ሁካ ወይም ሲሻ ማጨስ በጤንነት ላይ የሚያሰከትለው ነገር ይኖር ይሆን? በርግጥም አለ

በቅርብ ጊዜ በአንድ ጥናት በወጣው መገለጫ መሠረት ሁካ ማጨሥ በሰውነት ላይ የሚያሳየው ጉዳት እንዳለ ታውቋል፡፡

በማጠቃለል የጥናቱ ውጤት የሚያሳየው አንደኛ አጣዳፊ የሆነ በካርቦን ሞኖ ኦክሳይድ ጋዝ መመረዝ ሁለተኛ ደግሞ በልብ ትርታ ላይ ለውጥ በማምጣት አደገኛ የሆነ የልብ ምት መዛባት ጋር ግንኙነት ሊኖረው እንደሚችል ተዘግቧል፡፡ ዝርዘር ለሚወዱ ሰዎች ጥናቱን ከማካፈላችን በፊት ቨርጂኒያ በተባለ ሰቴት አንድ ደመቅ ያለ የሀበሻ (ይህን ቃል ስጠቀም እየከበደኝ ነው፤ ሌላ ጊዜ እንነጋገርበታለን) መናኸሪያ የሆነ ስካይ ላይን የሚባል ቦታ አለ፡፡ ሰልፋቸው አሳምረው ከተደረደሩት የንግድ ቤቶች አንደኛው ይኸው የሱረት ማጨሻ ቤት ነው፡፡ እንደ ሞኝ ከበሩ ራቅ ብዬ ለመመልከት ሞከርኩ፣ ወጣቶች በጥንድ ተቀምጠው እንደ አስም መድሃኒት ይህንኑ ጭስ ሲምጉ አየሁኝ፡፡ በአጋጣሚም ሁለት በኛ አነጋገር ጎረምሶች ወደ ውጭ ወጡ፤ አንደኛው ቡዝዝ ብሎ ዓለም በሱ ዙሪያ የምትሸከረከርበት ይመስላል፡፡ አቤት ይህን ሁሉ ውቅያኖስ አቋርጠው የመጡት ለዚህ ነው ወይ አልኩኝ፡፡ በመጠኑም ቢሆን የኛ ኮበሌውች ሌሎች ህገወጥ ዕፆች መተላለፊያ መንገድ ላይ ተሠንቅረው መያዛቸውን ሰምተናል፡፡

ወደ ጥናቱ ልመልሳችሁ

መጠነኛ ጥናት ቢሆንም በፕሮቶኮሉ መሠረት 33 ወጣቶች ሺሻ ከማጨሳቸው በፊትና ካጨሱ ከሰላሳ ደቂቃ ምርመራዎች ተደረጉ፡፡ ተሳታፊዎቹ በፈቃዳቸው ነው፡፡ የተደረገው ምርምራ አይነት ቫይታል ሳይን(VITAL SIGNS) ተብሎ የሚጠራው ወደ ህክምና ቦታ ሲኬድ የሚደረገው ፣ የደም ግፊት፣ የልብ ትርታ ፍጥነት እና ሌሎቹም ሲሆን፤ ሌላው ምርመራ ደግሞ የልብን የኤሌትሪክ ሥርጭት የሚዘግብ ኤሌክትሮ ካርድዮ ግራም (EKG  ) የተባለ ምርመራ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በደም ውስጥ በካርቦን ሞኖ ኦክሳይድ መመረዝ መለኪያ የሆነ ካርቦክሴ ሄሞግሎቢን የሚባል ኮምፓውንድን በደም ምርመራ መለካት ይጨምራል፡፡

ውጤቱ እደሚከተለው ነው

ከማጨሳቸው በፊትና ካጨሱ ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ

አማካይ ካርቦክሲ ሄሞግሎቢን የሚባለው ኮምፓውንድ ከ1.3% ወደ 23.7% ክፍ ብሎ ተገኝቷል

በአንዳንዶቹ ላይ መጠኑ እሰከ 44% ከፍ ብሎ ተገኝቷል፡፡ ይህ ደግሞ በካርቦን ሞኖኦክሳይድ ከመመረዝ ጋር እኩል ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ካርቦን ሞኖአኮሳይድ ጭስ አልባው ከተቃጠለ አሳት ወይም ከመኪና ሞተር የሚወጣ ጋዝ ሲሆን ለብዙ ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት ነው፡፡ በአሜሪካ አገር አዳዲስ የሚሠሩ ቤቶች ይህንን ጭስ አልባ ጋዝ የሚያፈነፍን መለኪያና ከዛም ማስጠንቀቂያ ድምፅ የሚሠጥ መሳሪያ እንዲኖራቸው ሕግ ያስገድዳል፡፡

ደም ግፊት ሁለቱም የላይኛውና (systolic) የታችኛው (diastolic) ከፍ ብሎ ታይቷል

በሰውነት ውስጥና አካል ላይ የኦክስጅን ሥርጭት መጠን ዝቅ ማለት

በልብ መመርመሪያው በኩል ደግሞ ብዛት ያላቸው የልብ ኤሌክትሪክ ሥርጭት መቃወስን የሚያሳዩ ምልክቶች ታይተዋል፡፡ ከአነዚህም መካከል ለሕይወት አስጊ የሆን የልብ ምት መቃወስ ምልክቶች ታይተዋል፡፡

እንግዲህ ዋናው ፍራቻ ምንድን ነው ቢባል፣ በካርቦን ሞኖኦክሳይደ የተመረዙ ሰዎች አጣዳፊ በሚሆንበት ጊዜ የልብ ምት በመዛባት ልብ ሥራውን አቁሞ ለህይወት ማለፍ ይዳርጋል፡፡ ራሳቸውን ማጥፋት የፈለጉ ሰዎች በቤታቸው መኪና ማቆሚያ ውሥጥ ሆነው በሩን ዘግተው የመኪናውን ሞተር አስነስተው ቁጭ በማለት ህይወታቸው ሲያልፍ ይታወቃል፡፡ በአጣዳፊ ሲሆን የካርቦንሞኖ ኦክሳይድ መጠኑ ከፍ ያለ ነው፤ በዚህ ጥናት ግን እዛ ደረጃ አልደረሰም አና ይህ መጠነኛ መመረዝ የሚያሰከትለው ዘላቂ ጉዳት ይኖር ይሆን?

እየተዝናኑ በመጠኑም ቢሆን መመረዝ ይባላል፡፡

Source: Yıldırım F, Çevik Y, Emektar E, Çorbacıoğlu ŞK, Katırcı Y. Evaluating ECG and carboxyhemoglobin changes due to smoking narghile. Inhal Toxicol. 2016 Sep12 [Epub ahead of print]. doi: 10.1080/08958378.2016.1224957. PMID: 27618930