የመዳፍ ንባብ በጋምቤላ (Palm Reading)

መዳፍን እያዩ ወደፊት ስለሚያጋጥመው ነገር መናገር ይቻላል ይባላል፡፡ ወደ ጋምቤላ ልውሰዳችሁና፤ በሀኪምነት ተመድበን ስንሰራ ሰለ መዳፍ ንባብ የሚያሰተምር መፅሐፍ አንደኛው ጓደኛቸን ይዞ መጣ፡፡ ከአዲስ አበባ፡፡ በጉጉት አየንና መዳፋቸን እጅ እጅ እስኪለን ድረስ መስመሮችን እያየን ለመተርጎም ሞከርን፡፡ በመዳፍ ላይ ካሉ መስመሮች አንዱ የህይወት መስመር ይባላል፡፡ Life line የገንዘብ ወይም የሀብትም አለ ሌሎችንመ ጨምሮ፡፡ ታዲያ ኮሰተር ብለን ሚስጥሩን ለማወቅ ሞከርን፡፡ ከጊዜ በኋላ እንደ አንባቢ ለመሆን ማሰብ ጀመርን፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ራሱ መፅሐፉን ገዝቶ ያመጣው ጓደኛችን ትንሽ ቆይቶ ይኼ ነገር አይረባም ውሸት ነው ማለት ጀመረ፡፡ አንድ ላይ ነው የተማርነው አንድ ላይ ነው የተመረቅነው፡፡ ስለዚህ በሚገባ እንተዋወቃለን አንግባባለንም፡፡ እኛ ደግሞ ትንሽ ችክ አልን፡፡ መረጃህ ምንድን ነው በማለት፡፡ እንደሚመስለኝ የየራሳችን መዳፍ ጥሩ ጥሩ ነገር ስላለው መሰለኝ ለማመን የፈለግነው፡፡

 ነገሩ እንግዲህ ጋምቤላ ሆሰፒታል ስንሠራ ከደጋ የመጡ ሠፋሪዎች አሉ እና ዎባውን ሊቋቋሙት አልቻሉም፡፡ ዘግይተው ከመጡ ከአቅማችን በላይ ይሆን ነበር፡፡

ታዲያ ይኸው የመፅሐፉ ባለቤቤት በተለይ የሕይወት መስመሩን በደንብ ነው የሚያስተውል የነበረው፡፡ እኛ ሳንሰማ በሽተኛ ህይወቱ አለፈ ሲባል ተደብቆ ይሄድና መዳፉን አይቶ እየተመለሰ ነበር፡፡ ተረኛ ባይሆንም፡፡ አንድ ሶስት ሰዎች ካይ በኋላ ሚስጥሩን አወጣው፡፡ የህይወት መስመር የሚባለው ነገር እንደ ርዝመቱ ሰዎችን ረዥም ዕድሜ ይኖራሉ የሚል ትርጉም አለው፡፡ ታዲያ ጓደኛችን የሞቱ ህሞማንን መዳፍ ሲያይ ያ የህይወት መስመር የሚባለው ነገር ረዥምና በሕይወት ለረዥም ጊዜ ይኖራሉ ከሚባሉ ሰዎች መዳፍ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ በተደጋጋሚ ሰላገኘው ነው ለካ አይረባም ያለው፡፡ ሚስጥሩን ከነገረን በኋላ መፅሐፉን ዞር ብለን አላየነውም፡፡ ትልቅ ቧልት መሆኑን በማረጋገጫ ስላስረዳን ጓደኛችንን አመሰገንን፡፡

 ስለዚህ መዳፍ በማንበብ የወደፊት ዕድልና ኑሮን ለማወቅ የምታስቡ ካላችሁ ዋጋ ቢሰ መሆኑን በጓደኛችን መረጃነት ስላረጋገጥን እንደማይረባ ለመግለፅም ነው፡፡

 የዎባውን ነገር ካነሳሁ፡፡ ከዚህ በፊት ለዎባ ተጋልጦ የማያውቅ ሰው በአስቸኳይ ህክምና ከላገኘ ህይወት የማለፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ እና እዚህ አሜሪካን አገር በተላላፊ በሽታ ባለሙያነት ስማር ፈርነጆቹ ዎባን እንዴት እንደሚፈሩት ስመለከት ባንድ በኩል ቢገርመኝም በሌላ በኩል ግን ጋምቤላ ያለቁትን የደጋ ሰዎች ህይወት ሳስታውስ ትክክል ነው ብይ አብሬ አክብሬአለሁ፡፡

