ለኤች አይ ቪ ቫይረስ ቢጋለጡም በቫይረሱ የማይለከፉ ሰዎች እንዳሉ ያውቃሉ ወይ

 

ሰዎች በተፈጥሯቸው ለበሽታ የተለያየ ምላሽ እንዳላቸው ግልፅ ነው፡፡ ወደ ኤች አይ ቪ ከመሄዳችን በፊት ሌሎች ቫይረሶችን እንመልከት

ለምሳሌ የጉበት በሽታ በማሰከተል በአለም ዝነኛው ቫይረስ ሔፓታይትሰ ቢ ነው(Hepatitis B)፡፡ ሰዎች ለዚህ ቫይረስ በሚጋለጡበት ጊዜ ከመቶ ሰማንያ አምሰት (85%) የሚሆኑት ሰዎች ቫይረሱን በተፈጥሮ መከላከያቸው ጠርገው በማውጣት በበሽታው ሳይለከፉ እንደሚቀሩ ይታወቃል፡፡

ሌላውን የጉበት በሽታ የሚያስከትለውን የሔፓታይትሰ ሲ ቫይረስ (Hepatitis C) ስንመለከት ለዚህ ቫይረስ ከተጋለጡ ሰዎች ከመቶ አስራአምስት (15%) የሚሆኑት ቫይረሱን ከሰውነታቸው ባላቸው የተፈጥሮ መከላከያ አማካኝነት ጠርገው በማውጣት በቫይረሱ ሳይለከፉ ይቀራሉ፡፡ የቀሩት 85% የሚሆኑት ግን ቫይረሱ በሰውነታቸው ውስጥ በመቅረት የጉበት በሽታ እና የጉበት ካንሰር ሊከሰትባቸው ይችላል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት ሔፓታይትስ ሲ ቫይረስን በህክምና ማዳን ከተቻለ ስንበት ብሏል፡፡ የዚህ ርዕስ ፀሐፊ ለዚህ በቂ ምስክር ነው፡፡ ብዛት ያላቸው ህሙማንን ከቫይረሱ በመፈወስ፡፡ ትልቁ ችግር መድሃኒቶቹ ውድ መሆናቸው ነው፡፡ አንደ ኪኒኒ (እንክብል) አንድ ሺ የአሜሪካ ዶላር በላይ ያወጣል፡፡ በአብዛኛው ህክምናው ለሶስት ወር ብቻ ስለሚሰጥ ስሌቱን ለአንባቢ እተዋለሁ፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ቫይረሶች የተጋለጡ ሰዎች በደም ምርምራ ለቫይረሱ ተጋልጠው እንደነበር ማወቅ ይቻላል፡፡ የዳኑትም ሆነ ቫይረሱን በሰውነታቸው ውስጥ ተሸክመው የቀሩት፡፡

እንግዲህ ወደ ኤች አይ ቪ ስንመለስ ለበሽታው ጨርሶ መጥፋት ሚስጥሩን የያዙት ስለሚባሉ ሰዎች ላካፍል፡፡ እነዚህ ሰዎች በተደጋጋሚ ለቫይረሱ ተጋልጠው ነገር ግን ባላቸው የተፈጥሮ መከላከያ ምክንያት በቫይረሱ ሳይለከፉ የሚቀሩ ናቸው፡፡ በእንግሊዝኛው አጠራር Highly Exposed Sero Negatives ይባላሉ፡፡ ለዚህም በቂ ጥናት ተደርጓል፡፡ በአፍሪቃ ውስጥ ሴትኛ አዳሪዎቸን በመከታተል በተደረገው ጥናት ሴቶቹ ያለምንም መከላከያ ግብረ ሥጋ ግንኙነት በተደጋጋሚ ቢያደርጉም ሌሎች እኩዮቻቸው በቫይረሱ ሲለከፉ እነሱ ግን ሳይያዙ ቀርተዋል፡፡ በጣም የሚያስገርም ሁኔታ ነው፡፡ በአሜሪካም በግብረ መሰል ፆታ ግንኙነት ያለምንም መከላከያ ሲያደርጉ የነበሩ ሰዎች ጓደኞቻቸው ሲለከፉ እነሱ ሳይለከፉ ቀርተዋል፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት የጉበት ቫይረሶች ሁኔታ የሚለየው እነዚህ በኤች አይ ቪ ቫይረስ ያልተለከፉ ሰዎች በደማቸው ውሰጥ ተጋልጠው እንደነበረም ምልክት የለም፡፡

የተለያዪ መላ ምቶች አሉ፡፡ ዋነኛው የነዚህ ሰዎች ሴሎች ቫይረሱን የማይቀበሉ አይነት ወይም ሴሎቹ በላያቸው ላይ ለቫይረሱ መግቢያ በር የሆኑ ሞሎኪሎች የላቸውም ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በሌሎች ለቫይረሱ መጋለጣቸው የታወቀ ግን በቫይረሱ ያልተለከፉ ሰዎችም ላይ ይታያል፡፡ ይህም በሥራ ምክንያት ለቫይረሱ የተጋለጡ የህክምና ባለሙያዎችንም ይጨምራል፡፡

