በእርግጥም ለወሊድ መቆጣጠሪያ የሚሆን ክትባት አለ

በወሬ በወሬ እየሰማን ጉዳዩን ብዙም ትኩረት አልሠጠነውም ነበር፡፡ የሚያመክን ክትባት አለ ሲባል፣ የመጀመሪያው ጥያቄ ውነት ነው ወይ የሚለው ነው፡፡ ከጓደኛዬ ጋራ ሀሳብ ስንለዋወጥ፣ ክትባቱ በስህተት ማምከን የሚችል መድሐኒት ጋር ተነካክቶ ይሆናል ወይም እንደዚያ የሚባል ነገር ሰምቻለሁ ነው፡፡ ነገሩ ትንሽ የሚከነክን ስለሆን በወሬ በወሬ ሳይሆን በሳይንሳዊ መንገድ የተሠሩ ጥናቶችን ለእንባቢ የሚያቀርቡ የህክምና ወይም የጤና መፅሔቶችን  ማገላበጥ ጀመርኩ፡፡ እና እራሴንም አስከሚገርመኝ ድረስ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ፅሑፍ አገኘሁ፡፡ ለካስ አዳማጭና አንባቢ ጠፍቶ ነው እንጂ ለወሊድ መከላከያ የሚሆነው ክትባት ከተሠራ ስንብቷል፡፡

በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1993 የታተመው አናልስ ኦፍ ኢንተርናል ሜዲሲን የሚባል መፅሔት ላይ በቁጥር Ann Med. 1993 Apr;25(2):207-12 ላይ የወጣ መረጃ በዚያን ጊዜ በህንድ አገር ለዚሁ ወሊድ ለመከላከል ታስቦ የተሠራ ክትባት እንዳለ ይገልፃል፡፡

ክትባቱ እንደተባለው ለቴታነስ ወይም ዲፍቴሪያ በሽታ መከላከያ በሚሠጠው ክትባት ላይ ተደርቦ የተሠራ ነው፡፡ በውስጡም HCG የተባለው ሆርሞን ክፍሎች ያሉበት ሆኖ፣ አላማው ክትባቱ በሚሠጥበት ጊዜ፣ የሰውነት ክፍላችን ለዚሁ HCG አጥቂ የሆነ አንቲ ቦዲ እንዲፈጥር ነው፡፡ እንግዲህ HCG (Human Chorionic Gonadotriphin) ለእርግዝና ከሚያሰፈልጉ ሆርሞኖች በጣም ወሳኝ የሆነ ነው፡፡ በክትባቱ ምክንያት የራስ ሰውነት ይህንን ሆርሞን ማጥቃት ሲጀመር እርግዝና እንዳይፈጠር ያደርጋል ማለት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ይህ ሁኔታ በጥናት ላይ እንደነበረና ደረጃ ወይም ክፍል ሁለት የሚባለውን የጥናት ክፍል እንዳለፈ ነው የጥናቱ ፀሐፊዎች ያሰፈሩት፡፡ በዚህ መሠረት ሴቶች ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ ማርገዝ አለመቻላቸው እንደጥሩ ውጤት ሆኖ ተዘግቧል፡፡ የኔም የግሌ ጥያቄ የነበረው፣ ይህ ነገር ቋሚ መካንነት ያስከትላል ወይ ነው፡፡ እንደ ጥናቱ ዘጋቢዎች፣ ይህ ሁኔታ ሊሚለስ ይችላል ነበር፡፡ ያ እንግዲህ በዚያን ጊዜ ነው፡፡

ዋናው ጥያቄ ክትባቱ ሲሰራና ተያይዞም አላማው ግልፅ በሆነ መንገድ እርግዝና መከላከያ ሆኖ ሲሆን፣ ክትባቱ የሚሠጣቸው ሰዎች የክትባቱ አላማ ተነግሯቸዋል ወይ ወይም አስቀድሞ ተገልፆላቸዋል ወይ ነው፡፡ እየተነገራቸው የተከተቡ ሰዎች ካሉ ምንም የሚያከራክር ነገር አይሆንም፡፡ ነገር ግን በሽፍን ሳይገለፅላቸው ክትባቱ እየተሠጠ ከሆነ ሌላ ጥያቄ ነው፡፡

በዚህ መፅሔት ዘገባ መሠረት ለወሊድ መቆጣጠሪያ ታስቦ የሚሠራ ክትባት መኖሩና ይህም ክትባት ለቴታነስና ለዲፍቴሪያ በሽታ መከላከያ በሚሰጠው ክትባት ላይ ተደርቦ እንደሚሠጥ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይሀ የፀረ ክትባት አቋም ያላቸው ሰዎች የሚያናፍሱትም ወሬ አይደለም፡፡ በመሠረቱ እኔ ራሴም የፀረ ክትባት አቋም የለኝም፡፡ ነገር ግን እንደህክምና ባለሙያ ለሰዎች የሚሠጥ ማንኛውም ነገር ለተቀባዮቹ መነገር አለበት የሚል ቀን ከቀን ከምሠራው ሙያ ጋራ የተያያዘ የሙያ ግብረገብ ስላለኝ ነው፡፡ እንደገናም ጥያቄው፣ ክትባቱ መኖሩና አለመኖሩ ሳይሆን፣ የሚሰጣቸው ወጣት ሴቶች ወይም ሴቶች ተነግሯቸዋል ወይ? ነው፡፡