጉ አትክልትና ፍራፍሬዎች (Natural) ዋጋ ጨመር ያለ ነው፡፡ ከቻልን የምንመገበውን እናስተውል፡፡ በመጨረሻም የምለው፣ እንዚህ ለፀረ ተባይ የተጋለጡ በዝቅተኛ መጠን የተመገቡ ሴቶች ችግር ያልታየባቸው መሆኑን እያስታወስን፣ ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ እነዚሀን የምግብ ክፍሎቸን ከመመገብ መቆጠብ የለብንም፡፡

መልካም ንባብ

ሁካ ወይም ሲሻ ማጨስ በጤንነት ላይ የሚያሰከትለው ነገር ይኖር ይሆን?        በርግጥም አለ

በቅርብ ጊዜ በአንድ ጥናት በወጣው መገለጫ መሠረት ሁካ ማጨሥ በሰውነት ላይ የሚያሳየው ጉዳት እንዳለ ታውቋል፡፡

በማጠቃለል የጥናቱ ውጤት የሚያሳየው አንደኛ አጣዳፊ የሆነ በካርቦን ሞኖ ኦክሳይድ ጋዝ መመረዝ ሁለተኛ ደግሞ በልብ ትርታ ላይ ለውጥ በማምጣት አደገኛ የሆነ የልብ ምት መዛባት ጋር ግንኙነት ሊኖረው እንደሚችል ተዘግቧል፡፡ ዝርዘር ለሚወዱ ሰዎች ጥናቱን ከማካፈላችን በፊት ቨርጂኒያ በተባለ ሰቴት አንድ ደመቅ ያለ የሀበሻ (ይህን ቃል ስጠቀም እየከበደኝ ነው፤ ሌላ ጊዜ እንነጋገርበታለን) መናኸሪያ የሆነ ስካይ ላይን የሚባል ቦታ አለ፡፡ ሰልፋቸው አሳምረው ከተደረደሩት የንግድ ቤቶች አንደኛው ይኸው የሱረት ማጨሻ ቤት ነው፡፡ እንደ ሞኝ ከበሩ ራቅ ብዬ ለመመልከት ሞከርኩ፣ ወጣቶች በጥንድ ተቀምጠው እንደ አስም መድሃኒት ይህንኑ ጭስ ሲምጉ አየሁኝ፡፡ በአጋጣሚም ሁለት በኛ አነጋገር ጎረምሶች ወደ ውጭ ወጡ፤ አንደኛው ቡዝዝ ብሎ ዓለም በሱ ዙሪያ የምትሸከረከርበት ይመስላል፡፡ አቤት ይህን ሁሉ ውቅያኖስ አቋርጠው የመጡት ለዚህ ነው ወይ አልኩኝ፡፡ በመጠኑም ቢሆን የኛ ኮበሌውች ሌሎች ህገወጥ ዕፆች መተላለፊያ መንገድ ላይ ተሠንቅረው መያዛቸውን ሰምተናል፡፡

ወደ ጥናቱ ልመልሳችሁ

መጠነኛ ጥናት ቢሆንም በፕሮቶኮሉ መሠረት 33 ወጣቶች ሺሻ ከማጨሳቸው በፊትና ካጨሱ ከሰላሳ ደቂቃ ምርመራዎች ተደረጉ፡፡ ተሳታፊዎቹ በፈቃዳቸው ነው፡፡ የተደረገው ምርምራ አይነት ቫይታል ሳይን(VITAL SIGNS) ተብሎ የሚጠራው ወደ ህክምና ቦታ ሲኬድ የሚደረገው ፣ የደም ግፊት፣ የልብ ትርታ ፍጥነት እና ሌሎቹም ሲሆን፤ ሌላው ምርመራ ደግሞ የልብን የኤሌትሪክ ሥርጭት የሚዘግብ ኤሌክትሮ ካርድዮ ግራም (EKG  ) የተባለ ምርመራ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በደም ውስጥ በካርቦን ሞኖ ኦክሳይድ መመረዝ መለኪያ የሆነ ካርቦክሴ ሄሞግሎቢን የሚባል ኮምፓውንድን በደም ምርመራ መለካት ይጨምራል፡፡