 ታዲያ ሀኪም ያልሆኑ ጓደኞቻችን ሲተርቡ፤ ቄሶቹ ፍታት ሰልችቷቸው በጥዋት ከሆስፒታሉ በር ይቆሙና ዛሬ ለሚሞተው ሁሉ ፍታት አድርገናል ይላሉ አያሉ ይተርቡን ነበር፡፡ ነገሩ የኛ አለማወቅ ሳይሆን፤ የደጋ ሰዎች በመሆናቸው ዎባው ጭንቀላት ወይም አንጎል ውስጥ የመውጣት ባህሪና በከፍተኛ ደረጃ ቀይ የደም ሴሎችን የመውረር ባህሪ ስላለውና ከዚያ በተጨማሪ ከሰፈራ ጣቢያቸው ዘግይተው ስለሚመጡም ነበር፡፡

ምስኪኖች ወገኖቻችን፡፡ እንደሰማነው ከሆነ አንድ አምሳ አለቃ የደርግ ባለሥልጣን ነው በሄሊኮፐተር የጋምቤላን አረንጓዴነት አይቶ ለሰፈራ ጥሩ ነው ብሎ የወሰነው አሉ፡፡

 እኛ ከመድረሳችን በፊት ብዙ ሰው አልቆ ነው የጠበቀን፡፡ ወገኖቼን ነብሳቸውን ይማር

የፖለቲካ ሃላፊዎች በቂ ጥናት ሳያደርጉ የሚወስኑት ውሳኔ ውጤቱ ይህ ነው፡፡

                           ከድጡ ወደ ማጡ
               Vaping (E – Cigarette) ና መዘዙ


ሲጋራና ሲጋራ ማጨስ ያሰከተለውና የሚያስከትለው ጉዳት ግልፅ በሆነበት ዘመን፣ ብልጣ ብልጥ አትራፊዎች ሌላ የሚጨስ ነገር ይዘው ብቅ ካሉ ሰንብተዋል፡፡ እሱም በእንግሊዘኛ  አጠራር ቬፒንግ (Vaping) የሚባለው ኤሌክትሮኒክ ሲጋሬት(E- cigarette)  ተብሎ የሚጠራው አጠቃቀም ነው፡፡ ይህ እንግዲህ በውስጡ ኒኮቲን የለውም ተብሎ፣ በአፋቸው ጭስ እንደ ማማ እንትና ምድጃ ቡልል እያለ ሲወጣ ነፍሳቸውን የሚያስደስታቸው ሰዎች ሰላሉ ነው የተፈበረከው፡፡ መኪና እየነዳችችሁ ስትሄዱ ሆነም ቀይ መብራት ላይ ስታቆሙ፣ ከጎረቤት መኪና መስኮት በኩል ጭስ መውጫ ወደ ውስጥ ገባ ወይ በሚያስብል ሁኔታ ጭስ ቡልቅ ሲል ይታያል፡፡ ካስተዋላችሁ ይህ ኤሌክትሮኒክ ሲጋሬት የሚባለውን ነገር ሲጠቀሙ ታገኛላችሁ፡፡ እንደ ጭስ የሚወጣው ነገር በተለያዩ ጣዕሞች ተቀምሞ ለአጫሾቹ ይሸጣል፡፡
     እንግዲህ እንደ ፋሽንም ሆኖ ወጣቶቹ በብዛት እየተረባረቡበት ነው፡፡ በአሜሪካ 10.8 ሚሊዮን ሰዎች ይህን ነገር ተጠቃሚ መሆናቸው በቅርቡ ተገልጧል፡፡ የኛም ወገኖች ከመልመዳቸው በፊት ሰሞኑን በጥናት የወጣውን አስደንጋጭ ነግር ላካፍላችሁ፡፡
     በቀረበው ጥናት መሠረት፣ ይህንን የኤሌክትሪክ ሲጋሬት ከሚጠቀሙ ሰዎች ምራቅ ይሰበሰብና ምርምር በሚደረግበት ጊዜ፣ በዚሁ ጭስ ምክንያት የሰውነት የዘር ሰንሰለት (DNA) የሚጎዱ ኬሚካሎች አንደሚፈጥር ይደረስበታል፡ እንግዲህ ከተጎዳ DNA ሰውነት ላይ ካንሰር የመብቀል ወይም የመፈጠሩ ሁኔታ ይጨምራል፡፡ ታዲያ ሲጋራ ማጨስስ በምን ተጠላ?
     ለጥናቱ ምራቃቸው የተሰበሰበው ሰዎች ለአስራ አምስት ደቂቃዎች ብቻ ካጨሱ በኋላ ነው ናሙናው የተወሰደው፡፡ እናም ይህ የሚጨሰው ነገር ከዚህ ቀደም ሰውነት ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ የሚታወቁ ኬሚካሎች ከመጠን በላይ በምራቃቸው እንደተገኘ ነው የሚያሰገነዝበው፡፡ ይህም ከማያጨሱ ሰዎች ምራቅ ጋራ ተወዳድሮ ነው፡፡
የሚከተሉት ኬሚካሎች መጠን ጨምሮ ነው የተገኘው፡፡ formaldehyde, acrolein, and methylglyoxal. በተለይም acrolein የተባለው ኬሚካል ከ30 እሰክ 60 ዕጥፍ በሆነ መንገድ መጠኑ ጨምሮ ነው የተገኘው፡፡ ይህ ኬሚካል ደግሞ የካንሰር ጠንቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው የሰውነት ሴሎች ላይ ጉዳት የሚያሰከትለው፡፡
     ይህ ጥናት በኦገስት 21 በቦሰትን ከተማ በተደረገው National Meeting & Exposition of the American Chemical Society ስብሰባ ላይ ነው የቀረበው፡፡
ባጠቃላይ እነዚህ ኢ - ሲጋሬት(E- cigarette) በሰውነት ላይ ሊያደርሱ የሚችሉት ጉዳትና የሚፈጠረው የጤንነት መቃወስ በአሁኑ ሰኣት ግልፅ ባይሆንም ጥብቅ ክትትል ወይም ጥናት እንደሚያስፈልግ ነው የጥናቱ አቅራቢዎች የገለጡት፡፡
ሆ ሆ፣ በኋላ ከማዘን…… ይላሉ ያገራችን ሰዎች፡፡ የሰውነት ሴሎችን የሚጎዳ የካንሠር ጠንቅ የሆኑ ኬሚካሎች መኖራቸው ከታወቀ የግድ ካንሰር እስኪመጣ መጠበቅ አለበት ወይ?
ላልሰማ አካፍሉ፡፡  የጫቱ ይበቃናል

