GOSH HEALTH


Community health 

education in Amharic 

የ1918 የህዳር በሽታ

በፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት
ትርጉም ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ

 ይህን አስገራሚ የወረረሽኝ ታሪክ በስፋት ለህዝብ ለማቅረብ የትርጉም ሥራውን እንደሠራው ለፈቀደልኝ ለዶ/ር አሉላ ፓንክረስት ምስጋና ማቅረብ እወዳለሁ፡፡ በተጨማሪም፣ ይህ ጽሁፍ መኖሩን ባውቅም፣ እኔ ሳልደክም ጽሁፉን አፈላልጎ ላቀረበልን ጓደኛችን ለአርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ምስጋና ይደረሰው አላለሁ፡፡

 ወደ ትርጉሙ ከመሄዴ በፊት፣ ከዚህ ቀደም ሰለዚህ አዲስ የመጣው ወረረሽኝ ማለትም ሳርስ ኮሮና ቫይረስ ቁጥር ሁለት የወደፊት አደጋ ሊሆን ይችላል በማለት በ1918 የተከሰተውን በአጠራር የስፓኒሽ ፍሉ የሚባለውን አስከፊ ወረርሽኝ በመጠኑም ቢሆን በቃለ መጠይቅ ላይ ገልጬ ነበር፡፡

በዛን ጊዜ የአለምን ህዝብ አንድ ሶሰተኛውን ይዞ፣ ለሃምሳ ሚሊዮን ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት የሆነው ይሀ ቫይረስ፣ አነሳሱ ከአጥቢ አንስሳት ወይም ከሰው ይሁን እንጂ፣ ቆየት ብሎ ከወፍ ዝርያ፣ የዘርሀረግ በመዳቀል፣ ወደ አሰከፊ ደረጃ የደረሰ ቫይረስ ነው፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1918 ይከሰት እንጂ በ1915 ጀምሮ ይታይ እንደነበረ የታሪክ ዘገባዎች ያስረዳሉ፡፡ ሰለ ዛን ጊዜው ቫይረስ የታወቀው፣ ወደኋላ፣ አጥኝዎች በቫይረሱ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን ማግኝት ችለው የቫይረሱን ርዝራዥ ከመረመሩ በኋላ ነው፡፡ በዚያን ጊዜም በአሜሪካ በሰድስት መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመግደል፣ በወቅቱ የነበረውን የአሜሪካ የዕድሜ ጣራ በ12 አመታት እንደጎረደው ተዘግቧል፡፡ ታዲይ ይህ ኢንፍሉዌንዛ አለም ዳር እሰከ ዳር ያዳረሰ ሰለነበር፣ በኢትዮጵያ የሆነውን ማወቅ አስፈላጊ ነበር፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ ነው፣ ይህንን ታሪክ ሥራዬ ብለው ደክመው የሠሩትን የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረሰትን ውለታ የምናስታወሰው፡፡ ከዚህ የምንማረው ነገር ቢኖር፣ ታሪክ፣ ሁሉም መፃፍ አለበት፡፡ መቼም ይህ ሌላ ጊዜ ሰው የማያስተውለው የሚመስለው ታሪክ፣ ወቅታዊ ሆኖ እንደገና ለህዝብ ቀርቦ፣ ከታሪክነቱ ባሻገር መማሪያ ሊሆን በቅቷል፡፡ እንደገናም በአገራችን አባባል፣ የፕሮፌሰር ፓንክረስትን ነብስ በገነት ያኑርልን፣ ትተውልን ለሄዱት ሥራም ክብርም ምስጋናም ይገባቸዋል አላለሁ፡፡

