​ጎሽ የጤና ትምህርትና ምክር በአማርኛ


አዘጋጅና አቅራቢ 
ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

Community health 

education in Amharic 

Health and History

ካንሰር ከሚያስይዙ ኬሚካሎች ጋር የተነካካው መድሐኒት
 09/24/2019

 ይህንን መድሐኒት የሚያመርተው ኩባንያ፣ በካንሰር ኬሚካሎች የተነካካውን መደሐኒቱን ከገበያ አውጥቷል፡፡ ይህ ዜና ለአብዛኛው የኛ ህብረተሰብ መድረሱን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሰለዚህ አጭር መልክት ይኸው፡፡
መድሐኒቱ፣ ዛንታክ Zantac ይባላል ዋናው ኮምፓውንዱ ራኒቲዲን Ranitidine ነው፡፡ አገልግሎቱ ለጨጓራ ህመም ነው፡፡ ብዛት ያላቸው ሰዎች እንደሚጠቀሙ ነው፡፡ በተለይ በዛንታክ ስም የሚሠራው መድሐኒት ነው ሲመረመር፣ ካንስር የሚያስይዙ N- nitrosodimethylamine(NDMA) የሚባሉ ኬሚካሎች እንዳሉበት የተገኘው፡፡ NDMA የ nitrosamine ኮምፓውንዶች ክፍል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም፣ ይህ ኮምፓውንድ ከሌሎች ለደም ግፊት ለሚሆኑ መድሐኒቶች ላይ በመገኘቱ ቁጣን አስነስቶ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ይኸው በዚህ በዛንታክ ላይ ታይቶ፣ የሚያመርተው ኩባንያ፣ ኖቫርቲስ፣ በአለም ዙሪያ፣ ከዚህ ኮምፓውንድ ጋር ንክኪ አለባቸው የሚባሉ ምርቶችን እያስወገደ ነው፡፡ እንግዲህ ቤትዎ ውስጥ ድንገት ካለም፣ ከመጠቀም መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡
ስለ መድሐኒቶች አሠራር በመጠኑ፡፡ መጀመሪያ መድሐኒት ሲፈጠርና ሲመረት፣ ምርምር ተደርጎ ጥራቱ ተጠብቆ በፈጠረው ካምፓኒ ሥር በንግድ ስሙ (ብራንድ) Brand name ይሸጣል፡፡ አምራቹ፣ ለአመታት ሌላ ተፎካካሪ እንደይሠራው በህግ በተጠበቀ መብት ብቻውን ለገበያ ያቀርባል፡፡ ያ የግል ባለቤትነት ግን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ያቆምና፤ ማምረቱ ለሌሎች ክፍት ይሆናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ሌሎች ሲያመርቱት (ጀነሪክ)Generic ይባላል፡፡ ነገር ግን ጀነሪክ ምርታቸውን ብራንድ ስም ሊሰጡት ይችላሉ፡፡ ይኸው ራኒቲዲን፣ ዛንታክ ተብሎ ይመረታል፡፡ ይህ ጀነሪክ የማምረት መብት ለሁሉም ክፍት ስለሆነ፣ የተለያያ አምራቾች በተለያየ ስም ያወጡታል፡፡ ለዚህ ነው፣ በኤስያ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ የሚመረት ተመሳሳይ መድሐኒት ወይም ኮምፓውንድ የተለያየ መጠሪያ ስም የሚኖረው፡፡ እነዚህ ጀነሪክ የሚባሉ ከዋናው ፈጣሪ ካምፓኒ ውጭ በሌሎች የሚመረቱ መድሐኒቶች ዋናው ጠቀሜታቸው ርካሽ መሆናቸው ብቻ ነው፡፡ እነዚህ እንደ ጆፌ አሞራ የሌላን ሥራ ፈጠራ የራሳቸው የሚያደርጉ፣ ለምርመርና ለጥናት፣ እናም መድሐኒቱ ፍቱን መሆኑን ለማስፈቀድ ከባዱን ወጭ ስለማያወጡ ዋጋውን ያወርዱታል፡፡ ሆኖም፣ በአብዛኛው ኮምፓውንዶቹ እንደ ብራንዱ መድሐኒት ፍቱን ቢሆኑም፣ አንዳንዴ የጥራት ጥያቄ ይነሳል፡፡ በብዛት እነዚህ ጀነሪክ መድሐኒቶች የሚመረቱት ባላደጉ ወይም በማደግ ላይ ባሉ አገራት ነው፡፡ ይህንን በብዛት ከሚሠሩ አገሮች ዋናዎቹ ቻይናና ህንድ ናቸው፡፡
ቸግሩ፣ በምግቡም እንዳየነው፣ የጥራት ድክመት ብቅ እያለ ነው፡፡ በሌላ በኩልም ግብረ ገብ የጎደላቸው፣ ገንዘብ መሥራት ብቻ አላማቸው የሆኑ ካምፓኒዎች መታየታቸው አይገርምም፡፡ ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌለው፣ የሰውን ህግ ይፈራል ብሎ መገመት አዳጋች ነው፡፡ የዛሬ ስንት አመት፣ ዎባ በገነነበት ቦታ እየሠራን፣ ለዎባ ከባድ መድሐኒት ነው ተብሎ የምንቆጥበው ፋንሲዳር Fansidar የሚባል መድሐኒት ነበር፡፡ ከአለም አቀፍ የጤና ደርጅት ደብዳቤ ደርሶን ስናነብ፤ ያ ለዎባ የተሠራው መድሀኒት አንድም የዎባ መድሀኒት ጠብታ እንኳን ያልነበረው፣ ክሎራፌኒኮል የሚባል ለሌላ በሽታ የሚውል chloramphenicol 25 ሚሊግራም ብቻ ነው ያለውና አትጠቀሙ ተብለን ተመከረን፡፡ እንግዲህ እግዚር ያሳያችሁ፣ ከባድ መድሐኒት ነው ብለን በጣም ለጠናባቸው ሰዎች የምንጠቀመው መድሐኒት ነው፡፡ ብንሰጣቸውም አይድኑም ነበር፡፡ እኔና ጓደኞቼ፣ “ቾክ” ነው የሠጡን አልን፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ፣ ውስልትናው ላይ የአፍሪካ አገራትም አሉበት፡፡ ስም መጥራት አልፈልግም፡፡ 
የዚህ ግን፣ ገንዘብ ለማዳን ይሁን አይታወቅም፣ የጥራት ጉድለቱ ካንሰር ከሚያስይዝ ኮምፓውንድ ጋር መነካካቱ ነው፡፡ አንድ ቤተሰቤ በዕድሜ ገፋ ያለች ሴትዮ፣ “ርካሽ ያደረጋል ታናሽ” ትላለች፡፡ ግን ምን ይደረግ? የብራንድ ዋጋው የሚቀመስ አይደለም፡፡ አሜሪካም ቢሆን፣ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ለገንዘብ ሲሉ ጀነሪክ እንደናዝ ያስገድዱናል፡፡ ለማን አቤት ይባላል? ህብረተሰቡን ማስተማሩ ይጠቅማል ብያለሁ፡፡ አደራ፣ በዚህ ምክንያት መድሐኒቶችን መሸሽ አግባብ አይሆንም፡፡ ይህ ከስንት ጊዜ አንዴ ብቅ የሚል ነገር ነው፡፡ እሰከዛው ግን ዛንታክ የሚባል ቅጠል በደጃፌ አይብቀል ነው ነገሩ፡፡

እባካችሁ አካፍሉ፡፡