ውጤቱ እደሚከተለው ነው

ከማጨሳቸው በፊትና ካጨሱ ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ

አማካይ ካርቦክሲ ሄሞግሎቢን የሚባለው ኮምፓውንድ ከ1.3% ወደ 23.7% ክፍ ብሎ ተገኝቷል

በአንዳንዶቹ ላይ መጠኑ እሰከ 44% ከፍ ብሎ ተገኝቷል፡፡ ይህ ደግሞ በካርቦን ሞኖኦክሳይድ ከመመረዝ ጋር እኩል ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ካርቦን ሞኖአኮሳይድ ጭስ አልባው ከተቃጠለ አሳት ወይም ከመኪና ሞተር የሚወጣ ጋዝ ሲሆን ለብዙ ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት ነው፡፡ በአሜሪካ አገር አዳዲስ የሚሠሩ ቤቶች ይህንን ጭስ አልባ ጋዝ የሚያፈነፍን መለኪያና ከዛም ማስጠንቀቂያ ድምፅ የሚሠጥ መሳሪያ እንዲኖራቸው ሕግ ያስገድዳል፡፡

ደም ግፊት ሁለቱም የላይኛውና (systolic) የታችኛው (diastolic) ከፍ ብሎ ታይቷል

በሰውነት ውስጥና አካል ላይ የኦክስጅን ሥርጭት መጠን ዝቅ ማለት

በልብ መመርመሪያው በኩል ደግሞ ብዛት ያላቸው የልብ ኤሌክትሪክ ሥርጭት መቃወስን የሚያሳዩ ምልክቶች ታይተዋል፡፡ ከአነዚህም መካከል ለሕይወት አስጊ የሆን የልብ ምት መቃወስ ምልክቶች ታይተዋል፡፡

እንግዲህ ዋናው ፍራቻ ምንድን ነው ቢባል፣ በካርቦን ሞኖኦክሳይደ የተመረዙ ሰዎች አጣዳፊ በሚሆንበት ጊዜ የልብ ምት በመዛባት ልብ ሥራውን አቁሞ ለህይወት ማለፍ ይዳርጋል፡፡ ራሳቸውን ማጥፋት የፈለጉ ሰዎች በቤታቸው መኪና ማቆሚያ ውሥጥ ሆነው በሩን ዘግተው የመኪናውን ሞተር አስነስተው ቁጭ በማለት ህይወታቸው ሲያልፍ ይታወቃል፡፡ በአጣዳፊ ሲሆን የካርቦንሞኖ ኦክሳይድ መጠኑ ከፍ ያለ ነው፤ በዚህ ጥናት ግን እዛ ደረጃ አልደረሰም አና ይህ መጠነኛ መመረዝ የሚያሰከትለው ዘላቂ ጉዳት ይኖር ይሆን?

እየተዝናኑ በመጠኑም ቢሆን መመረዝ ይባላል፡፡

Source: Yıldırım F, Çevik Y, Emektar E, Çorbacıoğlu ŞK, Katırcı Y. Evaluating ECG and carboxyhemoglobin changes due to smoking narghile. Inhal Toxicol. 2016 Sep12 [Epub ahead of print]. doi: 10.1080/08958378.2016.1224957. PMID: 27618930

ቡና መጠጣትና የጉበት በሽታዎች መሻል

በአብዛኛው የምንመገበውና የምንጠጣቸው ነገሮች በሰውነት ላይ ጉዳት ያደርሳሉ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ለሰውነት ጠቀሜታ ያላቸው ነገሮች እንዳሉ ከዚህም ከዚያም የሚወጡ ጥናቶች ይዘግባሉ፡፡