የ1918 የህዳር በሽታ


ክፍል አንድ 


በኢትዮጵያ ታሪክ ወረረሽኞች በየጊዜው የሚከሰቱ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ አብዛኞቹ፣ ያለምንም ጥርጥር ምንም ሳይዘገቡ ነው ያለፉት፣ እንዳውም ከዚህ በፊት በውል የሚታወቁ ወረርሽኞች በሚገባ አልተዘገቡም፡፡ ነገር ግን የ1918 ታላቁ ኢንፍሉዌንዛ በብዙ ፀሀፊያን በምስክርነት የታየና በተጨማሪም ከወረርሽኙ ከተረፉ አሁን በሕይወት ባሉ ሰዎች ትውስታው የሚነገር ነገር ነው፡፡ የነዚህ ሰዎች ገለጣ፣ በአገሪቱ ዘመናዊ የህክምና ተቋማት ከመከፈታቸው በፊት፣ አገሪቱን የመታው የመጨረሻው ታላቅ ወረርሽኝ ተብሎ ሊጠቀስ ሰለሚችለው ሁኔታ ጠለቅ ያለ ገፅታ ይሠጠናል፡፡

ኢትዮጵያና፣ ከሁሉም በላይ አዲስ አበባ በዚህ በብዙ የአለም ክፍሎች ሰፓኒሽ ፍሉ ተብሎ በሚጠራው አለም አቀፍ ወረርሽኝ በከፋ ደረጃ ነው የተጠቁት፡፡ በአካባቢው ግን በህዳር ወር በአብዛኛው በህዳርና በታህሳስ ወራት፣ ከፍተኛ ጉልበት ሰለነበረው፣  የህዳር በሽታ ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ የእንግሊዝ መንገደኛ የነበረው፣ ሰር ቻርልስ ሬይ፣ በሰጠው አስተያየት፣ “አቢሲኒያ በዚህ አስከፊ ቫይረስ ከሚገባት ድርሻ በላይ ነው የተጎዳቸው፣ እናም የበሸታ ሰለባ የሆኑ ሰዎች በአዲስ አበባ እንድ ዝንብ ነው የረገፉት” ይላል፡፡ ሁኔታውን ተከትሎ በቅርብ አዲስ አበባ የደረሰው ክርሰቲን ሳንፈርድ፣ የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ፣ አዲስ አበባ “በጣም በከፋ ደረጃ” ተጎድታለች ሲል ያረጋግጣል፡፡

እንደሌሎች ብዙ አገራት ሁሉ፣ በኢትዮጵያም ወረረሽኙ የተከሰተው በሁለት በተለያዩ ሥርጭቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው በፀደይና በበጋ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በ1918 በበልግ ወራት ነበር፡፡ የመጀመሪያው የወረርሽኝ ማዕበል፣ ሲነፃፀር፣ ቀለል ያለና በጊዜው ምንነቱ ያልታወቀ፣ ገና በሚያዝያ ወር ራሱን ብቅ ያደረገ ይመስላል፡፡ የስዊድን ተወላጁ ሚሲዮናዊ ካርል ሴደርክቨስት፣ በሚያዝያ 22 ከአዲስ አበባ በላከው ሪፓርት “በከተማው ብዙ ሰዎች ታመዋል፤ ከምዕራብ የኦሮሞ አውራጃዎች የመጡ ጥቂት ሰዎችም በመንገድ ላይ ታመዋል፤ እንደዛም ሆኖ እኛ ድረስ ዘልቀው ለመምጣት ችለዋል፡፡ እኔም ብሆን ትኩሳት አለብኝ፣ ነገር ግን እሰከ አሁን ድረስ አንደ ምንም ብየ አየተንቀሳቀስኩና ሥራ እየሠራሁ ነው፡፡” ብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ስዊድናዊው በመጨረሻ ራሱ አለፈ፤ በግንቦት 6 ወደ ስቶክሆልም በፃፈው ማስታወሻ፣ በያዘው ህመም ምክንያት ለሚሲዮን ዳይሪክተሩ ሪፖርት መላክ አለመቻሉን ይጠቅሳል፡፡

