GOSH HEALTH


Community health 

education in Amharic 


​​​​​​​​እየጨመሩ የመጡት በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ሊኖሯቸው የሚችሉ የበሽታ ስሜትና ምልክቶች 5/30/2020

በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች የሚኖሯቸው የበሽታ ሰሜትና ምልክቶች እየጨመሩ ነው፡፡ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሁሉም አንድ አይነት ሁኔታ አይታይባቸውም፡፡ ማለትም በቀላሉ ከሚለቃቸው ጀምሮ በጠና የሚታመሙና ህይወታቸው የሚያልፍም ድረስ ነው፡፡
ሰሜቶች በቫይረሱ ከተጋለጡ ከ2-14 ቀናት ባሉት ጊዜ ውስጥ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ሁሉም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሰሜቶች አንድ ላይ ላይገኙ ይችላል፡፡

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ስሜቶች ያሉባቸው ሰዎች በኮቪድ-19 ተይዘውም ሊሆን ይችላል፡፡

 1. ብርድ ብርድ ስሜትና ትኩሳት
 2. ሳል
 3. የትንፈሽ ሰሜት ማጠርና ለመተንፈስ መቸገር
 4. የድካም ስሜት
 5. የጡንቻና የሰውነት ህመም
 6. ራስ ምታት
 7. ድንገተኛ የማሽተትና የመቅመስ ችሎታ ማጣት
 8. የጉሮሮ መቁሰል
 9. አፍንጫ መታፈንና ንፍጥ መውረድ
 10. ማቅለሽለሽና ማስታወክ
 11. ተቅማጥ

 
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ይሁኑ እንጂ ሰዎች ሌሎች ተጨማሪ ስሜቶችና ምልክቶች ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ቫይረሱ የማየድርስበት የሰውነት ክፍል ሰለሌለ፣ በቆዳ፣ በአይንም በኩል የበሽታ ምልክት እያሳየ ነው፡፡ ስትሮክና የልብ ህመም ታይቷል፡፡ ልጆች ላይ የተከሰተው በኢንፍላሜሽን አማካኝነት የሚመጣው በሽታም ሌላ መገለጫ ነው፡፡


​​ኮቪድ-19 ጉልበቱን በሚያሳይበት ቦታ ከተያዙት 43% ይገድላል    6/03/20

በአሜሪካ በተቀዳሚነት በኮቪድ-19 ከተጠቁት ሶስት ክፍሎች አንዱ ነርሲንግ ሆም (የአዛውንቶች መጦሪያ) ቦታ ነው፡፡ ከዛ ቀጥሎ ቤተሰብ፣ ከዛ ደግሞ የጤና በለሙያተኞች ናቸው፡፡

የነርሲንግ ሆም ጥቃት ከሌሎች የሚለየው፣ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ምን ያህሉ እንደሚሞቱ ነው፡፡ የአሜሪካው CMS (Center for Medicaid and Medicare Services) ሪፖርት ከሠጡት አብዛኞች የነርሲንግ ሆም ተቋሞች ያጠናከረውን አስደንጋጭ መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ በቻርቱ እንደምታዩት፣ በበሽታው ከተያዙት ከ60 439 ሰዎች መሀከል፣ 25 923 ሞተዋል፡፡ በፐርስንት ሲሰላ 43 ነው፡፡ ግማሹን በሉት፡፡ በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ ምክንያት አለ፡፡ የነርሲንግ ሆም ሰዎች፣ በዕድሜ የገፉና በብዛት ሌሎች ተደራቢ በሽታዎች አንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ ተደጋግሞ እንደታየው፣ በኮቪድ ከተያዙ በኋላ አሰከፊ ውጤት የሚደርስባቸው ሰዎች ናቸው፡፡

ወደ ሀገር ቤት ብንመለስ፣ እንደ አሜሪካ አዛውንቶችን አንድ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚረዱ ተቋማት ብዛት እንደሌለ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን፣ እንደ ባህላችን፣ ወላጆችን በቤታቸው ወይም በየልጆቻቸው ቤት መጦር የተለመደ ነው፡፡ ፍራቻው ደግሞ፣ እነዚህ በየቤቱ የተቀመጡ የዕድሜ ባለፀጎችን፣ ሌሎች አብረዋቸው የሚኖረ ወጣ ገባ የሚሉ ሰዎች ቫይረሱን ሊያቀብሏቸው እንደሚችሉ ነው፡፡ ለዚህ እንግዲህ፣ እንደዚህ አይነት ሰዎች በየቤቱ ያሉባቸው ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ነው፡፡ በጥናት የረዳ ነገር የታየው፣ ወጣ ገባ የሚሉትም፣ አዛውንቱም ማስክ ቢያደርጉ ሠርጭቱን ይቀንሱታል፡፡

በተጨማሪማ፣ ወረርሽኙ አስከሚያልፍ ድረስ፣ እነዚህ በዕደሜ የገፉ ሰዎች ከቤት ውጭ መውጣትና ርቀው መሄድ እንዳይሄዱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ፣ ቤተክርስቲያንና ፀሎት ቤቶችንም ይጨምራል፡፡(ይከብዳል) ነገር ግን አማራጭ ሰሌለም ነው፡፡

መረጃው የሚያሳየው፣ የነርሲንግ ሆም ሠራተኞች በቫይረሱ ከመያዝ አላመለጡም፡፡ ደግነቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በንፅፅር ሲታይ አነስተኛ ነው፡፡ ማለትም ከ34442 ሠራተኞች መሀከል፣ 449 ሞተዋል፡፡

ሌላው አስፈሪ ቁጥር የወጣው ደግሞ፣ የአሜሪካው CDC ይፋ ያደረገው በቫይረሱ የተያዙ የጤና ባለሙያተኞች ቁጥርና በዚሁ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ነርስና ሀኪሞች ሌሎችንም ጨምሮ ነው፡፡ በቫይረሱ የተያዙት የጤና ባለሙያተኞች ቁጥር 66 770 ሲሆን ከነሱ መሀከል 323 ሞተዋል፡፡

እንደገና ወደ ሀገር ቤት ዞር ብለን ብንመለከት፣ የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረ መሄዱን አናያለን፡፡ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎችን ማጨናነቃቸው የሚቀር ነገር አይደለም፡፡ መለስ ብለን የአሜሪካውን ችግር ብናይ፣ በቂ የሆነ ሙሉ የጤና ባለሙያተኞች የሚለብሱት መከላከያ በበቂ ደረጃ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያም ቢሆን ይህ ችግር የከፋ እንደሚሆን ነው፡፡ ሰለዚህ ርዳታችን አንደሚያስፈልጋቸው አስቀድሞ መገንዘብም ያስፈልጋል፡፡


በኮቪድ ሥርጭት ቤተሰብዎን ለማዳን የሚረዳ ታላቅ ግኝት “የጨነቀ ዕለት” አለ ድምፃዊው 5/31/20

የሳርስ ኮሮና ቫይረስ ቁ2 (ሳኮ2) ከሰው ወደ ሰው በመሸጋገር አደገኛነቱን ወይም የተዋጣለት መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ታዲያ በጣም የሚሸጋገርባቸው ቦታዎችን ካየን፣ አንዱና ትልቁ በቤተሰብ መሀል በቤት ውስጥ ነው፡፡
ለምን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው

አንደኛ፤ ቅርበት፣ ማለትም በስድስት ጫማ (ሁለት ሜትር) መቀራረብ ሰላለ
ሁለተኛ ደግሞ፡፡ የመጋለጫ ጊዜ ረዥም ሰለሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ በሆስፒታል፣ አንድ በኮቪድ የተያዘ ሰው ምንም ማስክ ሳያደርግ ማሰክ ካላደረገ የጤና ባለሙያተኛ ጋር በቅርበት ግንኙነት ቢያደርግ፣ በቫይረሱ ለመያዝ ሁለት ደቂቃ በቂ ነው፡፡ ታዲየ ቤት ውስጥማ፣ እራሳችሁ ገምቱት፡፡

አንዱ ትልቅ ችግር የሆነው፣ በሳኮ 2 ተይዘው ስሜት አልባ የሆኑ ሰዎች ብዛት ነው፡፡ ሰሜት አልባዎቹ በሁለት ይከፈላሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ በቫይረሱ ቢያዙም የስሜት ምልክት ሳይኖራቸው አስከ መጨረሻው የሚዘልቁ ሲሆን፡፡ ቀሪዎቹ ግን፣ በቫይረሱ ተይዘው፣ መጀመሪያ ሰሜት ባይኖራቸውም ቆየት ብለው የበሽታ ሰሜት፣ ከመጠነኛ እሰከ ለህይወት አስጊ የሚሆን ድረስ ይታይባቸዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች፣ የበሽታ ሰሜት ከመጀመሩ ከአራት ቀናት በፊት(በአብዛኛው ደግሞ ከ48 ሰኣታት በፊት) ቫይረሱን ወደ ሌላ ሰው ያስተላልፋሉ ማለት ነው፡፡ እነዚሀ ሰዎች በጣም አደገኛ የሚያደርጋቸው ነገር ደግሞ፣ እንደታወቀው፣ የበሽታ ህመም ከመጀመሩ በፊት፣ ቫይረሱ በአፍንጫ ውስጥ ከመጠን በላይ ሰፍሮ ሰለሚገኝ ነው፡፡