የሞጋቾች ድራማ በመድረካቸው ማስተማር ሲችሉ 02/16/2018

ትዕይንታቸውን በዶክተሮች ዙሪያ አድርገው ለረዥም ጊዜ ተከታታይ ክፍሎች ያለው ድራማ እየሠሩ ነው፡፡ በዚህ አገር መለኪያ ያን ያህል መሰንበታቸው፣ እንኳን ደስ ያላችሁ የሚያሰብል ነው፡፡ የስኬት ውጤት ነው፡፡ እንግዲህ ድራማ ሲዘጋጅም ትምህርትም እንዲሠጥ ተደርጎ፣ ሰለሚያቀርበው ርዕስ ደግሞ በቂ ጥናት አደርጎ መፃፍ ነበረበት፡፡ እሰካሁን ድረስ፣ ያ የፈረደበት ኩላሊት ከማን ሆድ ዕቃ እንደሚወጣ ግልፅ ሳይሆን ልብ ሲያንጠለጥሉ ከርማዋል፡፡ እኔ የምጠቁመው ግን ስለኩላሊት ትክ ሲወራ (በነገራችን ላይ ነቅሎ ተከላ የሚባለው ንግግር አግባብ አይደለም)፡፡ በእንግሊዘኛ ከ Transplant  ወደ Replacment እየተሸጋገረ ነው፡፡ ነገሩ መተካት ስለሆነ ትክ ቢባል ይመረጣል፡፡ እንግዲህ የአካል ትክ ሲደረግ እንደ ሶማሊ ተራ መለዋወጫ ዝም ብሎ የሚገጠም ነገር አየደለም፡፡ ያ ሁሉ ሰው እሰጣለሁ ብሎ ሲንጋጋ በመጀመሪያ መነገር ወይም መጠየቅ የነበረበት ከተቀባይዋ ጋር ይስማማል (Match) ወይ ነበር፡፡ እንደተገኘ የማንም ኩላሊት ማንም ላይ አይተካም፡፡ ያንን መቼም ይሁን ብለን አለፍን፡፡


የከነከነኝ ነገር ግን፣ በቅርቡ ባሳዩት ክፍል፣ ያ በኩላሊት ፍቅር ሊገዛ የፈለገው ሰው በሽታ ተገኘብህ ተብሎ ሲነገረው፣ አቀራረቡና አነጋገሩ ትክክል ስላልመሰለኝ ነው፡፡ ሰውየው አለብህ የተባለው ሔፓታይትስ ሲ እና ሔፓታይትስ ቢ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ቫይረስ በህብረተሰቡ ስለሚገኝ በቫይረሱ የተለከፉ ሰዎችም ስላሉ ፣ ቫይረሱ ስለተገኘበት ለሞት የቀረበ የመጨረሻ ደረጃ አድርገው ማሳየታቸው ተገቢ አይደለም፡፡ ሳያውቁት ብዙ ሰዎችን ያሸብራሉ፡፡ ወይም አሸብረዋል፡፡