የማያባራው ትኩሳት፣ ትክክለኛነቱ በደንብ ስላልታወቀ፣ የታሰበው ታይፈስ (የአንጀት ተስቦ) ወይም ፈንጣጣ ነው ተብሎ ነበር፣ እናም በሚቀጥለው ወር በአዲስ አበባ ብዛቱ እየጨመረ ሄደ፡፡ በሐምሌ 21፣ በኤርትራ የኢጣልያ አገረ ገዥ የነበረው ደ ማርቲኖ ወደ ሮም በላከው ቴሌግራም፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢጣልያ ሚኒስትር፣ ካውንት ኮሊ በስልክ እንደነገረው ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ዋና ከተማ “በጣም ሀይለኛ የሆነ ወረርሽኝ” እየታጋጋለ ስለነበር የኢትዮጵያ መንግሥት ርዳታ ጠይቋል ይላል፡፡ ለዚህም፣ ኢጣልያዊውን ሀኪም፣ ዶክተር ፓስኩዋል ቨቱቺን ከመቶ ሺ የፈንጣጣ ክትባት ጋር እንደላከው ነው፡፡ ዶክተሩ በጂቡቲ በኩል ነበር ወደ ኢትዮጵያ የገባው፡፡ ነገር ግን፣ ክትባቱ፣ ግልፅ እንደሆነው ጠቀሜታም አልነበረው፤ ዶክተሩም እሰከ መስከረም ሶስት ድረስ በአዲስ አበባ ቆይቷል፡፡ ሁኔታው በእንዲህ እያለ በሽታው ግን ምንም የማባራት ሁኔታ አላሳየም፡፡ በከተማው ቀደም ብለው ከሞቱት መሀከል፣ የሀያ አራት አመት ወጣት የነበረው ግሪካዊው ሰታማቲዮስ ጋኖታኪስ በበሽታው ለመሞቱ ተረጋገጠ፡፡ ግሪካዊው የሞተው በነሓሴ 7 ነበር፡፡ የተከተለውን የበጋውን ወረርሽኝ፣ በአዲስ አበባ የብሪታንያ ሌጌሽን የነበረው ጅራልድ ካምፕቤል የገለጠው፣ “ብዙ” ሰዎች ሞተዋል፣ በመቃብር ቆፋሪዎች ሞት ምክንያት፣  የሞቱት ሰዎች የተቀበሩት “በስድስት ኢንች ጥልቀት” ብቻ ነበር ይላል፡፡ የውጭ ሌጋሲዮኖች፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርሰቲያን ቅጥር እንደዛ አይነት ቀብር መፈፀሙን በመቃወማቸው ምክንያት፣ ቀብሩ ከከተማው ውጭ ባሉ ቤተክርሰቲያች ቅፅር ግቢ ብቻ እንዲደረግ ትዛዝ ተላለፈ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊዘ ቅፅር ከከተማው ከፍ ብሎ ከገበያው ጎን ለጎንም ሰለነበር ነው፡፡

በነሓሴ መጨረሻ ላይ፣ ወረርሽኙ በስፋት የተሠራጨ ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በነሓሴ 21፣ አለቃ ክንፈ ሃዲሱ በወቅቱ በፃፉት ማስታወሻቸው እንደዘገቡት፣ እንደራሴው ራስ ተፈሪ መኮንን በበሽታው ተያዙ፡፡ ከአራት ቀናት በኋላ በነሐሴ 25 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) አንደራሴው በሐረር ለሚገኙት የፈረንሳይ ሚሲዮናዊ ለሞንሲኞር አንድሬ ዣሮሶ በፃፉት ደብዳቤ ፣ ሁሌም እንደሚጠሯቸው፣ “አባ እንድርያስ” በማለት “በትኩሳት በሽታ እየተሰቃየሁ ነው፣” “በሽታውም እየከፋ ነው፣” በማለት እንዲፀልዩላቸው ተማፀኑ፡፡ ራስ ተፈሪ ሲጨምሩም፣ በሳቸው አጠራር ዶክተር ለፓቲን የሚሉትን አርመናዊው ዶክተር ኦሃነስ ደቨልቴይን ስልክ ሊደውሉለት ሞክረው እንደነበር፣ በኋላ እንደተረዱት ግን፣ ዶክተሩ በራሱ ፍላጎት አዲስ አበባ መድረሱን ነው፡፡ በምስክርነት እንደታየው፣ ዶክተሩ በራሱ ውሳኔ በመምጣቱ፣ በሽተኛው፣ ራስ ተፈሪ፣ በዶክተሩ ወዳጅነት በጣም የተደሰቱ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ እናም ዶክተር ለፓቲን ባዘዘው መድሓኒት አማካኝነት ህክምና እያገኙ መሆናቸውንም ይገልፃሉ፡፡ በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ሲደረግ በነበረው ባህል መሠረት፣ ራስ ተፈሪ ብዛት ያላቸው ሥጦታዎች ለአብያተ ክርሰቲያናቱ ሠጥተዋል፡፡ አለቃ ክንፈም፣ “እንደ ሰበካው መጠን” ገንዘብም አብሮ መሠጠቱን ይገልፃሉ፡፡