አሁን ይሀንን በመረዳት ሁሉም ሰው ከቤት ውጭ ማስክ (የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርግ ተደርጓል)፡፡ ማን ቫይረሱ እንዳለበት ወይም እንደሌለበት የሚታወቅ ነገር አይደለም፡፡ ቆየት ብለው የሚታመሙ በወቅቱ የበሽታ ስሜት የሌላቸው ሰዎች ቫይረሱን ቢያስተላልፉም፣ እነሱ ራሳቸው መያዛቸውን አያውቁም፡፡ ሰለዚህ ጣት መቀሰር አያስፈልግም፡፡

ቸግር የሆነው በቤት ውስጥ ነው፡፡ እንደ ምኞታችን ቫይረሱ ከአካባቢው አልፎ እስኪሄድ ሁሉም ሰው በቤት ውስጥ ቢከተት ደስታውን አንችለውም፡፡ ነገር ግን፣ የኑሮ ጉዳይ አለ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ህብረተሰቡን የሚያገለግሉ እንደሌላው በየቤታቸው መቆየት የማይችሉ የጤና ባለመያተኞች፣ ፀጥታ አስከባሪዎች፣ የውሃ የመብራት አገልግሎት ሠራተኘቾ፣ ምግብኛ ሸቀጥ አቅራቢዎች የግድ ከቤት መውጣት ይኖርባቸዋል፡፡

ከነዚህ ውጭ ግን፣ በቤታቸው መቆየት እየቻሉ፣ የሞተ ሰው ካላዩ በስተቀር ኮሮና አልገባም የሚሉ፤ አኛን አይነካንም የሚሉ ወይም ብለው የሚያስቡ፤ ሌላውን ምክር ከቁብ የማይቆጥሩ ባሉበት ሁኔታ ምን ማድረግ ይቻላል፡፡

ከውጭ ማስክ ማድረግ ይቻላል ቤት ውስጥ ግን በተለይ፣ በቫይረሱ ከተያዙ ከፍተኛ የህመም ደረጃ ብሎም ህይወታቸው ሊያልፍ የሚችሉ ሰዎች ያሉበት ቤተሰብ ውስጥ ምን ማድረግ ይቻላል የሚለው ጥያቄ በማንም በዚህ ጉዳይ የሚጨነቅ ባለሙያም ሆነ ቅን ዜጋ አዕምሮ የሚብሰለሰል ነገር ነበር፡፡

አሁን አተገባበሩ ግራ የሚያጋባ ቢመስልም አንድ አዲስ ጥናት ወጥቷል፡፡ እንደ ሌሎቹ “ሰበር ዜና” ብዬ ባላጋራችሁም፣ ደስተኛ ከሆንኩባቸው ጥናቶች አንዱ በመሆኑ፣ በሰንበት፣ ጣቶችን ከታይፕ ጋር አገናኝቼ፣ ዜናው ለናንተ አስኪደርስ በጉጉት በመተክተክ ላይ ነኝ፡፡

እንደተለመደው በመረጃ ነው፡፡ ጥናቱ ከቻይና በኩል ነው የመጣው፤ የፅሁፉን ምንጭ በዚህ ፅሁፍ መጨረሻ ላይ አስቀምጫለሁ፡፡

መግቢያው ላይ የሚጠቁሙትም፣ በቤት ወስጥ መደረግ ሰለሚገባው ጥንቃቄ ከዚህ በፊት በጥናት የታየ መረጃ የለም ነው የሚሉት፡፡ ውነት ነው፡፡ በውጭ በኩል የሚደረጉ የመከላከያ እርምጃዎች ውጤት እንዳላቸው የታወቀ ነው፡፡

በጥናቱ መሠረት፣ ከ124 ቤተሰብ (ቤቶች) 335 ሰዎችን ያካተተ ጥናት ነው የተመለከቱት፡፡ በየቤቱ ቢያንስ ቢያንስ አንድ በኮቪድ መያዙ የተረጋገጠ ሰው አለበት፡፡ የጥናቱ ጊዜ ከየካቲት ማለቂያ እሰክ መጋቢት ማለቂይ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

የጥናቱ ውጤት የሆነው ደግሞ፣ በኮቪድ ከተያዘው በመጀመሪያው ሰው ምክንያት ምን ያህል የቤተሰቡ አባለት በኮቪድ ተያዙ ነው፡፡ ከመጀመሪያው ሰው ተነስቶ ወደሌሎቹ ሲሻገር ሁለተኛ ሥርጭት ይባላል፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘው ቤቶች ውስጥ የተደረጉትን የመከላከል ባሕሪዎችንም ተመልክተዋል፡፡

በውጤቱ የታየው፤ ከመጀመሪያው በኮቪድ ከተያዘው የቤተሰብ አባል ተነስቶ ወደ ሌሎቹ የመሻገር ማለትም ሁለተኛ ደረጃ ሥርጭቱ 23% ነበር (ከ335 ሰዎች 77 ተይዘዋል ማለት ነው)፡፡ ይህ ቁጥር አስተውላችሁ ከሆነ፣ ሌላ ጊዜ ካየነው ቁጥር በጣም ያነሰ ነው፡፡ እንዴት ከ335 ከተጋለጡ ሰዎች መሀከል፣ ያውም በቤት ውስጥ፣ 77 ሰዎች ብቻ ተያዙ? ጥሩ ነገሩም የመጣው ከዚህ ቁጥር ማነስ ጋር ተያይዞ ነው፡፡

ይሀ ቁጥር ማነስ የታየው፣ በኮቪድ ቫይረስ የተያዘው ሰውና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት፣ ሰውየው የህመም ስሜት ከመጀመሩ አስቀድሞ፣ ሁሉም በቤታቸው ውስጥ ማስክ በማድረጋቸው፣ የበሽታው ወይም የቫይረሱ ሥርጭት በ79% እንዲቀንስ ነው ያደረገው፡፡ በጣም ጠቃሚ ትልቅ መረጃ ነው፡፡ ከማስኩ በተጨማሪ፣ በየቀኑ በአልኮልም ሆን በክሎሪን ቤቱን ማፅዳት፣ እንደ አጥኝዎቹ ስሌት፣ ሥርጭቱን በ77% መቀነስ እንደሚችል ነው፡፡

እዚህ ላይ፣ እንደተጠበቀው፣ የበሽታ ምልክት ወይም ሰሜት ከጀመረ በኋላ፣ ማስክ ማድረጉ ጠቀሚታ አልታየበትም፡፡ እንዳያችሁት ወይም እንደምትገነዘቡት፣ ጉዳቱ የደረሰው ገና የበሽታ ሰሜት ሳይጀመር ነው፡፡ እንግዲህ በቀናት ሲታይ ወደኋላ ከአራት ቀናት በፊት በርግጥም ከ48 ሰአታት በፊት መከላከል ካልተደረገ፣ ቫይረሱ ተሻግሯል፡፡

በቤት ውስጥ አብሮ በመኖር ብቻ፣ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር በሚደረገው ቅርበት ያለው ግንኙነት ተደጋጋሚ መጋለጥ የቤተሰቡን አባላት በ18 ዕጥፍ የመያዝ አደጋ ላይ ይጥላቸዋል፡፡ ይህ እንግዲህ በትንፋሽ ከሚመጣው አደጋ ነው፡፡ በኮቪድ የተያዘው ሰው ተቅማጥ ቢኖረውስ፤ በዚህ ሁኔታ ደግሞ የቤተሰቡ አባለት በአራት ዕጥፍ በቫይረሱ የመያዝ አደጋ ላይ ናቸው፡፡

ሰለዚህ፣ ምን መደረግ እንደሚኖረበት ሁላችንም አኩል ሃሳብ ላይ የደረስን ይመስለኛል፡፡ አሳዛኝ ሆኖ ቤተሰብ ውስጥ ሀይለኛ ሥርጭት ሰለሚፈጠር፣ እንደቤተሰብ አብረን የምናደርጋቸው ነገሮች ላይ ነው የመጣብን፡፡

ምክሩ
1ኛ. ከቤት ወጥተው የሚሠሩ ከሆነ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ መራራቁ የሚመክረው፣ ካልተገደዱ በስተቀር እንዳይወጡ ነው፡፡
2ኛ. በቤት ውስጥ ከሌሎች ሰዎች ጋር አብረው የሚኖሩ ከሆነ፣ እስዎ በመውጣትዎ ምክንያት በቫይረሱ ለመያዝ የሚጋለጡ ከሆነ፣ የግድ ሊሆን ነው፣ ቤት ውስጥ ማስክ ማድረግ ሊኖርብዎት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ አዛውንቶች ካሉ፣ ሌላ በኮቪድ ከፍተኛ የህመም ሁኔታ ሊፈጥርባቸው የሚችል ተደራቢ በሽታ ያለባቸው ሰዎች በቤትዎ ወስጥ ካሉ የግድ ማሰክ ማድረግ ይኖርብዎታል፡፡
3ኛ› ከቤተሰብ አባላት ጋር በሚገናኙበት ጊዜ ማስክ የሚያስወልቅ ሁኔታ አብረው እንዳይሆኑ ያስፈልጋል፡፡ ይቅርታ፣ አብረው አይበሉም ማለት ነው፡፡ በተለይ አዛውንቶችና ታማሚዎች በቤትዎ ውስጥ ካሉ፡፡
4ኛ፡ ድንግት ከታመሙ፣ ራስዎን ሙሉ በሙሉ በማግለል (Isolation) ፣ ከሌሎቹ ጋር ያለዎትን ግንኙነት ያቆማሉ፡፡ ግን የግድ የመኖሪያ ሁኔታው ለማግለል የማይመች ከሆነ፣ ከዚህ ቀድም ታማሚው ብቻ ማስክ ያድርግ ከሚለው ምክር በተጨማሪ፣ አሁን በጥናት እንዳያችሁት የቤተሰብ አባላቱም ማስክ ያድርጉ፡፡ ይህ እንግዲህ ታማሚው መቆየት የሚችልበት የተለየ ክፍል በማይኖርበት ሁኔታ ነው፡፡
5ኛ. ታማሚው ተቅማጥ ካለበት፣ ተገቢው ንፅህና በየቀኑ፣ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ በተደጋጋሚ መደረግ አለበት፡፡
6ኛ. አይውጡ፣ ከወጡ ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጉ፡፡ ይህን ቫይረስ የሚያመላልሰው ሰው ነው ያውም ምንም የበሽታ ስሜት የሌለበት፡፡ ሰለዚህ ማንንም ማመን ይከብዳል፡፡ ለብዙዎቻችሁ ይህ ነገር ከባድ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን ለኮቪድ-19 በሽተኞች በየቀኑ ርዳታ የሚሠጡ የጤና ባለሙያተኞች ቤተስብ እንደ ተለመደው የሚደረገው የቤተሰብ አኗኗር ከተቀየረ ከርሟል፡፡ አሁን ጥረቱ ሌሎች የቤተሰብ አባላቶችዎችን ማዳን ነው፡፡
በቤተሰብ በኩል የሚካሄደው ሥርጭት ከቀነስ፣ በአብዛኛው ሥርጭት የሚመጣው ከዚህ በኩል ሰለሆነ፣ የበሽታው መዛመት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል፡፡
ያም ሆኖ ቫይረሱን ወደ ቤት ይዘው እንዳይመጡ ከቤት ውጭ መደረግ የሚገባቸውን ምክሮች ተግባራዊ አድርጉ፡፡ 

