አለም አቀፍ የዲያቤትስ ቀን November 14

አሳሳቢ የሆነው የዲያቤትስ ወይም የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ፣ ስኳር በሽታ ትንሽም ቢሆን ኑሮ በደላቸው ሰዎች ላይ ነበር የሚታየው፡፡ አሁን ግን ሳይለይ ሁሉም ላይ እየታየ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአለም ወደ ግማሽ ቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የስኳር በሽታ አለባቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ እንግዲህ 80 በመቶ የሚሆኑት የሚኖሩት ዝቅተኛና መጠነኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች ነው፡፡ ከተላላፊ በሽታዎች ውጭ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለው ይህ በሽታ የግድ ትኩረት ማግኝት አለበት፡፡

እንደሚታወቀው የስኳር በሽታ ሁለት አይነት ሲሆን፣ አይነት አንድና አይነት ሁለት ተብሎ ይጠራል፡፡ Type 1 ወይም አይነት አንድን ለማስቀረት ምንም የሚደረግ ነገር የለም፡፡ ሆኖም በተቃራኒው ግን Type 2 ወይም አይነት ሁለት የሚባለውን ግን መከላከል የሚያስችሉ መደረግ የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለአብዛኛው የስኳር በሽታ አይነት ደግሞ ይኸው Type 2 የሚባለው ነው፡፡

ስለ Type 2 የስኳር በሽታ ምንነት ትንሽ መግለጫ መስጠትም አስፈላጊ ነው፡፡ መተኮር የሚገባው ደግሞ እንዴት አድርጎ መከላከል እንደሚቻል ማስገንዘቡን ነው፡፡

የስኳር በሽታ የሚከሰተው በደም ውስጥ ከመጠን በላይ ስኳር ሲዘዋወር ነው፡፡ ይህም የሚሆነው፣ ስኳርን ከደም ዝውውር ወደየሴሎች አንዲገባ የሚያደርገው ከፓንክሪያስ ወይም ቆሽት (Pancrease) የሚመረት ኢንሱሊን የተባለ ሆርሞን በበቂ መጠን አለመመንጨት ወይም ሙሉ በሙሉ መሥራት ሳይችል ሲቀር ነው፡፡ ለሰውነታችን ሴሎች ስኳር (glucosee ) የሀይል ምንጭ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ሴሎቹ ሳይገባ ሲቀር በደም ዝውውር ውስጥ ከሚገባው በላይ ሲከማች ነው በሽታው የሚከሰተው፡፡ ለስኳር በሽታ ከዚህ ውጭ ሌላ ሚስጥር የለውም፡፡ ቸግሩ እንግዲህ ይህ ከመጠን በላይ የተከማቸው ስኳር ከጊዜ ብዛት በተለይም ክትትል ካልተደረገበት በሰውነታችን በተለያዩ ክፍሎች ዘላቂ ጉዳት ያደርሳል፡፡ እነዚህ ጉዳቶች ሕይወትን ከሚያሰጋ ሁኔታ ጨምሮ፣ በልብና በደም ሥሮች ላይ፣ በነርቭ ሴሎች ላይ፣ በአይን (የአይን መታወር ምክንያት መሆን) እና የኩላሊት በሽታንም ያካትታሉ፡፡
የስኳር በሽታ መኖሩን ለማወቅ የሚደረጉ ምርመራዎችን መመዘኛዎች በደም ውስጥ የስኳርን መጠን በመለካት ነው፡፡

የስኳር በሽታ አለበት ለማለት የሚከተሉት የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤቶችን ይመልከቱ

 1. ለሰምንት ሰአታት የሚሆን ምግብ ሳይበላ(ፆም) በደም ውስጥ የስኳር መጠን ሲለካ ቁጥር 126 mg/dl ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ
 2. ወይም 75 ግራም የመሆን ስኳር መጠን ከበሉ (ወይም በመጠጥ መልክ ከተጠጣ በኋላ) ከሁለት ሰአታት በኋላ በደም ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን ሲለካ 200 mg/dl ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ 
 3. ወይም በማንኛውም ጊዜ በደም ውስጥ የስኳር መጠን ሲለካ 200 mg/dl ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ፡፡ ወይም HBA1c የሚባል ምርመራ ሲደረግ መጠኑ ከ6.5% በላይ ከሆነ ነው፡፡ HBA1c የሚነግረው የደም ስኳር መጠን በዘጠና ቀናት ውስጥ እንዴት እንደነበር አማካይ ቁጥር በመግለፅ ነው፡፡