የእንደራሴው መታመም ዜና የውጭ ዲፕሎማቶች ድረስ ይደርሳል፡፡ በመስከረም 2፣ የብሪታንያ ሌጋሲዮን ሜጀር ዶድስ ወደ ሎንደን የውጭ ጉዳይ ጽ/ቤት ቴሌግራም ሲልክ፣ ተፈሪ “አዲስ አበባን በወረረው ታይፎይድ በሚመስል በሽታ እየተሰቃዩ ነው” ብሎ ነበር፡፡ ሲጨምርም፣ “በጊዜው፣ የራስ ተፈሪ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ አይደለም” ብሎ ነበር፡፡ በሚቀጥለው ቀን ግን፣ ተከታዩን መልክት መላክ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ በመልክቱም፣ ገዢው ስለታመሙ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ምንም አይነት ሥራ ማከናወን “አይቻልም” ብሎ ነበር፡፡ ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ፣ የኤርትራው አገረ ገዥ፣ ወደ ሮም በላከው ቴሌግራም፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው የኢጣልያ ሚኒስትር በስልክ የገለፀልኝ፣ ከነሐሴ 31 ጀምሮ ራስ ተፈሪ በፀና መታመማቸውንና ህመማቸው ደግሞ “በአዲስ አበባ በዚያን ጊዜ በስፋት የተሠራጨ ታይፈስ (የአንጀት ተስቦ) የመሰለ በሸታ ነው”፣ በማለት ነበር፡፡

በዚያን ጊዜ፣ ወረረሽኙ ኃይለኝነቱን እየጨመረ ነበር፡፡ በመስከረም በመጀመሪያው ሳምንት፣ በአዲስ አበባ ብዙ ሰለባዎችን ይዞ ሄዷል፡፡ ከመጀመሪያዎች ሰለባዎች አንዱ፣ የፊታውራሪ ኢብሳ ልጅ፣ አበበ ኢብሳ ነበር፡፡ አበበ፣ ወጣት የተማረና፣ በቅርቡ በተከፈተው የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ከሰባት አመታት በፊት ትምህረት የቀሰመና፣ የትምህርት ቤቱን የመጀመሪያ ሽልማት ከራሳቸው ከአፄ ምኒልክ እጅ የተቀበለ ሰው ነበር፡፡ እንደ አለቃ ክንፈ ዘገባ፣ አበበ በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ውስጥ ይሠራ እንደነበርና፣ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በፓጉሜ 1 አንደሞተ ነው፡፡ ያም ሆኖ፣ የዚህ ወጣት ሰው ሞት ከብዙዎች አንዱ ነው የነበረው፡፡ አለቃ ክንፈ ሲገልጡ፣ ለቀብር “የሄደው ሰው ቁጥር፣ ካልሄደው ሰው በላይ ነው የነበረው”፡፡ በሕይወት ያሉት ሰዎች፣ እንደ ቆሰለ አውሪ በፍርሃት እየተርበደበዱ ነበር፤ ምክንያቱም “ዛሬ በሕይወት የታየ ሰው በነጋታው ላይታይ ይችላል፡፡”