ምንጭ
Wang Y, Tian H, Zhang L, et al
Reduction of secondary transmission of SARS-CoV-2 in households by face mask use, disinfection and social distancing: a cohort study in Beijing, China
BMJ Global Health 2020;5:e002794.


ድረ ገፁን የጎበኙ ሰዎች ቁጥር

 In 2020   311, 263

ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

በኮቪድ-19 የተያዘው ዶክተር ፀፀቱን ገለፀ 7/27/2020 

ባልና ሚስት ዶክተሮች፣ በሥራ ቦታቸው በኮቪድ ላለመያዝ መደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ ሲያደርጉ የከረሙ ሲሆን፣ በቤታቸውም ቢሆን ከተወሰኑ ቅርብ ጓደኞቻቸውና ቤተሰብ ጋር ብቻ ነበር የሚገኙት፡፡ ጓደኞቻቸውም ሆነ ሌሎች የቤተሰብ አባለት ሁሉም መደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ ሲያደርጉ ነው የከረሙት፡፡ ባልና ሚስቱ በሀምሌ ወር በቀጠሮ ይዘውት የነበረውን የዕረፍት ጊዜ ይሰርዛሉ፡፡ ምክንያቱም ፕሮግረሙ የነበረው ፍሎሪዳ ነው፡፡ ፍሎሪዳ ደግሞ የኮቪድ-19 ሠርግና ምላሽ ቦታ ሆኗል፡፡

ታዲያ በሚኖሩበት በአለባማ ሰቴት በሚገኝ ሀይቅ አካባቢ ከሰው ራቅ ወዳለ ቦታ መሄድ ወሰኑ፡፡ ለዕረፍት፡፡ የቅርብ ጓደኞቻቸውንና የቤተሰብ አባላትንም ይጋብዛሉ፡፡ ከነሱም ጋር የባልና ሚስቱ ወላጆችም ተጠሩ፡፡ እንደዘገባው ወላጆቻቸው በ60 አመታት ዕድሜ ክልል ውስጥ ናቸው፡፡ ሁሉም የተጋበዙት ሰዎች፣ በኮቪድ ከመጣ ጠንቃቆች ነበሩ፡፡ በሀይቁ አጠገብ ውጭ ሜዳው ላይ ነው መገናኘትና ጊዜ ማሳለፈ የፈለጉት፡፡

እንደዛም ሲሆን የሚገባውን የርቀት ጥንቃቄ አድረገው፣ ወደ ዘጠና ፐርስንት የሚሆነውን ጊዜ ውጭ ነበር ያሳፉት፡፡ አንድ ላይ የተጠጋጉበት ጊዜም አልነበረም፡፡

ነገር ግን ማሰክ አላደረጉም፡፡

እናስ?

ለመዝናናት ከተገናኙት 11 ሰዎች፣ ባልና ሚስቱን ጨምሮ፣ ስምንት ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ይረጋገጣል፡፡ ሁለት አመት የሆናት ልጃቸውም ቢሆን ባላት የበሽታው ምልክት ምክንያ በኮቪድ-19 እንደተያዘች ጥርጣሬ አላቸው፡፡

ባጭሩ ባልና ሚስቱ የሚሉት፣ ቤተሰብና ጓደኞች ጋር ስለሆን፣ ተዘናጋን እናም ማስክ አላደረግንም ነው፡፡ ባልየው፣ የደረሰባቸውን ቸግር በትዊት አካውንቱ ወዲያውኑ ለቀቀው፡፡ ሀሳቡም እኛ የደረሰብን እይደረስባችሁ ነው፡፡ ሰለዚህ ሌሎቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ለመምከር ነው፡፡

ዶክተሩ የሚለው፣ ክርስትና፣ ሠርግ፣ ቡናቤት የመሳሰሉት ቦታዎች አልሄድንም፣ እናም ገለል ያለ ቦታ ሰለተገናኘን አደጋ የሚደርስብንም አልመሰለንም፡፡ እናም ሌሎቹ ከኛ ትምህርት እንደሚያገኙ ተስፋ አለን ይላል፡፡

እንግዲህ፣ የኮቪደ-19 ዋናው መተላለፊያ በትንፋሽ መሆኑን ሁላችንም የተረዳን ይመስለኛል፡፡ ተራርቃችሁ የሚባለው መተላለፊያው በትንፋሽ ሲሆን ቫይረሱን በተሸከሙ በአይን የማይታዩ ርጥበት ጠብታዎች (ድሮፐሌት) አማካኝነት ሰለሆነ፣ እነዚህ ርጥበቶች ደግሞ በክብደታቸው ምክንያት ከስድስት ጫማ በላይ ርቀው ስለማይሄዱ ነው፡፡

የለም የለም፣ የሰሞኑን ሙግት የተከታተላችሁ ካለችሁ፣ በድሮፕሌት ብቻ ነው የሚለው ሀሳብ ግፊት እየደረሰበት ነው፡፡ ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ሳይንቲስቶች፣ ለአለም የጤና ድርጅት(የኛ ሰው አለቃ የሆነበት መሥሪያ ቤት) ደብደቤ በመፃፍ፣ ይህ ቫይረስ በድሮፕሌት ብቻ ሳይሆን በአየር ብናኝ (ኤር ቦርን) አማካኝነት ይተላለፋልና፣ ድርጅቱ ይህንን ተቀብሎ ህዝቡን ያስታውቅ ይላሉ፡፡ ዱላና ግፊት የበዛበት ድርጅቱም፣ የኤር ቦረን መተላለፉን ሀሳብ በመቀበል፣ ሊሆን ይችላል ነገር ግን የተረጋገጠ ነገር የለም በማለት መግለጫ ያወጣል፡፡

ህም፣ ኤር ቦርን ሲባል፣ ከድሮፕሌት የሚለየው፣ ቫይረሱን የያዘው ከትንፋሽ የወጣው ነገር በአየር ላይ ተንሳፎ መቆየት ብቻ ሳይሆን ከስድስት ጫማ አልፎ በርቀት ይሄዳል፡፡ በዚህ መንገድ የሚተላለፉ ምናልባትም ከምታውቋቸው በሽታዎች አንዱ፣ ስመጥሩው ሳንባ ነቀርሳ ነው( ቲቢ)፡፡

በርግጥ ኮቪድ-19 በኤርቦርን ተላልፏል የሚል ጥናት አልወጣም፡፡ ለመሟገት ከሆነ ግን፣ በኤርቦር የማይተላለፍ ቢሆን ነው የሚገርመው፡፡ ምክንያቱም፣ ከዚህ ቀደም የመጡት የሳርስ ኮሮና ቫይረስ 2 (ኮቪድ-19 የሚያመጣው) ታላላቅ ወንድሞቹ፣ ሳርስ ኮሮና ቫይረስ ቁጥር አንድና፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘው ሜርስ ኮሮና ቫይረስ በኤርቦርን ይተላለፋሉ፡፡ በተለይም በ2002-3 ታይቶ የነበረው ሳርስ ኮሮና ቁጥር አንድ፣ በሆቴሎች ጎን ለጎን ባሉ ክፍል በአየር አማካኝነት ተላልፏል፡፡ ጥናቶች የሚሉት፣ የአይነምድርና የሽንት መውረጃ ቱቦዎች ሙሉ በሙሉ ዝግ ያልነበሩ ሲሆን፣ አይነ ምድር ያለበትን ፈሳሽ ወደ አየር እንዲበተን በማድረግ ነው ይላሉ፡፡ የትንፈሹ ላይበቃ ደግሞ በዚ በኩል፡፡ ነገሩ ምንድን ነው፣ ወደ አየር ብናኝ አትቀይሩት ነው፡፡ በዚህኛው በኮቪድ-19ኝም ቢሆን፣ ከተፀዳዱ በኋላ ውሀ ከመልቀቅዎ በፊት ክዳኑን ይዝጉት የሚል ምክር አለ፡፡