Type 2 ለመግለፅ፣ በአብዛኛው የሚታየው አይነት ማለትም ከስኳር በሽታ 90 በመቶ የሚሆነው አይነት ነው፡፡ የዚህኛው አይነት የስኳር በሽታ መንስኤው ኢንሱሊን የሚባለው ሆርሞን በበቂ መጠን ሳይመረት ሲቀር ወይም ሙሉ በሙሉ ሥራውን መሥራት ሳይችል ሲቀር ነው፡፡ በአብዛኛው በዕድሜ ገፋ ባሉ ሰዎች ላይ የሚታይ የነበረው ይህ አይነት የስኳር በሽታ አሁን ግን በልጆች፣ በወጣቶችና በጎልማሶች ላይ መታየት ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ይህ ደግሞ እየጨመረ በሚታየው የሰውነት ውፍረት፣ በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግና ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ምክንያት ነው፡፡

ለመሆኑ የስኳር በሽታ ስሜትና ምልክቶች ምንድን ናቸው፡፡

 • ከፍተኛ የውሀ ጥማትና አፍ መድረቅ
 • በብዛትና እየተመላለሱ ሽንት መሽናት
 • የአቅም መድከም ወይም ጉልበት ማነስና ከፍተኛ የድካም ስሜት
 • አጅና እግርን ውርር የሚያደርግ ስሜት ወይም በመርፌ ጠቅ ጠቅ የተደረግ የሚመስል ስሜት
 • ተደጋጋሚ የቆዳ በሽታ (በፈንገስ)
 • ቁስል ቶሎ ያለመዳን
 • አይን ብዥ ብዥ ማለት


ቸግሩ ግን ብዙ ሰዎች ስኳር በሽታ ቢኖርባቸውም ስሜት ሳይሰማቸውና ምልክት ሳይታይባቸው ሁኔታው ሳይታወቅ ለብዙ አመታት ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ እንግዲህ በሽታው ሳይታወቅ ለብዙ አመታት ከቆየ ደግም ከላይ እንደተጠቀሰው በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ጉዳት ያደርሳል፡፡

የዚህ በሽታ መንስኤ በውል ባይታወቅም ከሚከተሉት ሁኔታዎች ጋር ግን ጠንካራ ግንኙነት እንዳለው ይታወቃል፡፡

 1. ከፍተኛ የውፍረት መጠን፤ በዕድሜ መግፋት፤ በዘርና በቤተሰብ የመታየት ይጨምራል፡፡
 2. አንዳንዶቹን ለስኳር በሽታ የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን ሰዎች መቀየር እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ አነዚህም
 3. ከፍተኛ ውፍረትን፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብን፣ የሰውነት አንቅስቃሴ አለማድረግን፣ ሲጋራ ማጨስን ጨምሮ ነው፡፡


የአመጋገብ ነገር ሲነሳ መስተዋል ያለበት በስኳር የጣፈጡ መጠጦችን ከመጠን በላይ መጠጣት አንደኛው ትልቅ ምክንያት መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዝም በቂ ያልሆነ የፍራፍሬና የአትክልት መጠን አለመመገብ ነው፡፡ በሽታው ከታወቀም በኋላ ቢሆን የህክምና ዋናው አቀራረብ፣ ጤናማ ምግብ አመጋገብ (በተለይም ከፋብሪካ የሚመረቱ ምጥን ምገቦችን ከመመገብ ይልቅ በተፍጥሮ ሙሉ የሆኑ እንደ አትክልት ፍራፍሬ መመገብ)፣ የሰውነት እንቅስቃሴን መጨመር፣ ሲጋራ ማጨስን ማቆም፣ ጤናማ የሆነ የሰውነት ክብደትን መጠበቅ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ እንደሁኔታው በሀኪሞች ከሚሠጡ መድሀኒቶች ጋርም ነው፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው በዕድሜ ከገፉ ሰዎች በተጨማሪ በልጆችና በጎልማሶች መታየት ሰለጀመረ ምክሩ