ሁለቱም ሔፓታይትስ ቢ እና ሲ፣ የጉበት በሽታ በማስከተል የሚታወቁ ናቸው፡፡ ብዙ ጉዳትም ያመጣሉ፡፡ ነገር ግን ባጭር ጊዜ ውስጥ ሳይሆን ለአመታት በጉበት በመቀመጥ ነው፡፡ ያም የጉበት ጥብሰት የተባለ ሁኔታ ሲፈጥሩ ነው፡፡

አሁን ጊዜው ተቀይሮ ሔፓታይትስ ሲ ቫይረስን በአፍ በሚዋጡ እንክብሎች አማካኝነት በሁለት ወር ወይም ከዛ በላይ በሆነ ጊዜ ቫይረሱን ከሰውነት ማስወገድ ከተቻለ ሰንብቷል፡፡ በግምት ሳይሆን ከሥራና ከጥናት ልምድ በመነሳት ነው የምናገረው፡፡ በብዛት የተለያዩ መድሀኒቶች ስለወጡ ዋጋው እየወረደ መጥቶ ብዙ ህሙማን በመታከም ላይ ናቸው፡፡ ኢትየጵያም ውስጥ አንደኛው መድሐኒት በካምፓኒዎችና በተለያዩ ክፍሎች በተደረገው ሰምምነት በዝቅተኛ ዋጋ ኢትዮጵያ ከገባ ቆይቷል፡፡ እሰከማውቀው ድረስ በጥቁር አንበሳ፣ በቅዱስ ጳውሎስ በጎንደር ዩኒቨርሰቲ ሆስፒታል የሚገኙ ሀኪሞች እያከሙ ሰለሆነ ያልሰማ ካለ አካፍሉ፡፡ ስለዚህ የያዙትን መድረክ ተጠቅመው ሰውየውን ቫይረሱ አለብህ ግን በመድሐኒት ስለሚድን ወደ ዶክተር እከሌ ሂድ ቢሉት እንዴት ጥሩ ነበር፡፡

ስለ ሔፓታይትስ ቢ ደግሞ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ የጉበት በሽታ ቢያመጣም ሁሉም ቫይረሱ ያለበት ሰው ወደ ከባድ በሽታና ወደ ሞት አይሄድም፡፡ እዚህ ላይ የጉበት ጥብሰት ከሌላባቸው በስተቀር ነው፡፡ ያም ቢሆን ርዳታ አለው፡፡ ዋናው ነገር ለዚህኛው ቫይረስ፣ ጠርጎ ባያድንም ቫይረሱን የሚቆጣጠሩና የህሙማኑ ጉበት ወደ ጥብሰት እንዳይሸጋገር የሚያደርጉ መድሐኒቶች አሉ፡፡ ስለዚህ በነገርና በሀዘን በተሞላው በዚህ ድራማ ይህንንም ለማስተማር ሲሉ በድረማው ላይ ውጤቱን የተናገሩት ሀኪም ሰውየውን እንደዚህ አይነት ሁኔታ አለ ብለው ቢያማክሩት ኖሮ ሌላ ትምህርት በሠጡ ነበር፡፡ አሁንም ጊዜው ስላላቸው ይችን ጥቆማ አንበብው ባላሙያ አማክረው ወደ ትምህርት ቢቀይሩ መልካም ነው፡፡ በነገራችን ላይ እንኳንስ ሔፓታይትስ በኤች አይ ቪ የተለከፉ ሰዎችም በትክክል መድሐኒት ከወሰዱ የዕድሜ ጣሪያቸው ወደ ሌሎች እየተጠጋ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በቅርቡ አንድ የምርምር ኩባንያ ኤች አይ ቪን ለማዳን ጥናት ለማካሄድ ከአሜሪካ መንግሥት 11 ሚሊዮን ዶላር ተቀብሏል፡፡ ፍንጭ አለ ማለት ነው፡፡

ይህንን ስል የትኛውም ቫይረስ የተገኘበት ሰው የህክምና ባለሙያ ማየት የግድ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ለማንኛውም ሰለነዚህ በሽታዎች ለማስገንዘብ በአማርኛ በድረ ገፅ ከተቀመጠ ቆይቷል፡፡ አሁንም ከሞጋቾች ቀደም ብላችሁ ሰለነዚህ በሽታዎች በዚህ ድረ ገፅ የተቀመጡትን ፅሁፎች እንድታነቡ እጋብዛለሁ፡፡