በሆስፒታልም ውስጥ ቢሆን ያ ሁሉ ጥንቃቄ እየተደረገ፣ ከመቶ ሺ በላይ የጤና ባለሙያተኞች በዚህ ቫይረስ መያዛቸው፣ ከነሱም ውስጥ ከ560 በላይ ነርሶች፣ ዶክተሮችና ሌሎቸ ባለሙያተኞች ህይወት ማለፍ ከማሳዘኑም በላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነገር ነው፡፡

ዋናው ነገር፣ ከባልና ሚስት ሀኪሞች የምንማረው አንዱ ነገር መዘናጋት እንደማይስፈልግ ነው፡፡ በትንፋሽ ከሆነ የሚተላለፈው፣ ትንፋሽን መከወን ነው፡፡ ያም የትም ቦታ ቢሆን ነው፡፡ ማንም ሊታመን አይችልም፡፡ በተለይም በቫይረሱ ተይዘው የበሽታ ስሜት የሌላቸው ሰዎች ቁጥር በግልፅ እየታወቀ በመጣበት ጊዜ፡፡ ለነገሩ ከታወቀ እንኳን ቆይቷል፣ ዕድሜ ላላዋቂ ፈትፋች በይፋ ለመቀበል ተቸግረው ነበር፡፡ ባለፉት ፅሁፎች ባንዱ እንደገለጥኩት፣ ማስክ በቤትም ውስጥ ማድረግ የግድ ነው፡፡ በተለይም፣ ግድ የሌላቸው፤ የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ በማየት፣ ወጣ ገባ የሚሉ፣ በሽታው አይነካንም የሚሉ ሰዎች ባሉበት ቤት፣ መከላከል የግድ ነው፡፡ በርግጥ 80 ፐርስንቱ ከበድ ያለ ህመም የማይታይበት ቢሆንም፣ ይህ ቫይረስ ከደረስና ካገኛቸው ግን ሕይወታቸው የሚያልፉ ሰዎች እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡ ቫይሱን በግድ የለሽነት ማስተላለፍ፣ የሰው ህይወት ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚውን እንደሚጎዳ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ዋናው ተማፅኖ፣ ባካችሁ ለሌሎች ሰዎች ስትሉ ቫይረሱን ከማስተላለፍ፣ ለሌሎች ሰዎች አደጋ ከመፍጠርም ተቆጠቡ ነው፡፡ የጤና ባለሙያተኞች በዚህ መጠን መጎዳት ከቀጠሉ፣ ሌላውን በሽታ ማን እንደሚያክመው ሁላችንም መጠየቅ አለብን፡፡

እኔ እንደማየው ከሆኑ፣ በትክክለኛው መንገድ፣ ወገን ተጎዳ በማለት የሚችሉትን ሁሉ የሚያደርጉ ሰዎች እንዳሉ ግልፅ ነው፡፡ እያየንም ነው፡፡ ነገር ግን እንደዛ አይነቱ ስሜታዊ እንቅስቃሴ በፖለቲካ ላይ ብቻ ተወስኖ ሲቀር፣ የወገን ወይም የሰው ዘር መጎዳት ማለት የተለየ ትርጉም ያለ ይመስላል፡፡ ያውም እኮ ይህ ቫይረስ አሁን እያጠቃ ያለው ማንን እንደሆነ ግልፅ በሆነበት ጊዜ፡፡ ለነዚህ ሰዎች እኮ ነው ሰዎች የሚታገሉት፡፡ ነገር ግን በቫይረስ ከሆነ፣ ምንም አለመጣር ምን ይባል ይሆን፡፡ ይሄ ነገር የሰው ዘር ጠላት ነው፡፡ ሰለዚህ ጎራችሁን ለዩና ሥርጭቱን ለመቀነስ ከሚጥሩ ሰዎች ወገን ሁኑ፡፡

ዋናው ነገር፣ ተራርቀን ቁጭ ብለን እንተርፋለን የሚል ሃሳብ ካለ፣ እንገደና ተከልሶ መታየት አለበት፡፡ በትንፋሽ ነው፣ በትንፋሽ ነው፡፡ ሰለዚህ ትንፋሻችሁን ገድቡ፡፡ ከላይ የተጠቀሱት የሀኪሞቹና የቤተሰቦች በኮቪድ መያዝ የሚያሰተምረን ነገር አንዱ በግል ማስክ አለማድረግ የሚያመጣው ነገር ሲሆን፤ ሌላው ግን፣ አደጋ ያለው በቤት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ በክፍት አየር ባለበት ቦታ መሆኑ ነው፡፡ ሰለዚህ በቤት ውስጥ አብሮን ከሚኖር ሰው ውጭ ከሌሎች ጋር በምንገናኝበት ቦታ ሁሉ፣ ማስክ ማስክ ማሰክ፡፡ ማን አለበት ማን የለበትም የሚታመን ነገር አይደለም፡፡ መርሳት የሌለብን፣ ከዚህ ቀደም በጎሽ ድረ ገፅ እንተጠቀሰው፣ ቫይረሱን የያዝ ትንፋሽ በመደበኛ ንግግር እንደሚወጣ ነው፤ እንኳን ሳል፣ ንጥሻ፣ ጮክ ብሎ መናገር፣ መዘመር ተጨምሮበት፡፡

ወጣቶችም ቢሆን በኮቨድ-19 መያዛቸው ያውም በከፍተኛ ቁጥር መሆኑ ከታወቀ ቆይቷል፡፡ አዲስ ነገር የሆነው፣ በኮቪድ-19 ተይዘው ከታመሙት መሀል አስከ ሶስት ሳምንት ድረስ ወደሙሉ ጤንነት እንዳልተመለሱ በዘገባ ቀርቧል፡፡ ያም ቁጥር ወደ ሀያ ፐርስነት የሚሆኑት መሀል ነው፡፡

ከተከሰተበት ከ2019 ማለቂያ ጀምሮ፣ ይህ ቫይረስ ራሱን በመጠኑም ቢሆን እየለወጠ፣ ሁለት ነገሮችን ተክኗል፡፡ አንደኛ፣ ከሰው ወደ ሰው በመሸጋገር፣ ወደር የሌለው ችሎታ መፍጠር

ሁለተኛ፤ የሰው ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ ከመጠን በላይ የመራባት ችሎታ፡፡ ይህ ደግሞ ከዚህ በፊት ስንጠይቅ የነበረውን፣ ማለትም የቫይረሱ መጠን በሰውነት ውስጥ በጣም ከፍ ካለ የተለየ ችግር ይፈጥራል ወይ የሚለውን መልስ አግኝተናል፡፡ መረጃው የሚያሳየው የቫይረሱ መጠን በከፍተኛ ደረጃ የሆነባቸው ሰዎች በጣም ታማሚዎች መሆናቸውን ነው፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ፣ ይህ ቫይረስ ከዚህ ቀደም የመጡ ዘመዶቹ ያላሳዩትን ችሎታዎች ተክኗል፡፡ የቀረው ነገር፣ እንደነሱ ገዳይ መሆኑ ነው፡፡ ለማስታወስ ያህል ሳርስ ኮሮና ቁጥር አንድ ከያዛቸው ሰዎች አስር ፐርስንት ይገላል፡፡ መካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘው ቫይስ ደግሞ ከያዛቸው ሰዎች አስከ ሰላሳ አምስት ፐርስንት ይገላል፡፡ ፈጣሪ ይጠብቀን፡፡

በማሰክም መመለሱ እኮ ተመስገን ነው፡፡ ማሰክ ካደረገን ደግሞ ቦታና ሰው መምረጥ የለብንም፣ ካደረግንም በትክክል መሆነ አለበት፡፡ አላማው ትንፈሽ ለመገደብ ነው፡፡

አካፍሉ

ማስክ በማድረግ አፍና አፍንጫን መሸፈን ምን ያህል የኮቪደ-19 ሥርጭት ይቀንሳል?
የሚባልላቸውን ያህል ያስጥላሉ ወይ? 6/15/20 


በግልፅም ሆነ በሥውር፣ ዋናው የኮቨድ-19 ሥርጭት መከላከያው፣ ከሰው ራቁ የሚለው መልክት ነው፡፡ ከዛ በተጨማሪ፣ አፍና አፍንጫችሁን ሸፍኑ ነው፡፡ አፍና አፍንጫን ለመሸፈን የተለያዩ አይነት ማስኮች (መከለያ ወይም ጭምብሎች) አሉ፡፡ ለህብረተሰብ አገልግሎት የሚውሉት፣ በአንግሊዝኛው አጠራር (Surgical masks) የሚባሉት ሲሆን፣ ከጨርቅ የተሠሩ ማስኮችም ለአገልግሎት ይውላሉ፡፡ ለአገራችን ገበሬ ወይም የገጠሬው ሰው ደግሞ በጋቢው አፍና አፍንጫውን ከሸፈነም ይረዳል፡፡

ታዲያ እነዚህ ምክሮች እየተሠጡ፣ አዳማጭ ህዝብ ባለበት አገር፣ ግለሰቦች ሲጠቀሙባቸው አይተናል፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን፣ እንዲህ አይነት ምክር ሲሰጥና በተግባር ሲውል፣ በውል መሥራቱን፣ ከሠራም ምን ያህል ርዳታ መሥጠቱን በጥናት ማየት እንዴት ጥሩ ነገር ነው፡፡

እንደምኞታችንም፣ ይህንን በሚመለከት የወጣ ዘገባ አለ፡፡ በተደረገ ጥናት፣ መረጃው እንደሚጠቁመው፣ ፌስ ማስኮችን መጠቀም፣ በኒው ዮርክና ከተማና በኢጣልያ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በኮቢድ ከመያዝ አድኗቸዋል፡፡