ልጆችዎ የሚመገቡትን ምግብ ማስተዋል፣ ጣፋጭ ነገሮች ቢቻል ማስቀረት አለዚያም አልፎ አልፎ ብቻ፡፡ ለስላሳ መጠጦችን የመሳሰሉትንና የታሸጉ በፋብሪካ የሚዘጋጁ ጣፋጭ ምግቦችን አለማስለመድ ጠቃሚ ነው፡፡ ስኳር ቢወደድ ጥሩ ነው፡፡ ማንስ ይፈልገዋ?
ልጆች አንደልጅነታቸው የሰውነት እንቅስቃሴ እንዲጨምሩ መገፋፈት፣ ከቴሌቢዥን ወይም የመጫወቻ (Game) ሰአት መቀነስ የግድ ነው፡፡
የሰውነት ክብደት ከመጠን በላይ እንዳይሆን መከላከል (ለአዋቂም ሆነ ለልጆች)
በሽታው በዘር ወይም በቤተሰብ የመታየት ባህሪ ስላለው፣ ቤተሰብ ውስጥ ከታየ ሌሎች የቤተሰብ አባላት የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

አንግዲህ የዚህ በሸታ መጠን እየጨመረ የመጣው በከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በከተማ የሚኖሩ ሰዎች አመጋገብ ጤናማ አለመሆን ጋር ነው፡፡ ቀጥታ ከእርሻ የመጡ ሙሉ ምግቦችን ከመመገብ ይልቅ የታሸጉ የፋብሪካ ምግቦችን በብዛት ከመመገብ የመጣ ነው፡፡ ከዚህ ቀድም በጎሽ ድረ ገፅ እንደገለፅነው ምገቦችን ወይመ መጠጦችን ለማጣፈጥ የሚጠቀሙበት ፍሩክቶስ የተባለው የሰኳር አይነት ከስኳር በሽታ ጋር የተያየዘ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ባለገንዘቦች እራሳቸው የማይመገቡትን የምግብ አይነት ገንዘብ እስከፈራላቸው ድረስ ለሌሎች ከመሸጥ አይመለሱም፡፡ በሲጋራ የተነሳ የሚመጣውን ችግር ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ በሚቀጥለው ፅሁፍ ስኳር በሽታን ለመከላከል መደረግ ይገባቸውል የሚባሉትን ሁኔታዎች በዝርዝር እናቀርባለን፡፡

በኢትዮጵያ የስኳር በሸታ ቁጥር በቂ መረጃ ባይደርስም የሚከተሉትን አሃዞች መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ምንጭ (IDF)

 1. ዕድሜያቸው ከ20- 79 አመታት ከሆኑ ሰዎች መሀከል ከ7-9%  የሚሆኑ ሰዎች የስኳር በሽታ አለባቸው ተብሎ ይገመታል
 2. ይህ ቁጥር ከፍ ያለ ቢሆንም ከአንድ እሰከ አስረኛ ተራ ቁጥር ውጭ ነች፡፡ ቸግሩ በኢትዮጵያ ከ500 መቶ ሺ እሰከ 5 ሚሊዮን የሚሆነ ሰዎች ስኳር በሽታ እያለባቸው ግን ሳይታወቅ እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡
 3. ዕድሜያቸው 60 አመታት ሳይሻገር በስኳር በሽታ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ግምት ደግሞ  ስንመለከት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃው ውሰጥ ነው የምትገኘው፡፡ ማለትም 80 በመቶ ከሚሆኑት ውሥጥ፡፡ የሚያሳዝነው ግን ለስኳር በሽታ ወጭ በማድረግ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ መጠን ከሚያወጡት ሀገሮች መሀከል ነው የምትመደበው፡፡


 
መልካም ንባብ Please share this page