ሰዎች በብዛት ከሚያዘወትሯቸው መጠጦች አንዱ ቡና ነው፡፡ የተለያዩ ጥናቶች አንደሚያሳዩት፣ ከዚህ ቀደም በሰውነት ላይ ጥሩ ውጤት ያመጣል ተብሎ ነው ማጠቃለያው የሚወጣው፡፡ ከሥራ ባልደረቦቻችን ጋር እየቀለድንም ቢሆን ይህን ጥናት ያካሄደው ሰታርባክስ ነው ወይ እያልን ነበር፡፡

አሁን ግን ጠንከር ባለ ሁኔታ ቡና በተለይም የጉበት በሽታ ያላቸው ሰዎች ላይ ያለው ከፍተኛ ጠቀሚታ በጥናት እየታየ ነው፡፡ በቀን ከሁለት ኩባያ በላይ ቡና መጠጣት ያለውን ጠቀሜታ በዝርዝር ለማሰቀመጥ ሰለ ጉበት በሸታዎች በመጠኑም ቢሆን መግለፅ ጥሩ ነው፡፡

የጉበት በሽታ በሔፓታይትሰ ቢ(Hepatitis B)፣ በሔፓታይትስ ሲ (Hepatitis C) ቫይረሶች አማካኝነት ይከሰታል፡፡ መጥፎ ውጤቱም ጉበቱን በማቁሰል የጉበት ጥብሰት (ሲሮስስ cirrhosis of the liver)፣ የጉበት መድከም (liver failure) እና የጉበት ካንሰር ናቸው፡፡ የጉበት መድከም አስኪከሰት ድረስ በጉበት ውስጥ የሚካሄደው ጥብሰት ምንም ምልክት የማይሰጥ መሆኑን አንባብያን ሊረዱት ይገባል፡፡ በጎሽ(www.Goshhealth.org) ድረ ገፆች ስለነዚህ በሽታዎች ሰፋ ያሉ ፅሁፎችን ያንብቡ::

ከቫይረስ ልክፍቶች ውጭ ደግሞ በአልኮሆል አማካኝነት ተመሳሳይ የጉበት በሽታ የሚከሰት ሲሆን ሌላ እምብዛም በህብረተሰቡ የማይታወቅ በአልኮሆል ያልመጣ በጉበት ውስጥ ከመጠን በላይ ጮማ መከማቸት የሚያስከትለው (Non Alcoholic Fatty liver disease ) የሚባል በሽታ አለ፡፡ ይህ (fatty liver disease) የሚባል ሁኔታ በአልኮል አማካኝነትም ይከሰታል፡፡

እንግዲህ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆን ከሁለት ኩባያ ወይም ከዛ በላይ በየቀኑ ቡና መጠጣት የሚከተሉትን ለውጦች ሲያስከትል ታይቷል፡፡

  1. በጉበት በሽታ ምክንያት በደም ምርመራ የሚታዩ ሶሰት ነገሮችን ማለሳለስ

      2. ከዚህ ጋር በተያያዘም የጉበት ጥብሰት መፈጠርን ማዘግየት

      3. የጉበት ጥብሰት በመዘግየቱ ምክንያት ደግሞ የጉበት መድከምን ማዘግየትና መከላከል
      4. ተያይዞም የጉበት ካንሰር የመከሰት ሁኔታን መቀነስ
      5. በዚህም ምክንያት ደግሞ በጉበት በሽታ ምክንያት የሚከሰት ሕይወት ማለፍን ማዘግየት
      6. የሔፓታየትስ ሲ ቫይረስ ያለባቸው ሰዎች ላይ ደግሞ ቡና በመጠጣታቸው ምክንያት ለሔፓታይትስ መድሀኒቶች ጥሩ ምላሽ መስጠት ናቸው፡፡

እነዚህ ጥናቶች ከዚህ በፊት የታዘገቡም ቢሆን፤ የዚህ መልክት ፀሀፊ በቅርቡ በኒው ኦርሊንስ ከተማ በተደረገው በአሜሪካ የተላላፊ በሽታ ስፔሽያሊስቶች ስብሰባ በመገኘት ከባለሙያተኞ የቀረበውን መረጃም አዳምጦአል፡፡