ጥናቱ የተመለከተው፣ ሰዎች የፌስ ማሰክ ከመጠቀማቸው በፊት የነበረው የሥርጭት መጠን በማየትና፣ ሊከሰት የሚችለውን ቁጥር ስሌት ውስጥ በማስገባት፣ በኒው ዮርክ ከተማ በተደረገው ጥናት፣ ሰዎች ፌስ ማስክ ማድረግ ከጀመሩ በኋላ የታየውን ቁጥር በማየት፣ ከአፕሪል 17 ጀምሮ እሰከ ሜይ 9 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ስሌቱ የሚያሳያው በኒው ዮርክ ከተማ ብቻ 66 000 (66ሺ ሰዎች) ከመያዝ አምልጠዋል፡፡ ይህንን 66ሺ ሰዎች ቁጥር፣ የፊስ ማስክ በመጠቀማቸው በኮቪድ-19 ከመያዝ የተረፉትን ሰዎች፣ ተይዘው ቢሆንስ ኖሮ ብለን ብናስብ፣ በግርድፉ ምን ያህል ሰው ይሞት ነበር ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ያም እንግዲህ 66ሺ ሰዎች መልሰው የሚያራቡትን ወይም የሚያሠራጩትን ቁጥር ለጊዜው ትተን ነው፡፡ አሁን ባለው በኒው ዮርክ ስቴት ከተያዙ ሰዎች ምን ያህሉ ሞተዋል የሚለው አሃዝ በፐርሰንት ብናይ፣ 8% ነው፡፡ እናም፣ 66ሺ ሰዎች ተይዘው ቢሆን ኖሮ በአነስተኛው ግምት፣ ተጨማሪ 5280 ሰዎች ይሞቱ ነበር ማለት ነው፡፡

ሌላው ጥናቱ የተመለከተው ቦታ ደግሞ ኢጣልያ ነው፡፡ በተመሳሳይ ስሌት ያስተዋሉት ነገር፣ በህግ ሁሉም ሰው ማሰክ እንዲያደርግ በመደረጉ፣ ከአፕሪል 6 እሰከ ሜይ 9 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ78000 (78ሺ) ሰዎች በላይ በቫይረሱ ከመያዝ አምልጠዋል፡፡ እንደ ኒው ዮርኩ ሁሉ፣ ያን ያህል ሰዎች ተይዘው ቢሆን ኖሮ፣ ምን ያህል ተጨማሪ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ ለሚለው ጥያቄ፣ ሳይንሳዊ ባይሆንም፣ በቀላሉ በኢጣልያ በቫይረሱ ከተያዙት መሀከል የሞቱትን ሰዎች ፐርስንት ስናይ፣ 14.5% ነው፡፡ በርግጥ በኢጣልያ ብዙ ሰዎች እንደሞቱ ይታወቃል፡፡ በነገራችን ላይ፣ በኒው ዮርክ የተሠራጨው ቫይረስ ዝርያ፣ ከኢጣልያ እንደመጣ ነው የሚነገረው፡፡ ያውም አንድ ግለሰብ፡፡ ወደ ስሌቱ ስንመለስ፣ 78ሺ ሰዎች ተይዘው ቢሆን ኖሮ፣ ተጨማሪ 11310 ሰዎች ይሞቱ ነበር ማለት ነው፡፡

ይህንን ውጤት ከተመለከትኩ በኋላ፣ በሜሪላንድ ሰቴት፣ በዋና ጎዳናዎች ላይ የተፃፈውን ፅሁፍ አስታወስኩና እውነት ነው አልኩኝ፡፡ ፅሁፉ የሚለው “Face masks save lives” ነው፡፡

እንግዲህ መረጃ አገኘን፡፡ ማስታወስ ያለብን የኮቪድ-19 ቫይረስ መተላለፊያው ዋናው መንገድ፣ በትንፋሽ ነው፡፡ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች፣ ስሜት ይኑራቸውም ወይም አይኑራቸው በትንፋሻቸው የሚወጣው ቫይረስ የሌላ ሰው አፍ፣ አፍንጫ፣ አይን ላይ ካረፈ ነው፡፡ ለዚህ ነው ማስኮቹ ይሀን ያህል ጥሩ ውጤት ሊያሳዩ የቻሉት፡፡ መቼም በድሮፕሌትና በኤርቦርን መተላለፍ መሀከል ያለው ውዝግብ እንደቀጠለ መሆኑን ጠቆም ላደርግላችሁ እወዳለሁ፡፡ ውዝግቡ ቢቀጥልም፣ በቫይረሱ ለተያዙ ሰዎች ወይም መያዛቸውን ለማያውቁ ሰዎች፣ ትንፋሻችሁን አታጋሩ ነው መልክቱ፡፡ በማስክ ገድቡትና ሌሎችን ከመያዝ አድኑ፡፡ ሰብአዊነት ነው፡፡

ለዚህም የጤና ባለሙያተኞችና፣ የሆስፒታል ሌሎች ሠራተኘቾ፣ በሽተኞችም፣ በተለይ በሆስፒታሎችና የጤና ርዳታ መስጫ ቦታዎች፣ አፍና አፍንጫን በማሰክ እንዲሽፍኑ የሚደረገው፡፡ ችግሩ በቂ መጠን አላቸው ወይ ነው፡፡

አሁን አያየን ያለነው፣ የምን ግዴ የማስክ አጠቃቀም ጉዳት አለው፡፡ አፍን ሸፍኖ፣ አፍንጫን ክፍት ማድረግ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ ከተሸፈኑ ሁለቱንም መሆን አለበት፣ እንዲያውም እኮ አይንም ሸፍን እንዲል እንፈልጋለን፡፡ አጠገብዎ አንድ ሰው ቢያስነጥስና በአፍ የወጣው ረጨት አይን ላይ ቢያርፍ፣ ቫይረሱ መግቢያ አገኘ ማለት ነው፡፡ ሰለዚህ ሁላችንም ስንወጣ ማሰክ ብናደርግ ከዚህ አደጋ ይከላከልልናል፡፡ የአይን መነፀር ወይም መከለያ ቢያደርጉ፣ እኔ በበኩሌ የምደግፈው ነገር ነው፣ በተለይ አፍና አፍንጫውን ሳይሸፍን የሚንጎራደድ ሰው ካሉ፡፡ ከዚህ ላይ፣ ያችን የስድስት ጫማ ርቀት መጠበቁ ይረዳል፡፡

ዋናው መልክት ትንፋሻችን እንገድብ፣ ማስኩ ለታየታ አይደለም፣ መንግሥት አድርጉ ሰላለም ብቻ አይደለም ማድረግ ያለብን፡፡ እንዲዚህ አይነት መረጃ ካየን፣ ከልባችን አምነን መሆን አለበት፡፡

ዋቢ Proceedings of the National Academy of Sciences ​

የሳረስ ኮሮና ቫይረስ ቁጥር 2 (ሳኮ2) ወይም ኮቪድ-19 ሥርጭት ከሚታወቀው በላይ በአስር ዕጥፍ ይበልጣል፡ 07/23/2020
 

በየጊዜው አዳዲስ ግኝቶችን በማሳየት እንደዚህ አይነት በሽታ ታይቶም አይታወቅም፡፡ ከጥያቂዎች አንዱና ዋናው፣ በህብረተሰቡ ውስጥ በሽታው ምን ያህል ተሠራጭቷል የሚለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ የበሽታ ምልክት የሌለባቸው ሰዎች ቫይረሱን በስፋት እያሠራጩት እንደሆነ ከታወቀ ስነብቷል፡፡ አንደዛ ከሆነ ደግሞ፣ አሁን በየቀኑ የሚነገሩን አሀዞች፣ ማለትም፣ ምን ያህል ሰው በቫይረሱ እንደተያዘ የሚያሳዩት ቁጥር ትክክለኛ መጠኑን ያሳያል ወይ? ከነዚህ አሃዞች ተነስቶስ ሥርጨቱ ቀላል ነው ወይም ከባድ ነው ማለት ይቻላል ወይ ነው ጥያቄው፡፡ ይህ ቫይረስ ሰዎችን እየገደለ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ቁጥሩ በየቀኑ እየተንጠባጠበ ሰለምንሰማ ክብደቱን ልንገነዘብ የቻልን አይመስልም፡፡ በአብዛኛው ብዛት ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ ስለሚያገግሙ፣ አብዛኞች ደግሞ ምንም የበሽታ ምልክት ሳያሳዩ ሰለሚቀሩ ክብደቱን በሚገባው ደረጃ አትኩሮት መሰጠት አልተቻለም፡፡

ግልፅ እንደሆነው በዚህ ቫይረስ ተጠቂ የሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎች አሉ፡፡ እናም ይህ ቫይረስ ዞሮ ዞሮ እነዚህ ሰዎች ላይ ከደረሰ አስከፊ ውጤት ነው የሚኖረው፡፡ እኔ ራሴ ሁልጊዜም የምለው ነገር፣ ይህ ቫይረስ ዞሮ ዞሮ የሚገለው ሰው ያገኛል ነው፡፡ ስለ ሥርጭት መቀነስና ስለጥንቃቄ ስንመክር፣ ይህ ቫይረስ እነዚህ ሰዎች ላይ እንዳይደርስ ሁሉም ሰው ተገቢውን ጥንቃቄ ያድርግ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን አንድ በጣም አሳሳቢ ነገር አለ፡፡ ይህም፣ ሥርጭቱ ከሚጠቀሰው በላይ ከሆነ፣ ድንገት ይሀ ቫይረስ ባህሪውን ቀይሮ ከፍ ባለ ደረጃ የሰው ሕይወተ የሚቀጥፍ ከሆነ ወይም ቢሆን የሚደርሰውን አደጋ መገመት ይቻላል፡፡ በዚህ ሥርጭት ከቀጠለ ደግሞ ወደዛ ላለመቀየሩ ዋስትና የለም፡፡