አሁን በኤቸ አይ ቪ ህክምና የሚታይ የማያውቁ ሰዎችን የሚያስገርመው ሁኔታ ባልና ሚስት አንደኛቸው ቫይረሱ ሲኖርባቸው አንደኛቸው ሳይኖረባቸው መታየት ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ይህ እንግዲህ በተፈጥሮ በምንም አይነት መንገድ ለቫይረሱ ቢጋለጡም ቫይረሱን ሰውነታቸው ውስጥ እንዳይቀር የማድረግ የተፈጥሮ የመከላከያ ችሎታ ያላቸው ሰዎች መኖራቸውን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ከዚህ ወገን ከሚመደቡ መሀከል ኤች አይ ቪ ካለባቸው ነብሰ ጡር ሴቶች የሚወለዱ ህፃናት ናቸው፡፡

የነዚህ በተፈጥሮአቸው በኤች አይ ቪ የማይለከፉ ሰዎች ቁጥር 15% ድረስ እንደሚሆን ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከኤች አይ ቪ ልክፍት ድኗል ተብሎ የሚታወቀው የበርሊኑ በሽተኛ በነበረበት የደም ካንሰር ምክንያት የራሱን የደም ሴሎች ጠርገው በማውጣት በምትኩ ከነዚህ በኤች አይ ቪ ቫይረስ አይለከፉም ከሚባሉ ሰዎች ደም በመውሰድ ትክ ስላደረጉለት ነው፡፡ ሰውየው አሜሪካዊ ነው፡፡ አስካሁን የኤች አይ ቪ መድሃኒት አይወስድም፡፡

በሌላ ርዕስ ደግሞ ቫይረሱን ማስወገድ ሳይችሉ ቀርተው የተለያየ መንገድ ሰለሚሄዱ ሰዎች እናካፍላለን፡፡

አንግዲህ ማን በተፈጥሮው በቫይረሱ እንደማይለከፍ ለማወቅ ምርምራ ስለማይደረግ ተገቢውን ጥንቃቄ ከማድረግ መቆጠብ ተገቢ አይደለም፡፡ በባልና ሚስት ወይም በጉዋደኞች መሀከል አንደኛቸው ሳይያዙ ቢቀርም ሚስጥሩ የተፈጥሮ ሁኔታ ሊሆን ቢችልም በግብረ ሥጋ ግንኙነት ጊዜ ተገቢውን መከላከያ ማድረግ ተገቢ አንደሆነ አንመክራለን፡፡

በኢቮሉሽን ለሚያምኑ ሰዎች “Survival of the Fittest” የሚባለው ፍሬ ሀሳብ ይህንንም ይጨምራል፡፡ ኤች አይ ቪ ቫይረስ በአጣዳፊ አንደ ኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ አይነቶች ቶሎ የሚገድል ቢሆን ሳይሞቱ የሚተርፉ ሰዎች እንዳሉ ነው፡፡ በቅርቡ በኢቦላ ቫይረስ ያየነው ይህንኑ ነው፡፡

እንግዲህ ሳይንቲሰቶቹ የዚህን ምስጢር በመፍታት ኤች አይ ቪን ለማዳን በሚደረገው ጥረት ከተሰማሩ ስንብተዋል፡፡  ኤች አይ ቪን ማዳን የሚባል መርሆና እንቅስቃሴ እየጨመረ የመጣ ነገር ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት ከክትባት ጀምሮ ሌሎች መድሃኒቶችን በመስጠት ሙከራው የቀጠለ ነው፡፡ ለዚህ ሙከራ በሙሉ ፈቃደኝነት በጥናቱ ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎችን ማመስገን ተገቢ ነው፡፡እሰከዚያ ድረስ በቫይረሱ የተለከፉ ሰዎች ሳይደበቁ መድሃኒት በመውሰድ የመከላከያ አቅማቸወን ገንብተው መቆየት ተገቢ ነው፡፡ ለጥቆማ ያህል በጥናቱ የሚሳተፉ ሰዎች መድሃኒታቸውን በመውሰድ ቫይረሱ በደም ውስጥ እንዳየዘዋወር በማድረግ (በሴሎች ውስጥ ግን ተደብቆ ይቆያል) የመከላከያ አቅማቸውን ገንብተው የሚገኙ ሰዎች ናቸው፡፡

በህክምና አለም ለሔፓታይትስ ሲ ቫይረስ መድሃኒት ይመጣል ብለን አስበን አናውቅም ነበር መጠቀም እስክንጀምር ድረስ፡፡ ኤች አይ ቪም ዕጣ ፋንታውን እንደሚያገኝ ተስፋ አለን፡፡ በመድሃኒቶች ምክንያት ያለውን ለውጥና የእድሜ መርዝመ በጎሽ ድረ ገፅ የተቀመጡትን ይመልከቱ፡፡