ሁኔታው በዚህ እንዳለ፣ የእንደራሴው ጤንነት ወደ ከፋ ደረጃ እየሄደ ስለነበርና በጣም የፀና ህመም ላይ ሰለነበሩ፣ በፓጉሜ 3 (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር)፣ ቁርባን መቀበል የግድ አስፈላጊ መሆኑ ተስምቷቸዋል፡፡ አለቃ ክንፈ ሲያክሉ፣ እንደራሴው ገና ወጣት ሰለነበሩ የሰዎችን ሀዘኔታ አግኝተዋል፡፡ በርግጥም በዚያን ጊዜ፣ እንደራሴው ዕድሜያቸው ሃያ ስድስት አመት ነው የነበረው፡፡ ሜጀር ዶድስ በዚያን ቀን በላከው ቴሌግራም፣ ተፈሪ በድንገት በሽታው እየባሰባቸው ነው፤ ነገር ግን ዶክተሮች ተስፋ አላቸው ብለዋል ብሎ ነበር፡፡ ወደ ኋላ፣ ሰለዚህ ሁኔታ ሲናገር፣ በፓጉሜ የነበረው የራስ ተፈሪ ሁኔታ ትልቅ ጭንቀት ነው የፈጠረው፤ ምንም እንኳ ሁኔታው በተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚታወቅ ቢሆንም፣ በነዚያ ቀናት፣ እንደራሴው በሞትና በህይወት መሀል እየተመላለሱ ነበር ይላል፡፡ ካምቤል ወደ ኋላ ሲያስታወስም፣ የሚገልጠው፣ ችግር የነበረው፣ እንደራሴው አንድ ሳምባቸው ተነክቶ ስለነበር ነው፡፡ የተፈሪ ሁኔታ በመንግሥት አካላት በኩል በጣም አሳሳቢ ሰለነበር፣ እንደ አለቃ ክንፈ አገላለጥ፣ በዚያን ጊዜ የጦር ሚኒስቴር የነበሩት ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ፣ ወደ ወላሞ ከሚያደርጉት ዘመቻ በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ  እንዲመለሱ ሰለተወሰነ፣ ፊታውራሪ በዛው ሳምነት ውስጥ አዲሰ አበባ እንደሚገቡ እየተጠበቀ ነበር፡፡ የህመምተኛው ሁኔታ በፓጉሜ ሁለት በጣም የከፋ ደረጃ ከደረሰ በኋላ ግን እንደገና መለስ ማለት ጀመረ፡፡ ዶድሰ ሲጠቅስም፣ ከእንደራሴው የግል ሀኪም ከፈረንሳዊው ሀኪም ከዶክተር ለ ፔፕ በነጋታው ማረጋገጫ ሪፖርት ሲደርሰው ሁኔታውን በትልቅ የዕፎይታ ሰሜት ነው የተቀበለው፡፡ እንደዛም ሆኖ የራስ ተፊሪ ሁኔታ ለብዙ ቀናት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ሰነበተ፡፡ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስም በመስከረም 7 (እኤአ) አዲስ አበባ ገቡ፤ ነገር ግን የሳቸው መመለስ ለመንግሥት የፀጥታ ዋስትና ለመስጠት ቢሆንም፣ እንደ ካምፕቤል ዘገባ፣ እሳቸው ራሳቸው በወረርሽኙ ተያዙ፤ ፊታውራሪውም ለተወሰነ ጊዜ ከፍተኛ አደጋና ከሞት አፋፍ ላይ ነበሩ፡፡

በሳቸው ህመም ምክንያት የሚኖረውን የፖለቲካ ውጤት፣ ራስ ተፈሪ፣ ገፋ ባለ ዕድሜያቸው ሲያስታውሱ፣ ለኢጣልያው መልክተኛ ለኮሊ የነገሩት ነገር፣ “እኔ ብሞት ኖሮ አገሬ አልቆላት ነበር፡፡ ሌላ ማንም ማንም አልነበረም፡፡” ብለዋል፡፡