ለማንኛውም፣ በቅርቡ JAMA በተባለ መፅሔት የወጣ ጥናት ላካፍላችሁ፡፡ የጥናቱ አላማ፣ በአሜሪካ በአንዳንድ አካባቢዎች ምን ያህል ሰው የሳርስ ኮሮና ቫይረስ አንቲቦዲ እንዳለው ለማወቅ ነው፡፡ ለሳኮ 2 አንቲቦዲ ያላቸው ሰዎች ደግሞ፣ ቀድም ብሎ የበሽታ ምልክት ወይም ስሜት ኖራቸው ወይም አልኖራቸውም ለቫይረሱ ተጋልጠው እንደነበር መረጃ ነው፡፡

የኮቪድ-19 ምርምራ ሁለት አይነት አቀራረብ ነው ያለው፡፡ የመጀመሪያው፣ ቫይረሱን በቀጥታ ከሰውነት ክፍል ከሚገኝ ናሙና መገኘቱን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ ምርመራ በአፍንጫ በኩል በሚላክ ቀጠን ባለ ብሩሽ አማካኝነት ከተገኘው ፈሳሽ ቫይረሱ መኖሩን ለማወቅ RT- PCR (Reverese Trancriptase polymerase chain reaction) የተባለ ምርመራ በመጠቀም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት፣ ሰዎች በኮቨድ-19 ለመያዛቸው፣ ወይም ከተያዙና ከተረጋገጠ በሁዋላ፣ ከቫይረሱ ነፃ መሆኖቸው የሚታወቅበት መንገድ ነው፡፡

ሁለተኛው የምርመራ ዘዴ ደግሞ፣ በቫይረሱ ተይዘው የነበሩ ሰዎች ሰውነት የሚሠጠውን ምላሽ በመመርኮዝ የሚሠራ ነው፡፡ ምርመራውም፣ በቫይረሱ ተይዘው የነበሩ ሰዎች፣ ቫይረሱን ለማጥቃት ሰውነት የሚፈጥራቸውን የእንቲቦዲ አይነቶች መኖራቸውን ማወቅ ወይም መለካት ነው፡፡ የዚህ አይነቱ ምርመራ፣ በዚህ ወቅት፣ ያለው ጠቀሜታ በአንድ ህብረተሰብ ወይም አካባቢ ምን ያህል ሰዎች ተጋልጠው እንደነበር ለማወቅ የሚደረግ ዘዴ ነው፡፡ ከዛ ውጭ፣ አንድ ሰው፣ ሰለተጋለጠ ወይም አንቲቦዲም ሰላለው፣ አንደገና ላለመያዝ የሚችልበት ሁኔታ ውስጥ ነው ብሎ ለለመስከር ይህ አይነቱ ምርመራ የሚሠጠው ድጋፍ የለም፡፡ ብዙ የጤና ተቋማት፣ ይህንን ምርመራ፣ ሰዎች ከቫይረስ ነፃ ናቸው ወይም ታመዋል፣ አለዚያም አልታመሙም የሚል ውሳኔ ለመድረስ እንዳይጠቀሙበት ይመክራሉ፡፡

ወደ ጥናቱ ዘገባ ስንመለስ፣ በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች፣ ከማርች 23 አስክ ሜይ 12፣ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ ከተለያዩ ሰዎች የተሰበሰበን የደም ናሙና ለአንቲቦዲ ምርመራ ይደረጋል፡፡ ከተሞቹ፣ በዝርዘር ወደ አስር የሚኑ ሲሆን፣ ከሳንፍራንሲስኮ ጀምሮ፣ ካሊፎረንያ፣ ከነቲከት፣ ደቡብ ፍሎሪዳ፣ ሉዊዚያና፣ ሚኒያፖሊስና ሴንት ፖል፣ ሚኒሶታ፣ ሚዙሪ፣ ኒው ዮርክ፣ ፊላደልፊያ፣ ፔንስልቪኒያ፣ ዩታህ፣ እና የዋሽንግተን ሰቴት ምዕራባዊ ክፍልን ይጨምራል፡፡

ለምርምራ ደም የተወሰደው በአጠቃላይ ከ16025 ሰዎች ሲሆን፣ ከነዚህ መሀል 55.2 ፐርስንቶ ሴቶች ናቸው፡፡ በዕድሜ ሲታይ ደግሞ ዕድሜያቸው 18አመትና ከዛ በታች የሆኑት በፐርስንት 7.5 ነበሩ፡፡ ከ65 አመት በላይ የሆኑ ሰዎች ደግሞ 36.5 ፐርሰንት ነበሩ፡፡ ብዙ ሰዎች ለቫይረሱ አንቲቦዲ አልነበራቸውም፡፡ በተደረገው ምርመራ ለሳኮ2 ቫይረስ አንቲ ቦዲ የነበራቸው ሰዎች ቁጥር እንደቦታው የተለያየ ነበር፡፡ ያም በሳንፍራንሲሰኮ ቤይ አካባቢ አንቲቦዲ የነበራቸው ወይም የተገኘባቸው ሰዎች መጠን 1% ሲሆነ፣ በኒውዮርክ ከተማ ከተማ ደግሞ ምርመራ ከተደረገላቸው ሰዎች ወደ 6.9% የሚሆኑት እንቲቦዲ እንደተገኘባቸው ያሳያል፡፡ የዚህ ጥናት ውጤት የሚያሳያው፣ በዚህ በተደረገው ምርመራ አማካኝነት በኮቪድ-19 ተይዘዋል ተብሎ በይፋ ከሚታወቀው ቁጥር በላይ ብዛት ያላቸው ሰዎች ለቫይረሱ ተጋልጠው እንደነበር ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ በበሽታው ተይዘዋል ተብሎ በይፋ ከተጠቀሰው  ቁጥር በላይ ከስድስት አስከ 24 ዕጥፍ የሚሆኑ በሪፖርቱ ያልተዘገቡ ሰዎች ለቫይረሱ ተጋልጠው እንደነበር ነው፡፡ በተለይም በሰባት አካባቢዎች፣ ማለትም (በከነቲከት፣ ኒውዮርክ፣ ፍሎሪዳ፣ ሉዊዚያና፣ ሚዙሪ፣ ዩታህና የዋሽንግተን ሰቴት ምዕራብ ክፍል)፣ በቫይረሱ ተይዘዋል ተብሎ ከተቀሰው ቁጥር አስር ዕጥፍ የሚሆኑ ሰዎች፣ ለቫይረሱ ተጋልጠው አንደነበር ያሳያል፡፡

እንግዲህ ይህ የሚያስረዳን ነገር ቢኖር፣ የቫይረሱ ሥርጭት መጠን ከሚጠቀሰው ሪፖርት በላይ መሆኑንና፣ ብዛት ያላቸው ሰዎች፣ በቫይረሱ ተይዘው፣ ወይም የበሽታ ስሜት አልነበራቸውም፣ ቢኖራቸውም መጠነኛ ሰለሆነ ወደ ህክምናና ወደ ምርመራ ሳይሄዱ በመቀየታቸው በሪፖርቱ ውስጥ አለመካተታቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን እነዚህ ሰዎች ደግሞ ለቫይረሱ ሥርጭት ምክንያት መሆናቸውን መገንዘብ ያሰፈልጋል፡፡ ባጠቃላይ ሲታይ የዚህ ቫይረስ ሥርጭት በሪፖርት ከሚታወቀው በብዙ ዕጥፍ በበለጠ በአካባቢው ወይም በህብረተሰቡ ውስጥ እንደሚገኝ መረዳት ያሰፈልጋል፡፡ ታዲያ ይህን መጠኑ በልክ ያልታወቀ ሥርጭትን ለመቀነስ፣ ብሎም ደግሞ በሽታው ሊጠናባቸው ወይም የህይወት ህልፈት ምክንያት ሊሆንባቸው ወደሚችል ሰዎች እንዳይደረስ ሁሉም ሰው የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ የአፍን የአፍ መሸፈኛ ማድረግ ሥርጭቱን ለመቀነስ ከሚረዱ ሥራዎች አንዱ መሆኑን በማወቅ ሁሉም ሰው ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ብዛት ያላቸው ስቴቶች፣ የዚህ ጠቀሜታ እየቆየ ነው የገባቸው፡፡ ዘግይተውም ቢሆን ማስክ ወይም መሸፈኛ እንዲደረግ እይመከሩ ነው፡፡፡ ሁለተኛው መንገድ ደግሞ፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚያገናኝ ማንኛውም ነገር  በጥንቃቄ እንዲሆን፣ ያ ከመሆኑ በፊት ግን በጣም አሰፈላጊ ካልሆነ በቀር፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚያገናኙ ስብስቦችን አለማድረግ ይመከራል፡፡ የእንድ ቤተሰብ አባል ካልሆኑ በስተቀር፣ ይህ ነገር አልፎ እስከሚሄድ ድረስ በቤት መቆየት ከፈተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ በዚህ ደግሞ በበሽታው ምክንያት ከፍተኛ ጥቃት ሊደርስባቸው የሚችሉ በእድሜ የገፉ (ከ65 አመት በላይ) ወይም ሌሎች ተደራቢ በሸታዎች ያሉባቸው ሰዎች ከሌለች በበለጠ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ቢጠነቀቁም አብረዋቸው የሚኖሩ፣ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ህመም ላይ አንወድቅም ብለው የሚያስቡ ሰዎችም የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ሲባል በተመሳሳይ ሁኔታ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ለሌሎች ሰዎች ሲባል መደረግ የሚገባውን ነገር ማድረግ ሰብአዊነት ነው፡፡ በቅርቡ እንደታያው፣ በቤቶች ወይም በክፍሎች ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም አይነት ስብስብ እንዲቆም እየተመከረ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ከመዝናኛ ቤቶች ጀምሮ እስከ አምልኮ ወይመ ፀሎት ቤቶች ድረስ ነው፡፡ በት/ቤቶች ይከፈቱ አይከፈቱ የሚለውን ሙግት መከታተልና ምክንያቱን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ በት/ቤት ከመጣ ትልቁ ፍራቻ፣ መምህራኑ ሊያዙ ይችላሉ፣ በተጨማሪም ተማሪዎች ቫይረሱን ይዘው ወደየቤታቸው ይወስዳሉ ነው፡፡ ከታማሚው በላይ ቫይረስ አመላላሹ ላይ ትኩረት መሠጠት አለበት፡፡ ሰለዚህ ከዚህ ጥናት መረዳት የምንችለው በየአካባቢያችን ያለው የቫይረሱ ሥርጭት በይፋ ከተነገረው ቁጠር በላይ እንደሚሆን ነው፡፡