እንደ መረጃ አቅራቢዎች በቀን የቡናው መጠን በጨመረ ቁጥር ጠቀሚታው እየጨመረ አንደሚሄድ ነው ያስገነዘቡት፡፡

በዚህ ምክንያት ለጉበት በሽታ መከሰት አደጋ ላይ ያሉ ሰዎች ቡና እንዲያዘወትሩ ምክር እንዲሠጥ ነው የተሰማማነው፡፡ ለዚህም ነው ይህ ፅሁፍ የቀረበው፡፡

በሽተኞቼን እየመከርኩ ነው፡፡

ቡና በመጠጣት የሚከተለውን ሌላ አደጋ ማሰተዋል ደግሞ ተገቢ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የደረት ቃር(Gastro esophageal reflux disease, GERD) ላለባቸው ሰዎች ቡና እንዳይጠጡ ምክር ይሠጣል፡፡ የጨጓራ (ulcer) ያለባቸው ሰዎችም እንዲሁ፡፡ ከሙያ አንፃር የምመክረው፤ ለጉበት በሽታ የተጋለጡ ሰዎች የጨጓራ መድኃኒቶችን እየወሰዱ ቡና እንዲያዘወትሩ ነው ምክሩ፡፡ ምክንያቱም አንድ ጊዜ የጉበት ጥብሰት ከተከሰተ ወይም የጉበት ካንስር ከተከሰት አካሄዱ ወደ ከፋ ደረጃ ማለትም ወደ ሕይወት ማለፍ የሚያሽቆለቁል ሰለሆነ ነው፡፡

እንደኔ ከሆነ የኢትየጵያ ቡና ሳይሻል አይቀርም (እየቀለድኩ ነው)፡፡ ነገር ግን አዲስ አባባ የታሸጉ ቡናዎች በከረጢት ለመግዛት ስንሞክር የተሠጠን ምክር አሁን ድረስ ይከነክነኛል፡፡ ይሄን አይነት አትግዙ ምክንያቱም ቡናው ውስጥ ምናምን ይጨምሩበታል ተብለን አንድ ቦታ ብቻ ሄደን ገዝተናል፡፡ ስሙን አልናገረም፤ ግን ቡና ጠጭዎች የትኛው ንፁህ እንደሆን ያውቃሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ፣ ኩባያ ሲባል እዚህ አውሮፓና አሜሪካ ያለውን መጠን መገንዘብ ነው፡፡

ይህንን ፅሁፍ ማጋራት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ የፌስ ቡክ አካውንት ለሌላቸው ሰዎች ደግሞ በጎሽ ድረ ገፅ ሰለተቀመጠ ወደ ጎሽ ድረ ገፅ መምራት ተገቢ ነው፡፡

ዋቢ

Impact of coffee on liver diseases: a systematic review.
Saab S, Mallam D, Cox GA 2nd, Tong MJ.
Liver Int. 2014 Apr;34(4):495-504. doi: 10.1111/liv.12304. Review

Coffee and non-alcoholic fatty liver disease: brewing evidence for hepatoprotection?
Chen S, Teoh NC, Chitturi S, Farrell GC.
J Gastroenterol Hepatol. 2014 Mar;29(3):435-41. doi: 10.1111/jgh.12422. Review

Coffee has hepatoprotective benefits in Brazilian patients with chronic hepatitis C even in lower daily consumption than in American and European populations.
Machado SR, Parise ER, Carvalho Ld.
Braz J Infect Dis. 2014 Mar-Apr;18(2):170-6. doi: 10.1016/j.bjid.2013.09.001

Association of coffee and caffeine consumption with fatty liver disease, nonalcoholic steatohepatitis, and degree of hepatic fibrosis.
Molloy JW, Calcagno CJ, Williams CD, Jones FJ, Torres DM, Harrison SA.
Hepatology. 2012 Feb;55(2):429-36. doi: 10.1002/hep.24731.