በመስከረም 7 ከሞቱት ከውጭ ታዋቂ ሰዎች አንዱ፣ የእንደራሴው የግል ሀኪም የነበረው፣ የሊባኖስ ተወላጁ፣ ዶክተር አሳድ ቻይባን ነበር፡፡ የሰውየው ድንገተኛ ሞት የውጭ ሰዎችን ማህበረሰብ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ነው ያስገባው፡፡ እንደ ዶድስ አገላለፅ፣ የሰውየው ሞት፣ የትዕይንት ስሜት ነው የፈጠረው፤ ምክንያቱም፣ የሊባኖሱ ዶክተር፣ ራስ ተፈሪ ከታመሙበት ጊዜ ጀምሮ ያለ መታከት ሲከታተላቸው ስለነበረ ነው፡፡ ከሃምሳ ስድስት አመታት በኋላ፣ የዶክተር ቻይባን አሟሟት እንደገና፣ በአዲስ አበባ ለረዥም ጊዜ ይኖር በነበረው አውስትሪያዊው አልፍሬድ አቤል ለዚህ ፀሀፊ(ፕሮፌሰር ፓንክረስትን) የነገረው፣ የዶክተሩ አሟሟት ይልቁንስ ሚስጥራዊ ነው የነበረው፡፡ ምክንያቱም፣ ዶክተሩ በዚያን ገዜ ገና የሰላሳ አምስት አመት ወጣት ነበር፡፡ ይህ ዕድሜውም፣ የሱ በሽተኛ በነበሩት፣ በሕይወት ተርፈው ጤነኛ በሆኑት ንጉሥ፣ ውለታውን ለማክበር ሲሉ በጉለሌ ቢተክርስቲያን በተቀበረው በዶክተሩ መቃብረ ላይ በቆመው ሀውልት ተረጋግጧል፡፡ ዶክተሩ፣ በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እያለ ነበር በሁለት ሶሰት ቀናት ውስጥ የሞተው፡፡ የሞቱ ምክንያት፣ እንደ አቤል አገላለጥ፣ አስከ ጥቅምት አጋማሽ ድረስ ምን አንደሆነ በሰፊው አልታወቀም ነበር፡፡ በጥቅምት አጋማሽ፣ ውነተኛው ወረረሽኝ ሲፈነዳ ግን፣ በዚያን ጊዜ፣ ዶክተሩ የሞተው በስፓኒሽ ኢንፍሉዌንዛ መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡ የመቃብሩ ጎላ ያለው ሀውልት ላይ የተፃፈው ፅሁፍ፣ በአጭሩ የሚጠቅሰው፣ “የሙያው ሰለባ” የሚል ነው፡፡

በዚህ ጊዜ ወረርሽኙ የከተማውን ኗሪዎች በስፋት እየያዘ ነበር፡፡ አለቃ ክንፈ ሲገልፁ፣ “በአዲስ አበባ ብዙ ሰዎች እየሞቱ ነበር፣” ጨምረው በሀዘን የሚገልፁት፤

“በጦር ሜዳ ላይ፣ ወንድሙ በወንድሞ አስከሬን ላይ ተራምዶ እንደሚሄደው ሁሉ፣ ማንም ቢሆን በየመንገዱ ዳር ሞቶ የወደቀውን ሰው ለመቅበር አልተጨነቀም፡፡ ዝም ብለው አልፈው ተራምደው ይሄዱ ነበር፡፡ በቤተክርስቲያኖች ቅፅር በቂ መቃብር ቦታም አልነበረም፤ ሰለዚህ፣ ሰዎች፣ ገና ወደፊት ይሠራሉ በሚባሉ ቤተክርሰቲያናት ግቢ እንዲቀበሩ ተወሰነ፡፡ በዚህ ምክንያት ማንም ሰለ ሰበካው የተቸገረም አልነበረም፡፡”

ከዚህ ቀደም የተደነገገው በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርሰቲያን ግቢ ሰው እንዳይቀበር የሚከለክለው ህግ ተሻረ፤ ካምቤል፣ በማሽሟጠጥ፣ ያስተዋለውን ሲገልፅ፣  “በህልሙ፣ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሟቾችን የራሱ እንዲያደርጋቸው ስለነገረው፣ ጉዳዩ፣ ሀላፊ ለነበረው ቄስ የሚስማማ ነገር አልነበረም፡፡” አለቃ ክንፈም  ቢሆኑ የዚህን የቀብር ቸግር ሲጠቅሱ፣ “ብዙ ሰዎች ሰለሞቱ፣ ቁጥራቸው ከቀባሪው በላይ ሰለነበርና፣ የመቃብር ቆፋሪዎች ዕጥረትም ሰለነበር፣ ሰዎች ዘመዶቻቸውን በሌሎች ሰዎች መቃብር ላይ ደርበው መቅበር ጀመሩ፡፡” ይላሉ፡፡