ማስክ ለምኔ

 የኮቪድን ሥርጭት ለማቀዝቀዝ አይነተኛ ከሆኑ መንገዶች አንደኛው፣ አፍና አፍንጫን መሸፈን ነው፡፡ ይህ ለምን እንደሚጠቀም ወይም ለምን እንዳሰፈለገ ሰዎች በትክክል መገንዘብ አለባቸው፡፡

1ኛ. ቫይረሱ ለመሠራጨት አንዱ ትልቁ ምክንያት በቫይረሱ ተይዘው የበሽታ ስሜት የሌለባቸው ሰዎች መኖራቸው ነው፡፡ ይህ ቁጥር አሰቃቂ በሆነ ደረጃ አስከ ስልሳ ፐርሰንት ድረስ ሊወጣ ይችላል፡፡ ጉዳዩ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አያውቁም፡፡ ሰለዚህ ከሰው ጋር መቀላቀልና ቫይረሱን የማሰተላለፍ አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ከነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ የበሽታ ስሜት ይጀምራቸዋል፤ ግን ቫይረሱ መተላለፍ ከጀመረ ቆይቷል፡፡

2ኛ. ይህ ቫይረስ በትንፋሽ አማካኝነት እንደሚተላለፍ ይታወቃል፡፡ ዋናው መተላለፊያ መንገድም ይኸው ነው፡፡ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ሲየስሉ ወይም ሲያነስጥሱ፣ በመተንፈሻ አካላቸው ውስጥ የተሰገሰገውን ቫይረስ ወደ አየር ይበትኑታል፡፡ በተለይም እርጥበት አዘል በሆኑት በ5 ማይክሮን መጠን በሚሆኑት ጠብታዎች ውስጥ የቫይረሱ መጠን በጣም ከፍተኛ በሆነ ደረጃ ነው የሚገኘው፡፡ ለምሳሌ በአንድ ጠብታ (ድሮፕሌት) ከ700ሺ በላይ የቫይስ ኮፒዎች ወይም ከዛ በላይ እንደሚገኙ የታወቃል፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ ይህን ያህል ቫይረስ የተሸከመው ድሮፕሌት የሌላ ሰው፣ አፍ፣ አፍንጫና አይን ላይ ሲያርፍ በቀላሉ ዘልቆ በመግባት (ኢንፌክሽን) የሚፈጥረው፡፡ በክብደታቸው ምክንያት በአብዛኛው ከስድስት ጫማዎቸ ወይም ሁለት ሜትር በላይ ርቀው የማይሄዱት እነዚህ ለአይን የተሠወሩ ጠብታዎች (ድሮፕሌት) በአስቀያሚው ክልላቸው ውስጥ ያልጠረጠረ ሰው ከተገኘ፣ ተያዘ ማለት ነው፡፡ ራቅ በሉ የሚለው መልክትም የመነጨው ከዚህ ነው፡፡

ችግሩ፣ ማስነጠስም ማሳልም ሳይኖር በተራ ንግግር፣ እነዚህ ቫይረሱን የተሸከሙ ጠብታዎችን ማመንጨት እንደሚቻል ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ታዲያ በቫይረሱ መያዙን ያላወቀ ሰው አጠገቡ ሆነው የቤተ ዘመድም ይሁን የጓደኛ ወሬ እያወራ ቫይረሱን ወደስዎ እያቀበለዎ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡
ለዚህ ነው፣ ሁሉም ሰው ማስክ ያድርግ የሚለው ወሳኝ ምክር የመጣው፡፡
አፍና አፍንጫውን ሳይሸፍን የሚጠጋዎት ሰው ካለ፣ ወይም መልክቱ አልገባውም፣ ወይም አልደረሰውም፣ አለዚያ ግን የወዳጅነት መቀራረብ ለመሆኑ ጥያቄ መነሳት አለበት፡፡
ዋናው መንገድ፣ ሁሉም ሰው በቫይረሱ እንደተያዘ አይነት በማሰብ፣ ለሌላ ሰው ላለማስተላለፍ በማለት በሰብአዊነት ስሜት አፍና አፍንጫን መሸፈን የዘመናዊነት አስተሳሰብ ምልክት ነው፡፡ ከታናሽ ወንድሜ ጋራ በዚህ ጉዳይ ስንወያይ አንድ የነገረኝ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ወደ ሆነ መስሪያ ቤት ለመግባት አንድ ላይ የመጡ ሁለት ወንዶች፣ አንደኛው ማስክ ያለው ሲሆን፣ ማስከ የሌለው ባለጉዳይ ሰለነበር፣ ወደ መስሪያ ቤቱ መግባት ነበረበት፡፡ አብሮት የመጣው ሰው በለጋስነት አፉ ላይ የነበረውን ማስከ አውልቆ፣ ይህንን አድርገህ ግባ ብሎ ሲያውሰው እንደተመለከተ በመገረም ነገረኝ፡፡ ፍቅር እስከ መቃብር ይሏል ይች ነች፡፡
የከተማው ሰው ማሰክ ለማድረግ ይተራመስ እንጂ፣ የገጠሩ ያገሬ ሰው፣ አፍና አፍንጫውን በጋቢ ከሸፈነ ይበቃዋል፡፡ ለዛም ሁለት ሜትር በላይ ርዝመት ያለውን ዱላውን ወይ በትሩን ይዞ የሚጠጋውን ሰው እየመተረ ራቅ ካለ፣ ከመያዝ ያመልጣል፡፡ ይህ ደግሞ ለገጠሬው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ሰለዚህ የገጠር ዘመዶቻችን ማስክ ከማደል ድነናል ማለት ነው፡፡ በፎቶው እንዳያችሁት፣ አፍና አፍንጫቸውን ሸፈን እንዲያደርጉ መምከር ተገቢ ነው፡፡
ተራው ማስክ የበለጠ አገልግሎት ያለው በቫይረሱ ከተያዘ ሰው የሚወጣውን ቫይረስ ገድቦ ለማስቀረት ሰለሆነ፣ በእንግሊዝኛው አጠራር Universal masking የሚለው ምክር ወሳኝ ነው፡፡

ችግሩ፣ በኮቪድ-19 ከተያዙ ሰዎች ጋር የሚሠሩት የጤና ባለሙያተኞች ላይ ነው፡፡ እያቃሰተና እያሳለ ከሚወራጭ በሽተኛ አጠገብ ሆነው ርዳታ ለመስጠት የሚታገሉት የጤና ባለሙያተኞች፣ እንደ አውነቱ ከሆነ በቂ መከላከያ ካላደረጉ፣ በቫይረሱ ለመያዝ፣ ባሉበት ከበሽተኛው ጋራ ባላቸው ቅርበት፣ ሁለት ደቂቃ ይበቃል፡፡

ልብ በሉ፤ አንድ የጤና ባለሙያተኛ፣ ነርስ ወይም ሀኪም ከተጋለጠ፣ መጋለጡም ከታወቀ፣ ለአስራ አራት ቀናት ከሥራ ይገለላል፡፡ እንደዚህ የተጋለጡ ሰዎች ደግሞ በብዛት የሚወጡ ከሆነ፣ የሠራተኛ ዕጥረት መፈጠሩ ግልፅ ነው፡፡ በርግጥ ይህን የሠራተኛ ዕጥረት በማየት የተጋለጡ ወይም በቫይረሱ የተያዙ ባለሙያተኞች በሰባት ቀን ወደ ሥራ እንዲመለሱ የሚለው ህግ ተሸሮ ወደ አስር ቀን ተራዝሟል (በአሜሪካ)፡፡ እሱም ቢሆን፣ የቀሩትን አራት ቀናት በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲሠሩ ተደርጎ ነው፡፡ ሰለዚህ ጤናማው መንገድ አስራ አራት ቀናት ከሥራ መገለል ነው፡፡ እንግዲህ የተጋለጡትንም የተያዙትንም በቀላሉ ምህረቱን ይላክላቸው ካልን በኋላ ግን፣ መልሰን ብናስበው፣ በነዚህ ባለሙያተኞች የሥራ ቦታቸው አለመገኘት፣ አይደለም በኮቪድ-19 የተያዘውን ህሙም ቀርቶ፣ ሌላውን ህሙም መርዳት የሚችል ሰው ላይኖር ነው፡፡ ፍራቻው፣ በኮቪድ ከተያዙት በላይ፣ በቂ ርዳታ ማግኘት ሳይችሉ በሌላ ህመም የሚሰቃዩ ሰዎች የሞት ቁጥር ሊጨምር ይችላል ነው፡፡

ለነዚህ ባለሙያተኞች፣ ከሌላው አብሮ ከሚለበሰው መከላከያ ልብስ በተጨማሪ፣ ተራ ማስክ ሳይሆን፣ N95 የተባለ፣ ኮሮና ቫይረስ ሾልኮ ሊሄድበት የማይችል ማስክ መጠቀም የግድ ነው፡፡ ካልሆነ ግን ባለሙያተኞቹ አደጋ ላይ ናቸው፡፡ በቅርቡ በሚያሰቅቅ ሁኔታ፣ ከኢትዮጵያ፣ በጎንደር ሆስፒታል፣ በኮቪድ መያዙ ከተረጋገጠ ሰው ጋር በመጋለጣቸው ከመቶ በላይ የሚሆኑ ሠራተኞች ከሥራ መገለላቸውን ሰማን፡፡ ባለሙያተኞቹ አስፈላጊው ማስክ ቢኖራቸው ኖሮ ያን ያህል ሰው ሆስፒታልን ከመሰለ የሥራ ቦታ አየገለልም ነበር፡፡ ያወቅነውና ያረጋገጥነው ነገር፣ በቂ ማስከ አለመኖሩን ነው፡፡ አሜሪካን በመሰለ አገር ከስለሳ ሰባት ሺ በላይ የጤና ባለሙያተኛ በቫይረሱ መያዙ በተረጋገጠበት አገር፣ ሶስት መቶ ሀያሶስት ነርስና ዶክተር ህይወታቸው አልፏል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ትችላለች ወይ?

የማስክ ዕጥረት በግልፅ ትልቅ አደጋ ነው፡፡ አደጋው ደግሞ ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚሆንም አይደለም፡፡ ቆም በሉና አስቡ፣ ምን ማድረግ ይችላሉ፡፡ አንዱ ቀለል ያለው ነገር ቢኖር፣ የሚቻልዎትን በመለገስ፣ ማስክ ተገዝቶ በቀጥታ ለጤና ባለሙያተኞች አንዲደርስ ማድረግ ነው፡፡ የጎንደር ሆሰፒታል፣ የኮቪድ ሆሰፒታል ተብሎ መወሰኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለሱዳን አዋሳኝ ከሆነው ከመተማ በቫይረሱ ለተያዙ ሰዎችም ርዳታ እንዲሠጥ በመደረጉ፣ በተአምር ካልሆነ በስተቀር ከፍተኛ አደጋ ላይ ናቸው፡፡ 

ግድ የለም ይነጋል የሚደረገውን አንድ ላይ እናድርግ

በኮቪድ-19 የሞቱት ሰዎች እነማን ናቸው? 7/11/2020

 በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው፣ በአሜሪካ በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱ ሰዎች እነማን አንደሆኑ የሚገልፅ ዝርዝር መረጃ ወጣ፡፡ ይህ ዝርዝር አስፈላጊ የሆነውም፣ እንደሚነገረው፣ በኮቪድ-19 ምክንያት ማይኖሪቲ የሚባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ከድርሻቸው በላይ በኮቪድ መያዝ ብቻ ሳይሆን በኮቢድ ምክንያትም እንደሚሞቱ ሲነገር ሰለከረመ ነው፡፡

የአሜሪካው የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ባውጣው ሪፖረት፣ ከጃንዋሪ 1፣ 2020 እስከ ሜይ 18፣ 2020 በነበረው ጊዜ ውስጥ 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በኮቪድ 19 መያዛቸው ይታወቃል፡፡ ያ ቁጥር አሁን ከ 3.1 በላይ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የሟቾች ቁጥር 83ሺ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ከ134 ሺ በላይ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ወደ ሲዲሲ ከሚላከው ሪፖርት፣ ከ50ዎች ስቴቶችና ዲስትሪክት ኦፍ ኮሎምቢያን (ዲሲ) ጨምሮ 52166 በኮቪድ-19 መያዛቸው በላቦራቶሪ የተረጋገጠና ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች መረጃ የተጠናከረውን ዝርዝር ነው ያቀረቡልን፡፡ የነዚህ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች የተሰበሰበው ከየካቲት 12 አስከ ግንቦት 18 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

ከነዚህ 52 166 ሰዎች መሀከል

55.4% ወንዶች
79.6% ዕድሜያቸው ከ65 አመት ወይም ከዛ በላይ የሆኑ ነበሩ
በዘር ሲታይ ደግሞ
13.8% ሂስፓኒክ
21.0% ጥቁሮች
40.3% ነጮች
3.9% ኤስያኖች ነበሩ 

በተጨማሪም፣ ከዘር ውጭ ተደራቢ በሽታ ያለበቸው ሰዎችን ለማወቅ ተጨማሪ መረጃ ከተገኘባቸው ሰዎች፣ ቁጥራቸው እድሜያቸው ከ65 አመት በታች የሆነ 8134 ሰዎች ተጨማሪው መረጃ በሚያሳየው መሠረት ቢያንስ ቢያንስ አንድ ተደራቢ በሽታ ነበረባቸው፡፡ ተደራቢ በሽታ ወይም የቆየ በሽታ ሲታይ፣

በብዛት የታየው የልብና የደም ዝውውር በሽታ በ60.9%
የስኳር በሽታ 39.5%
የቆየ የኩላሊት በሽታ 20.8%
የቆየ የሳምባ በሽታ 19.2%

 ዕድሜያቸው ከ65 አመታት በላይ ከሆነ የሞቱት ሰዎች መሀከል፣ 69.5% የሚሆኑት አንድ ወይም ከዛ በላይ የቆየ ወይም ተደራቢ በሽታ ነበረባቸው፡፡ በዕድሜ ተከፋፍሎ ሲታይ ዕድሜያቸው ከ65 አመት በታች በሆኑ ሰዎች በብዛት የታየው ተደራቢ በሽታ የስኳር በሽታ በ49.6% ነበር፣ ዕድሜያቸው 85 አመትና ከዛ በላይ በሆኑት ሰዎች፣ የስኳር በሽታ የነበረባቸው 25.9% ነበር፡፡

ሪፖረቱን በዝርዝር ስንመለከት፣ ተጨማሪ መረጃ ከተሰበሰበላቸው 8976 ሟቾች መሀከል፣ 84.3% ሆስፒታል ገብተው ነበር፡፡ እንግዲህ ሆስፒታል ሳይደርሱ የሞቱም አሉ፡፡ በተጨማሪም ሆስፒታል ሳይደረስ በነረሲንግ ሆም ወስጥ እያሉ የሞቱም ይገኙበታል፡፡ ድንገተኛ ክፍል አያሉ ወደ ውስጥ ወደ ሆሰፒታል ሳይቡም የሞቱም አሉ፡፡ ህመም ከተሰማቸው ጀምሮ ሕይወታቸው እሰካለፈበት ድረስ በአማካይ አስር ቀናት ነው የወሰደው፡፡ ይህ እንግዲህ ሕመም የጀመረበት ቀን መረጃ በተሰበሰበ ሟቾች ቁጥር ውስጥ ነው፡፡

ሆሰፒታል ገብተው ከሞቱት መሀል፣ በአብዛኛው በአምስት ቀናት ውስጥ ነው የሞቱት፡፡ ባጠቃላይ ሲታይ፣ ዕድሜያቸው ከሟቾቹ መሀከል 75% የሚሆኑት ወይም አንድ ወይም ከዛ በላይ ተደራቢ በሽታ አለባቸው አለዚያም ዕድሜያቸው ከ65 አመታት በላይ ነበር፡፡ አነዚህ የህብረተሰቡ ክፍሎች ናቸው እንግዲህ በቫይሱ እንዳይያዙ ከፍተኛ ጥረት የሚደረገው፡፡ ለዚህም ነው እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ከራስ በላይ በማሰብ በቫይረሱ ላለመያዝ ጥረት ማድረግ ያለበት፡፡ ከምንም ጊዜ በላይ ለሌላ የቤተሰብ አባል፣ ጓደኛ፣ ቤተዘመድ ወይም የሥራ ጓደኛ ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ ለቫይረሱ መጋለጥ የሚየበቁ ቦታዎችን ለይቶ ማወቅ፤ በቤት ውስጥ ማን እንደሚኖር ቫይረሱ ቢይዛቸው ከፍተኛ አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችሉ ይሆን ብሎ መጠየቀት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን፣ ይህ ቫይረስ ባህሪውን እየቀየረ የወጣቶችንም ዕድሜ እየቀጠፈ መሆኑን ማወቅም ተገቢ ነው፡፡ ዋናው፣ በምንኖርበት አካባቢ፣ ወይም የህብረተሰብ ክፍል የቫይረሱ ሥርጭት ምን ያህል መሆኑን ለይቶ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን፣ በቫይረሱ ተይዘው፣ ግን የበሽታ ስሜት ወይም ምለክት የሌለባቸው ሰዎች ቫይረሱን እያስተላለፉ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ ደግሞ እንደ ሲዲሲ ሪፖርት አርባ ፐርስንት ይሆናሉ፡፡ ቫይረሱን አደገኛ ካደረጉት ነገሮች አንዱ ይህ ነው፡፡

የመረጃ ምንጭ MMWR / July 10, 2020 / Vol.69

Copyright 2013. Gosh Health. 

All Rights Reserved.