ካምፕቤል ሰለቀብሩ ጉዳይ በወቀሳ መልክ የሚገልጠው፣ “የኋለኛው ሟቾች በነሐሴው ወረርሽኝ የሞቱ ሰዎች ላያቸው ላይ ነው የተቀበሩት” ብሎ ነው፡፡ ሰለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በፃፈው የሚጠቅሰው፣ “ቄሱ ጉቦውን አገኘ፤ ውሾቹም ቢሆን የሚበሉት አገኙ፣ ምክንያቱም የሟቾቹ አንዳንድ አካለት በመቃብሩ የተሸፈኑም አልነበረም፡፡ ስለዚህ፣ በዚህ በኢንፍሉዌንዛ ወረረሽኝ በመሀሉ፣ የኮሌራና የሌሎች በሽታዎች ወረረሽኝ ሊከሰት እንደሚችል በፊታችን የተደቀነ ነበር፡፡” ይላል፡፡

ብዙ ሰዎች፣ በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ሲደረግ እንደነበረው ልምድ፣ የወረርሽኙ ማዕከል የነበረውን ከተማውን እየለቀቁ መሸሽ ጀመሩ፤ አለዚያም፣ ራሳቸውን በየቤታቸው ዘግተው በመቀመጥ በተቻላቸው መጠን ምንም አይነት እንግዳ አንቀበለም አሉ፡፡ “መጀመሪያ ከተማውን ጥለው ከሸሹት አንዱ”፣ እንደ ካምፕቤል ገለፃ፣ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መሪ የነበሩት ግብፃዊው አቡነ ማቲዎስ ነበሩ፡፡ ጳጳሱ ከአዲስ አበባ በምዕራብ በኩል ሰላሳ ኪሎሜትሮች ርቀት በሚገኝ በመናገሻ ተራራ ለብቻቸው ተከልለው ቁጭ ብለው ነበር፡፡ የጳጳሱ፣ ከተማውን፣ ንግሥት ዘውዲቱንና እንደራሴውን ራስ ተፈሪን ጥለው መሄዳቸው፣ እንደ አለቃ ክንፍ አባባል፣ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች በኩል መጥፎ ስሜት ነው የፈጠረው፡፡ የከተማው ሰው፣ ጳጳሱን፣ ያለ መንፈሳዊ ርዳታ ዝም ብለን እንድንሞት ጥለውን ሄዱ የሚል ጉርምርምታ ያሰማ ነበር፡፡ እንደ ካምቤል ዘገባ ከሆነ፣ ሌሎች አነስ ያለ ማዕረግ ያላቸው ሰዎች የጳጳሱን ምሳሌ ተከተሉ፤ ከነዚህ መሀል የከተማው ከንቲባ ወሰኔ ዘአማኑኤል ነበሩ፡፡ በኋላ ግን ከተማውን እንዲቆጣጠሩ ተመልሰው እንዲመጡ ተደረገ፡፡

ከመጀመሪያው የወረርሽኝ ማዕበል የተረፉት፣ እንደራሴውን፣ ራስ ተፈሪን ጨምሮ፣ እያገገሙ ነበሩ፡፡ እንደራሴው በሳቸው በኩል በጣም ፈጣን የሆነ ማገገም ነው የታየባቸው፡፡ በዶድስ ሪፖርት መሠረት፣ የእንደራሴው ሀኪሞች፣ በመስከረም ሰባት ሲገልጡ “ያልታሰበ ሌላ ነገር መጥቶ እያገገሙ ያሉበትን ሁኔታ ከላቃወሰው በስተቀር፣ እንደራሴው ከአደጋ ውጭ  ስለሆኑ በስድስት ሳምንታት ውስጥ ወደ ሙሉ ሥራቸው መመለስ ይችላሉ፡፡”  ብለው ነበር፡፡ ምንም እንኳን የዚህ አይነት የህከምና አስተያየት ቢሰጥም፣ የእንደራሴው ህመም፣ ለከት ወደ ሌላው ሹክሹክታ ነው የተሻገረው፡፡ በዚያን ቀን የዶድስ ሪፖርት፤

“ራስ ተፈሪ ከሶስት ሳምንት በፊት በቤተመንግስቱ ውስጥ ሞተዋል የሚለው ወሬ ጠንከር ብሎ ብዛት ባላቸው ሰዎች ሲነገር ሰለነበርና፣ የተሠጠው የውሽት ሪፖርት ወይም አስተያየት ህዝቡን ለማረጋጋት ነው የሚል ሁኔታም ሰለነበር፣ የቀረበው ሀሳብ፣ የመስቀል ዕለት፣ ራስ ተፈሪ በቤተመንግሥቱ በረንዳ በኩል ለህዝብ እንዲታዩ የሚል ነበር፡፡”

“ራስ ተፈሪ ሞተው ቢሆን ኖሮ፣ በሀገሪቱ ጠቅላላ ከፍተኛ ረብሻ ሊፈጠር እንደሚችል ትንሽ ጥርጣሬም አልነበረም፡፡ ነገር ግን፣ ራስ ተፈሪ እያገገሙ ከሆነ፣ መስቀል በሰላም ያልፋል የሚል ተስፋ ነበር፡፡”

ሕዝቡን ሥርአት ማሰያዝ፣ የከንቲባ ወሰኔ ሥራ ነበር፤ ሰውየው ከተመለሱ በኋላ፣ “ከተማውን በራስ ተፈሪ ስም እየተቆጣጠሩት ነበር፡፡”

ተፈሪም ቢሆን ከተማውን ለማረጋጋት፣ ከሳምንት በኋላ ለህዝብ ታዩ፡፡ እንደ አለቃ ክንፈ ዘገባ፣ ራሰ ተፈሪ በመስከረም ሃያ ሌሎች ባላባትና በላሥልጣኖችን ተቀላቀሉ፡፡ በዛን ቀን፣ ከኤርትራ፣ ደ ማርቲኖ፣ ቴሌግራም ሲልክ የገለጠው፣ “ተፈሪ በሽታውን በቀላሉ ተወጥተው፣ በማገገም ላይ ናቸው” የሚል ነበር፡፡ የህይወት ታሪክ ፀሐፊው፣ ከዚህ ቀደም እንደራሴው ለአብያተ ክረስቲያነቱ የሠጡትን ሥጦታ በማስታወስ፣ መንፈሳዊ በሆነ መንገድ የገለጠው፣ “ፈጣሪ ምህረቱን ልኮላቸው ተፈወሱ” ይላል፡፡ በሽተኛው ራሳቸው፣ ዙፋኑን ከያዙ በኋላ፣ በራሳቸው የህይወት ታሪክ ሲፅፉ፣ “በጠና ታመው እንደነበር፣” ነገር ግን “በፈጣሪ ቸርነት እንደተረፉ ነው፡፡“

ያም ሆኖ፣ የእንደራሴው የህዝብ ታይታ በጣም አጭር ነው የነበረው፡፡ ምክንያቱም እንደገና ሊያዙ ይችላል ተብሎ ሰለተፈራ፣ በተቻለ መጠን ከውጭ ወይም ከሌላ ሰው ጋር በማይገናኙበት ሁኔታ ራሳቸውን ለማግለል ሞክረዋል፡፡ እንደ ካምፕቤል አገላለፅ፣ “እንደራሴው የሁኔታውን አስከፊነት እንደተረዱ፣ ከባለቤታቸው፣ ከልጆቻቸውና ከጥቂት ጠባቂዎች ጋር በመሆን ራሳቸውን በቤተመንግሥቱ ግቢ ዘግተው ተቀመጡ፣ ከዶክተሩ ውጭ ሌላ ማንም ሰው መግባትም ሆነ መውጣት አይችልም ነበር፡፡” እንደዛም ሆኖ፣ ራስ ተፈሪ፣ በጥቅምት 20፣ ዶድስን ተቀብለው አነጋገሩ፣ በዚህ ምክንያት፣ በነጋታው ካምፕቤል ሪፖርት ሲያደርግ፣ እንደራሴው፣ “ሥራቸውን ለማካሄድ በበቂ ሁኔታ አገግመዋል” ብሎ ነበር፡፡ የእንደራሴው መታመምና የፖለቲካው ውጤት እንደቀጠለ ነበር፡፡

“አጠቃላይ የነበረው አመለካከት ከህመማቸው ወዲህ የነበራቸው የፖለቲካ ሀይል በሚገባ ጨምሯል፤ 

​ክፍል ሁለት ወደፊት ሰለሚቀርብ ተከታተሉ፡፡

ክፍል ሁለት